ሐምሌ 28 ፣ 2013

በየጊዜው እየናረ የሚሄደው የባህላዊ አልባሳት ዋጋ

ባህል ንግድ

የባህላዊ አልባሳት ዋጋ እየናረ በመምጣቱ ሸማቾች ከግዢ ይልቅ ኪራይን እንደ አማራጭ መውሰዳቸው ይነገራል።

በየጊዜው እየናረ የሚሄደው የባህላዊ አልባሳት ዋጋ

በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አከባቢ ለሰርግ ሥነ ስረዓት የሚሆን ባህላዊ ልብስ ለመግዛት ወስነው የተለያዩ ሱቆችን ተዘዋውረው ያዩ 3 ሰዎች በልብሶቹ ዋጋ መናር ምክንያት የመግዛት ሃሳባቸውን ቀይረው ለመከራያት እንደወሰኑ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል። 1 የሀበሻ ቀሚስ ዋጋ ከ5 እና 6ሺ ብር በላይ በመሆኑ ሸማቾቹ ኪራይን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል።

''ምንም እንኳን መከራየቱ የተሻለ ቢሆንም የኪራይ ዋጋ ግን ርካሽ የሚባል አይደለም፤ ለ1 ቀሚስ  800 ብር ነው የከፈልነው  ከ1 እና 2 አመት በፊት በግማሽ ይቀንስ ነበር'' ትላለች ከሰርገኞቹ መካከል የሆነችው እያየሽ አዱኛ።

ሽሮሜዳ አካባቢ በባህላዊ ልብስ ሽያጭ ላይ የተሰማራው ዳዊት አየለ የሁሉም ማህበረሰብ የመግዛት አቅምን ያገናዘበ አቅርቦት እንዳለ ጠቅሶ ዋጋቸው ከፍ የሚሉት የባህል አልባሳት በእጅ የተጠለፉት እንደሆኑ ይናገራል።

መርካቶ ሸማ ተራ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የባህላዊ አልባሳት መሸጫ ሱቅ የሚያስተዳድረው ልኡል ተፈሪ የዳዊትን ሀሳብ ይጋራል። ልኡል የሴቶች ባህላዊ ቀሚስ ከ1ሺ 500 ብር ጀምሮ እስከ 15ሺህ ብር ይሸጣል። የወንዶች አልባሳት ዋጋ ከሴቶቹ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ እንደሆነ የሚናገረው ልኡል ከ1,000 ብር ጀምሮ እስከ 2, 300 ብር ዋጋ ያላቸው አልባሳት በሱቁ ይሸጣሉ። የባህላዊ  ልብሶቹን የዋጋ ልዩነት ምክንያትም ሲያብራራ

''ደንበኞቻችን በእጅ የተጠለፈ የሀበሻ ልብስ ይመርጣሉ'' ይላል ልኡል አክሎም በልብሱ ላይ የሚጠለፈው ጥልፍ የሚይዘው የቦታ ስፋት በዋጋው ላይ መበላለጥ እንደሚያመጣ ይናገራል። በእጃቸው ለሚጠልፉት ሰዎች ለአንድ ልብስ ከ3 እስከ 4ሺ ብር እንደሚከፈል የሚናገረው ልኡል እንደምክንያትም የጥልፍ ስራ 1 እና 2 ሳምንት ጊዜ በመፍጀቱ ሳቢያ መሆኑን ይጠቅሳል። ነገር ግን በሲንጀር (የመስፊያ ማሽን) የሚጠለፉ አልባሳት በእጅ ከሚሰሩት ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ቅናሽ እንዳለውም አክሎ ያብራራል የባህላዊ ልብስ ነጋዴው።

ነጋዴው እንደሚናገረው የባህላዊ ልብስ የሚወደደው ከሽመናው ጀምሮ ጥልፍ እስከሚጠለፍበት ያለው ሂደት በባህላዊ መንገድ በእጅ የሚሰራው ስራ በመብዛቱ ሲሆን አልባሳቱን ለመስራት የሚያስፈልጉ ግብአቶችም የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸው እንደ ምክንያት ይጠቅሳል። ለምሳሌ ያህል በ15 ቀናት ውስጥ አንድ በትንሽ መጠን የተጠቀለለ ክር ከ40 ብር ወደ 80 ብር ማደጉን እንዲሁም 1 ሜትር ሻማ ጨርቅ ከ50 እና 60 ብር ወደ 70 ብር ከፍ ማለቱን ነጋዴው ይናገራል።

ባህላዊ ልብስ ከሌሎች አልባሳት ተለይቶ እንዲወደድ ያደረገው ጉዳይ ግብአት ከሆነ ሌሎች አልባሳት የሚጠቀሙበት የጨርቅ አይነት እና አሰራር ተጠቅሞ መስራት አይቻልም? ለሚለው ጥያቄያችን "በእርግጥ በጣም የሚወደደው የሚሰራበት ጨርቅ እና ጥልፋ በእጅ ስለሚሰራ ይመስለኛል። ሌላ ልብስ በሚሰራበት ጨርቅ ቢሰራ ለምሳሌ በተለምዶ የቻይና በምንለው ጨርቅ ቢሆን ልብሱ ይኮማተራል!" በማለት ምላሽ ሰጥቶናል ልኡል።

የልብስ ነጋዴው ልኡል አያይዞም ሸማኔው በባህላዊ መንገድ የሚሰራው ጨርቅ እየተለወጠ በልብስ መስሪያ እየታገዘ መስራት መጀመሩን ጠቁሞ ገንዘቡ ከመቀነስ ይልቅ መጨመር ለእሱም ጥያቄ መሆኑን ነግሮናል። እንዲሁም ነጋዴው እንደሚለው ከጨርቁ ባለፈ  ህብረተሰቡም በጥልፍ መስሪያ(ሲንጀር) ለመግዛት ብዙም ፍላጎት አለመኖሩ እና ነጋዴው ተመሳሳይ ምርት በቦታ ልዩነት ብቻ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ለልብሱ መወደድ ሌላ ምክንያት ነው።

ቦሌ መድሀኒአለም ህንፃ ላይ ብርቅ ዲዛይን ውስጥ በሽያጭ ላይ ያገኘናት ዲዛይነር ሩት ተስፋዬ ቦታው በራሱ ከሽሮሜዳ እና መርካቶ አከባቢ ከሚሸጠው ባህላዊ ልብስ አንፃር ልዩነት እንደሚፈጥር ትናገራለች። የወንዶች አልባሳት ከ3ሺ ጅምሮ እስከ 6ሺ ብር እና የሴቶች ባህላዊ ቀሚሶች ከ6ሺ ብር እስከ 17ሺ ብር የሚሸጡ አልባሳትን በሱቁ አስጎብኝታናለች ዲዛይነሯ።

እንደ ምክንያት የምታነሳው የልብሶቹ ጥራት ስለሚለያይ እና ለሽያጭ ቦታው ለኪራይ የሚከፈለው ገንዘብ ብልጫ ስላለው ነው።

ሽሮሜዳ በጥቃቅን እና አነስተኛ በመደራጀት ከሸማኔዎች ጨርቅ በመቀበል ጥልፍ በማስጠለፍ እና ለነጋዴዎች በመሸጥ፣ በእራሱ ሱቅ ባህላዊ አልባሳትን በመሸጥ ስራ የሚተዳደረው ታሪኩ ካሳ፤ የተሰራ ጨርቅ ከሸማኔ ተቀብሎ በተለያየ ቅርፅ ጥልፍ በመስራት ለመለበስ ዝግጁ የሆነ ልብስ እንደሚያዘጋጅ ይናገራል።

