ነሐሴ 3 ፣ 2010

የኢትዮጵያ ሕዝብ...  "ነጯን ጥንቸል ተከተላት"

ፖለቲካኑሮSocietyፊልም

መድረሻውን መሰቀል አደባባይ ያደረገው የሰኔ 16 ሰላማዊ ሰልፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳትፏል። በቀናቶች ልዩነት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች…

የኢትዮጵያ ሕዝብ...  "ነጯን ጥንቸል ተከተላት"
መድረሻውን መሰቀል አደባባይ ያደረገው የሰኔ 16 ሰላማዊ ሰልፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳትፏል። በቀናቶች ልዩነት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሚሊዮንች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከቀያቸው ተፈናቅለው ለእንግልትና ለስቃይ ተዳርገዋል። ይባስ ብሎ የመጣውን የመልካም ለውጥ አየር ሊበክሉ ያለሙ የሚመስሉ አስደንጋጭ ዜናዎችም እየተደመጡ ነው፡፡ አሁን በየቦታው የሚነሳውን ተቃውሞና ሁከት አንድምታ ምን እንደሆነ ለማውቅ አርቆ አሳቢ መሆን ባይጠይቅም ውጤቱ ሊያመጣ የሚችለውን አስከፊ ገፅታ ለመገንዘብ ግን ረጅም ጥሞናን ይጠይቃል።ሰላማዊ ሰልፉ መልካም ውጤት አስገኝቶ እንደነበረው መፈናቀሉ ደግሞ በተቃራኒው አቻ የሚሆን አሰከፊ ውጤት አስመዝግቧል። በዚህም ሁለት ተቃራኒ ሃይሎች ትግል ላይ እንዳሉ መገንዘብ ይችላል። ለዚህ የሁለት ተቃራኒ ሃይሎች ፍልሚያ የቀረው ሰው ተግባር ምን መልክ እንዳለው ለመገንዘብ መሞከርም ቀላል አይደለም። የሁለቱ ቡድኖች ግብግብ ለኃይል ሚዛን የጉልበት መፈተሻ ቢመስልም በሂደት መከራና ሞት ጥሎ የሚያልፍ የለየለት ፀብ ለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ኢትዮጵያዊው “ሜትሪክስ”በ1999 ለዕይታ የበቃው ዘ ሜትሪክስ (The Matrix) የተሰኘው ሳይንስ ፊክሽን ፊልም ዓለም የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ እጅግ እንዲዘቅጥና ለራሳቸው ዘላቂ ጥቅም እንዲውል በሚተጉ ወታደር ሳይንቲስቶች [ማሽኖች] ቁጥጥር ስር ውላ ታሪኩ ይጀምራል። በሲኒማ የVfx ቴክኖሎጂ አብዮት ብቻ ሳይሆን ያመጣው ለብዙ ፍልስፍና እና ኃይማኖታዊ ህሳቤዎች ከፕሌቶ Allegory of the Cave እስከ Jean Baudrillard's Simulacra and Simulation ድረስ ማጣቀሻ መሆን የቻለ ፊልም ነው፡፡ በማህበረሰብ ፓለቲካ ውስጥ አሁንም ድረስ ሰዎች ከሚጠቅሷቸው የእንስሳት ዕድር [animal farm] 1894 እና Brave new world መጻሐፍት እኩል ያለነበትንና መጪውን የዓለም ስርዓት የተነበየም ጭምር ነው፡፡የሰውን ልጅ የቀን ተቀን እንቅስቅሴውና የሰውነት ሙቀቱን ሳይቀር ለሃይል ማመንጫነት የተጠቀሙት እነኚህ ማሽኖች ይህን የባርነት ቀንበር እንዳያስተውል ማትሪክስ በተባለ አጭበርባሪ ወጥመድ [ማዕቀፍ] አስረውት ይታያል። ማሽኖቹ በየቦታው ጦር ከማደራጀት በዘለለ አበክረው ሲስሩበት የነበረው ሰዉን በአስፈላጊው ሁኔታ እጅግ በቀላሉ በማስቆጣት [ህሊናውን በመስለብ] በደመ ነፉሱ እየተመራ የሚያጠፋ በፈለጉት ሰዓትና ጊዜ የሚታዘዝ ንቁ ሎሌነት መቀየርን ጭምር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የኮምፒዩተር ባለሙያ የሆነው ኒዮ ይህን እውነታ በማስተውል የማሽኖቹ ሴራ ተገልፆላቸው ራሳቸውን ነፃ ካወጡ እንደ ሞረፊየስ ትሪኒቲና ኦርክል ካሉ ሌሎች ነፃ አውጪዎች እርዳታ በመታገዝ የሰውን ልጅና መኖሪያውን ፅዮንን ከባርነት ነፃ ለማውጣት የሚያደርገውን ፍልሚያ የሚያሳይ ፊልም ነው። በዚህም ሁለት ተቃራኒ ሃይሎች ግብግብ ላይ እንዳሉ ይስተዋላል። ይህም አሁን ያለውን የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በድምብ ለማብራራት ይጠቅማል።በኢትዮያጵያ ላለፉት ዓመታት የነበረው የነጻነት ትግል ገዢው አስተዳደርና ተጨቋኙ ማህበረሰብ [የኢትዮጵያ ህዝብ] አሰላለፍ ተመሳሳይ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ገዢዎች በማትሪክስ ላይ እንደምናያቸው ማሽኖች ህዝቡ ጋር ሳይደርሱ በፊት መጀመሪያ የቀየሩት ያለበትን ዓለም ነው፡፡ ወዶ ፈቅዶ ለባርነቱ አቤት ባይ እና የአላማቸው መገልገያ እንዲሆን ፍርሃት ላይ የተመሰረተ አጭበርባሪ ማዕቀፍ [ኢትዮጵያዊ ማትሪክስ] ቀድመው ነው የጫኑበት። በዚህ ምክንያት በዘርና ድህነት ምክንያት በፍርሃት ተጠምዶ ተራምዶ የሚራምደው ጀግና አጥቶ ማዕቅፉ ውስጥ ግራና ቀኝ ሲላጋ ቆይቷል።ፍርሃት አያ አይምሬ! ዘ ሜትሪክስ በተሰኘው ፊልም ከወጥመዱ ላመለጡ ቡድኖች የነበረው ፈተና መንታ ነው፡፡ አንደኛው ዓላማቸውን ተረድቶ ተራምዶ የሚያራምዳቸው ጀግና ማጣት ሲሆን ሁለተኛው በቅጡ በምን ስርዓት ስር እንዳለ ያልተረዳው ሳይውቅ የማሽኖቹ ተባባሪ የሆነው የማህበረሰብ ክፍል ነበር፡፡ ማሽኖቹ ሰውን የሃይል ምንጫቸው አድርገው ለረጅም ዘመን በባርነት ሲገዙ ሁለት ዋነኛ ተግባራትን አበክረው እየከወኑ ነው። አንድ በፍርሃት በመሸበብ ስለ አካባቢው ያለውን እውነታ እንዳይረዳ እውቀት አልባ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እውነቱ ጋር ደርሶ ነፃ የወጣውንም ሆነ ነፃ አወጣለው ያለውንም አሳደው በማጥፋት ነው።የትኛውም ዘመን ላይ የጨቆኞች ዋንኛ መሳሪያ ፍርሃት ነው። ሌላው ሌላው መቧደን በሙሉ፤ በመሃይምነት ማስቸገርም ሆነ በዘር መተብተብ ጭምር ፍርሃት የተለበጠባቸው ጌጦች እንጂ በራሳችን ካልቆምን ብለው የሚያስቸግሩ አካሎች አይደሉም። ፍርሃት አብሮን ያለ የሰውኛ ባህሪያችን ነው። ኔልሰን ማንዴላ “ብርቱ ሰው ማለት የማይፈራ ሳይሆን ፍርሃትን ድል የሚነሳ ነው ” እንዳሉት ፍርሃትን በዕወቀት ጎልብተን እስካላሸነፍነው ድረስ እውነታ ጋር መድረስም ሆነ በጀግንነት መንገስ አንችልም። ሰው እውነትን እስካልያዘና ፍርሃቱን እስካላስወገደ ድረስ ብቻውን ለመቆም የሚያስችል የህሊና ልዕልና አይኖረውም። በመጀመሪያ ብቻውን ለመቆም ጥንካሬ የሌለው ሰው ምን ሃይማኖተኛ ቢሆን ምን የተማረ ቢሆን ምን ባለሃብት ቢሆን ከመቦደን [ከዘረኝነት] አያመልጥም።ፍርሃትን ማሸነፍ እጅግ ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ወደ ግብ መድረሻ የመጨረሻ ፈተናም ጭምር ነው። ለዚህም የሶቅራጥስን እና የኢየሱስን የመጨረሻ ፈተና ማየት ያሻል፡፡ ሶቅራጥስ ከቅጣቱ ያመልጥ ዘንድ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ፅዋውን የተጎነጨው ፍርሃቱን አሸነፎ ነው። ሶቅራጥስ ዕወቀቱ የተመዘነውም ሆነ በዘመን የነገሰው አንድም ፅዋውን በመጠጣቱ ነው። በደቀ መዛሙርቱ ተመሳሳይ የፈሪ ምክር የተመከረው ኢየሱስም ተላልፎ ከመሰጠቱና ሊያስመልጡት ሰይፍ ያነሱትን ደቀመዛሙርቱን ገስፆ ፍርሃትን ከመጋፈጡ በፊት ያደረጋት ፀሎት ‘አባት ሆይ ብትወድስ ይቺ ፅዋ ከኔ ትለፍ’ የምትል ናት። ላስተዋለ ይህች ፀሎት የፅዋውን ከባድነት ብቻ ሳይሆን የፍርሃትንም ሃይለኝነት በሚገባ ታሳያለች።ለዚህም ነው ማሽኖቹ ፍርሃትን ተጠቅመው የሰውን ልጅ ቀፍድደው በመያዝ አላማቸውን ለማሳካት የሚታትሩት። ይኽም [ዓላማቸው] የሃይል [የጥቅማቸው] ምንጭ የሆነውን የሰውን ልጅ ለዘላለሙ በባርነት መግዛት ነው። በኢትዮጵያችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ሰዎች መበዝበዝ ከጀመሩና ነፃነታችውን ከተቀሙ ረጅም ዘመን አስቆጥረዋል። አልፎም በፍርሃት ተተብትበው በዘረኝነት በድህነትና በሌሎችም ተራ ምክንያቶች እየተቋሰሉ ለገዢዎቻቸው የሃይል [የጥቅም] ምንጭ በመሆን ማለቂያ አልባ የሚመስል ክብ ውስጥ ገብተዋል።በኢትዮጵያችን ሰው ዘረኛ የሆነው ፍርሃቱ ወደር ስላጣ ነው፤ አድር ባይ የሆነው ነገረኛ የሆነው ጎጠኛ የሆነው ተካፍሎ የማይበላው ለሞራል ህግም ሆነ ለመለኮታዊ ትዕዛዝ ለመገዛት አሻፈረኝ ያለው ፈሪ ስለሆነ ነው። አመክንኞ የጠፋው፤ ዕውቀት በአፍጢሙ የተደፋው፣ መተናነቅ የበረታው ፍርሃት ህልውናውን ስለፈቀፈቀው ነው።እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ፍርሃት ስር የሰደደበት ሜትሪክስን የሚቆጣጠሩት ማሽኖች ጋር ነፃ አውጪዎቹ እንኳን ሳይቀሩ ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ፍርሃት አቅም አልሰጥ ብሏቸው እናያለን። ይህን ፍርሃትን የመናድ ታሪክ የሚጀምረውና አጥቂዎቹን ማሽኖች ወደ ተሳዳጅነት ቦታ የሚቀይራቸው ይህን የማሽኖቹን ስውር አላማ የተረዳው ጀግናችን ኒዮ ነው። አሁን ባለው የእኛ አገር ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ ይህን የኒዮን ሚና ተክቶ እየተጫወተ ይመስላል። (እግዜር ይርዳው)ጀግናን ፍለጋ 101በፊልሙ ነጻ አውጪዎቹ ይህንን ጀግና ለመፈለግ ብዙ ታትረዋል፡፡ አምስት የሚያህሉ ሰዎች በተለያዩ ጊዜ የተመረጠው መሪ ነው ብለው አምነው ተቀብለው ከግብ ሳያደርሷቸው ከመንገድ ቀርተውባቸዋል፡፡ ስድስተኛው ግን በእርግጥም እነርሱ ዘ ዋን የሚሉት ነበረ፡፡ በሜትሪክስ ስርዓት ስር እንዳለ ያልተገነዘበ የኮምፒዩተር ፕሮግራመር ቶማስ አንደርሰን በኮምፒዩተር ስሙ ኒዮ በስራ ላይ ሳለ ብልጭ እያለ የሚጠፋው ዘ ሜትሪክስ የሚል ስንኝ ሲያወዛግበው የኖረ ሰው ትሪኒቲ በተባለች ሴት ጥሪ ይደርሰዋል፡፡ መንገዱንም በሩ ላይ ያለችውን ነጭ ጥንቸል እንዲከተል ትዕዛዝ ይሰጠዋል፡፡የቴድሮስ ገብሬ በይነ-ዲስፕሊናዊ የተሰኘ መፅሐፍ እንዳስቀመጠው ጀግና ከጥሪው ጀምሮ እስከ ግቡ [ጸሐፊው የአሳ ነባሪ ሆድ የሚለው] ድረስ ብዙ ውጣ ውርዶች ማለፍ ግዴታው ነው። ጥሪው ልክ ዘ ሜትሪክስ ላይ ኒዮን “ነጯን ጥንቸል ተከተላት” እንደሚለው ወይም አብርሃምን “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።” እንደሚለው የመፀሀፍ ቅዱስ ቃል ሊሆን ይችላል። ጥሪው አሰገዳጅነትን ጨምሮ ብዙ አይነት መልኮች ሊኖሩትም ይችላል። ብሶት የመልኮቹ አንድ ገፅታ ነው። ኑሮ ተወደደ ፥የመናገር ነፃነት አጣን፥ የመስራት ነፃነት አጣን፥ የፖለቲካ ምዳሩ ጠበበ፣ ሌብነት ተንሰራፋ፣ የዘርና የሃይማኖት መድሎ አየለ ወዘተ… ከአስተያየትነት በሂደት ወደ ብሶትነት ተቀይሮ ሲያበቃ “ጥሪ” ይወለዳል።በኢትዮጵያችን ብሶቶች በየትውልዱ ተሰምተዋል። አንዳቸውም ግን ወደ ትክክለኛው ጀግና አልመሩትም ይልቅስ ወደ ባሳበት ሽፍታ ገፍተውታል። የጀግና የሚመስል ተክለ ሰውነት ያላቸው ጉልቤዎች ቢነሱም በጊዜ ሂደት ትክክለኛ መልካቸው ተገልጦ ህዝብን ለከፋ እንግልትና ለሌላ ባሪያ አሳዳሪ ዳርገው በታሪክ ማህደር ላይ በቅሌት መዘገብ ሰማቸውን አስፍረው አልፈዋል። ሞርፊየስ ኒዮን ሲያገኝ “ህይወቴን ሙሉ ስፈለግህ ነበር” እንዳለው ይህም ትውልድ ጀግናውን ፍለጋ ዘመኑንን ሙሉ ብሶቱን ሲያሰማ ኖሯል።ጀግናን ፍለጋ የሚደረገው ጎዞ ከሚጠይቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ተመሳሳይ ተክለ ሰውነት [መንፈሳዊም ሆነ ስጋዊ ብቃት] ያላቸውን ሌሎች ጀግኖች መስዋትነት ነው። እነዚህ የዋናውን ጀግና ትግል ለማቅናት የሚደክሙ ሰዎች ትልቁን ምስል መመልክት የሚችሉ ባለ ራዕዮች ናቸው። ከላይ ባነሳነው ፊልም ላይ ያሉት ሞርፊየስ ትሪኒቲና ኦርክል የተሰኙት ገፅ ባህሪያት አላማቸው ኒዮን [ጀግናውን] ፈልጎ ማግኘት ቢመስልም ትልቁ ግባቸው ግን የሰውን ልጅ ከባርነት ተላቆ ነፃ ይወጣ ዘንድ መርዳት ነው።በኛም አገር ሁኔታ እጅግ ከማሽኖቹ ጋር የሚመሳሉ ጉልቤዎች በየጊዜው ይነሳሉ። ተግተውም ህዝቡ ከታሰረበት የባርነት ሰንሰለት እንዳይላቀቅ ይሰራሉ [የጀግና የሚመስል ተክለ ሰውነት በታየ ቁጥር ጠልፎ ለመጣልና በአጭር ለመቅጨት ባለ ሃይላቸው ይጥራሉ፤ ይግረ።] ይህም ህዝብን ማሰሪያ ሰንሰለት ፍርሃትና አላዋቂነት ይጨምራል። የዚህ ሰንሰለት አንዱ አካል ሰው መታሰሩን እንዳያቅ የሚደርግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በፍርሃት የሚያቀጭጭ ከባድ መዋቅር ነው።የታሳሪውን ግማሽ ፍርሃት ሲበላው ከቀረው ውስጥ መታሰሩን የሚያቅ ጥቂት ነው። መታሰሩን አውቆ ነፃ ለመውጣት የሚተጋው ጥቂት ነው። ተግቶ ነፃ የወጣ ደግሞ ከጥቂቱ እጅግ ጥቂት ነው። ነፃ ከወጡት ደግሞ ለሌሎች ነፃ መውጣት የሚተጋው ኢምንት ነው። ከዛ ኢምንት ውስጥ ነው ጀግናው የሚፈለገው። ምክኒያቱም ቴዎድሮስ ገብሬ እንዳብራራው ሰው መጀገን የሚጀምረው እሱ ከቆመልት አላማ ከፍ ላለ ግብ መታገል ሲጀምር ነው።ከቆመለት አላማ ከፍ ያለውን ግብ ግማሽ ቢያሳካ ጀግና አይሆንም ታጋድሎውን በድል መፈፅም አንዴ የገባበት ግዴታው [ውዴታውም ሊሆን ይችላል] ነውና። በዚህ ምክኒያት ጀግናው ከግቡ እንዳይደርስ ማሽኖች ከውጪም ከውስጥም በብርታት መጋደላቸው አይቀርም። ኒዮን እጅግ ዋጋ የሚያስከፍል ትግል የገጠመው አብሮ የነፃነት ታጋይ መስሎ ከቆየውና በኃላ ከከዳ ሳይፈር ከተባለ ወዳጁ ዘንድ ነው። ከሳይፈር ጥቃት በተአምር አምልጦ ነው ለድል የበቃው።ሰው ሁሉ በሽታው ራስ ራሱን ነው!በእኛና በአገኘነው ጀግና መሃል ያለው የግኑኝነት መስመር የመሪና የተመሪ አይደልም፡፡ ሜትሪክስ ላይ እውነታውን ያላወቀው ህዝብ ጉዳቱ ከነፃ አውጪዎቹ አለመወገኑና ራሱን ለዘላለም ባርነት መዳረጉ ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው ነፃ አውጪዎቹን ለማጥፋት የተዘጋጀ ሃይለኛ ወጥመድ መሆኑም ጭምር ነው። በባርነት መያዙን ያላወቀው ክፍል ለማሽኖቹ በሁሉም ቦታ የመገኝት ነፃነት አስገኝቶላቸዋል። አላዋቂው ህዝብ አእምሮ ውስጥ የማሽኖቹ ሃሳብ ስላለ መላ አካሉን ነፃ አውጪዎቹን ለማጥቂያነት እንዲጠቀሙበት ያገደዳል። የማሽኖቹ ዕውቀትና የተንኮል ምጥቀት መገለጫ አንዱ ሁኔታም ይህ ነው። ኒዮ [ጀግናው] ትግል የሚገጥመው ከማሽኖቹ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅ ሃሳባቸውን ከተሸከመው ከቀረው ዓለም ጋር ጭምር ነው።በእኛም አገር ሁኔታ በዕውቀት ጎልብቶ ከፍርሃቱ የተላቀቀ ሰው ጀግናውን ከጥቃት የሚከላከለው ከማሽኖቹ ብቻ ሳይሆን ይህን የነሱን ሃሳብ እንደተሸከመ ከማያውቀው ከሰፊው ህዝብ ጋር ጭምር ነው። የጀግናችንም ሆነ የአስተዋይ ሰው ተጋድሎ ማሽኖቹ በህዝቡ ላይ የቀበሩበትን ሃሳብ ማለትም ጥያቄን በሃይል የመፍታትን ከአመክኖዮና ለምን ባይነትን የመጥላት አባዜ ጋርም ጭምር ነው።