ሐምሌ 29 ፣ 2013

ትኩረት የተነፈገው የድሬዳዋ ከተማ ጽዳት

City: Dire Dawaአካባቢማህበራዊ ጉዳዮች

በግልጽም ሆነ በስውር ቆሻሻ ያለከልካይ የሚጣልባቸው አካባቢዎች የከተማዋን ጽዳት በከፍተኛ ሁኔታ የበደሉ ስለመሆናቸው ሪፖርተራችን በከተማዋ ተዟዙራ ባካሄደችው ቅኝት ታዝባለች፡፡

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ትኩረት የተነፈገው የድሬዳዋ ከተማ ጽዳት

ድሬዳዋ ከምትታወቅባቸው መገለጫዎቿ ውስጥ አንዱ ጽዳቷ እንደነበር ቀደምት ነዋሪዎቿ ይመሰክራሉ፡፡ ከ62 ዓመት በላይ በድሬዳዋ ከተማ የኖሩት ወ/ሮ እመቤት ተወልደብርሃን “በጽዳቷ ከአስመራ ከተማ ቀጥሎ በሁለተኝነት የምትቀመጠው ድሬዳዋ ነበረች” ይላሉ፡፡ ወ/ሮ እመቤት ከተማዋ ጽዱ የነበረችበትን ምክንያት ሲያብራሩ ኃላፊዎች ለጽዳት የነበራቸው ትኩረት መሆኑን አጽንኦት ይሰጡበታል፡፡ ከምድር ባቡር ትራንስፖርት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለጉብኝት የሚመርጧት ከተማ እንደመሆኗ በጎ ገጽታዋን ላለማጠልሸት የሚጥሩ የአስተዳደር ሰዎች ስለበሯት ነው የሚለው የአስተያየት ሰጪአችን ሐሳብ ነው፡፡

ከነምበር ዋን ወደ አሸዋ በሚወስደው መንገድ ልባሽ ጨርቆች መሸጫ አካባቢ፣ ወደ አሸዋ ገበያ መግቢያና መውጫ አካባቢ፣ ከኮኔል ወደ ከዚራ በሚደስደው ድልድይ፣ ወደ ሳቢያን መሻገርያ አካባቢ፣ ከቀፊራ የገበያ ስፍራ በላይ በኩል፣ የጎርፍ መከላከያ ግድቡ ያለበት አካባቢ፣ ከሺሊሌ የክርስቲያን መቃብር ወደ ገንደገራዳ የሚወስደው ድልድይ፣ ከኮካኮላ ፋብሪካ ወደ ደቻቱ መተላለፊያ የአስፓልቱ መግቢያና መውጫ፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉሙሩክ ግቢ አጥር ስር፣ ሳቢያን አንበጣ መከላከያን ይዞ እስከ ሰኢዶ ጫፍ በቱቦ ውሀ መውረጃ፣ መልካ ቀበሌ 09 ድልድዩን ተሻግሮ ት/ቤት አጥር  ቆሻሻ በብዛት የሚገኝባቸው የከተማዋ መንደሮች ናቸው፡፡  

በግልጽም ሆነ በስውር ቆሻሻ ያለከልካይ የሚጣልባቸው እነዚህ አካባቢዎች የከተማዋን ጽዳት በከፍተኛ ሁኔታ የበደሉ ስለመሆናቸው ሪፖርተራችን በከተማዋ ተዟዙራ ባካሄደችው ቅኝት ታዝባለች፡፡

በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የከተማዋን ጽዳት መጓደል አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡን ታዛቢዎች የጽዳት መጓደሉን አስከትለዋል ብለው የሚያምኗቸውን የተለያዩ ምክንያቶች ዘርዝረዋል፡፡

ለከተማዋ ነዋሪ የጤና ጠንቅ እየሆነ ያለው አሁን ላይ የሚታየውን በከፍተኛ ደረጃ ለአካባቢ ፅዳትና ለከተማዋ ውበት መጥፎ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ የሚገኘው ቆሻሻን በየቦታው መጣል፣ በየጥጋጥጉ መፀዳዳትና የፍሳሽ ቆሻሻን ወደ መተላለፊያ መንገድ መልቀቅ በድሬደዋ ከተማ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ 

የተጠራቀመው ቆሻሻ ከሙቀቱ ጋር ተዳምሮ በሽታ አስተላላፊ ዝምብ እና ትንኞችን ያመጣል፡፡ ሽታ የፈጠረው ያቆረ ውሃ የፈጠራቸው ትንኞች እንደ ወባ፣ ነግዲ (በነፍሳት አማካኝነት የሚተላለፍ ሰውን እና እንስሳትን የሚያጠቃ በሽታ)፣ ችጉንጉንያ (በነፍሳት አማካኝነት የሚተላፍ፣ ሰዎችን የሚያጠቃ፣ በሙቀት አካባቢዎች ባሉ ሐገሮች የሚከሰት መድሃኒት የሌለው በሽታ) እና ይህንን የመሳሰሉ ሞቃታማውን የአየር ጠባይ እንደ ምቹ ሁኔታ የሚጠቀሙ በሽታዎች ያስከትላል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 3 ወ/ሮ መኩ ቤት ለቤት በመዞር ቆሻሻ በመሰብሰብ ሥራ ላይ ተሰማርታለች፡፡ በየእለቱ የጸዳ አካባቢ ለመመልከት ብትደክምም ሐሳቧ ባለመሳካቱ ትቆጫለች፡፡ የጽዳት ሰራተኞች ቁጥር እና ለጽዳት ሥራው የሚያዘው በጀት በየጊዜው የሚጨምረውን የከተማዋን ሕዝብ ብዛት ያላገናዘበ እንደሆነ ነግራናለች፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል የከተማዋን ሕዘብ በማስተባበር የጽዳት የዘመቻ ሥራዎች ቢካሄዱ ይበጃል የሚል ሐሳብ አላት፡፡

ይሄው የከተማዋን ፅዳት መጓደል ተከትሎ የሚስተዋሉ አሉታዊ ድርጊቶች ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ በየእለት ተለት እንቅስቃሴ የሚያስተውለው በተለይ በከተማዋ ዋና ዋና ከሚባሉት አካባቢዎች አውራ መንገዶች፣ የታክሲ እና ባጃጅ መነሻና መድረሻዎች፣ ህዝብ በሚበዛባቸው የመገበያያ ቦታዎች፣ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ ከንግድ ድርጅቶች ከሆቴሎችና ከመሳሰሉት በምን ቸገረኝ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ያለአግባብ የሚጣሉት ቆሻሻዎች የከተማዋን ነዋሪ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡

ከከተማዋ መስፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የህዝብ ቁጥር መጨመር ታሳቢ አድርጎ የቁሻሻ መጣያዎች በየቅርብ ርቀቱ ሊኖር ይገባ ነበር ሲል ቁጭቱን የገለፀው ናትናኤል ሀሰን የተባለ የድሬደዋ ነዋሪ በየአካባቢው የተጠራቀመ ቆሻሻ ማየት የተለመደ እንደሆነ ገልፆ የሕብረተሰቡ ለቆሻሻ ያላው ግዴለሽነት እንዳለ ሆኖ በቆሻሻ አወጋገድ ዙርያም እንዳስተዳደርም ችግር እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በከተማዋም ፍሳሽ የሚተላለፍበት መውረጃ ቦይ አሁን ላይ የለም የሚያስብል ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ይህ መሆኑ ለከተማዋ የፅዳት መጓደል አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግሯል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ገብርኤሏ መስፍን የተባለች የድሬደዋ ነዋሪ በየአካባቢው የህዝብ መፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ መንገድ ላይ የሚፀዳዳ ሰው እንዲኖር አድርጓል ስትል የገለፀች ሲሆን እነዚህ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ቢሰሩ ግን የተወሰነ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ትገልፃለች። 

ለዓመታት በየአካባቢው የተከማቸውን የቆሻሻ ክምር የማስወገድ ስራ በዋነኝነት የሚመለከተው የድሬደዋ አስተዳደር የጽዳትና ውበት ኤጀንሲን እንደመሆኑ የተነሱትን ቅሬታዎች አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን አቶ ሺመልስ ዘውዴን በስልክ መስመራችን ላይ አግኝተናቸዋል፡፡ አቶ ሺመልስ የድሬዳዋ ከተማ የጽዳት እና ውበት ኤጀንሲ የትምህርት እና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው፡፡ የከተማዋን ጽዳት አስመልክቶ የተነሳውን ቅሬታ አስመልክተው በሰጡን ማብራሪያ በከተማዋ ሁሉም ቀበሌዎች ተዘዋውረው ቤት ለቤት የቆሻሻ ማንሳት ስራ የሚሰሩ 16 ማኅበራት መኖራቸውን በማስቀደም ነው፡፡ በውስጣቸው 900 አባላትን የያዙት ማኅበራቱ ከጽዳት እና ውበት ቢሮ የሚቀርቡላቸውን 15 ተሽከርካሪዎች በመጠቀም ደረቅ ቆሻሻ ይሰበስባሉ፡፡ በግል የተሰማራ የቆሻሻ አንሺ ድርጅትም በ5 ተሽከርካሪዎች ታግዞ የከተማዋን እለታዊ ደረቅ ቆሻሻ እያነሳ ስለመሆኑ ነግረውናል፡፡

በ2006 ዓ.ም. የተጀመረው ይህ ተግባር እስከያዝነው ዓመት ድረስ እየቀጠለ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ለውጥ አልመጣም ስለመባሉ አንስተን ለጠየቅናቸው ሲመልሱ “ለከተማዋ ጽዳት ኃላፊነት ያለበት የሚያጸዳው አካል ብቻ አይደለም ነዋሪውም ነው፡፡ ነዋሪው ቆሻሻውን በአግባቡ ቢጥል ችግሩን ለማቃለል የራሱን ድርሻ ይወጣል፡፡ ቶሎ ቶሎ ማንሳት ላይም ልንበረታ ይገባል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቢሯቸው ቆሻሻን ከማንሳት እና ነዋሪዎች ስለ ቆሻሻ አወጋገድ እንዲገነዘቡ ከማስተማር በዘለለ አጥፊዎችን መቅጣት እንደማይችል ጠቅሰው ሕግ ማስከበር ቢሮ ሕግ በሚተላለፉ ወገኖች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ በዚህ አጋጣሚ ጠይቀዋል፡፡ ከፍተኛ የቆሻሻ ክምችት ካለባቸው የከተማዋ አካባቢዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የአሸዋ ገበያ መግቢያ እና መውጫን ጨምሮ ሙሉውን ለማጽዳት እንዲቻልም ከሐሮማያ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር በማስጠናት ላይ እንደሚገኝም ሰምተናል፡፡ 

አስተያየት