ሐምሌ 13 ፣ 2010

የከንቲባ ምርጫ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት

ፖለቲካ

አዲስ አበባ ከተማ አዲስ ምክትል ከንቲባ እንደተሾመላት ተነግሯል። ይሁንና ምክትል ከንቲባው የተሾሙበት አካሄድ ከተለመደው የህግ አሰራር ወጣ ያለ በመሆኑ…

የከንቲባ ምርጫ እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት
አዲስ አበባ ከተማ አዲስ ምክትል ከንቲባ እንደተሾመላት ተነግሯል። ይሁንና ምክትል ከንቲባው የተሾሙበት አካሄድ ከተለመደው የህግ አሰራር ወጣ ያለ በመሆኑ ሕዝብ ሊወያይበት ይገባል።የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አቶ ታከለ ኡማ ባንቲን (ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ) በምክትል ከንቲባነት ማዕረግ መሾሙ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ተሿሚው የከተማው ምክር ቤቱ አባል አለመሆናቸው የተሾሙበትን የህግ አካሄድ ሕገ መንግስታዊ ይዘት አጠያያቂ አድርጎታል።እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ(ሰኔ 2010 ዓ.ም.) በከተማው መተዳደሪያ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/2003 አንቀጽ 13 ንኡስ አንቀጽ 2፡ረ መሠረት ምክር ቤቱ የከተማውን ከንቲባና ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤቱ አባላት መካካል እንዲመርጥ ይደነግግ ነበር። ይሄው አዋጅ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ፡ ምክትል አፈ ጉባኤና ጸሃፊው ከምክር ቤቱ አባላት እንዲመረጡ ያዝዛል። ይህም የከተማዋ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፥ ከንቲባና ምክትሉን ጨምሮ የምክር ቤት አባላት የሆኑ፡ ስለዚህም በሀገሪቱ የምርጫ ሕግና አሰራር መሰረት በከተማዋ ሕዝብ የተመረጡ መሆናችውን ያረጋግጣል።ቻርተሩ የከተማዋ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች በከተማዋ ሕዝብ የተመረጡ እንዲሆኑ መደንገጉ፡ የኢትዮጲያ ሕገ መንግሥት ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት (አንቀጽ 49፡2) መገለጫ ነው።ይሁንና ባለፈው ወር ሪፖረተር ጋዜጣ እንደዘገበው የአዲስ አበባ መተዳደሪያ ቻርተር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደተሻሻለ ተነግሯል። በዚህም መሠረት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ውጭ መመረጥ እንዲችል ተደርጐል። የአዲሱ ም/ከንቲባ ሹመት ይህን ማሻሻያ ተከትሎ የመጣ ነው።በተጨማሪም የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተተኪ ከንቲባ ላለመምረጥ በመወሰኑ ም/ከንቲባው እንደ ዋና ከንቲባ ሆነው እንዲሰሩ ይደረጋል። ስለዚህም ከከተማዋ የቀድሞ ቻርተር በተቃራኒ በሕዝብ ያልተመረጠ ሰው እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆኖ እንዲያገልግል ተደርጓል።ይህ አካሄድ የተለያዩ ጥያቄዎችን አስነስቷል።አንደኛ፤ የከተማዋ ከንቲባ እና ም/ከንቲባ የምክር ቤት አባላትና የሕዝብ ተመራጮች መሆን አለባቸው ብሎ በግልጽ ያሰቀመጠውን ቻርተር ማሻሻል ለምን አስፈለገ?እንዲህ የከተማዋን አሰተዳደራዊ መዋቅር መሰረታዊ በሆነ መልኩ የሚቀይር ማሻሻያ ጠንካራና አሳማኝ በሆነ ምክንያት መደገፍ ይኖርበታል። ይህ ማሻሻያ የኢትዮጲያ ሕገ መንግሥት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሰጠውን ራስን በራስ የማሰተዳደር መብት ይጻረራል። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደዚህ አይነት በከተማዋ መንግሥታዊ መዋቅር ላይ የሚደረግ መሰረታዊ ለውጥ እንዲሳተፉ እድል ሊሰጣቸው ይገባል።ሌላው ጉዳይ ደግሞ ይህ ከተለመደ ወጣ ያለ አካሄድ ምን ያህል ለአዲስ አበባ ሕዝብ ግልጽ እንደተደረገ ይመለከታል። ማሻሻያዎችን በተመለከተ፤ የአዲስ አበባ ቻርተር አንቀጽ 65 የሚከተለውን አስቀምጧል፤ «የቻርተሩ ማሻሻያ ሃሳብ በከተማው ምክር ቤት ወይም አግባብ ባለው የፌደራል መንግሥት አካል ሊቀርብ ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቻርተሩን ማሻሻያ ሃሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ተቀባይነት ሲያገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እንዲያገኝ ያስተላልፋል»።የመስተዳድሩ ቻርተር ማሻሻያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ በአንዳንድ ጋዜጣዎች ከመመዝገቡ ባለፈ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊዎች የማሻሻያ ሃሳቡን ማን(ምክር ቤቱ ወይስ ፌደራል መንግስት)መጀመሪያ እንዳቀረበው በቀላሉ ሊያገኙ አልቻሉም።በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ማሻሻያ ላይ የተጫወቱትን ሚና በመረጃ መረብ (internet) ላይ በቀላሉ ማግኘት አልተቻለም። ከላይ እንደተገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቻርተሩ ላይ የሚቀርቡ ማንኛውም ማሻሻያ ሃሳቦችን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ተቀባይነት ካገኘ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እንዲያገኝ የማስተላለፍ ሚና አላቸው።ማሻሻያው መጽደቁ በመገናኛ ብዙሃን ስለተዘገበ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሚናቸውን ተጫውተዋል ብሎ መገመት ይቻላል። ነገር ግን ይህ መሆኑንንም የሚያረጋግጡ መረጃዎች በመረጃ መረብ ላይ ለማግኘት አልተቻለም። በተያያዘም በአዲስ አበባ ም/ቤትም ሆነ በተወካዮች ም/ቤት ደረጃ እዚህ ማሻሻያ ላይ የተደረጉ ክርክሮችን/ውይይቶችን ሕዝቡ እንዲረዳ ማድረግ ያስፈልጋል።ሁለተኛ፤ የቀድሞው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ከምክር ቤቱ ጋር አብረው የአገልግሎት ጊዜያቸውን አለመቀጠላችው ጥያቄ ይጭራል። እውነት ነው ከንቲባው ልክ እንደ ሌሎቹ የአዲስ አበባ ም/ቤት አባላት የአምስት አመት አገልግሎት ዘመናቸውን እንዳጠናቀቁ ይታወቃል። ነገር ግን የተወካዮች ም/ቤት በሃገሪቱ በነበረው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት የአዲስ አበባ ም/ቤት ተወካዮች ምርጫን በአንድ አመት እንዲራዘም ሲወስን የሚቀጥለው ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ነባሩ ም/ቤትና አባሎቹ በስራ ላይ እንዲቀጥሉ ወስኗል። ይህን ተከትሎ ከንቲባውም እንደሌሎቹ አባላት እስከ ቀጣዩ ምርጫ በቦታቸው ሆነው ከአዲሱ ም/ቤት ከንቲባ እስኪሾም መቀጠል ይችሉ ነበር። ቻርተሩም እንደሚደነግገው(አንቀጽ 21፡3) «የከንቲባው የስራ ዘመን የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ይሆናል። ሆኖም በራሱ ፍቃድ ሲለቅ በምክር ቤቱ ከሃላፊነት ሲታገድ ወይም የምክር ቤት አባልነቱን ሲያቋርጥ»።ከንቲባው በራሱ ፍቃድ ቢለቅም የአዲስ አበባ ም/ቤት ከራሱ አባላት ውስጥ አዲስ ከንቲባ መርጦ መተካት ሲችል ለምን ቻርተሩን ለማሻሻልና አዲስ አካሄድ ተጠቅሞ የአዲስ አበባ ም/ቤት አባል ያልሆነ ሰውን እንደ ምክትል ከንቲባ(በተዘዋዋሪ የም/ቤት አባል ያልሆነ ዋና ከንቲባ) መረጠ?እነዚህ ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ቻርተሩን በማሻሻል ሂደት የተሳተፉ ሰዎችን ጨምሮ ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል።በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሃገራችን ኢትዮጲያ ወደ እውነተኛና ዘላቂ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት እየተሻገረች ነው ተብሎ ተስፋ በሚጣልበት ሰአት ዜጎቿ በተለያየ ደረጃ ካሉ የመንግስት አካላት እና ፖለቲከኞች ከፍተኛ ግልጽነትን መጠየቅ አለባቸው። ምክንያቱም ኢትዮጲያ ውስጥ ለሚገነባው ዲሞክራሲ ዘላቂነት መሠረት የሚሆኑት ጠንካራ ግለሰቦች ሳይሆኑ ብዙ ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማት ናቸው።እንዲሁም በአዲስ በአበባ ፖለቲካ ምህዳር ከቀድሞ በተሻለ መልኩ ቀጥተኛ ተሳታፊነት ይኑረን የሚሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ባሉበት ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በከተማው ሕዝብ ያልተመረጡ የበላይ የስራ አስፈጻሚዎች ከተማዋን እንዲመሩ የሚያደርግ አካሄድ ተቀባይነት የሌለውና ልንታገለው የሚገባ ነው።

አስተያየት