ሐምሌ 12 ፣ 2013

በየክረምቱ የጎርፍ ስጋት ያጠላባት ከተማ

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

ድሬዳዋ በክረምት ወቅት ስጋት ከሚያድርባቸው ከተሞች ውስጥ ስትሆን የቁጥር ማነስ እና መብዛት ካልሆነ በቀር በየዓመቱ የሚመጣው ክረምት ጉዳት አድርሶባታል፡፡ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ግንባታዎች ቢከናወኑም ነዋሪዎቿ ዛሬም ስጋት አላቸው፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

በየክረምቱ የጎርፍ ስጋት ያጠላባት ከተማ

በዘመናዊ አደረጃጀታቸው ቀዳሚ ከነበሩ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ድሬዳዋ አንዷ ነች፡፡ በጀመረችበት መንገድ መቀጠል ተስኗት ቀዳሚነቷን ለሌሎች ከማስረከቧ በፊት የነበራት ሁለንተናዊ መልክ እጅጉን ማራኪ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክሩላታል። ጥቂት የማይባሉ ታዛቢዎች ደግሞ እድገቷ የኋሊት ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡

ማስተር ፕላንን መሰረት ያደረገው አመሰራረቷ፣ የቀደመ ውበቷ ዛሬ ታሪክ ነው። የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓቷን ለአብነት ስንመለከት ዝናብና በአብዛኞቹ አካባቢዎች የሚነሳ ፍሳሽ እንኳ በአግባቡ የሚሄድበት የከተማዋ ስርዓት አይስተዋልም።

ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ ጎርፍ በዋና መንገዶች ላይ በመሄድ የትራፊክ እንቅስቃሴን ጭምር የሚያውክበት ጊዜም በርካታ ነው። ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈው የአሸዋ መውረጃም መጠኑ ከፍ ያለ ጎርፍ ከመጣ ብዙ ጉዳት ያስከትላል። በአብዛኛው ይህ ጎርፍ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ከገንደ ሎሌ በመነሳት አሸዋን ያቋርጥና በቀፊራና አዲስ ከተማ በማለፍ ወደ ኮካና መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን፣ ወደመናኸሪያ፣… እያለ ይቀጥላል፡፡

ለድሬደዋ ስጋት የሆነው ጎርፍ ምንጭ በአንድ በኩል በደጋው ወይም በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ አካባቢ የሚጥል ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ነው፡፡ በአካባቢዎቹ አደጋ እንደሚያስከትል የሚያሰጋ ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ከጣቢያ ለቀበሌ ስልክ በመደወል ሕብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ ይነገራል፡፡

ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ወ/ሮ ዘውድነሽ ጠና የተባሉ አዛውንት በአሁኑ ሰዓት ጎርፉ ወደ ነዋሪው እንዳይገባ መገደቢያ ደለል በየቤቱ እንዲያደርግ እየተነገረ እንደሚገኝና በዚህም ምክንያት ስጋት ላይ መውደቃቸውን ነግረውናል፡፡

“ጎርፉ የሚመጣው ድሬደዋ ውስጥ ስለዘነበ ሳይሆን ከድሬዳዋ በቅርብ ርቀት የሚገኙት እንደ ቁልቢ፣ ደንገጎ፣ ገነት መናፈሻ የተባሉት አካባቢዎች ላይ በኃይል ከዘነበ ለድሬደዋ ስጋት አለ፡፡ ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜ ያልታሰበ ጎርፍ በሚመጣበት ወቅት ሕብረተሰቡ ስለማያውቅ ለከፋ ችግር የሚጋለጠው፡፡ ድሬደዋ ላይ ምንም ሳይዘንብ ድንገት ጎርፍ መጥቶ ብዙ ቤትና ንብረት እንዲሁም ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ሊቀጥፍ ይችላል” ብለዋል፡፡

ድሬደዋ አስከፊ ቀን ያሳለፈችበት ተብሎ የሚገመትበት ነዋሪዎቿን ከነንብረታቸው ጥርግርግ አድርጎ የወሰደባት ሁኔታ የድሬዳዋ አስተዳደር ከዛሬ 16 ዓመት በፊት ሐምሌ 28 ቀን 1998 ዓ.ም. ሌሊት በከተማው ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ የበርካታ ሰዎች ህይወት የቀጠፈና በሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች መጠለያ ማጣትና ንብረት መውደም ምክንያት መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

