ሐምሌ 17 ፣ 2010

ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ

ፖለቲካPolitics

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለጤናዎ እንደምን አሉ? ደህና ስለመሆንዎ የምጠይቀው እንዲሁ ለጽሑፌ መግቢያ እንዲያመቸኝ አይደለም፡፡…

ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለጤናዎ እንደምን አሉ? ደህና ስለመሆንዎ የምጠይቀው እንዲሁ ለጽሑፌ መግቢያ እንዲያመቸኝ አይደለም፡፡ በእርግጥ በሶላታቸው በቅዳሴያቸው እንደሚያስብዎት እንደ ኢትዮጵያ እናቶች እና አባቶች ባይሆንም ክፉ እንዳይነካዎት ማሰቤ አልቀረም፡፡ የሀገራችንን ትላንት በተረዱበት አግባብ እና ነገዋን ለማበጀት መውጣትዎን መውረድዎን በማየት ብዙኃኑ ኢትዮጵዊ ቸር ውለው እንዲያድሩ ይመኛል፡፡እኔ ደግሞ ለእርስዎ በጎ እንድመኝ የሚያደርገኝ ተጨማሪ ምክንያት አለኝ፡፡ የግል ምክንያት ነው፡፡ ያልታሰረ ማን ነበር ብለው እንዳይስቁብኝ እንጂ ታስሬ ነበር፡፡ የህብረተሰቡን ደኀንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ በጸረ ሽብር ህጉ ተከስሼ ለሦስት ዓመታት ከእስር ቤት ፍርድ ቤት ተመላልሻለኹ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት ቃለመጠይቅ እኔ እና ወዳጆቼን እየወነጀሉ ሲናገሩ ነበር፡፡ እርስዎ ግን በእንደራሴዎች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ይቅርታ መጠየቅዎ ሳያንስ መንግስታዊ ሽብር መፈጸሙን  አምነዋል፡፡ ይህ እንደ እኔ የሞራል፣ የጤና እና ከስራ የመባረር ጉዳት ለደረሰበት ዜጋ ካሳ ባይሆንም የመንፈስ እርካታ የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የግል ውለታ እንደተደረገልኝ ይሰማኛል፡፡ላለፉት ሦስት ወራት በሰሯቸው በዚህ እና ሌሎች ዐበይት ሀገራዊ ጉዳዮች ደስተኛ ከሆኑ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ይህንን ተስፋዬን ከቤት እስከ አደባባይ ገልጬዋለኹ፡፡ ይህ ተስፋ እንዳለ ሆኖ በሀገሪቷ እየተካሄደ ያለው ሪፎርም ምን መልክ መያዝ እንዳለበት ብዥታ ያለ ስለመሰለኝ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ጽፌያለኹ፡፡ ደብዳቤው ግልጽ እንዲሆን የወደድኩት ብዥታውን እና ግርታው ሁላችን ጋር በመኖሩ፣ እርስዎም ሁሉ ነገር ፊት ለፊት እና በግልጽ እንዲሆን ስለመከሩ እና ምንአልባትም በግልጽ ላልተቀመጠው የሀገሪቷ ፍኖተ ካርታ(Roadmap) የዜግነት አስተዋጽኦ ባበረክት ብዬ በማሰብ ነው፡፡ከየት... .ወዴት?አሁን ወዳለንበት ነባራዊ ሁኔታ እንዴት ደረስን የሚለውን ማየቱ በኋላ ለማነሳው ዐሳብ መደላድል ስለሚሆነኝ ከዚያ እጀምራለኹ፡፡ እዚህ ያደረሰን ቀደም ባለው  ጊዜ መንግስት ራሱን ለማረም ምንም ዝግጁነት ስላልነበረውና በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ማጣቱ መሆኑን ሁሉንም የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ አንድ ማኀበረሰብ ለመንግስት ዕውቅና የሚሰጠው ካለበት ነበራዊ ሁኔታ እና እሴቶቹ በመነሳት መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ይህ ለመንግስት የሚሰጥ ቅቡልነት እና ውክልና መደበኛ እና መደበኛው ያልሆነ ሲሆን መደበኛ ያልኩት ውክልና በምርጫ አማካኝነት በኮሮጆ የሚሰጥ ነው፡፡ ሌላው መደበኛ ያልሆነው መንግስት የሚጠበቅበትን ህዝባዊ አገልግሎት ማቅረብ ሲችል፣ የማኀበረሰቡን ሰላም እና ደኀንነት ሲጠብቅ፣ የተቋማት ነጻነት ሲኖር፣ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከሞላ ጎደል ሲከበሩ፣  ያን መንግስት እንዴት ተጠያቂ ማድረግ እና ማውረድ እንደሚችል ማኀበረሰቡ ሲያውቅ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ራሱን ማረም ያልቻለው መንግስት ሁሉንም አይነት ተቀባይነት በማጣቱ ከቦታው መነሳቱ ተገቢ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ቀጣዩን የሀገሪቱን መሪ መምረጥ ላልቻለው የኢትዮጵያ ህዝብ በመቶ ሰማንያ ሰዎች(የኢህአዴግ ምክር ቤት) እርስዎን ሾሙለት፡፡ ህዝብ ራሱ ላልመረጠው ሰው እውቅና እንዳይሰጥ የተፈጥሮ ጠባዩ ይመራዋል፡፡ እርስዎ ቢያስታውሱትም የዘነጋ ስለሚኖር እርስዎ ምርጫ እንዲያሸንፉና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲገቡ ብዙዎች (የእርስዎ ተፎካካሪ የሆነው ኦሮሞ ፌደራሊሰት ኮንግረስ(ኦፌኮ) አባላት ጨምሮ) ከእኔ ጋር እስር ቤት እንደነበሩ ማስታወስ አይከፋም፡፡ ስለዚህ እርስዎ ከህዝብ ይሁንታን ያገኙት በሁለተኛው መንገድ ነው፡፡ በሚያስደንቅ የህዝብ አገልጋይነት መንፈስ ባደረጉት እንቅስቃሴ የብዙዎች ቀልብ ገዝተዋል፡፡ይህ ማለት ግን ህዝብ እርስዎን ለዘላለም ማንገስ ይፈልጋል ማለት አይደለም፡፡ እርስዎን ተጠያቂ የሚያደርግበት ሳይፈልግዎ ሲቀር ደግሞ ማሰናበት የሚችልበት ስርዓት ይፈልጋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተመርጠው ስልጣን ስላልያዙ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር መሆኑን እርስዎም ሆነ በዙሪያዎ ያለው ሰው ሊዘነጋው አይገባም፡፡ምን አይነት መንግስት?ብዙውን ጊዜ እንደዚህ አይነት ሀገራዊ ቀውስ በሚኖርበት ሰዓት የሽግግር ወይንም የባለአደራ መንግስት መመስረት የተለመዱ አሰራሮች መሆናቸውን ብዙዎች ያሰምሩበታል፡፡ የሽግግር መንግስት ሁሉንም የማኀበረሰብ ክፍል እና የፖለቲካ ኃይል በማካተት መንግስታዊ ኃላፊነቶች እየተወጣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ተቋማት የሚመሰረቱበት መንገድን የሚያመቻች ሲሆን ባለአደራ መንግስት ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ለባለሙያዎች የሚሰጥ ምርጫ ተካሂዶ ህዝብ የመረጠው መንግስት እስኪመጣ ድረስ መንግስታዊ ኃላፊነቶችን ብቻ እየተወጣ የሚቆይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ሁለቱም የጊዜያዊ መንግስት አይነቶች መዋቅራዊ እና የፖሊሲ ውሳኔዎችን የመወሰን ስልጣን ውክልና እንደሌላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ምክንያት የማስፈፀም አቅማቸውም ደከም ያለ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ ተፈላጊ የሆኑበት ምክንያት መተማመን እንዲኖር፣ ፍትሓዊ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር፣ ህዝብ ያልመረጠው አካል በህዝቡ ዐቢይ ጉዳዮች ላይ እንዳይወስን ግንዛቤ መወሰዱን መናገር ይቻላል፡፡ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት የሄደችበት መንገድ መደበኛ ያልሆነ መንግስት በሚያስፈልጋት ደረጃ የተመሰቃቀለ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም እየጠየቁ የነበሩት፤ ያሉት፡፡ ሌላው እርስዎ ጥሪ ያደረጉላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ግዝፈት እና ከገዢው ፓርቲ ጋር ያላቸው የቁመና መተካከል የሽግግር መንግስት ሊቋቋም ነው እንዴ የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ወደሀገር ውስጥ የሚገቡት እና የገቡት የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸው ምን እንደሆነ አልገለጹም፡፡ ምርጫ ቦርድም ወደሀገር ውስጥ ከገቡት ድርጅቶች መካከል ማንም መዝግበኝ ያለ ድርጅት የለም ማለቱ ይታወሳል፡፡ ይህ የሚሳየው ሀገሪቷ ወዴት ለመሄድ እንዳሰበች ፍኖተ ካርታዋ እንዳልተዘጋጀ፣ ተዘጋጅቶም ከሆነ ለህዝብ ግልጽ እንዳልተደረገ ነው፡፡በእርስዎ በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ መሪነት በርካታ ግዙፍ ውሳኔዎች እና ስራዎች እየተሰሩ በመሆናቸው በቁጥር ባይደገፍም አብዛኛው ሰው በሚያደርጉት ነገር ደስተኛ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እንዳንዱ ተግባራት እኔን ጨምሮ በርካታ ሰውን እጃችንን በአፋችን ላይ ያስጫነ ነበር፡፡ ይህ ግን ሁሌ በእርሶ መልካም ፈቃድ ብቻ የሚደረግ መሆን የለበትም፡፡ ሀገሪቱ የሁሉም እስከሆነች ድረስ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ሁሉም ያንን ተከትሎ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡እኔ በበኩሌ እስካሁን ባለው አረዳዴ የባላአደራ መንግስትም ሆነ የሽግግር መንግስት አስፈላጊነት አይታየኝም፡፡ ይህንን እንድል ያደረገኝ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ሪፎርም ለማካሄድ ያለውን ቁርጠኝነት እምነት የሚጣልበት ሆኖ ስላገኘኹት ነው፡፡ ይህ ማለት ሁሉንም ነገር ለመንግስት ሰጥቶ ሌላው አካል ቤቱ ይቀመጥ እያልኩኝ አይደለም፡፡ አስተዳደሩ በህዝብ ዘንድ እና በሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ የለውጥ ሂደቱን ለመምራት እንደሚችል መተማመኛ ለመስጠት ማደረግ የሚገባው ስራዎች አሉ፡፡ መደበኛ መንግስት መሆኑ የሚሰጠው ጉልበት የማስፈጸም አቅሙ የተሻለ ስለሚደርገው ከሽግግርም ሆነ ከባለአደራ መንግስት በተሻለ የለውጥ ሂደቱን መምራት ይችላል ብዬ እገምታለኹ፡፡የለውጥ ሂደት እንዴት?የመጀመሪያው የህዝባዊ አገልግሎት እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት በዋናነት አስፈላጊ በሆኑ ተቋማት ባለሙያዎች እና የሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች በመሪነት እና አባልነት እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል፡፡ የመረራ ጉዲና(ፕሮፍ) የኢትዮጵያ ብሮድካሰት ባለስልጣን የቦርድ አባል ሆነው መመረጣቸው እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እንደመልካም ጅምር ቢሆንም ገና ብዙ የሚቀሩ መስሎ ይሰማኛል፡፡ በሁሉም በቦርድ በሚተዳደሩ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ምሁራን እና ባለሙያዎች ኃላፊነት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ብዙ ብቁ ኢትዮጵያውን ባለሙያዎች ለባዕዳን ድርጅቶች እያገለገሉ ስለሚገኙ ሀገራቸውን የሚረዱበት ዕድል መስጠት ብልህነት ነው፡፡ በጸረ ሙስና፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ የመሳሰሉ ተቋማት ደግሞ ገለልተኛ የሆኑ ባለሙያዎች ተሹመው በሀገሪቱ ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ እና የሀገር ሀብት እንዳይባክን የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ መፍቀድ ይገባል፡፡ሌላው መዘንጋት የሌለበት ዐብይ ጉዳይ የሕጋዊነት እና ሕገ መንግስታዊነት ጉዳይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለተፈጠሩ አለማግባባቶች እና ቀውሶች የፖለቲካ ስልጣን ሕጋዊነት ያገኘበት ሂደት ዋናው ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሕገ መንግስቱ ጸድቆ ወደስራ የገባበት ሂደት ሁሉን ያሳተፈ እና ሚዛናዊ እንዳልነበር የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር የሚናቅ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት በሀገሪቱ ለሚፈጠሩ ቀውሶች እንደተቀበረ ቦምብ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ዓላማው ላይ ላዩን በማሳመር ከመሄድ ይልቅ ውስጥ ለውስጥ የተቀበረውን ፈንጂ ማምከን እንደሆነ እየወሰዳቸው ባላቸው እርምጃዎች እያሰተላለፋቸው ባሉ መልዕክቶች እየገለጸ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ሁሉንም የፖለቲካ ኃይል ያለ ልዩነት ወደ ሀገር ቤት ገብቶ በሀገር ግንባታ ሂደት እንዲሳተፍ እየተደረገ ያለው፡፡ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተወሰኑ በሕገ መንግስቱ አንቀጾች፣ በብሔር በተደራጀው ፌዴራላዊ አወቃቀር፣ በፓርላመንታዊ ስርዓት፣ በሰንደቅ ዓላማው እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መግባባት እንደሌለው እውቅና እንደሰጠ ያሳያል፡፡ ስለዚህ የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በፊት ከነበረው አስተዳደር የሚለየው የተቃወመውን ሁሉ ጸረ ሰላም፣ የሻዕቢያ ተላላኪ እና ሽብርተኛ ብሎ ከመፈረጅ ይልቅ በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ለሁሉም የሚበጅ ስርዓት መፍጠር ይቻላል ብሎ በማመኑ ይመስለኛል፡፡ ለሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጥሪ ሲያደርግ የቀድሞው አስተዳደር ሲሰራቸው የነበሩ ስራዎችን በመቀጠል ሳይሆን ቆም ብሎ ሀገራዊ መግባባቱ እና ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሽግግሩ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ የምችላቸው እና የማልችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል ብዬ አምናለኹ፡፡ከዚህ መንፈስ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ነገር የለውጥ ሂደቱ ላይ ሚሊዮኖች ጥርጥር እንዲያሳድሩ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በግማሽ ልብ ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል፡፡ አሊያም ጥሪውን ከናካቴው ላይቀበሉም ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንም የማንፈልገው አዙሪት ውስጥ እንዳይከተን ያሰጋል፡፡የሚደረጉ እና የማይደረጉ ከዚህ በመነሳት እንደ ወደዴሞክራሲ የሚደረግ ሂደትን የሚመራ መንግስት ማድረግ የሚገባው እና የማይገባው ጉዳዮችን ላመልከት፡፡ተገቢ እርምጃዎች የሚሆኑት በቀድሞው አስተዳደር የተፈጸሙ ስህተቶች ነገር ግን አዲሱ አስተዳደር ባለው አቅም እና ስልጣን ማረም የሚችላቸውን ነገሮች ናቸው፡፡ እርስዎ ወደስልጣን ከመጡ ጀምሮ ያደረጓቸው በርካታዎቹ ነገሮች እዚህ ዘርፍ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው፡፡ የህሊና እስረኞችን መፍታት፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስን መልሶ መገንባት፣ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት፣ ለኤርትራ ጉዳይ እልባት መስጠት፣ አፋኝ ሕጎች የሚሻሻሉበት አልያም የሚሰረዙበትን መንገድ መቀየስ፣ የሚዲያ ነጻነትን መፍቀድ፣ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ ፈር ማበጀት፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማስታረቅ፣  የመሳሰሉት ጎላ ጎላ ያሉት ናቸው፡፡መንግስታዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣ ሀገሪቱ ከዚህ ቅድመ-ዴሞክራሲ (pre-democratization) ሁኔታ ወጥታ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንድትገባ ማድረግ ተጨማሪ መንግስት ማድረግ የሚችለው እና የሚገባው ነገሮች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡በቀድሞ አስተዳደር የተሰሩ ስህተቶች ሆነው አሁን መስተካከል የማይችሉ እና በሀገሪቱ ታሪካዊ እና ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት እንደችግር የሚታዩ ጉዳዮች ይህ አዲስ አስተዳደር ሳይጨምር ሳይቀንስ ባሉበት ከማቆየት በቀር ምንም ሊነካካቸው የማይገቡ ነገሮች እንዳሉ አስባለኹ፡፡ ይህንን የምልበት ብዙ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ እነዚህ ጉዳዮችን ለመፍታት ይህ መንግስት በዴሞክራሲያዎ ምርጫ ተመርጦ ስላልመጣ ፖለቲካዊ ውክልና የለውም፡፡ እንደምሳሌ አጨቃጫቂውን አንቀጽ 39፣ በዘር የተደራጀውን ፌዴራላዊ አወቃቀር መውሰድ እንችላለን፡፡  ውስብስብ በመሆናቸው እና ተፎካካሪ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች በመኖራቸው መንግስት ወደ አንደኛው አድልቶ ለውጦችን ቢያደርግ  ወትሮም በቋፍ ያለው ሀገራዊ መግባባት ይጠፋል፡፡ ወደሀገር ቤት የጠራቸው የተለያየ ፍላጎት እና ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ተሳትፎ ሳይጀምሩ ቅርጽን የሚቀይሩ ነገሮች መኖራቸው እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህንን የመሳሰሉ ከበፊቱ አስተዳደር የተረከባቸውን ፍትሓዊ እና ነጻ ምርጫ ተካሂዶ ህዝብ ሲፈልግ እንዲያጸናቸው አልያም እንዲሽራቸው የሚተዋቸው ነገሮች መኖራቸው መዘንጋት እንደሌለበት ይሰማኛል፡፡ የሰውነት እና የዜግነት መብቱ ግምት ውስጥ ሳይገባ፣ እንደወገኖቹ ሳይቆጠር በቀቢጸ ተስፋ የሚኖረው፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ጉዳይ ህዝብ ውስኔ ከሚፈልጉ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ሰቆቃወ - አዲስ አበቤየአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት ሐምሌ 11፣ 2010 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የከተማዋ ከንቲባ የአቶ ድሪባ ኩማ የስልጣን ዘመናቸው መጠናቀቁን ተከትሎ የምክር ቤቱ አባል ያልሆኑት አቶ ታከለ ኡማን በምክትል ከንቲባነት በመሾም እንደከንቲባ እንዲያስተዳድሯት ወስኗል፡፡ መንግስትዎ ካለው የፖለቲካ ስልጣን ወሰን ያለፈበት እና ወደ አንድ ወገን ያደላ ውሳኔ በመስጠት ፖለቲካዊ ጉልበቱን በመጠቀም የሕግ ጥሰት መፈጸሙን አምናለኹ፡፡ በመጀመሪያ ምክትል ከንቲባው ወደስልጣን ሲመጡ የህግ ጥሰት መፈጸሙን ገልፀው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፡፡ የእኔ ክርክር ግን ከዚህ የተሻገረ ነው፡፡እርስዎ እንደሚያውቁት የአዲስ አበባ ህዝብ በባለፉት አስተዳደሮች በርካታ በደል ተፈጽሞበታል፡፡ በተለይ በ1997 በተካሄደው ምርጫ ቅንጅትን መምረጡን ተከትሎ ልጆቹን በአደባባይ ከማጣት ጀምሮ የጭቆና ቀንበር ተጭኖበት እንዳይሆን ሆኗል፡፡ ችግሩ የሚጀመረው የህዝብ ይሁንታን ሳያገኝ እና ሁሉን አካታች ውይይት ሳይደረግበት ከጸደቀው ሕገ መንግስት መሆኑን ይዘነጉታል ብዬ አልገምትም፡፡ሲጀምር “እኛ ብሔር ብሔረሰቦች…” ብሎ ከቁጥር የሚያገለው ሕገ መንግስት በአንቀጽ 47 የፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላትን ሲዘርዘር አዲስ አበቤን ከነመኖሩም ይዘነጋዋል፡፡ የሚገርመው ወረድ ብሎ በአንቀጽ 49 ተጠሪነቱን አባል ላልሆነበት ፌዴሬሽን ያደርገዋል፡፡ በዚሁ አንቀጽ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም እንደሚጠበቅለት ይደነግጋል፡፡ ይህ ለአዲስ አበባ ህዝብ ሰውነት ያገኘውን ሰብዓዊ እና በዜግነት ያገኛውን የዜግነት መብቶች የሚገፍ እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን የሚጥስ መሆኑ አያከራክርም፡፡ በዚህ ላይ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢህአዴግ በፈጸመው የተበላሸ አሰራር እና ሙስና የከተማው ህዝብ በፍጹም ደህነት ውስጥ እንዲዳክር፣ በዙሪያው ያለው ገበሬ ደግሞ ከገዛ መሬቱ አለአግባብ እንዲፈናቀል፣ ከተማይቱ ባልተጠና እና ኢ-ፍትሓዊ በሆነ መልኩ እንድትሰፋ በማድረግ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ ገበሬውን ከመሬቱ የበለጠ ለማፈናቀል እና እንዳሻቸው ለመቸብቸብ እንዲመቻቸው በማሰብ ሊተገብሩት የነበረው ማስተር ፕላን ውድ ኢትዮጵያውን ደም እንዳይፈፀም ሆኗል፡፡“በረራ” እና “ፊንፊኔ” ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ከፋፋይ እና አድሎአዊ ሕገ መንግስት መንፈስ የተመሩ ሰዎች የተሳሳተ የታሪክ ትርክት ውስጥ በመግባት ጭራሽ ‘የከተማዋ ስም አዲስ አበባ ሳይሆን “ፊንፊኔ” ነው፡፡’ የሚል ክርክር ይዘው መጥተዋል፡፡ ይህ በማኀበራዊ ሚዲያ ላይ ተወርቶ ብቻ ቢቀር መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ሀሳቡ ፋፍቶ እና ደልቦ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ የቀረበ ሰነድ ሆኗል፡፡በዚህ ብቻ አይደለም የሸገር ሰው እየዳከረ ያለው፡፡ በተመሳሳይ የዘውግ፣ የማንነት መንፈስ ‘የለም የአዲስ አበባ የኋላ ታሪኳ ሲጠና አዲስ አበባ ሳይሆን መባል ያለባት “በረራ” ነው’ የሚል ቡድን ተነስቷል፡፡ እነዚህ ግብግቦች የስም ብቻ ጦርነት ብቻ እንዳልሆነ እርስዎ በግልጽ ይረዱታል፡፡ አዲስ አበቤም ተጨማሪ ውበት ስለሚሆነው ስሞቹን ያለምንም ማንገራገር ተጨማሪ ስሞችን በደረበ ነበር፡፡ እየሆነ ያለው ግን ክርስቶስን መስቀል ላይ ለመሞት ሲያጣጥር አልባሱን ለመውሰድ እንደተጣጣሉት ወታደሮች ያለ ነገር ነው፡፡በመደመር ውስጥ ማስገደድ፡- ሕገ-ወጥ ሹመትመጀመሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የልዩ ጥቅምን አዋጅ ላልተወሰነ ጊዜ በማራዘም ነገሮች የሚረጋጉበትን ስልት መንደፉ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በመቀጠልም የከተማው ምርጫ ለአንድ ዓመት እንደዘገይ መደረጉ መጠቀስ ያለበት በሳል ውሳኔ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን የተደከመውን ድካም ከንቱ በሚያስቀር መልክ አዲሱ ምክትል ከንቲባ የተሾሙት፡፡ በመሰረቱ ሰውየው ባለፉት የቅርብ ዓመታት የፖለቲካ ሂደት ገለልተኛ ያልነበሩ፣ የእርስዎ አስተዳደር ያለውን ሁሉን አካታችነት መንፈስ የሌላቸው፣ ከተማውን “ፊንፌኔ” ለማድረግ የሚደረገው ከንቱ ጥረት ዋና ተዋናይ ናቸው፡፡ በግልጽ የሚታዩት ጽሑፍ እና የምስል ማስረጃዎች የሚሳዩት ከላይ ካየናቸው ሁለት አመለካከቶች የአንደኛው አቀንቃኝ መሆናቸውን ነው፡፡ አመለካከቱ መያዝ በራሱ መጥፎ ባይሆንም ህዝቡ ፍላጎቱ ሳይጠየቅ  በዚህ ለውጥ ወቅት መሾም አግባብ አይደለም፡፡  እርሳቸውን መሾም ከላይ ለማስረዳት የሞከርኩት መንግስትዎ ከቀድሞ አስተዳደር ተረክቦ እንዳለ ጠብቆ በዴሞክራሲያዊ መንገድ አሻሚ ጉዳዮች እንዲፈቱ የተጣለበትን ሀላፊነት እንዳይወጣ የሚደርግ ነው፡፡ ይህ የአንድ ወገን የበላይነት ያለበት አሰራር አደገኛ መሆኑን ለእርስዎ መናገር እንደድፍረት እንዳይቆጠርብኝ እሰጋለኹ፡፡የፖለቲካ ስልጣንን ተጠቅሞ የህዝቦችን ወንድማማችነት በሚያጠፋ መልኩ የሚወሰድ የጉልበት እርምጃ ከሕወሃት ልንማረው የሚገባ ስህተት ነው፡፡ የምስለኔ አገዛዝ ያረጀ እና ያፈጀ ነው፡፡ ነገር ግን ሕወሃት መራሹ ኢህአዴግ የምርጫ ዘጠና ሰባት ምርጫን ተከትሎ ያደረገውም እንዲሁ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት መንግስትዎ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወደመደመር በጠሩበት በዚህ ጊዜ እንዲህ አይነት የማንአለብኝት እርምጃ ለሁላችንም አይጠቅመንም፡፡ አንድ ጸሐፊ የእርስዎን የመደመር ጥያቄ ንድፈ ሐሳባዊ ሲያደርገው በመደመር ውስጥ ማስገደድ የለም ሲል ገልጾታል፡፡ ታዲያ አዲስ አበቤ ምን እዳ ኖሮበት ነው ተገዶ የሚደመረው?ስጋት እና ተስፋእርግጥ ነው ይህ ሕገ ወጥ እና ሀፍረተ ቢስ ውሳኔ የተወሰነው በችግር ውስጥ ሆኖ ለማመቻመች እንደሆነ እጠረጥራለኹ፡፡ በዚህ መልኩ ግን ሀገር የሚመራ አይመስለኝም፡፡ እንዳይከፋው በማለት ከማባበል የፖለቲካ አዙሪት መውጣት የእርስዎን ተክለ ስብዕና ይመጥናል፡፡ ከንግግርዎ እንደገባኝ መንግስትዎ ያለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በሚገባ ስለተረዱ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ፍኖተ ካርታ የግድ ያስፈልግዎታል፡፡ እንደ አንድ ንቁ ዜጋ ካርታውን ፈልጌ ስላላገኘኹኝ በነሲብ መሄድ የትም እንደማያደርሰን እያሰብኩኝ ስጋት ገብቶኛል፡፡ ስለመደመር፣ ስለፍቅር እና ይቅርታ የሚራምዱት ሐሳብ የፍኖተ ካርታው አካል ሆኖ የመንግስትዎን “እሴቶች” መወሰን ይገባዋል ብዬ አምናለኹ፡፡ እነዚህ እሴቶች የታወቁ ቢሆኑ ኖሮ የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ እንዲህ ያለ ውሳኔ ባላስተላለፉ ነበር፡፡ ይህ የተደረገው ደግሞ የከተማው ህዝብ ለእርስዎ እና ለኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የገለጸውን ፍቅር እና አክብሮት ባወደሱ ማግስት መሆኑ ብዙ ሰው ክፉ ክፉን እንዲያስብ አድርጎታል፡፡እጅግ የሚገርመው የምክትል ከንቲባው ያልመረጣቸው ህዝብን፣ የተወሰነ ማኀበረሰብን በመጨቆን የተመሰረተ ብለው የሚያስቡት ህዝብን፣ ስያሜውን እንኳን ለመቀበል የማይፈልጉትን ህዝብን ደፍረው፣ ሹመቱን ተቀብለው ሊያስተዳደሩት መምጣታቸው ነው፡፡ ላግዝ ቢሆን የወገን ደንብ ነው፡፡ እርሳቸው ግን ሳይመርጣቸው ሊወስኑበት ነው የመጡት፡፡ ታዲያ ይህንን ህዝብ በፍትሕ እና በርትዕ የሚያገለግሉት ይመስልዎታል? እኔ ግን አይመስለኝም፤ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ሌላው መንግስትዎ ሊጠነቀቅበት እና ሊያስቆመው የሚገባው ነገር አዲስ አበባን የጦር አውድማ የማድረግ አባዜ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ የአዲስ አበባ ህዝብ እንደጠላት የሚያይበት የተሳሳተ አመለካከት በእርስዎ የስልጣን ዘመን ቢያከትም እመርጣለኹ፡፡ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ እንደ ሀገረ መንግስት ባላት ታሪክ ያከማቸችው “እምቅ ማኀበራዊ ሀብትን” ሰብስባ የያዘች ከተማ ናት፡፡  ነገር ግን ይህ እንቁ እንደ አልባሌ ተቆጥሮ ሲረገጥ ነው የኖረው፡፡ እኔ እንኳን እያየኹት ስንት ስህተት ተሰራ፡፡ ስንት ጥፋት ተፈጸመ፡፡ ባደረጉት አንድ ንግግር የአዲስ አበባ ህዝብን አስተሳሰብ እንደሞዴል ማቅረብዎን አስታውሳለኹ፡፡ አዲስ አበባ ወደፊት ልንገነባው ለምናስበው ፍትሓዊ እና የበለጸገ ማኀበረሰብ እንደመነሻነት የምንጠቀመው ኢትዮጵያዊነትን ሸሽጎ የያዘ ነው፡፡ አዲስ አበባን ካላዋቂ ሳሚ መጠበቅ ኢትዮጵያን ከብሔራዊ ውርደት ማዳን ነው፡፡በመሰረቱ የአዲስ አበባ ህዝብ ለፍቶ አዳሪ ነው፡፡ እንደሌላው ወገኑ በችግር ውስጥ የሚዳክር መሆኑን አያጡትም፡፡ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ይታየው በቅርቡ የጎበኙት እና ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራምን ማየት የችግሩን ጥልቀት ለመረዳት ያስችላል፡፡ በአንዳንዶች ከተሜው የገበሬው ጠላት ተደርጎ የሚሳለው ሸውራራ አመለካከት መነሻው ከየት እንደሆነ ለመረዳት ይከብዳል፡፡ ሲጀመር ገበሬውን ሲያፈናቅሉት የኖሩት የኢህአዴግ ሹመኞች እንጂ ምስኪን አዲስ አበቤ አይደለም፡፡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር ቢፈቀድለት ከገበሬው የገዛ ወገኑ ጋር ፍትሓዊ ግንኑነት መስርቶ መኖር በቻለ ነበር፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ሆኖም ከተማውን ለከበበው ክልላዊ መንግስት የገቢ ዋስትና  አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ ገበሬን አፈናቅለው መሬቱን ሲቸበችቡ መኖራቸው ሳያንስ፣ ለገበሬው ተቆርቋሪ ሆነው መምጣታቸው ሲገርመን፣ ጭራሽ ሀገር በአዲስ ጎዳና መጓዝ ጀመረች ስንል እነዚሁ ሹመኞች ራሳቸው ከተማዋን እንዲያስተዳደሩ መፍቀድ ታሪካዊ ስህተት ይመስለኛል፡፡እርስዎ እንዳሉት አንድ ማኀበረሰብን ለመርዳት እሴቶቹን መረዳትን ይጠይቃል፡፡ የዜግነት ፖለቲካ ይሰፍን ዘንድ ደግሞ ሀገር በቀል ልምዶችን መሰረት ማድረግ ተገቢ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አዲስ አበባ ፍጹም ናት ባይባልም ሰው በዜግነቱ ብቻ እንዲከበር መነሻ የሚሆን እርሾ አታጣም፡፡ በአዲስ አበባ ዴሞክራሲን መፍቀድ በመላው ኢትዮጵያ የዜግነት ፖለቲካ እንዲያብብ መንገድ መጀመር ነው፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብን ህዝብ ራሱን እንዳያስተዳደር መከልከል የዜግነት ፖለቲካን መግደል ይመስለኛል፡፡ የዜግነት ፖለቲካን መግደል ትውልድ ይቅር የሚለው ስህተት ይሆን? አይመስለኝም፡፡ 

አስተያየት