የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ በተከሰተው ከባድ ድርቅ ሳቢያ በ9 ዞኖች የሚገኙ 1,115 ት/ቤቶች መዝጋታቸውና 152 ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መፈናቀላቸውን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ገልጸዋል።
ሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲቃድር መሀመድ "በአብዛኛው የሶማሌ ክልል ነዋሪ ላይ የተደቀነው ድርቅ አደጋ የመማር ማስተማር ሂደቱን ጎድቶታል” ብለዋል።
ኃላፊው በተጨማሪም “ከክልሉ መንግሥት እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን በመርዳት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ ነው” ያሉ ሲሆን የውሃ ማጓጓዣ፣ የምግብና እንስሳት መኖ አቅርቦት እንዲሁም በድርቁ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት መሆነቸውን አንስተዋል፡፡
በድርቁ ምክንያት 395 የ2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን 720 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለህጻናት የትምህርት አገልግሎት መስጠት አልቻሉን ሰምተናል፡፡
የህጻናት አድን ድርጅት (Save the children) በአምስት ዞኖች ከ56,000 በላይ ተማሪዎችን ለመመገብ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ ተማሪዎች ቁጥር ከ152 ሺህ በላይ ሲሆን ይህም ድርቁ ተባብሶ ከቀጠለ ቁጥሩና ጎዳቱ ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል።
በሌላ በኩል በክልሉ ስላለው የተማሪዎች ትምህርት የማቋረጥ መጠን ያነጋገርናቸው አቶ አብዲቃድር መሀመድ ሹክሪ እንደተናገሩት የተማሪዎቹ ትምህርት ማቋረጥ ችግር በ4 ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን እነዚህም ግጭት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እና አርብቶ አደርነት ባህል ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
በዚህም ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት በክልሉ በርካታ የአርብቶ አደር አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ለተማሪዎችን የትምህርት አገልግሎት እሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሶማሊ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲቃድር መሀመድ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ማቋረጡ 14 በመቶ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 6 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች እንደ ቅደምተከተላቸው ወደ 11 በመቶ እና ወደ 5 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተቅዶ እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል።