You can paste your entire post in here, and yes it can get really really long.
"Critical and liberating dialogue, which presupposes action, must be carried on with the oppressed at whatever the stage of their struggle for liberation. The content of that dialogue can and should vary in accordance with historical conditions and the level at which the oppressed perceive reality. But to substitute monologue, slogans, and communiques for dialogue is to attempt to liberate the oppressed with the instruments of domestication. Attempting to liberate the oppressed without their reflective participation in the act of liberation is to treat them as objects which must be saved from a burning building; it is to lead them into the populist pitfall and transform them into masses which can be manipulated". (Paulo Freire; Pedagogy of the Oppressed)*************ከቀናት በፊት የቀድሞው የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን በረከት ስምዖን በደብረ ማርቆስ ከተማ በአንድ ሆቴል ውስጥ አርፎ ይገኛል በሚል በርካታ ወጣቶች ሆቴሉን ከበው አስወጡልን ከማለት አልፈው የእርሱ ነው ያሉትን መኪና አቃጥለዋል፡፡ እንዳሉት ቢያገኙት ወግረው ከመግደል እንደማይመለሱ ከስፍራው ይወጡ የነበሩት ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡*************የኢህአዴግ መንግስት በኤርትራ ተወርሬያለሁ ብሎ ባድመን እና ሌሎች የተወረሩ ቦተዎችን ለማስመለስ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተደረገው ጦርነት ከመቶ ሺህ (ቁጥሩን የሚያስበልጡትም የሚያሳንሱትም አሉ) በላይ ኢትዮጵያውያን ተማግደዋል፡፡ ባድመም አልተመለሰም፣ የሞቱትና የተፈናቀሉትም አልተካሱም፣ ለሆኑት ጥፋቶች ሁሉ ማንም ኃላፊነት አልወሰደም፡፡ ነገር ግን ያለፈው ሙሉ በሙሉ እንደተረሳ ሁሉ ሰሞኑን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሃያ ዓመታት የቆየው ጦርነትና ሽመቃ እንደተጠናቀቀና ሰላማዊ ግንኙነት እንደተጀመረ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች አሳውቀዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ግንኙነቱን አስመልክተው “በፍቅር ያለፈውን ቁርሾ አናስታውስም” ብለው ተናግረዋል፡፡ ጎልተው ባይወጡም በፈንጠዝያው መሃል የፍትሕና የመርህ ጥያቄዎች ግን ከዚህም ከዚያም እየተሰሙ ነው፡፡*************ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና በአማራ ቴሌቭዥን በተላለፉት የታሳሪዎች ስቃይ ምስክርነቶች በኢትዮጵያ ንጹሃን ዜጎች ላይ በእስር ቤቶች ውስጥ የተፈፀሙ ለጆሮ የሚከብዱ ድብደባዎች፣ ግርፋቶች፣ አካል ማጉደሎች ወዘተርፈ... በአጠቃላይ ኢ-ሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶች ተሰምተዋል፡፡ እስካሁን ማንም ኃላፊነት