ነሐሴ 24 ፣ 2014

ዕድሜ ጠገቦቹ የጎንደር የኤሌትሪክ ምሰሶዎች

City: Gonderታሪክከተማ

ጎንደር ከተማ እየተስፋፋች፣ አዳዲስ የመንገድ ስራዎች በተሰሩባቸው ጊዜያት አብዛኛዎቹ ምሰሶዎች ተነቅለው ወድቀዋል

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ዕድሜ ጠገቦቹ የጎንደር የኤሌትሪክ ምሰሶዎች
Camera Icon

ፎቶ፡ ጌታሁን አስናቀ ( አሁንም አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙት የጎንደር እድሜ ጠገብ የኤሌትሪክ ምሰሶዎች)

የጎንደር ከተማን እየጎበኘ ላለ ሰው ትኩረቱን ከሚስበው ጥንታዊው የፋሲል ግቢ በተጨማሪ በከተማው ካሉ ጥንታዊ ገፅታዎች መካከል በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተተከሉት ከ200 በላይ እድሜ ጠገብ የኤሌክትሪክ የብረት ምሰሶዎች ይገኙበታል።

በዚያን ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ የተተከሉት የብረት ምሰሶዎች አብዛኛዎቹ አራት ማዕዘን ቅርጽ አላቸው። አራት ቋሚ ብረቶችን በአንድ ላይ አጣምረው ወጥረው የያዙ ጠንካራ ብረቶች አሏቸው። አንዳንዶቹም የአሁኑን ዘመን ምሰሶ ቅርጽ የያዙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጎንደር ከተማ የመብራት አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ አዳዲስ ምሰሶዎችን ቢዘረጋም በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ አንዳንድ ምሰሶዎችም ጠንካራ ከመሆናቸው የተነሳ እስካሁን ድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። 

ከፒያሳ እስከ አራዳ፣ ከፋሲል ክ/ከተማ እስከ ዞብል ክ/ከተማ እንዲሁም የጎንደር አቢያተ ክርስቲያናት ባሉባቸው ቦታዎች እነዚህ ምሰሶዎች በብዛት ይገኛሉ። አሁንም መሃል ፒያሳ ከኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ የሚገኘውን የአጼ ቴዎድሮስን አደባባይ በብርሃን ያደመቀው ምሰሶ በአጼ ሃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ መሆኑን አንጋፋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ጎንደር ከተማ እየተስፋፋች፣ አዳዲስ የመንገድ ስራዎች በተሰሩባቸው ጊዜያት አብዛኛዎቹ ምሰሶዎች ተነቅለው ወድቀዋል። 

ከአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምረው አገልግሎት ሲሰጡት የነበሩትን ጠንካራና እድሜ ጠገብ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን የከተማዋን ህዝብ ትኩረት ያደርግባቸው እንደሆነ ለመታዘብ አዲስ ዘይቤ ተዟዙራ ለመቃኘት ሞክራለች። ሆኖም አብዛኛዎቹ ነዋሪያን እነዚህን ምሰሶዎች አስታውለዋቸው እንደማያውቁ ይናገራሉ።  

ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ምሰሶዎቹ እንደቅርስ እንዲታዩ ለማድረግ ማሰባቸውን ገልፀው እስካሁን ድረስ ግን በዚህ መልኩ እውቅና እንዳልተሰጣቸው ነግረውናል። 

በከተማዋ የሚገኙት እነዚህ እድሜ ጠገብ በርካታ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች አሁን በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላስተዋላቸው ቀልብን ይስባሉ፣ ትዝታን ያጭራሉ። 

በከተማዋ ከእነዚህ ጥንታዊው ምሰሶዎች በተጨማሪ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የእንጨት ምሰሶዎች ሲኖሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክት የእንጨት ምሰሶዎችን ወደ ኮንክሪት ለመቀየር ወደስራ መግባቱን አሳውቋል። ለአዲሱ የኮንክሪት ምሰሶ ኤሌክትሪክ ዝርጋታ ስራ የጥንቶቹን የአጼ ሃይለስላሴ ምሰሶዎችን እንደሚጠቀሙባቸው ታውቋል።

አስተያየት