ማስታወቂያ

እውነተኛውን መረጃ ማጥራት የጊዜው ፈተና

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስጥቅምት 19 ፣ 2014
City: Bahir Darማህበራዊ ጉዳዮች
እውነተኛውን መረጃ ማጥራት የጊዜው ፈተና

የተሳሳተ መረጃ ዓለምን እየበከለ፣ ህይዎትን እየቀጠፈ፣ አለመረጋጋትን እያጋለ፣ የሁከት የብጥብጥ መንስኤ እየሆነ በኢትዮጵያ የከረሩ የጥላቻ ንግግሮች መዘውተር ከዘመኑ የ‘ኦንላይን’ ሚዲያ አገልግሎት ጋር ተዳምሮ የሀገረ መንግሥትን እስከ መገልበጥ፣ ፖለቲካን አለማስከን እና ኦከኖሚን እስከ መጉዳት እንደተሸጋግሩ አስተውለናል።

እንደዘርፉ ተንታኞች የዩኔስኮ የ2021 ሪፖርት በሀገራችን መረጃን ማሳሳት፣ መረጃን ማዛባት፣ መረጃን መበከል እና ፕሮፓጋንዳ ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት የሚሰተዋሉ ችግሮች መሆናቸው ይጠቀሳል። የሐሰት ዜናና መረጃ ስርጭት በፕረስ ነፃነትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ እያደረሰ ያለው አደጋ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲልም እ.አ.አ በ2019 በኢትዮጵያ በተከበረው የዓለም የፕሬስ ቀን መሪ ቃሉን የፕረስ ነፃነትና የሐሰት “ዜና” በማለት መሰየሙ ይታወሳል።

የሐሰት ዜናዎች እና የሚዲያ ትምህርት አለመዳበርም በኢትዮጵያ ብጥብጥ ጨምሯል ሲል የአውሮፓ የሰላም ተቋም የአውሮፓ የሰላም ተቋም የውሸት ዜና የተሳሳተ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ፡ የተጋላጭነት ግምገማ ሪፖርት ያሳያል። በፖለቲካ ልዩነት ግለሰቦች እርስ በርስ ተዋግተዋል፣ ተገድለዋል፣ ተገዳድለዋል፣ የጎሳ ፉክክር ወይም የሃይማኖት አክራሪነት፣ እንዲሁም በመሬት፣ በድንበር እና በሌሎች ላይ የሚነሱ የተለያዩ አለመግባባቶች በኦንላይን (በበይነ መረብ እና ማኅበራዊ ሚድያዎች) እና ኦፍላየን (ኢንተርኔት የማይጠቀሙ) ሚዲያው ያሉ የጥላቻ ንግግሮች በጣም አድጓል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ሁኔታ “ኢትዮጵያን ወደ ከፋ ግጭት ይወስዳት ይሆን?” ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ኖሬዌይ በሚገኘው ኤን ኤል ኤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ተርየ ሸዳል “ኢትዮጵያ እኛ እና እነሱ በሚሉ የብሄር ተኮር ጎራዎች፣ በብሄር በተከከቡ ሚዲያዎችና ዘገባዎች ሁሉ ሰበዓዊነት እየራቃቸው ከብሄሩ ሚዲያ ውጭ ያሉ አካላትን ጥቃት ዕያዩ ዕንዳላዩ ማለፍ እና የራሰን በግነት ማራገብ ወይም ከሚዛናዊነት በራቀ ሁኔታ ትኩረት መንፈግ እየተሰተዋለባቸው ነው” ሲሉ ብሄርና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በሚለው ጥናታቸው ይገልፃሉ።

ለምሳሌ በሰኔ 2011 ዓ.ም. የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አምባቸው መኮንን፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ አቶ መኮንን እና ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገድለዋል። እ.ኤ.አ. በጥቅምት ወር 2019 በኦሮምያ ክልል ዙርያ ያሉ ግጭቶች በተካሄደበት ወቅት ቢያንስ 86 ሰዎች በልተጣሩ መረጃዎች ህይወት ጠፍቷል። እ.ኤ.አ. በሰኔ 2020 የታዋቂው ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ 166 ሰዎች ውድ ህይዎታቸውን አጥተዋል። በአዲስ አበባ እና በኦሮምያ ክልሎች በተከሰተው ውድመት እና መፈናቀል ሳቢያ ሞትና መቁሰል ደርሷል።