አልወሰደም፡፡*************የሱማሌ ክልል ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌ ደግሞ በሰሞኑ የኢትዮጵያ የለውጥ ግርግር መሃል የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የመጀመሪያ መቶ ቀናትን በማስመልከት በድንገት በተናገረው ንግግር ውስጥ የቀድሞውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን በተመለከተ እንደዘበት የተናገረው ከላይ የተቀነጨበውን የብራዚላዊው ፈላስፋና ምሁር ፓውሎ ፍሬይሬን ዕምቅ ፅሁፍ ይገልፀዋል፡፡ አብዲ ኢሌ እንዲህ ብሏል፤“ይቅር እንባባል ከሆነ…ሁሉን ነገር ይቅር እንባባል፤ [ግን] ይወጣ፡፡”አራቱ የጎጃም (ደብረ ማርቆስ)፣ የአስመራ-አዲስ፣ የኢቲቪ-አማራ ቲቪ፣ እና የሶማሌ ትዕይንቶች ብቻ በቀል፣ ፍትህ፣ ይቅርታ፣ እና እርቅ…የመሳሰሉት ጥያቄዎች በመደመር ተድበስብሰው ሊያልፉ አንደማይችሉ ያስታወሱ ይመስለኛል፡፡ የበረዶው ግግር ጫፍ እንደሚሉት ናቸው፡፡ሽግግሩና ጥያቄዎቹበቅርቡ በኢትዮጵያ የተከናወነውን የስልጣን ሽግግር ተከትሎ አሳሳቢ እና ወሳኝ ከሆኑት መወያያ ጉዳዮች መካከል እንደሀገር ቀጣዩ ጉዞአችን ምን መምሰል አለበት የሚለው ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ጥያቄ ጋርም ተያይዞ ሳይነሳ ሊታለፍ የማይችለው የፍትሕና የእርቅ ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ በኩል ያለፈውን ትቶ የወደፊቱ ላይ ብቻ አተኩሮ መጓዝ ከበቀልና ቂም ይታደጋል የሚል ፍላጎት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያለ ፍትህ፣ እውነትና እርቅ ወደ ፊት መጓዝ አይቻልም የሚል ጉትጎታ የመደበኛና ኢ-መደበኛ ተዋስኦው ማጠንጠኛ ሆነዋል፡፡በእርግጥ የፍትሕና የይቅርታ ጥያቄ ለመጠየቅ የሚያበቃ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርና ዋስትና ተገኝቷል ወይ ብሎ ለሚጠራጠር ሰው አጥጋቢ የሆነ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ማረጋገጫ መስጠት ባይቻልም በተለይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቃለ-መሃላ በፈፀሙበት ቀን ካደረጉት ንግግር ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያነሱት የፍቅር፣ የይቅርታ፣ እና የመደመር ጥሪ፤ እንዲሁም እየታየ ያለው የለውጥ መንፈስ የእርቅና የፍትሕ ጥያቄ ወደ መሃል መድረክ እንዲመጣ፣ ዜጎችም በጥያቄ እንድንወተውት ጋብዟል፡፡የበደል አዙሪትበ1966 ዓ.ም በወጣቶች እና ተማሪዎች ተቀስቅሶ በኢትዮጵያ የተቀጣጠለውን አብዮት ተከትሎ ወታደራዊው የአነስተኛ መኮንኖች ኮሚቴ ደርግ ስልጣኑን በጊዜያዊ አስተዳዳሪነት ሰበብ ሲረከብ ማንም ክፉ ቀን ወይንም መልካም ቀን መጣ ብሎ መደምደም አልቻለም ነበር፡፡ ነገር ግን ደርግ (መንግስቱ ኃ/ማርያም) በይስሙላ ምርመራና ችሎት ስልሳዎቹን የዘውዳዊው ሥርዓት መኳንንትና ባለሟሎች ስብስብ በአንድ ሌት በጥይት ደብድቦ ሲፈጅ ብዙኃኑ የዘመኑ ተራማጆችና ምሁራን የጨለማ ዘመን እንደመጣ መረዳታቸው አልቀረም፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ ሕወሃት/ኢህአዴግ ከ17 ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ሀገር ማስተዳደር ከመጀመሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላትን ሲበትን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አውራ አስተማሪዎችን