ዳኛቸው ወርቁ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ድርስት ከሳቴ ብርሃን (ጀማሪ) ነው በሚባለው አደፍርስ ውስጥ አደፍርስ የተሰኘው ዋና ገጸ ባህሪ አጎቱ ጋር ደብረሲና ችሎት ከተሰየመ በኃላ ከነገርተኞች ጋር በነበረው ውይይት የቤተሰብን አቋም ያፋለሰው ችግር ምን እንደሆነ ለመረዳት የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር ለመብዛቱ ብዙ መላምቶችን ከተሰብሳቢው ይደርሰዋል፡፡ ሆኖም የነገሩን ስር ለማጥራትና ችግሩን ለመፍታት ከልቡስ ጥላ ይጀምራል ሲያብራራም “…ልቡስ ጥላ የምለው ከአእምሮ ክፍሎች በአነስተኛው ውስጥ የሚገኝ ልዩ ልዩ ነገሮችን ማየትና… ማውጠንጠን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ የሚጠራቀም…መያዣ መጨበጫ የሌለው የሚመስል ምስቅልቅል ሁኔታ ነው፡፡ ከቤተሰባችን ይወረሳል ከልዩ ልዩ መጻሕፍት ይዘራል…” እያለ ሰለንቃተ ህሊና ዲስኩሩን ይጀምራል፡፡ ነገርተኞቹ አላስወራ ቢሉትም ከምናየው ከኃይማኖቱ ከዘልማድ ከተረት ለየዕለት ተግባራችን ከክፉም ከደጉም ከሚያስደስተንም ከማያስደስተንም እና ከተለያዩ ነገሮች ወደ አይምሯችን እየገባ የሚጠራቀም የማይጨበጥ ግን የሚገዛን ነገር ግን የማናውቀው መሆኑን “…ብዙን ጊዜ እንዴት እንደተጠራቀመ ለማወቅ ያዳግተናል::” በማለት ያትታል፡፡ ማሽኖቹም ሃሳባቸውን ህዝብ አይምሮ ላይ አደፍርስ ባለው መልኩ ነው የሚከማቹት። ባስፈለጋቸው ሰዓት በአንድ ቁልፍ መክፈት ነው።አሁን ባለው የኛ አገር ሁኔታ ይህ ትውልድ የጀግና ተክለ ሰውነት ያለው መሪ እያየ ይመስላል። መሪው ይጀግን ዘንድ ፍርሃቱን አሸንፎ ማሽኖቹን ባሪያ ፈንጋዮቹን ታግሎ ነፃና ሰላማዊ አገር ለማስረክብ በፍጥነት ወደ ግቡ መገስገስ አለበት። የተቀረው ነፃ አውጪ ጀግናውን በዕውቀትም በጉልበትም ማገዝ ይኖርበታል። ይህ የሚጀምረው ግን ከእያንዳንዱ ልቡስ ጥላ ስር ነው፡፡ መቼ እንደተጠራቀመ ያልተረዳው የፍርሃትና የዘረኝነት አባዜ መንግሎ በጣለ ጊዜ ነው፡፡ በመጣ መሪ አንደሚነዳ ሳይሆን እንደ አንድ ሀገር ልጅ በአንድነት ለመኖር ያለነጋሪ ጥቅሙን አውቆና ተረድቶ ለመጎዝ የወሰነ ጊዜ ነው፡፡በአንድነት ጀግናን ከግቡ ይደርስ ዘንድ በነጻ አዕይምሮ ማገዝ የሁሉም ድርሻ መሆን አለበት። ሪሎድድ በተባለው የማትሪክስ ሁለተኛ ክፍል ላይ ኦርክል የተባሉት በዕውቀት ያረጁ ሴትዮ “ለአንድ ነገር በጣም ጉጉ ነኝ ኒዮ ፤ወደ ፊት ለሚመጣም ዘመን። እናም እመነኝ! አውቃለው ወደዚያ የሚወስደን ብቻኛው መንገድ አብሮነት ነው።” እንዳሉት እኛም ከፊታችን ወዳለው ግብ የሚወስደን መንገድ አብሮነታችን [አንድነታችን] ነው። ምክንያቱም አንድም ጀግናችን የሚሰነዘርበትን ዱላ ብቻውን ተከላክሎና አምልጦ አይዘልቀውም ሁለትም ጀግናችንን አለማገዘችን ጀግናችን ላይ ለሚሰነዝርበት እያንዳንዱ ጥቃት አዎንታዊ ፍቃድ እንደ ሰጠን የሚያሳይ ምልክት ነውና። በዚህ ሰዓት ጀግናን ለመርዳት ጠጠር ማቀበል ባህር ከፍሎ ከማሻገር ያልተናነሰ ተዓምር መስራት ነው። የጀግናችን ግቡ እና ትልቁ ሽልማቱ የኢትዮጵያችን ትንሳኤ እስከሆነ ድረስ !!!

አስተያየት