ሐምሌ 24 ፣ 2010

በኢትዮጲያ እና ኤርትራ አዲስ የሠላም ጉዞ ውስጥ የአልጀርስ ስምምነት እና የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔ ሚና

ፖለቲካምጣኔ ሀብትታሪክ

መንደርደሪያኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ አዲስ የሰላም ሒደት አምርተዋል፡፡ ወደ መቶ ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጦርነት ከተካሔደ በኃላ ሀገራቱ…

በኢትዮጲያ እና ኤርትራ አዲስ የሠላም ጉዞ ውስጥ የአልጀርስ ስምምነት እና የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔ ሚና
መንደርደሪያኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደ አዲስ የሰላም ሒደት አምርተዋል፡፡ ወደ መቶ ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጦርነት ከተካሔደ በኃላ ሀገራቱ በተኩስ አልባ ጦርነት ውስጥ ከርመዋል፡፡ ጦርነቱ በአልጀርስ በተደረገ ስምምነት ቢቋጭም፣ በስምምነቱ የተመሠረቱ የግልግል ዳኞች ውሳኔ አፈጻጸም ግን እልባት ሳያገኝ አስራ ስምንት ዓመታት አልፈዋል፡፡ በተለይ ወደ አንድ ሺህ ኪሎሜትር የሚጠጋውን የሀገራቱን የድንበር ወሰን ለመወሰን የተቋቋመው ኮሚሲዮኑ  የሰጠው የድንበር ማካለል ውሳኔ ተፈጻሚነት ሀገራቱን ሊያስማማ አልቻለም፡፡ ኮሚሲዮኑ በሦስት አቅጣጫ ያሉ ድንበሮችን ሲያካልል፤ በአንዱ (በደቡብ)   አቅጣጫ ያለው የድንበር ጉዳይ ለአለመስማማታቸው ዋና ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ የገዢው ፓርቲ የውስጥ የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ እያሳየነው፡፡ በትህነግ (ሕውሃት) የበላይነት ሲዘወር የኖረው የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲም የለውጡ ወላፈን ደርሶታል፡፡ ይህንንም ለውጥ ተከትሎ ኢትዮጵያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የአልጀርስ ስምምነቱን እና የድንበር ኮሚሲዮኑን ውሳኔ ለመፈጸም መስማማቷ ተገልጿል፡፡ ይሄም በባለ 5  ነጥቦች ስምምነት አንቀጽ 4  ላይ ተካቶ በሀገራቱ ፍቃድ የሕግ አስገዳጅነት እንዲኖረው ሆኗል፡፡ ነገር ግን የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔ አፈጻጸም አሁንም የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔ አፈጻጸም ከመንግሥታት አልፎ በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ለልዩነቶች ምክንያት የሆነው ለምንድነው፣ መስማማት ላይ ሊደረስስ የሚቻለው እንዴት ነው?  የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጸሐፊው ስለሀገራቱ የግጭት መንስኤ፣ ግጭቱን ለመፍታት ስለተደረገው የአልጀርስ ስምምነት፣ ስለግልግል ዳኝነት፣ ስለድንበር ኮሚሲዮኑ የክርክር  እና ውሳኔ ሒደት እና ክፍተት ለመዳሰስ ጥረት ያደርጋል፤ እንደመደምደሚያም አጭር የመፍትሔ ሐሳብ ያቀርባል፡፡የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት የወዲያው ምክንያትለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት መነሻ የድንበር ግጭት መሆኑ ይገለጻል፡፡ ሁለቱም ሀገራት ድንበሬ ተጥሷል በሚል ተወነጃጅለዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ኤርትራ እ.ኤ.አ በግንቦት 6 ቀን 1998 ዓ.ም ላይ በባድሜ አካባቢ የተመደቡ የጸጥታ ሚሊሻዎቼ ላይ ጥቃት ማድረሷ፣ ይህንንም ተከትሎ ይርጋ ከተማን እና ባድሜን በከፊል መቆጣጠሯ ለጦርነቱ መነሻ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ኤርትራ ደግሞ በበኩሏ ከዚያ በፊት እ.ኤ.አ በሐምሌ ወር 1989 ዓ.ም ኢትዮጵያ በባድሜ አቅጣጫ ዓዲምሩግ ወደ ተባለው አቅጣጫ ድንበር ጥሳ ገብታ አስተዳደሩን መበታተኗ እና የኤርትራንም ሹማምንት ማባረርዋ ለግጭቱ መነሻ እንደሆነ ተከራክራለች፡፡ በድንበር አለመስማማታቸው ሀገራቱን ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዲገቡ የወዲያው (Immediate Cause) ቢሆንም የግጭቱ መንሥዔ ግን ከድንበር የዘለለ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ጉባዔዎች ድንበሩ ላይ በማተኮር ድንበርን እንዲያካልሉና ችካል እንዲተክሉ፣ ኃይል በመጠቀም የዓለም አቀፍ ሕግ የተላለፈውን ሀገር እንዲለዩ፣ እናም እያንዳንዱ ሀገር በጦርነቱ ምክንያት የደረሰበትን ኪሳራ አጣርተው የካሳ መጠን ለመወሰን ሲሞክሩ ነበር።ስለዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት በጥቂቱ:  የዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት  ሀገራት አለመስማማታቸውን የሚፈቱበት አንደኛው እና ዋነኛው አካሄድ ነው፡፡ የግልግል ዳኝነት ጉባኤ የሚመሠረተው የተለየ አንድ ጉዳይን ብቻ ለመመልከት ሲሆን አባላቱም በተከራካሪ ወገኖች የሚመረጡ ይሆናሉ፡፡ ለዳኞቹም ሆነ ለሒደቱ የሚከፈሉ ክፍያዎች የሚፈጸሙት በተከራካሪዎቹ ወገኖች ነው፡፡ አንድ ጉዳይ በግልግል ዳኝነት እንዲታይ የተከራካሪ ወገኖች ይሁንታም የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ይሁንታ በተለያዩ ሁኔታዎች ሊሰጥ ይችላል፤ በግልግል ዳኝነት ስምምነት (ማለትም ምንም አይነት አለመስማማት ቢፈጠር ጉዳዩን በግልግል ዳኝነት እንዲታይ) ፣ በአጠቃላይ ስምምነት ውስጥ በሚኖርና አለመስማማትን በግልግል ዳኝነት ስለመፍታት በሚገልጽ ድንጋጌ ወይም፣ አለመስማማቱ ከተፈጠረ በኋላ በሚደረግ ስምምነት የተከራካሪ ወገኖች ይሁንታቸውን ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የግልግል ዳኞች፤ አጠቃላይ የሕግ እና እኩልነት መርህን እንደሚከተሉ ግምት ቢወሰድም፣ ስልጣኑ (ምን ጉዳይ ላይ አከራክሮ መወሰን እንደሚችል እና ምን ማስረጃ እንደሚጠቀም) የሚወስኑት የተከራካሪ ወገኖች ሲሆኑ፣ ጉባኤው ይሄንን ስልጣኑን ተላለፎ የሚሰጠው ውሳኔ ውጤት አይኖረውም፡፡ የግልግል ዳኞች የሚወስኑት ውሳኔ የመጨረሻ እና ገዢ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ውጤታማ እና እኩሌታን የሚያሰፍን የዳኝነት አካሄድ መሆኑ ይነገርለታል፡፡የአልጀርስ ስምምነት እና ኮሚሲዮኖቹየአልጀርስ ስምምነት የተደረገው እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሐምሌ 11 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር፡፡ የስምምነቱ ዓላማ ሁለቱን ሀገራት ወደ ዘላቂ ሰላም ማሸጋገር እና መልሶ ማቋቋም ነበር፡፡ ስምምነቱ በይዘቱ ውስን ሲሆን 8 አንቀጾችን ብቻ ያካተተ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ድንጋጌዎች ላይ ሁለቱ ሀገራት በዘላቂነት ኃይል ከመጠቀም እንደሚቆጠቡ እና በጦርነቱ ጊዜ የተያዙ የወታደር እና ሲቪል ግለሰቦችን ሀገራቱ እንዲረካከቡ ግዴታዎችን የሚጥሉ ናቸው፡፡ የስምምነቱ ዋነኛ ክፍል የሚባሉት አንቀጽ 3፣ 4፣ እና 5 ለግጭቶች መፍትሄ እንዲሰጡ የተለያዩ ኮሚሲዮኖች (የግልግል ዳኝነት ጉባኤዎችን) የሚቋቋሙበትን አግባብ ይደነግጋሉ፡፡በአንቀጽ 3 መሠረት የሚመሠረተው ገለልተኛ አካል ሲሆን የሚቋቋመውም በአፍሪካ ህብረት (የዛኔው የአፍሪካ አንድነት) ስር ነበር፡፡ አባላቱ የአፍሪካ አንድነት ኃላፊ ከተባበሩት መንግሥታት ኃላፊ እና ከሀገራቱ ጋር በመከካር ይሾሟቸዋል፡፡ የተቋሙ ስራም የጦርቱን መነሾ፣ ማን ቀድሞ ግዛት እንደደፈረ እና ኃይል እንደተጠቀመ ማጣራት ሲሆን ይሄ ገለልተኛ ተቋም እውነታውን አጣርቶ ሪፖርት ለአፍሪካ አንድነት የሚያቀርብ ነበር እንጂ ሀገራቱን የሚያከራክር አልነበረም፡፡ሆኖም ግን ይህ አካል በስምምነቱ መሠረት አልተመሠረተም፡፡ሁለተኛው በስምምነቱ የተቋቋመው አካል ነጻ የሆነ የድንበር ኮሚሲዮን (Neutral Boundary Commission) ነው፡፡ይህ አካል በአምስት አባላት ሲቋቋም፣ ሀገራቱ ሁለት ሁለት አባላትን ይሾሙና የኮሚሲዮኑ ፕሬዝዳንት ደግሞ በእነዚህ አራት አባላት ይሾማሉ፡፡ ኮሚሲዮኑ በሀገራቱ በሚቀርብለት የቀኝ ግዛት ስምምነቶች እና ተፈጻሚነት ባላቸው የዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት በሀገራቱ መካከል ያለውን ድንበር የማካለል (delimitation) እና ችካል የመትከል (demarcation) ሀላፊነት ነበረው። ኮሚሲዮኑ የሚጠቀምባቸው የቀኝ ግዛት ስምምነቶች፤ (እ.ኤ.አ.) የ1892 (የተፈጸመው በኢትዩጵያ እና ጣሊያን መካከል ሲሆን የሚያካልለው የመሀል ክፍሉን ነው)፣ የ1894 (የተፈጸመው በኢትዮጵያ፣ ጣሊያን እና እንግሊዝ መካከል ሲሆን የሚያካልለው የምዕራብ ክፍሉን ነው) እና የ1900 (የተፈጸመው በኢትዮጵያ እና ጣልያን መካከል ሲሆን የሚያካልለውም የምስራቁን ክፍል ነው) ናቸው፡፡ ኮሚሲዮኑም ሀገራቱን ካከራከረ እና የቀረቡለትን የቀኝ ግዛት ስምምነቶች እና ሌሎች ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ የድንበር ማካለሉን ውሳኔ በ125 ገጽ በሚያዚያ 6 ቀን 2002 ዓ.ም ላይ በሄግ (ሆላንድ) ላይ ሰጥቷል፡፡ የችካል መትከሉ ሒደት ግን ሀገራቱን ሳያስማማ ላለፉት 18 ዓመታት ሳይፈጸም ቆይቷል፡፡ሦስተኛው ተቋም ነጻ የግልግል ዳኝነት ኮሚሲዩን (Neutral Claims Commission)ሲሆን የተመሠረተውም በአልጀርሱ ስምምነት አንቀጽ 3 መሠረት ነው፡፡ የተሰጠው ስልጣንም በጦርነቱ ምክንያት ሀገራቱ የደረሰባቸውን ጉዳት እና ኪሳራ የማጣራት እና የካሳ ክፍያ ውሳኔም የመስጠት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ኮሚሲዩኑ ሁለቱን ሀገራት አከራክሮ እና መረጃዎችንም ከሰማ በኃላ ሀገራቱ የደረሰባቸውን የጉዳት መጠን በመግለጽ በልዩነቱ ኤርትራ 10,515,655 የአሜሪካን ዳላር ለኢትዮጵያ እንድትከፍል ወስኗል፡፡ ከዚህ በሻገር ኮሚሲዮኑ ኤርትራ የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር አንቀጽ 2(4) በተመተላለፍ በቅድሚያ ኃይል የተጠቀመችው እሷ ነች በሚል ወስኗል፡፡የድንበሩም ሆነ የካሳው ኮሚሽን ውሳኔዎች አልተፈጸሙም፡፡ በተለይ የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔ ለሀገራቱ ዘላቂ አለመስማማት ዋነኛው ምክንያት ሆነ፡፡ የድንበር ማካለሉ ውሳኔ ላይ ሀገራቱ ለመስማማት የአለመቻላቸው ዋነኛው ምክንያት ደግሞ መጀመሪያውኑ ግጭቱ ከድንበር የዘለለ ሆኖ ሳለ፤ የግጭት አፈታት ሒደቱ ግን በድንበር ማካለል ላይ ብቻ የተገደበ፣ አጠቃላይ የግጭቱን መንስኤዎች ከግምት ውስጥ ያልከተተ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የድንበር ኮሚሲዮኑ አወቃቀር፣ የክርክሩ ሒደት እና ውሳኔውም ላይ የተለያዩ ክፍተቶች ነበሩ፡፡የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ግጭት ከድንበር ባሻገርግጭቱን ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ፍትህ (ህግደፍ/ PFDJ) እና ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ(ሕውሃት/TPLF) የ“ቀዳሚ እና ተከታይ” ግንኙነት ጋር የሚያገናኙ ብዙ ናቸው፡፡ ሽምቅ ተዋጊዎቹ ወደ መንግሥትነት ሲመጡ የበፊት የበላይነት ፍኩቻቸውን ይዘው መጥተዋል፡፡ በፊት የነበራቸውን የጫካ ግንኙነት ቀይረው እንደመንግሥት እና ሀገርን የሚወክል ተቋም ድርድር ማድረግ አለመቻላቸው አለመስማማታቸው ወደ ደምአፋሳሽ ጦርነት ለመቀየሩም አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ ሁለቱ መንግሥታት ገና በሁለት እግራቸው ሳይቆሙ ሰፋፊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስምምነቶችን ፈጽመው ነበር፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ነጻ ሀገር ከሆነች እና ጦርነቱ እስኪከሰት ድርስ ሀገራቱ የነበራቸውን ግንኙነት ከጫጉላ ሽርሽር ጋር የሚያገናኙም አሉ፡፡ በቅጡ ያልተጠኑ እና መሠረተ ቢስ ግንኙነትቶች የሀገራቱ መገለጫዎች ሆነው ነበር፡፡ የአስመራ የስምምነቶች ጥንቅር (Asmera Pact) ውስጥ 25 የተለያዩ ዝርዝር የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ፓሊሲዎችን ለማቀናጀት የታሰቡ እና ነጻ የንግድ ቀጠናዎችን ከመመሥረት ጋር የተያያዙ ስምምነቶች ተፈርመው ነበር፡፡ በእነዚህ ስምምነቶች መሠረት ኤርትራን የአገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ እና የውጪ ንግድ መናኸርያ አድርጎ፣ ኢትዮጵያን ከውጪ የሚመጡ ምርቶችን የሚተኩ እና የግብርና ምርቶችን እንድታመርት አቅጣጫ የሚያስቀምጡ ስምምነቶች ተደርገዋል፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት እ.ኤ.አ ከ1993 እስከ 1996 ድረስ 60 በመቶ የሚሆኑት የኤርትራ ምርቶች የሚላኩት ወደ ኢትዮጵያ ነበር፡፡ ኤርትራም ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት ንግድ በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታገኝ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሀገራቱ ለየብቻቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በማውጣት እና የየራሳቸውን የመገበያያ ገንዘቦችን በማተም ያልተማከለ የንግድ ስርዓት መመሥረታቸው ወደ አለመስማማት ፣ በኋላም ወደ ግጭት፣ ቀጥሎም ወደ ጦርነት ለመሄዳቸው ዋነኛው ምክንያት ነበር፡፡ከዚህ ባሻገር ኤርትራ የአፍሪካ ቀንድ የልማት ቀጠና ለመሆን ማሰቧ እና ይሄም በደካማ እና በተከፋፈለች ኢትዮጵያ ላይ እውን ሊሆን እንደሚችል የወሰደችው ግምትም የኢሳያስን አስተዳደር ወደ ጦርነት እንዳመራው ይነገራል፡፡ ሀገራቱ የሕዝባቸውን የልማት እና የፖለቲካዊ ተሳትፎ ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላቸው የሕዝቡን ትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር የታሰበም ነው የሚሉ ክርክሮች አሉ፡፡ በተለይ ኤርትራ አዲስ የተመሠረተች ሀገር እንደመሆኗ የሕዝቧን ሀገራዊ ስሜት ከማጠናከር አኳያ በፊት “በቀኝ ግዛት” ከያዘቻት ሀገር ጋር ወደ ጦርነት መግባት እንደአማራጭ ልትወስድ እንደምትችል እሙን ነበር፡፡ታዲያ እኚህ ሁሉ የተወሳሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ማኅበረሰባዊ ልዩነቶች ለግጭት ምክንያቶች  ሆነው ሳለ የግልግል ዳኞች ድንበር እንዲያካልሉ በመወሰን ብቻ ችግሩ እንዴት እንደሚፈታ አሰቡ? ይሄን ለመመለስ የአልጀርስ ስምምነትን ይዘት እና የድንበር ኮሚሲዮኑን የግልግል ዳኝነት ሂደት እና ውሳኔ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡የኮሚሲዮኑ የድንበር ማካለል ሒደት እና ውሳኔ ክፍተቶችበመጀመርያ ኮሚሲዮን እንደማስረጃ የሚጠቀማቸው የቀኝ ግዛት ስምምነቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ውድቅ ስለሆኑ ለድንበር ማካለሉ እንደማስረጃ መቅረብ አልነበረባቸውም፡፡ የቀኝ ግዛት የድንበር ማካለል ስምምነቶቹን ጣልያን ኤርትራን ወክላ በ1947 ዓ.ም ውድቅ ስታደርግ፣ ኢትዮጵያም በአዋጅ ቁጥር 6/1952 መሠረት ስምምነቱ ውቅድ እንደሆነ በሕግ ደንግጋለች፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለቱም ሀገሮች ስምምነቶቹን እንደማስረጃ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መስማማታቸው ከዓለም አቀፍ የስምምነት ሕግ (Law of Treaty) አንጻር አግባብ አልነበረም።ከዚህ ባሻገር በአልጀርስ ስምምነት መሠረት ኮሚሲዮኑ በሒደቱ ላይ የሀገራቱን የጋራ ጥቅም እና እኩልነት አጠቃላይ የሕግ መርህዎች (ex aequo et bono) ላይ ተመስርቶ ውሳኔ መስጠት እንደማይችል ተደንግጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የድንበር ኮሚሲዮኑ የማኅበረሰቡን አወቃቀር እና የመልክአምድሩን ሁኔታ ግምት ውስጥ ሳይከቱ ውሳኔ እንዲሰጡ ምክንያት ሆኖአል፡፡ ይሄም ቢሆን ከቀኝግዛት ስምምነቶቹ ባሻገር ኮሚሲዮኑ “ተፈጻሚነት ያላቸው የዓለም አቀፍ ሕጎች” እንዲጠቀም ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት ኮሚሲዮኑ ስምምቶቹን የመተርጎም ብቻ ሳይሆን ሌላ ከድንበር አወሳሰን ጋር የሚያያዝ የዓለም አቀፍ መርህን፣ ማለትም ግዛቱን ሉዓላዊነት ባለቤትነት ይዞ የመቆየት መርህ (Principle of effectivités) ግምት ውስጥ ለመክተት ሞክሯል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አወዛጋቢውን የባድሜን ግዛት ከጦርነቱ በፊት ይዛ እና የሉአላዊ ግዛቷ አድርጋ እያስተዳደረች መቆየቷን ለማስረዳት አልቻለችም፡፡ በመጀመሪያው አቤቱታዋ ላይ ምንም ክርክርም ሆነ ማስረጃ ካለማቅረቧ ባሻገር በቃል ክርክሩም ሆነ በሁለተኛው አቤቱታዋ (Counter Claim) ላይ በበቂ ሁኔታ ባለመከራከሯ እና ማስረጃም ባለማቅረቧ ኮሚሲዮኑ “በማስረጃ እጥረት” በሚል ግዛቱን ለኤርታራ ወስኗል፡፡ሲቀጥል የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔ ላይ የምዕራብ ክፍሉን በሚመለከት የተገለጸው ውሳኔ ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ የባድሜ ግዛት ከውሳኔው ጋር በተያያዘው ካርታ ላይ በግልጽ አልተመላከተም፡፡ ይሄም ሁለቱም ሀገራት ባድሜ እንደተወሰነላቸው አድርገው መግለጫ ለመስጠታቸው ምክንያት እንደሆነ ይገለጻል፡፡የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔ በጥድፍ-ጥድፍ መሰጠቱም አንዱ ድክመቱ ነበር፡፡ የአልጀርስ ስምምነት የድንበር ኮሚሲዮኑ ውሳኔውን እንዲሰጥ የተሰጠው ጊዜ ክርክሩ ከተጀመረ በኃላ ባሉት 6 ወራት ውስጥ ብቻ ነበር።በተጨማሪም የካርታ ንባብ እና የመልክአ ምድር ጥናት ባለሙያዎችን በሚመለከት የተባበሩት መንግሥት የካርታ ጥናት ክፍል የሙያ ድጋፍ የሚሰጥበት አግባብ እንጂ፣ በኮሚሲዮኑ ውስጥ በቋሚነት አባል የሆኑ የካርታ ንባብ እና የመልክአ ምድር ጥናት ባለሙያዎች አልተካተቱም፣ ይሄም በኮሚሲዮኑ ብቃት ላይ አሉታዊ አስተዋጾ ነበረው፡፡ ኮሚሲዮኑ በቦታው ላይ ተገኝቶ ጥናት ባለማካሄዱ ውሳኔውን ግልጽ እና ሙሉ እንዳይሆን፣ “ጭፍን ፍትህም” እንዲሆን ምክንያት ሆኖአል፡፡ከዚህ በሻገር የድንበር ኮሚሲዮኑ ባድሜን በሚመለከት የሰጠው ውሳኔ ጉዳት እና ካሳን ለመወሰን ከተቋቋመው ኮሚሲዮን ውሳኔ ጋር ይቃረናል፡፡ ጉዳት እና ካሳ ለመወሰን የተቋቋመው ኮሚሲዮን ኤርትራ እ.ኤ.አ በግንቦት 6 ቀን 1998 ዓ.ም የባድሜን ግዛት በመወረር ኃይል ተጠቅማለች፣ በዚህም የተባበሩት መንግሥታትን አንቀጽ 2(4) ተላልፋለች በሚል ሲወስን የድንበር ኮሚሲዮኑ ግዛቱ ለኤርትራ ይገባል በሚል መወሰኑ በአንድ ስምምነት በተመሠረቱ ኮሚሲዮኖች መካከል የነበረውን ተቃርኖ የሚያሳይ እና በሒደቱም ላይ ክፍተት እንደነበር የሚያመላክት ነው፡፡እንደ መፍትሔ-ሐሳብየተጀመረውን ሰላም ዘላቂነት ማረጋገጥ - ሀገራት ፍቃዳቸውን የሰጡባቸውን ስምምነቶች የመፈጸም ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ በስምምነታቸው መሠረት የሚመሠረቱ የግልግል ዳኞች ውሳኔ አስገዳጅ እና የመጨረሻ ውሳኔዎች ናቸው፣ ይህም በአልጀርሱ ስምምነት ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ሀገራት በስምምነት የመሠረቱት ተቋም የሰጠውን ውሳኔ በስምምነት ሊያፈርሱት አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ የሀገራት ሉዓላዊነት የዓለም ዓቀፍ ሕግ ዋነኛ መርህ መሆኑን ልብ ይሏል፤ ከተስማሙ ያሻቸውን የመወሰን መብት አላቸው፡፡ አሁን ሁለቱ ሀገራት በቅን ልቦና ወደ ሰላም ለመጓዝ ፍቃደኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይህንን የሰላም ጉዞ ዘላቂነት ለማረጋገጥ ደግሞ በሕዝቦች፣ በተለይ በድንበር አካባቢ በሚገኙት ሕዝቦች መካከል የማኅበራዊ ግኑኝነቶች መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ የሁለቱም ሀገራት የሀይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች ስለእርቅ፣ ይቅር መባባል እና አብሮነት ማስተማር አለባቸው፡፡ መንግሥታቱ በሚሰጡት መግለጫዎችም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን በሚሰሯቸው ዘገባዎች፤ ግጭቱ እየተፈታ መሆኑን በሚያጎሉ ትርክቶች ላይ ትኩረት መስጠት፣ የሕዝቡንም አመለካከት ከግጭት ይልቅ በሰላም እንዲቃኝ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ሀብት አንጻር በፍትሃዊነት በሚጠቅሙበት ሁኔታ የተዋቀረ የንግድ ግንኙነቶች መጠናከር አለባቸው፡፡ ከ100  ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ ያለውን የባሕር መውጫ የመጠቀም መብት፣ የወደብ ተጠቃሚነቷን በዘላቂነት ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡የድንበር ኮሚሲዮኑን ውሳኔ በፖለቲካዊ መግባባት ማስተካከል - የሰላም ስምምነቱ ከጸና እና ሀገራቱም በቅን ልቦና ለመደራደር ፍቃደኛ ከሆኑ የድንበር ችካሉ ሒደት በስምምነት የማይፈጸምበት ምክንያት የለም፡፡ ሁለቱም ሀገራት ከሚፈልጓቸው ግዛቶች