ሲያባርር እርምጃዎቹን በጥንቃቄ በሚከታተሉት ዘንድ የነበረውን አፈራርሶ ሊጓዝ የቆረጠ ቡድን እንደመጣ ማረጋገጫ ነበር፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት የተከናወኑት ሁለት የመንግሰት ለውጦችን ተከትሎ ከላይ የተጠቀሱትን ዓበይት ማሳያዎችን ጨምሮ የቀደመውን ሥርዓት በጭፍን የማጥፋትና ልሂቃኑን የመበቀል ሌሎች በርካታ አሰቃቂና አሳዛኝ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡በኢትዮጵያ ሰፍኖ በቆየው የኢህአዴግ አምባገነን ሥርዓትም በርካታ ዜጎች ተሰደዋል፣ ተገርፈዋል፣ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፣ በጎዳናዎች ላይ ጥይት ተተኩሶባቸው ተገድለዋል፣ ለአዕምሮ ሕመምተኛነት ተዳርገዋል፣ ሃብትና ንብረታቸውንም ተቀምተዋል፡፡ ሄርዝለር (Hertzler J.O) አምባገንኖች ተቃውሞን በማጥፋትና ስልጣናቸው በማደላደል ፓርላማና ፍርድ ቤቶችን ይቆጣጠራሉ፣ የሃገር ሃብትን ያግበሰብሳሉ፣ የኢኮኖሚ አውታሮችን በሙሉ በእጃቸው ያስገባሉ፣ የውጭ ግንኙነቶችን ይጠቀልላሉ፣ ተቋማትን ያሽመደምዳሉ፤ የደኅንነትና የጦር ኃይልን አፍርሶ በማዋቀር ተቃዋሚዎችን በእስር፣ በማሰቃየት ተግባር፣ በስደትና ግድያ ያስወግዳሉ፣ የመረጃና የመገናኛ መንገዶችን በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ያውላሉ፣ ሕዝብን በማሸበር ፍርሃትን ያሰርፃሉ ብሎ ያብራራው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት እንደተፈፀሙ ማንም ሊክድና ሊያስተባብለው አይችልም፡፡ቢሆንም ለለውጥ የሚታትሩ ኢትዮጵያውያን የሰሞኑ የለውጥ ንፋስ ሳይነፍስም በፊት ቀጣዩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወነው ለውጥ ከበቀል የነፃና ያለፈውን ሁሉ ከመደምሰስ የተቆጠበ ይሆን ዘንድ እንዲመኙ አስገድዷቸዋል፡፡ የባለፈውን እየተበቀልንና እየደመሰስን የመቀጠል የበደል አዙሪትም አንድ ቦታ ላይ መገታት እንዳለበት ይማፀናሉ፡፡ ነገር ግን ግፍንና በደልን እንዳልተፈጠሩ ሁሉ በማዳፈንና በመተው መጓዝ ለሀገር መታከም እና መዳን የሚረዳ እንዳልሆነ በቺሊ፣ በአርጀንቲና፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በሩዋንዳ እና በሌሎችም ሃገራት የጭቆና እና/ወይም ግፍ ማብቃትን ተከትሎ የተደረጉ እውነትን የማውጣትና እርቅ የማከናወን ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡ በእነዚህ ሀገራት የተፈፀሙ ግፎች ለሰሚ ከመክበዳቸው የተነሳ በደሎቹን አልፈው እንደሀገር መቀጠላቸው ሁሉ ያስደምማል፡፡ በአርጀንቲና ተቃዋሚዎችን ለመመርመር አይጥ ሆዳቸውን ቀዶ እንዲገባ ተደርጓል፤ በደቡብ አፍሪካ የነጮች የበላይነትን የተቃወሙ ጥቁሮች ከአስፈሪ ውሻዎች ጋር ግብግብ እንዲገጥሙ ተደርጓል፤ በሩዋንዳ በፖለቲከኞችና በጦር መኮንኖች አጋፋሪነት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ቱትሲዎች በሦስት ወር ውስጥ ተጨፍጨፈዋል፡፡ እነዚህ ሀገራት የወረደባቸውን መዓት እና ያሳለፉትን ግፍ ሁሉን ባሳተፈ ኑዛዜና እርቅ ሊሻገሩት ችለዋል፡፡ በኛ ሃገር የኢህአዴግ አገዛዝ የተፈፀሙ ግፎችና በደሎች ዓይነትና መጠን ከነዚህ ሀገራት ጋር ባይስተካከልም፤ በኔ እምነት በኢትዮጵያ የተፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አርጀንቲናን የሚያስታውሱ፣ በዘር ላይ ተመስርቶ የተነደፈው ጭቆናና ግፍ ደቡብ አፍሪካን የሚያስታውሱ፣ እንዲፋፉ የተደረጉት እምቅ ጥላቻዎችና የዘውግ ግጭቶች ሩዋንዳን የሚያስታውሱ ናቸው፡፡እርቅ ወይስ ቅጣትዛሬም በአንድ በኩል እውነቱ ሁሉ እንዲነገር፣ ግፍ የተሰራባቸው ፍትሕን እንዲያገኙ የሚጠይቅ ግፊት፤ በሌላ በኩል ይቅርታና ምሕረት እንደሚበጅና ያለፈውን እንድንረሳ የሚጣራ ውትወታ የተፋጠጡበት የጊዜ አደባባይ ላይ እንገኛለን፡፡ ነገር ግን አምባገነን ሥርዓቶች ከፍተኛ በደል ያደረሱባቸውና በይቅርታና በምሕረት ወደፊት የተጓዙ ሀገራትን ተሞክሮ ስናጤን ሁለቱ ጥያቄዎች ፈፅሞ ተቃራኒዎች እንዳልሆኑ እንገነዘባለን፡፡ የበደለውን ከቀጣን ይቅርታ አይኖርም፤ የበደለውን ካልቀጣን ፍትህ አይገኝም ለሚሉ ፈታኝ ሀሳቦች መሻገሪያ የሚሆኑ ገላጋይ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ በተለይ ወንጀል የሰሩ፣ ግፍ ውስጥ የተካፈሉ ሰዎች የሰሩትን እንዲናዘዙ በማደረግ እርቅ እና ይቅርታ እንዲያገኙ የተደረገበት የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ በአስከፊ ወይም በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ላለፉ ሁሉ መነሻ የእርቅ ተሞክሮ ሆኗል፡፡ በሌሎችም በርካታ ሀገራት እንደታሪካቸው፣ እንደባህላቸው፣ እንደተፈፀሙት ግፎች በተደራጀ መንገድ የእርቅና የምሕረት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በደቡብ አፈሪካ፣ በአርጀንቲና፣ በሩዋንዳ የተከናወኑ የእርቅ ተግባራት እንዴት እንደተከናወኑና ምን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ በርካታ የሕግ፣ የስነ-ልቦና፣ የባሕልና ህብረተሰብ ጥናቶች ተሰርተዋል፡፡ ሁሉም የሚያረጋግጡት ሀገርን ከቂምና ከበቀል ታድጎ ወደ ይቅርታ የሚያመጣው አድበስብሶ ማለፍ ሳይሆን እውነቱን መጋፈጥና ማከም እንደሆነ ነው፡፡ በተለይ “ያለፈውን ልንተወው አይገባም፣ እናውራው፤ ፍትህ ይስፈን” የሚሉ ጉትጎታዎችን ቂምን እንዳለመርሳትና በቀልን እንደመፈለግ አድርጎ ማቅረብ ፍፁም የተሳሳተና ወደኋላ ዞሮ ባለማየትና በመርሳት ፍትህ እና እርቅ ይገኛል ብሎ ከማሰብ የሚመነጭ ምኞት ነው፡፡መርሳት መጥፎ ነውበአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ለ27 ዓመታት በግለሰቦችና በቡድኖች ላይ የደረሱ በደሎች፣ የተፈፀሙ ግፎች በመፈክር፣ በሆይ ሆይታ፣ በሰላምና ፍቅር ዝማሬ ሊሽሩ ይችላሉ? “ፍቅር ያሸንፋል” “ያለፉትን በደሎች እንርሳ” ብንል የእውነት መዳንና መርሳት እንችላለን?የበርካታ ሀገራት የይቅርታና የምሕረት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት መርሳት የሚቻልም የሚመከርም ነገር እንዳልሆነ ነው፡፡ ጦርነት፣ ግፍ፣ ጭቆና ወዘተ.. ከተፈፀመ በኋላ እንዳልተፈጠሩ ሁሉ ባለማውራት፣ ባለማስታወስ፣ በማድበስበስ፣ በማላከክ ለመጓዝ የሚደረጉ ሙከራዎች ሀገር ላይ የይቅርታ መንፈስ እንዳይኖር፣ ሃገራዊ ድብታ እንዲያንዣብብ፣ የቂምና የበቀል ፍላጎት እንዲብላላ፣ መዳን እንዳይኖር…በማድረግ የአሁኑን እና መጪውንም ጊዜ እንደሚያበላሹ በርካታ ጥናቶች ያትታሉ (በእነ ኬረን ሉንድዎል/Karen Lundwall እና ሁዋን ሜንዴዝ/Juan Mendez በእርቅና በፍትህ ዙሪያ የተከናወኑና የተሰናዱ የጥናት ፅሁፎች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው)፡፡ ጊዜ ጉዳትን ይደብቃል እንጂ አያክምም፡፡ ይልቁንም ትውስታን ማስተካከል የሚመክሩት መንገድ ነው፡፡ ግፎችንና በደሎችን ከተጋፈጥናቸውና ካወራንባቸው፣ ይቅርታና እርቅ ከሰፈነ አሰቃቂ የሆኑት የጋራም ሆነ የግል ትውስታዎቻችን በቀልን ከማነሳሳት ይልቅ መማሪያነታቸው ይጎለብታል፡፡ በኢትዮጵያ በ1960ዎቹ እና 70ዎቹ የተከሰተውን የቀይሽብርና የነጭ ሽብር ደም መፋሰስና ሰቆቃ እንደሀገር አለመጋፈጣችን፣ አለማውራታችን፣ ይቅር አለመባባላችን ለመጡት ትውልዶች ጭምር ስነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ሸክም ከመሆን አልፎ ከስህተቶቻችንም ጭምር እንዳንማር በማድረግ ፖለቲካዊም ሆነ ሌሎች ባህሎቻችን ላይ መጥፎ ተጽዕኖ እንዳሳረፈበት እስካሁን የምናየው ሐቅ ነው፡፡ምን ይሻላል?