ሐምሌ 30 ፣ 2013

የሸቀጦች የዋጋ ንረት በጎንደር

City: Gonderገበያኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማው መባባሱን ያመለከተውን የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲን መረጃ መነሻ በማድረግ በጎንደር ከተማ ያለውን የሸቀጦች ዋጋና የማኅበረሰቡን አቀባበል በጥቂቱ እንዳስሳለን።

Avatar: Ghion Fentahun
ግዮን ፈንታሁን

የሸቀጦች የዋጋ ንረት በጎንደር

በሃምሌ  ወር 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ  የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት 26.4 በመቶ እንደነበር የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በሳምንቱ አጋማሽ ባወጣው መረጃ አመላክቷል። የዋጋ ግሽበቱ 24.5 በመቶ ከነበረው ቀዳሚ ወር የሁለት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ኤጀንሲው ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡ የሃምሌ ወር የምግብ ዋጋ ንረት የአስር ዓመቱን ከፍተኛ 32 በመቶ በመሆን አስመዝግቧል፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችም እንዲሁ 19 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን ሪፖርቱ ያሳያል። 

በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪው መባባሱን ያመለከተው ኤጀንሲው መረጃን መነሻ በማድረግ በጎንደር ከተማ ያለውን የሸቀጦች ዋጋና የማኅበረሰቡን አቀባበል በጥቂቱ እንዳስሳለን።

በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አበቡ የኑሮውን ሁኔታ አስመልክተው «ኑሮ አልጨበጥ ብሏል። በነጋ በጠባ መጨመር እንጅ መቀነስ የለም። ዛሬ ላይ ኩንታል ጤፍ አምስት ሺ ይባላል። የበርበሬ፣ የአተር፣ የምስር፣ የስኳር ዋጋም ንሯል፡፡ ጎመንና ቃሪያ እንኳን የበዓል ምግብ ሊሆኑ ምንም አልቀራቸው» በማለት የኑሮ ውድነቱ ከአቅማቸው በላይ እየሆነ እንደሆነ ተስፋ በቆረጠ አንደበት ለአዲስ ዘይቤ አስተያየት ሰጥተዋል። የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ በገበያዎች ተዘዋውሮ የጥቂት ሸቀጦችን ዋጋ ባጣራው መሰረት ጤፍ በኩንታል 4ሺህ 5መቶ በላይ፣ 5 ሊትር ፈሳሽ ዘይት 630፣ 1 ኪሎ ስኳር 70፣ ሽንኩርት በኪሎ 25፣ 1 ኪሎ ድንች 18፣ ምስር በኪሎ 100 ብር፣ ደረቅ እንጀራ 10 ብር፣ 1 ኪሎ በርበሬ 350 እና ኪሎ ስጋ 400 ብር እንደሚሸጥ ተመልክቷል። ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ ግን ካለፈው ወር ጋር በተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ዋጋ እየተሸጡ እንደሚገኙ የከተማው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ይሁን እንጂ በአልኮል፣ በአልባሳት፣ በግንባታ እቃዎች፣ መድሃኒትና ጌጣጌጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አዲስ ዘይቤ አረጋግጣለች።

ወ/ሮ ሀሊማ ዳውድ በችርቻሮ ንግድ የተሰማሩ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው። ልጓም አልባ የሚመስለው የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ምክንያቱ ምን እንደሆነ መረዳት እንደቸገራቸው ይናገራሉ። «እኔ የማውቀው ነገር የለም። እኛ ከአካፋፋዮች ነው ሸቀጥ የምናመጣው። እነሱ ዋጋ ሲጨምሩብን እኛም እንጨምራለን። አከፋፋዮች ከላይ ዋጋው ስለጨመረ የዋጋ ማስተካከያ አድርገናል ይሉናል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ከዋጋው ይልቅ የሸቀጡ መገኘት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሸቀጥ እንደበፊቱ እንደልብ ይገኝም። ያውም ጥዋትና ከሰዓት ዋጋ እየጨመረ በቂ ሸቀጥ የለም። ከቤሳ ምላጭ ጀምሮ ምንም ያልጨመረ ነገር የለምኮ። ወላሂ ሰው ግን እንዴት አንጀት እንደሚበላ። የያዘውን ብር ምኑን ከምን እንደሚያደርገው ግራ ሲጋባ ማየት እንደ ነጋዴ ሆኖ ላየው ሰው ያሳዝናል” ሲሉ ሃሳባቸውን ለአዲስ ዘይቤ አጋርተዋል። 

«እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት መነሻው ከየት ነው?» በማለት በአንድ አማካሪ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩት የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መስፍን አትርሳው አዲስ ዘይቤ አነጋግራቸዋለች። “ለኑሮ ውድነት መባባስ ቀዳሚው ምክንያት በተከታታይ እያደገ የመጣው የዋጋ ግሽበት ነው። የሸቀጦች ዋጋ በተከታታይነት ማደግ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላለው ማኅበረሰብ ፈተና ነው።” ይላሉ ዶ/ር መስፍን።

“የምርት መቀነስ፣ የአቅርቦት ከፍላጎት ጋር አለመመጣጠን፤ የዓለምአቀፉ የኢኮኖሚ ስርዓት ኮቪድን በመሰሉ የተለያዩ ምክንያቶች አለመረጋጋት፣ ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ምስቅልቅሎሽ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የብር የመግዛት አቅም መዳከም ለገበያ ዋጋ መናርና ለኑሮ ውድነት አባባሽ ምክንያቶች ናቸው” ይላሉ ዶ/ር መስፍን።

ዶ/ር መስፍን መፍትሔ የሚሉትን ሐሳብ እንዲህ አስቀምጠዋል። “በመጀመርያ የሀገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት መመለስ አለበት። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ሰላም ሲኖር ተረጋግቶ መስራት፣ ማምረትና ያመረቱትን ወደ ተጠቃሚው በአግባቡ ማሰራጨት ይቻላል። ንግድ የሚሳለጠው፣ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚጨምረው፣ ጥቅል ዓመታዊ ምርት እድገት የሚያሳየው ሰላም ሲረጋገጥ ነው። በሌላ በኩል የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሚጨምሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በጥቅሉ የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመፍታት መዋቅራዊ የሆነ የኢኮኖሚ ስርዓት ማሻሻያ ያስፈልጋል” ብለዋል ዶ/ር መስፍን። 

በመጨረሻም “ሕብረተሰቡ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት በመንግሥት በኩል ከሚጠበቀው ማሻሻያ ባሻገር የቀደመ የመሰረታዊ የሸቀጥ አጠቃቀሙን መከለስ ይጠበቅበታል። ለብክነት የሚዳርግ አጠቃቀምን ማስወገድ ያስፈልጋል” በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

አስተያየት