ሐምሌ 29 ፣ 2013

ጎንደር እንዴት ሰነበተች

City: Gonderወቅታዊ ጉዳዮች

የአማራ ክልል መንግሥት ካወጀው የክተት አዋጅ ከሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር ተዳምሮ በጎንደር ከተማ ማኅበረሰብ ውስጥ እየታየ ያለውን ድባብ የአዲስ ዘይቤ የጎንደር ዘጋቢ በጥቂቱ ዳሷል።

Avatar: Ghion Fentahun
ግዮን ፈንታሁን

ጎንደር እንዴት ሰነበተች

በሰሜን ኢትዮጵያ ተጀምሮ በቅረቡ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የተጀመረው ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል። በጦርነቱ የብዙኃን ነብስ ጠፍቷል፤ ንብረቶችና መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፤ በርከት ያሉ ዜጎች ተሰደዋል እንዲሁም አካል መጉደል ደርሷል።

የፌደራል መንግሥቱ በጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት በኩል በፕሬስ ሴክሬታሪያቷ ቢለኔ ሥዩም አማካኝነት ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በተሰጠው ወቅታዊ ጉዳይን የተመለከተ መግለጫ "የፌደራል መንግሥት አሁንም ተናጠላዊ የተኩስ አቁም ላይ ነው" ተብሏል። በፌደራል መንግሥቱ አሸባሪ ተብሎ የተሰየመው ህወሓትም በአማራና በትግራይ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ላይ ጥቃት እያደረሰ እንዳለ ሴክሬታሪያቷ ተናግረዋል። 

በሌላ በኩል የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ "የመንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት የሚባለው እቃቃ ጨዋታ ነው። ተኩስ የምናቆመው ያስቀመጥነው ቅድመ ሁኔታ ሲሟላ ብቻ ነው" በማለት ጦርነቱን ቀጣይነት የሚያመላክት ነገር ተናግረዋል። በአናቱም "የጠየቅነው ጥያቄ በአግባቡ ካልተመለሰ በጦርነት እናስመልሳለን። ፌደራል መንግሥቱ አጎራባች ክልሎችንና ራሱን መከላከል የሚችልበት አቋም ላይ አይደለም።" በማለት ዛቻ መሰል አስተያየት ሰጥተዋል። አቶ ጌታቸው "ትግራይ ላይ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂው የአማራ ልሂቅ ነው። ለደረሰው እያንዳንዱ  ጥፋትም ሂሳብ እናወራርዳለን" ሲሉ ተደምጠዋል ።

ይህንን የሰሞኑን ወቅታዊ ሁኔታ የአማራ ክልል መንግሥት ካወጀው የክተት አዋጅ ጋር ተዳምሮ በጎንደር ከተማ ማኅበረሰብ ውስጥ እየታየ ያለውን ድባብ የአዲስ ዘይቤ የጎንደር ዘጋቢ በጥቂቱ ዳሷል።

የጎንደር ከተማ ማኅበረሰብ ከሞላ ጎደል በማንነቱ አደጋ እንደተጋረጠበት ያምናል። አደጋውን ለመቀልበስ እንደማያቅማማ ከሁኔታዎቹ መታዘብ ይቻላል፡፡ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ አራዳ፣ ፒያሳ፣ ቡልኮ፣ ሳይንስ አንባ፣ ቼቼላ፣ ኮሌጅ፣ እንኮየ መስክ፣ ማራኪና አዘዞ አካባቢዎች ተዘዋውሮ አሁን ባለው የክልሉ እና የሐገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በኅብረተሰቡ ላይ የፈጠረውን ስሜት ታዝቧል።

በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ ሊባል በሚችል ደረጃ የክልሉ መንግሥት ያወጀውን የክተት አዋጅ በበጎ ጎኑ እንደተመለከቱት የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አሉ። ሰዎች ሰብሰብ ብለው በተቀመጡበት ቦታ ቀዳሚ አጀንዳቸው "የሰሜኑ ጦርነት" ነው። በየአካባቢው በሚገኙ ጎዳናዎች የጀበና ቡና ሊጠጡ የተሰበሰቡ ሰዎች፣ በሬስቶራንት ምግብ ለመብላት ማዕድ የከበቡ ግለሰቦች፣ ታክሲ ውስጥ ጎን ለጎን የተቀመጡ ተሳፋሪዎች፣ ከመሸ መጠጥ ቤት ሰብሰብ ብለው የሚጨዋወቱ ጓደኛሞች፣ ገበያ ውስጥ የሚነጋገሩ ገበያተኞች፣ የ"ATM" አገልግሎት እየተጠቀሙ የሚነጋገሩ ወዳጆች፣ ሆስፒታል ውስጥ ለህክምና መጥተው ወግ ቢጤ የጀመሩ ታካሚዎች ዋነኛ አጀንዳቸው ስለጦርነቱና ስለወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁነት ሆኗል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ከድር ያሲን ስስለወቅታዊው ሁኔታ፣ ስለ ክተት አዋጁ አና አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ "የአማራ ልሂቃን ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን" ማለታቸውን ተከትሎ ጠቅለል ያለ ሐሳብ ያነሳሉ።

"ክልሉ ያወጀው የክተት አዋጅ እጅግ አስፈላጊ ውሳኔ ነው።" በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ፤ ሀሳባቸውን ይቀጥላሉ። "አማራ ዳግም የህወሓት የግፍ ሰለባ አይሆንም። የክተት አዋጁ ሁሉን አማራ ይመለከታል። ለአማራ ህልውና መስዋዕትነት መክፈል ብጽእነት ነው። እኛ የዩኒቨርሲቲው መምህራን አማራ ለሚያደርገው ራስን የመከላከል ፍትሃዊ ጦርነት ደሞዝና እውቀታችንን በመለገስ ላይ ነን። ወደ ግንባር የዘመቱ ጓደኞቻችንም አሉ” በማለት ያብራራሉ።

በሌላ በኩል አራዳ ሰፈር የጀበና ቡና እየጠጡ አዲስ ዘይቤ ያገኘቻቸው አቶ መልካሙ ተፈሪ ከአዲስ ዘይቤ ለተነሳላቸው መሰል ጥያቄ  "የክልሉን የክተት አዋጅ ተቀብለን ልጆቻችንን ወደ ግንባር የላክነው መርቀን ነው፤ ደስ ብሎን ልከናቸዋል፤ ማንነታችንን ዳግም አሳልፈን አንሰጥም።" ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። 

በሁሉም የጎንደር የመኖርያ ሰፈሮች ያለው ወቅታዊ ድባብ ተመሳሳይ መሆኑን እና በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ጆሮ እንደማይሰጥ እና “ህወሓት ዳግም ተመልሶ ጉዳት እንዳያደርስ” ሁሉም በየፊናው የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ ይናገራል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ዘመቻውን ለማገዝ የማስተባበር ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በጋራ ጥረቱ ወደ ግንባር የሚዘምቱ ብዛት ያላቸው ፋኖ እና ሚሊሻዎችን ማግኘት ተችሏል፡፡ እናቶችም ለታጋዮች የሚሆን ስንቅ (ዳቦ ቆሎ፣ በሶና የመሳሰሉት) በማዘጋጀት ላይ እንደሆኑ ከአካባቢው የሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ግንባር ለመዝመት የሚመዘገበውን፣ ወርሃዊ ደሞዙን የሚለግሰውን ጨማሮ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችም ከጥሬ ገንዘብ በተጨማሪ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በማበርከት ላይ እንደሆኑ መታዘብ ይቻላል፡፡ ከድምር ውጤቱ የከተማው ነዋሪ ማኅበረሰብ በወቅታዊውን የፖለቲካ ድባብ በንቃት በመከታተል ላይ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል። 

አዘዞ ከተማ ውስጥ በንግድ ሥራቸው ላይ እንዳሉ ያገኘናቸው አባት ለአዲስ ዘይቤ የጎንደር ዘጋቢ አስተያየታቸውን ሲሰጡ "እኛ ሰላም እንፈልጋለን፤ ጦርነት ለማናችንም አይጠቅመንም። አንድ ሀገር ላይ ተስማምቶ፣ ተከባብሮ በሰላም መኖር የተሻለ ነበር። እኔ ካልገዛሁ፣ እኔ ካልበደልኩ ሰላም የለም የሚል ኃይል እንደ ህዝብ ፈልገን ሳይሆን ተገደን በገባንበት ጦርነት ህልውናችንን እናረጋግጣለን።  እግዚአብሔር ለሀገራችን ሰላሙን ያምጣላት።" ብለዋል፡፡

አስተያየት