በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳዉሮና ኮንታ ዞኖች የመብራት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀዉስ መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ሁለቱንም ዞኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርገዉ እና በዳዉሮ ዞን የሚገኘው " አባ" የተባለዉ ትልቁ የኃልይ ማሰራጫ ጣቢያ ላይ በደረሰ ከፍተኛ ብልሽት ምክንያት ከመጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መሉ በሙሉ መቋረጡን ታውቋል ።
የዳዉሮ እና ኮንታ ዞን ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚጠቀሙ እንደ ግንባታ፣ ማሽን፣ የእህል ወፍጮ ቤትና የመሣሠሉት ሥራዎች መቆማቸውን ገልጸዋል።
የዳዉሮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እድሜዓለም እያሱ ማሰራጫ ጣቢያው ላይ ብልሽት በመድረሡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሚያዝያ 6 ጀምሮ መቋረጡንና ችግሩን ለማስተካከል የተደረገው ጥረትም ውጤታማ አይደለም ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
በዳዉሮና አካባቢው በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘዉ ግልገል ጊቤ 3 ወደ 1780 ሜጋ ዋት (MW) ገደማ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለኬንያ ቢያቀርብም በአቅራቢያው ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ኃይል ማቅረብ ነበርበት የሚል ቅሬታ በአካባቢው ነዋሪዎች ይቀርብበታል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ገብሬ በዳዉሮ ዞን "አባ የሚባለው ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ በደረሠ መቃጠል ችግሩ መከሠቱንና መለዋወጫ እቃዎችን ከቦታ ቦታ ለማምጣት ባጋጠሙ ችግሮችና ቴክኒካል ብልሽቶች ችግሩን ለመፍታት ጊዜ መውሠዱን ገልጸዋል።
አቶ ብርሃኑ ከሁለት ቀን ባነሰ ጊዜ ዉስጥ የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለመመለስ የጥገና ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘዉ ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር እንዲዘረጋ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
ሚያዝያ 9 ፣ 2015
በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ዳውሮና ኮንታ ዞኖች ከመጋቢት 6/2015 ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡ ተገልጿል።
አገልግሎቱ የተቋረጠው በዳውሮ ዞን "አባ" ተብሎ በሚጠራው የማሠራጫ ጣቢያ ላይ በደረሠ ብልሽት ምክንያት ነው ተብሏል።