ከበደልና ከቂም በቀል አዙሪት የምንወጣበት ሌላ ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ያለፍንባቸው አስከፊ የግልና የጋራ ግፎች ያደረሱብንን ጉዳቶች የምናክምበት እና የምናስተካክልበት ወርቃማ ዕድል አግኝተናል፡፡ (ወይስ አላገኘንም ይሆን???) ግፍ ቢል የማዕከላዊና የቃሊቲ እስር ቤቶች ሰቆቃ ብቻ የሚታያቸው አሉ፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጉሮሮዎች ላይ የተመነተፉትና የተመዘበሩት በቢልዮን የሚቆጠሩ ብሮችና የሀገር ሀብቶች ሀገር ለማስቀጠል ባይነሱ እንኳን ከፍርድ ቤቶች እስከ ቀበሌ፣ ከንግድ ዘርፍ እስከ ‘ሲቪል ሰርቪስ’፣ ከሃይማኖት ተቋማት እስከ ዩኒቨርስቲዎች የተፈፀሙ በደሎችና ግፎች የትየሌሌ ናቸው፡፡ ቤታቸውን በግፍ ተቀምተው ሜዳ ላይ የተጣሉ፣ የንግድ ድርጅታቸውን ተነጥቀው ባዶ የቀሩ፣ ከስራ ገበታቸው ያለ በቂ ምክንያት የተባረሩ፣ ከሀገር የተሳደዱ፣ የተደፈሩ፣ ልጆቻቸውን ያጡ…ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ ፍቅርና መደመር የሚሏቸው አይጨበጤ ሐሳቦች ውበት በደልን አይሽሩም፣ በቀልን አያስቀሩም፡፡ ታስቦባቸው ሲሰሩ እውነትን መናዘዝ፣ እርቅ፣ ይቅርታ፣ ካሳ፣ ምሕረት ሕብረተሰብን ያክማሉ፡፡ያለፉት ለውጦች የቀደሙትን በመደምሰስ ሁሉን ከዜሮ ማስጀመራቸው ሀገራችንን ያስከፈላት ዋጋ ከባድ ቢሆንም ከዛ የምንወስደው ትምህርት ግፍ ፈፃሚዎችና ሰለባዎቹ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው በመፈክርና በሆይሆይታ ያለ እርቅ፣ ያለ ካሳ፣ ያለ ፍትህ የሚተላለፉበት ሌላ ስህተት መሆን የለበትም፡፡ ሁለት ወሳኝ ነገሮችን ከወዲሁ ማድረግ ይቻላል፡፡በመጀመሪያ በተገቢ ሁኔታ ነፃ ሀገራዊ ውይይቶች እንዲደረጉ ማዘጋጀትና መደገፍ ያሻል፡፡ ውይይቶቹ አይነቶቻቸውና ቅርፆቻቸው የተለያዩ (ባህላዊ፣ አካዳሚያዊ፣ ማሕበራዊ፣ ሚዲያ-መር ወዘተ.) እንዲሆኑ መደረግ አለበት፡፡ ነፃነቶቻቸው የተጠበቁ ቢሆንም ግባቸው እውነቱን መጋፈጥና ማዳን መሆን አለበት፡፡ ለአንድ ቡድን ፖለቲካዊ ትርፍ፣ ለመሪ ማሞካሻ፣ ወይም ለበቀል መወጣጫ እንዳይውሉ ሀቀኝነትን እና ከለላን ይፈልጋሉ፡፡በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያን ሁኔታ ያገናዘበ ሁነኛ የእርቅ ኮሚሽን ሊቋቋም ይገባል፡፡ ይሄ ኮሚሽን ከሁሉ በላይ በተገቢ ሰዎች የተዋቀረ፣ ሙሉ የመንግስት ድጋፍ ያለው፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ግን የፀዳ ሊሆን ይገባል፡፡ የእርቅ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የተፈፀሙትን በደሎች በማጤን የሚበጀውን የእውነት፣ የይቅርታ፣ እና የእርቅ እቅድ ከመንደፍ እሰከ ማስፈፀም አቅሙ እንዲኖረው ሆኖ ሊደራጅ ይገባል፡፡እውነትን ገሃድ የማውጣት፣ እርቅ፣ ካሳ፣እና ይቅርታ ሆኖልን ከተገበርነው የሚያስፈራ ሳይሆን የሚያክም ጉዞ ነውና ከዜሮ ከመጀመር እንደሚታደገን አምናለሁ፡፡ ያለ እውነት ምሕረት ሊኖር አይችልም፤ ያለምሕረትም እውነት ይጎዳል፡፡ ሁለቱን አመጣጥኖ በጥበብ መሄድ ከፊት ለፊታችን ያለ ፈተና ነው፡፡ ልንወድቅበት አይገባም፡፡