ታሪኩ ከሸማኔ ጨርቆችን የሚገዛው ከ3ሺ እስከ 14ሺ ብር ሲሆን ለምሳሌ መነን የሚባለውን ጨርቅ በ1ሺ 5መቶ ብር ይገዛል ከእዛም ለጥልፍ 1ሺ 2መቶ ብር ይወጣበታል። ነገር ግን ይህን ልብስ ታሪኩ ለነጋዴ የሚያስረክበው በ3ሺ ብር መሆኑን እና ትርፋቸው 3መቶ ብር ብቻ መሆኑን ነግሮናል።

ታሪኩ እንደሚናገረው ከ2ወራት በፊት 8 እና 10ሺ ከሸማኔው ይገዙ የነበሩ ልብሶች ናቸው አሁን 14ሺ ብር እየተገዙ የሚገኙት። እንዲሁም 4መቶ ብር ይሸጥ የነበረ ክር ወደ 1,200 ብር ከፍ ብሏል። "አሁን አሁን የእጅ ጥልፍ ወደ ማሽን እየተቀየረ መጥቷል" የሚለው ታሪኩ ጠላፊ ሰው ቀጥሮ ማሰራት ከእቃዎቹ መወደድ ጋር ተደማምሮ ስራውን አክብዶታል ይላል።

"ከ3 ወር በፊት በ12 ብር ይሸጥ የነበረ ክር 40 ብር ገብቷል" የሚለው እና የግብአት መወደድን የሚያብራራው ደስታ ደሳለኝ ወለቴ አከባቢ በሽመና ስራ የተሰማራ ግለሰብ ነው። ድር እና ማግ ላይም የ17 ብር ጭማሪ መኖሩን የሚናገረው ደስታ አንድ ልብስ ተመርቶ ሲቀርብ ከሽያጩ ይልቅ የወጣው የጥሬ እቃ ገንዘብ እንደሚበልጥ ይናገራል። 7መቶ ብር የሚሸጥ ባህላዊ ልብስ 320ብር ለጥሬ እቃ እና 6መቶ ብር ለጉልበት ሰራተኛ ማውጣቱን እንደምሳሌ በመጥቀስ ሸማኔው ኪሳራ ውስጥ ነው ይላል።

ከፍተኛ ዋጋ አለው ተብሎ የሚጠራው በ5ሺብር ለነጋዴው የሚሸጥ ልብስ ለ1ወር ያህል ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን ይህም ልብሱ የሚሰራበት መንገድ በባህላዊ ሽመና ስለሆነ ነው ይላል ደስታ። በተጨማሪም ለ1ወር የሚሰራው ልብስ ሌላ አጋዥ ሰሪ ሰው ሳይቀጠር እራሱ ደስታ ሰርቶ የሚያተርፈው ትርፍ ከ2ሺ ብር አያልፍም።

ደስታ እንደሚለው በልብስ መስሪያ ማሽን (ሲንጀር) በ1 ቀን የሚጠልፍ እና ለ1ወር ሽመና የሚሰራ ሰው ተመሳሳይ ገንዘብ ነው የሚያገኘው። እንዲሁም የባህላዊ ልብስ ውድ እንዲሆን ያደረገው በሻጭ እና ገዢ መሀል ሚሰራው ደላላ እንዲሁም ነጋዴ መሆኑን ደስታ ተናግሯል።

"የሽመና ስራ ኪሳራ ነው፣ ብዙ ሸማኔዎች ህይወታቸውን መግፋት ከብዷቸው ወደ ክፍለ ሀገር እየሄዱ ነው" የሚለው ደስታ የአዲስአበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ በ2004 ዓ.ም ሸማኔውን ከውጭ ሀገራት ጋር የገበያ ትስስር እንደሚኖር ያበሰራቸውን ዜና ምን ላይ እንደደረሰ ምላሽ እንዲሰጥ እንዲሁም በጥሬ እቃ ገበያ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ጥያቄ ያቀርባል።

አስተያየት