ውስጥ የታጠፉባቸው አሉ፡፡ የድንበር ኮሚሲዮኑ ባስቀመጠው መሠረት ድንበሮቹ በመሬት ላይ ቢካለሉ ከተሞችን እንደሚከፍሉ፣ ቤተሰቦችን እንደሚበታትኑ እና ማኅበራዊ ሕይወትንም እንደሚያምታቱ ማንም የማይክደው ኩነት ነው፤ ኮሚሲዮኑም ከውሳኔው በኃላ ይህንን ገልጾታል፡፡ ከዚህ በሻገር ማህበረሱቡን አስገድዶ ወደ ሌላ ሀገር ግዛት ማካተት ውጤቱ ሌላ የነጻነት ተዋጊ መፍጠር፣ ወደ ሌላ ግጭት ማምራት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የችካል መትከሉ ሒደት ግዴታ በድንበር ኮሚሲዩኑ ውሳኔ መሠረት መሆኑ ቀርቶ ከተለያዩ ግዛቶች ማቻቻል ይቻላል፣ በዚህም ሁለቱንም ሀገራት ሳያጣላ መፈጸም ይችላል፡፡የድንበር ማካለሉን/ ችካል መትከሉን የሚያሰፈጽሙ ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን ማቋቋም፣ ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ እና ወጪውንም ማፈላለግ - የድንበር ማካለሉን እና ችካል መትከሉን ስራ ለማስፈጸምም ከሁለቱም ሀገራት ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን መኖር አለበት፡፡ የችካል መትከል ስራውን ለማካሄድ በአልጀርስ ስምምነቱ መሠረት የተቋቋመው ኮሚቴ ተበትኗል፡፡ አሁን እነሱን መመለስ ቀላል ካለመሆኑ ባሻገር (የአባላቱ ፍላጎት እና ሁሉም በሕይወት መኖራቸውም አይታወቅም) ተገቢም ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሀገራቱ የውጪ ጣልቃ ገቦች እንብዛም ሳይሳተፉ ወደ ስምምነት እንደመጡት ሁሉ (የዱባይ፣ የሳውዲ አረቢያ እና የአሜሪካ አደራዳሪነት ቢኖርም ሀገራቱን ከማገናኘት የዘለለ ብዙ ስራ እንዳልሰሩ ልብ ይሏል) ድንበራቸውን ለማካለልም የራሳቸውን አባላት ቢያካትቱ የተሻለ ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” እንዲል። የውጪ ዜጎች መሳተፍ ካለባቸው የባለሙያዊ እርዳታን በመስጠት ላይ ብቻ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የኮሚቴ አባላት ስራቸው በአግባቡ እንዲሰሩ ደህንነታቸው ሊረጋገጥ ይገባል።  በዚህም ምክንያት ሁለቱም ሀገራት የመከላከያ ሰራዊታቸውን ከድንበር አካባቢ ራቅ ማድረግ እና በሲቪል እና ፖሊስ ጥበቃዎች ስር ማድረግ አለባቸው፡፡ ለእንደዚህ አይነት ስራዎች ለስራውም ሆነ ለባለሙያዎቹ ክፍያ ከፍተኛ ወጪ ስለሚያስፈልግ ሀገራቱ ይህንን ወጪ በአስቸኳይ ማፈላለግም ይኖርባቸዋል፡፡የሒደቱን ግልጽነትና አሳታፊነት ማረጋገጥ - የችካል መትከሉ ሒደት ግልጽ እና አሳታፊ መሆንም ይኖርበታል፡፡ በተለይ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ፍላጎታቸውን ከመንግሥት ጋር በግልጽ እና ተከታታይነት ባለው ውይይት መመካከር ይኖርባቸዋል፡፡ ሒደቱም ላይ የሚሳተፉበትን አካሄድ መንግሥታቱ ማመቻቸት አለባቸው፡፡ በተለያዩ መዋቅራዊ ደረጃዎች ሕብረተሰቡ በሒደቱ ውስጥ መወከል፣ የሒደቱም ባለቤት መሆን ይኖርበታል፡፡ መንግሥታቱ ሒደቱን በየጊዜው ለሕዝብ የማሳወቅ ግዴታም አለባቸው፡፡

አስተያየት