ጎርፉ በሚመጣበት ወቅት መጠኑ ከፍ ባለ ጉዳት ስለሚያስከትል ድልድይ በሰዓቱና በሚፈለገው ጥራት መገንባት ተገቢ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ አደገኛ ጎርፍ ከተከሰተ በኋላ ድልድይ የተሰራ ሲሆን ድልድዩ የሚጠቅመው ግማሹን ውሀ ለመቀነስና ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲፈስ ለማድረግ ያለመ ቢሆንም አሁንም ብዙ ጉዳቶች እየደረሱ ይገኛል የአካባቢው ነዋሪም ስጋት ውስጥ ይገኛል፡፡ በተለይ አሁን የክረምት ወቅት እንደመሆኑ መጠን ስጋቱ ጨምሯል፡፡

ጎርፍ ወይም የውሃ መጥለቅለቅ ማለት በተለምዶ ደረቅ የሆነ መሬት በውሃ መሞላት ነው። ጎርፍ ብዙ ጊዜ በመኖሪያና የንግድ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደርሳል። የጎርፍ ዋና ጉዳቶች የሰውና እንስሳት ሞት፣ የሕንጻዎች መፍረስ እና የመንገድ፣ ድልድይና ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ መበላሸት ናቸው። የመሠረተ ልማት መውደም የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ እና ማመንጫዎችን ከሥራ ውጭ ሊያደርግ ይችላል። የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ደግሞ በርካታ ሂደቶችን ያስተጓጉላል። ለምሳሌ የውሃ ማጣሪያ እና ማቅረቢያ ተቋማት አገልግሎት አቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ የረጅም ጊዜ ጉዳቶችንም ያስከትላል ተብሎ ይታመናል ለምሳሌ የቱሪዝም መዳከም፣ የጥገና ወጪ እና የቁሳ ቁስ ዋጋ ንረት በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርገው ተጽዕኖ በአብዛኛው ጊዜ ከከፍተኛ መጥለቅለቅ በኋላ ይታያል። የሰውና የእንስሳት ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም የሥነ ልቦና ችግርን ጨምሮ ኢኮኖሚን ይጎዳሉ፡፡

እነዚህ ጉዳቶች በአሁኑ ሰዓት ለድሬደዋ ጎርፍ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ላይ ከበድ ያለ ዝናብ የሚጥል ከሆነ ለነዚህ ሁሉ ቀውሶች ልክ እንደ ከአሁን ቀደሙ ሊያጋጥማት እንደሚችል የሚገመት ነው፡፡

ጎርፍ ከመከሰቱ በፊት በትንበያ ቅድመ ጥንቃቄዎች እንዲወሰዱ እና የሚመለከተው ሕብረተሰብ እንዲጠነቀቅ ጊዜ ይሰጣል። በቀበሌዎች አማካኝነት የዚያ አካባቢ ነዋሪዎች እንዲጠነቀቁ መነገሩ ጥቅም እንዳለው የተናገሩት ወ/ሮ ዓለምነሽ ግሩሙ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አዛውንት ሲሆኑ ነገር ግን ይህ ብቻ ከስጋት ነፃ ሊያደርጋቸው እንደማይችልና የዚያን ጊዜ ተሰርቶ የነበረው ግድብ በአሁን ሰዓት አደጋ የመከላከል አቅሙ አነስተኛ በመሆኑ የተሻለ መፍትሄ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን አሁንም ግድቡን እያለፈ እንደሚመጣባቸው ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት በድሬዳዋ አስተዳደር የጎርፍ አደጋን ሊከላከሉ የሚችሉ ስራዎችን በ162 ሚሊዮን ብር ወጪ ሲሰራ መቆየቱን የአስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን ገልጿል። የባለሥልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ፀጋዬ በድሬዳዋ በተለያዩ አካባቢዎች ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት የመንገድ መሰረተ-ልማት የመገንባት፣ የመንከባከብና የማስተዳደር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ያሉ ሲሆን የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በ“ጋቢዮን” የማሰርና በማዳበሪያ አሸዋ በመሙላት ጎርፍ የመከላከል ስራዎች እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው በ 02,05,07,08,09 ቀበሌዎች ላይ መከናወኑን ያወሱት ኃላፊው 15ሺ በአሸዋ የተሞላ ማዳበሪያ  ለ02,08 እና 05 ቀበሌዎች እንዲከፋፈል መደረጉን ተናግረዋል። አክለውም በአጠቃላይ ከመንገድ መንከባከብ ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ ለጎርፍ ተጋላጭነቱን በመቀነስ ረገድ ክፍተቶች እንዳሉና ማህበረሰብ ከስጋት ነፃ እንዳልሆነ ጠቅሰው ክፍተቱ ሊታረም እንደሚገባም ገልፀዋል።

አስተያየት