ግጭቶችን ተከትሎ በኢትዮጵያ በስፋት የሚሰራጨውን ያልተረጋገጡ መረጃዎች ተፅእኖ በተመለከተ የመንግሥት ምላሽ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጥ ነው።

በማኅበራዊ ሚድያዎች ሐቅን በማጣራት የሚታወቀው የሕግ ባለሙያ አቶ እሸቱ ሆማ ቀኖ የሀሰተኛ መረጃዎች መነሻ ከመንግሥታዊ ተቋማት በሚወጡ የተጣረሱ ዘገባዎች እና ሪፖርቶች ናቸው ይላል። “በተለይም በመንግሥት በጀት የሚንቀሳቀሱ የፌደራል እና የክልል ሚዲያዎችን መረጃዎች ሐቅ የማጣራት ድርጊት ካከናወንን በርካታ እርስ በእርስ የሚጋጩ መልዕክቶችን እናገኛለን” ይላል።

እንደ ኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን መረጃ ከ25 ሚልየን በላይ ዜጎች ዜናቸውን በኢንተርኔት አማካኝነት ከፌስቡክ እና ከሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ያገኛሉ። ስለዚህ የበይነመረብን አገልግሎት ማቋረጥ 'የሃሰት ዜና'፣ የጥላቻ ንግግር እና የተሳሳቱ መረጃዎች ለታዳሚዎቻቸው እንዲሰራጩ እና መረጃዎች እንዲገደቡ በር በመክፈት የሰዎችን የመረጃ ነፃነት በእጅጉ ይገድባሉ። በዚህም ምክንያት የመግባባት፣ ሪፖርት የማድረግ ችሎታ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የሀሰት ዜና ስርጭት እንዲኖር በር ከፍቷል።

የሐሰት ዜና ስርጭትን መገደብ ላይ ትኩረት ሰጥተው ከሚንቀሳቀሱ ምሁራን መካከል ሃንት ኦልኮት እና ማቲው ጌንትዝኮው ተጠቃሽ ናቸው። ጸሐፊዎቹ “የሐሰት ዜና ሆን ተብሎ እና በተረጋገጠ መልኩ ሐሰት የሆነ መረጃ ማስራጨት ነው። እናም አንባቢዎችን፣ ተመልካች እና አድማጮችን ሊያሳስቱ ይችላሉ” ብለዋል።

“ሐሰተኛ ዜና” የዜና ወይም የመረጃ ዓይነት ሲሆን ሆነ ብሎ መረጃን ማዛባት ወይንም የፈጠራ ወሬን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እና ኦን ላይን ሚድያዎች መንዛት ነው። ይህንን መሰሉ አካሄድ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ይዘወተራል። አብዛኛው የሐሰት ዜና ሁለት ሃሳቦችን ደባልቆ ይይዛል እነሱም መረጃን ማሳሳት እና መረጃን ማዛባት ናቸው።

“ሐሰተኛ ዜና ወይም መረጃ” (Fake News) የሚለው ቃል ትርጉም የተሳሳተ መረጃን ወይም ሐሰተኛ ዜናን ጉዳት ያደርሳል ብሎ በለማስብ ወይም ትክክለኛ መሆኑን ሳያረጋግጡ ለሌላ አካል ማስተላለፍ እና በማጋራት የሚፈጠር ስሁት የመረጃ ስርጭት ነው።  ሐሰተኛ መረጃ ከሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተለይቶ ዓይታይም። በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ አንድ የጤና ባለሙያ የሆነ ሰው የሰውን ሙሉ ጤንነት እንደሚጎዳው ሁሉ በሀሰተኛ መረጃም የማኅበረሰብን ሰላማዊ ጤንነት ይናጋል። አንድነት ይፈርሳል። ልዩነትን በማጋነን ጥላቻ ይዘራል። ተጽዕኖው ሲያድግ የእርስ በርስ መጠፋፋት ሊያስከትል ይችላል።

በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  በ2012 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 1185 /2012 ሐሰተኛ መረጃ ወይም ዜና ማለት “ሐሰተኛ መረጃ” መረጃው ሐሰት የሆነና የመረጃውን ሐሰተኝነት በሚያውቅ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳያደርግ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው ይለዋል።

በአዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 5 መሰረት የሃሰት መረጃን በብሮድካስት፣ በሕትመት ወይም በማኅበራዊ ሚድያ በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ማሰራጨት የተከለከለ መሆኑን  ይደነግጋል። በዚህ አንቀጽ መሰረት አንድ መረጃ ሀሰተኛ መሆኑ ብቻ በወንጀል የሚያስጠይቀው መቼ እንደሆነ ለመረዳት በአንቀጽ 2(3) የተቀመጠውን የሃሰተኛ መረጃ ትርጉም በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል። በአንቀጽ 2(3) መሰረት “ሃስተኛ መረጃ” እውነት የሆነ መረጃ ሲሆን መረጃው ውሸት መሆኑን በሚያውቅ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሃሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው።

የአዋጁ አንቀፅ 6 ንኡስ አንቀጽ 2 ስር የተደነገገው ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨትን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ የሚታይ ሀሳብን ነው።  ይኸውም አንድ ንግግር እንደ ሃሰተኛ መረጃ ተወስዶ የማይከለከለው ንግግሩን ያሰራጨው ወይም ተናጋሪው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በእርሱ ሁኔታ ካለ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ወይም ንግግሩ የጥሬ ሃቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ መሆኑ ተገልጾአል። መሰል ልዩ ሁኔታዎች መደንገግ የሚያስፈልገው ሕጉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቀነስ ነው።

በዚህ ወቀት ዓለማችን በመረጃ መዛባት፣ ብክለት እና በአሳሳች መረጃዎች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዜና እየተፈተነች ነው። በዋናነት በኢትዮጵያ የሚሰተዋሉ ሐሰተኛ መረጃ ዓይነቶች መረጃን በመበከል፣ መረጃን በማሳሳት፣ በመረጃን በማዛባት እና በፕሮፓጋንዳ ላይ የተመሰረቱ ናቸው ሲሉ በሀርቫርድ ኬነዲ ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት ክሌር ዊልሞት፣ ኤልቨን ቴሌታራስ እና አሌክሲ ድሪው ያብራራሉ።

መረጃን መበከል (Disinformation) ሐሰተኛ መረጃ ጉዳት እንዲያደርስ በማሰብ ሆነ ተብሎ ሲጋራ የመረጃ ማዛባት ወይም የመረጃ ብክለት ይባላል።  

ሆነ ተብሎ ጉዳት ለማድረስ የሚዘጋጅና የሚሰራጭ መረጃ (Disinformation) ይህ ዓይነቱ ሀሰተኛ መረጃ ሆነ ተብሎ የተወሰነ ዓላማ አንግቦ የሚዘጋጅ ሲሆን የመረጃው ጠንሳሽ /አመንጭ/ እንዲሁም መረጃውን የሚያዘጋጀው እና የሚያስራጨው አካል መረጃው ሃሰተኛ መሆኑን በደንብ እያወቀ እንደ ትክክለኛ መረጃ ለሌላ አካል የሚስተላልፍበት ሂደት ነው። ሰለዚህ ሆን ተብሎ አንድን ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ተቋም ወይም አገር ለመጉዳት የሚዘጋጅ የሃሰት መረጃ ነው።

መረጃን ማሳሳት (Misinformation) መረጃውን የሚያሰራጩ አካላት መረጃው ሀሰተኛ መሆኑን ሳይረዱ እና ሳይነዘቡ እንዲሁም ባለማወቅ በሚያሰራጩበት ጊዜ የሚፈጠር የሃሰተኛ መረጃ ፍሰትን የሚገልጽ ነው። ይህ ሁኔታ በአብዛኛው በብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ማጋራት፣ መውደድ፣ እንደገና በራስ ገፅ አትሞ ማጋራት፣ መልዕክት መለዋወጥ ላይ ይስተዋላል። ምክንያቱም ሰዎች ያገኙት መረጃ (ፎቶ፣ ዜና እና መጣጥፍ፣ የተንቀሳቃሽ ፊልም እና ድምፅ/ እውነተኛ ይመስላቸውና ለሌሎች የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ያጋራሉ። እነዚህ ሰዎች ግን ጉዳት ለማድረስ አስበው ሳይሆን የመረጃውን ተደራሽነት ለማስፋት በማለም የሚያደርጉት የመረጃ ቅብብሎሽ መረጃን ማሳሳት ይባላል (Misinformation)። ብዙ ጊዜ በባህላችን የተሳሳተ መረጃ ነግረህ አሳሳትክኝ እንደምንለው ያለ  ነው።

መረጃን ማዛባት (mal-information) ሆነ ተብሎ እና ታቅዶ ጉዳት ለማድረስ በማስብ እውነተኛ መረጃ ሃቁን በማፋለስ የሃሰት መረጃዎችን በመጨመር ማጋራት ወይም በመከል ነው። መረጃን መበከል ይባለል።  በሌላ አገላለፅ በእውነተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ጎጂ መረጃ የማሰራጨት ሂደት የመረጃ ብክለት (Malinformation) እንለዋለን። አውነተኛ መረጃን ተመርኩዞ መጠነ-ሰፊ ጉዳት ለማድረስ የሚሰራጭ መረጃን የማዛባት ሂደትን ይመለከታል። የዚህ ዓይነቱ መረጃ መነሻው ትክክለኛ ቢሆንም መረጃው የሰዎችን ስብዕና፣ የግልና የቤተሰብ ነጻነት፣ ንብረት እና የመሳሰሉትን ለጉዳት ያጋልጣል።

በሐሰት ዜና ስርጭት የማይፈተን የለም። ዜጎች እና መንግሥት፣ በተመሳሳይ መንግሥትም በሐሰት ሪፖርቶች ህዝብን የማሳሳት ዝንባሌዎች የበዙ ናቸው። ሚዛናዊ ያልሆነ ወይም የተዛባ መረጃ በማስተላለፍ በሰዎች አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚደረግ ጥረትን ለማመልከት ነው። አንዳንዶች ፕሮፓጋንዳ ሲባል ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው “መዋሸት፣ እውነትን አዛብቶ ማቅረብ፣ ማታለል፣ ተጽዕኖ ማሳደር፣ የሌሎችን አዕምሮ ለመቆጣጠር መሞከርና ሥነ ልቦናዊ ጦርነት” ነው፤ በመሆኑም ፕሮፓጋንዳ “ተገቢ ያልሆነ፣ ጎጂ እንዲሁም መሠሪ የሆነ ዘዴ” እንደሆነ ፕሮፓጋንዳ ኤንድ ፐርስዌዥን ይናገራሉ።

ፕሮፓጋንዳ ቀለምና ሽታ እንደሌለው መርዛማ ጋዝ ሁሉ ፕሮፓጋንዳም ሳይታወቀን አስተሳሰባችንን ሊመርዘው ይችላል። ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ላናስተውል እንችላለን፤ በመሆኑም የባሕርይ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ቫንስ ፓካርድ እንደተናገሩት “ብዙዎቻችን፣ በአስተሳሰባችን ላይ ከምንገምተው በላይ ተጽዕኖ እየደረሰብን ነው።” አንድ ምሁር እንደገለጹት ደግሞ በርካታ ሰዎች በፕሮፓጋንዳ ተመርተው “ለማመን የሚከብድ አደገኛ ነገር ፈጽመዋል።” የዘር ማጥፋት ዘመቻን፣ ጦርነትን፣ ዘረኝነትን፣ ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነትን እና ሌሎች ምክንያታዊነት የጎደላቸው ነገሮችን’ ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል ሲል ኢዝሊ ሌድ—ኤ ሂስትሪ ኦቭ ፕሮፓጋንዳ ይገልፃል።

“እውነት ጫማውን እስኪያደርግ ውሸት የዓለምን አጋማሽ ሊያዳርስ ይችላል።”​ ማርክ ቱዌይን እንደተናገረው በእኛም ሀገር “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንላለን። አንቶኒ ፕራትካኒስ እና ሌሊየት አረንሰን የተባሉ ተመራማሪዎች “በእያንዳንዱ ቀን የተለያየ መልክ ያለው የማሳመኛ መልእክት ውርጅብኝ ይወርድብናል። እነዚህ መልእክቶች ለማሳመን የሚሞክሩት የእሰጥ አገባ መልክ ባለው ክርክርና ውይይት ሳይሆን አንዳንድ ምስሎችን በመጠቀምና በጣም መሠረታዊ የሆኑትን ሰብዓዊ ስሜቶች መሣሪያ በማድረግ ነው። ከፋም ለማ የኛ ዘመን የፕሮፓጋንዳ/ የሀሰት መረጃዎችን ማጥራት የሚያሻበት ዘመን ሆኗል” ብለዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪአየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.