የካቲት 30 ፣ 2015

የሚዘራውም በመንግስት ተመርጦ፣ ዋጋውም በመንግስት ተተምኖ እንዴት ይሆናል?

City: Bahir Darወቅታዊ ጉዳዮችንግድምጣኔ ሀብት

“ለውሃ መሳቢያ ማሽን ቤንዚን አጥቼ በጥቁር ገበያ እየገዛሁ ያመረትኩትን ስንዴ በፈለኩት ዋጋ ለፈለኩት አካል መሸጥ እፈልጋለሁ”- አርሶ አደር

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

የሚዘራውም በመንግስት ተመርጦ፣ ዋጋውም በመንግስት ተተምኖ እንዴት ይሆናል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በኦሮሚያ ክልል ባሌ የተጀመረው ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ተግባር ይፋ የተደረገው ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ዜና ከተከተሉት አበይት ጉዳዮች መካከል የዱቄት ፋብሪካዎች በግብዓት እጥረት መቸገራቸውና ስራ እስከማቆም መድረሳቸው እንዲሁም የቦረና ድርቅ ዋነኞቹ ነበሩ። 

ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለዓለም አቀፍ ገበያ የመሸጥ ሀገራዊ ዕቅድ መባሉም በሀገር ውስጥ ከተፈጠሩት አንገብጋቢ ጉዳዮች አንፃር 'እንዴት ለራሳችን ዜጎች ሳንሆን ለውጭ ገበያ ይታሰባል?' በሚል ሙግት እየገጠመው ይገኛል።

በአማራ ክልል አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው አርሶ አደሮች የሚዘሩት የእህል አይነት እና የዋጋ ተመን በመንግስት አካላት መወሰኑ እንደጎዳቸው ይገልፃሉ። አትንኩት አውለው በአማራ ክልል ወረታ አካባቢ የሚኖር አርሶ አደር ነው። ከዚህ ቀደም በራሱ ተነሳሽነት ሽንኩርት እያመረተ ለገበያ ያቀርብ እንደነበረ የሚገልፀው አርሶ አደሩ፣ ዘንድሮ የግብርና ባለሙያዎች ከስንዴ ውጪ ሌላ ነገር ማምረት አይቻልም በማለታቸው ስንዴ ብቻ ለማምረት ተገዷል። 

አርሶ አደር አትንኩት አውለው ስንዴ ለማልማት የውሃ መሳቢያ ማሽን (ፓምፕ) ተጠቅሞ ያመረተ ቢሆንም ለውሃ መሳቢያ ማሽኑ ቤንዚን እንደልብ ባለመገኘቱ በብዙ ተፈትኛለሁ ብሏል። ይሁን እንጂ “ምርቱ ሲደርስ መንግስት የራሱን ዋጋ አውጥቶ ለህብረት ስራ ማህበራት ብቻ ነው የምትሸጡት ማለቱ አሳዝኖኛል” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በ2015 ዓ.ም 250 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ እስካሁን 213 ሺህ 232 ሄክታር መሬት ማሳካት መቻሉ ተገልጿል። በምርት ደግሞ በሄክታር 40 ኩንታል ለማድረስ የታቀደ ሲሆን በአጠቃላይ 10 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ እንደሚገኝ ይጠበቃል። በክልሉ በርካታ ሄክታር መሬት በስንዴ እንዲሸፍን ማስቻል በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ውጭ ሀገር የስንዴ ምርት መላክ ዕቅድ አካል መሆኑ ይነገራል።

አሁን ከስንዴ ምርት እና ግብይት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ጭንቀት የአንድ አርሶ አደር ብቻ አይደለም፣ ስንዴ በስፋት እየተመረተ በሚገኝበት አማራ ክልል የግብይቱ ጉዳይ በአርሶ አደሮች፣ በዱቄት ፋብሪካ ባለቤቶች እና በመንግስት መካከል ውዝግብ ፈጥሯል።

የክልሉ መንግስት የግብርና ቢሮ በበጋ መስኖ የተመረተ ስንዴን ነጋዴዎች እና የዱቄት ፋብሪካዎች መግዛት እንዳይችሉ በይፋ መወሰኑ ስጋቱ እንዲጨምር አድርጓል። የግብርና ቢሮው እንዳስታወቀው በፌዴራል ደረጃ በተወሰነው መሰረት ስንዴ መግዛት የሚችሉት የህብረት ስራ ማህበራት እንዲሆኑ ከመገደቡ ባለፈ የአንድ ኩንታል ስንዴ መሸጫ ዋጋ 3 ሺህ 200 ብር ሆኖ አርሶ አደሮችም በዚሁ ዋጋ እንዲሸጡ ተወስኗል።

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ስንዴ ያመረቱ አርሶ አደሮች እስከ 4 ሺህ ብር ድረስ በኩንታል እየሸጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ከባህር ዳር ዙሪያ አንዳሳ ቀበሌ የመጣው አርሶ አደር ቢምረው ታሪኩ እንደ አርሶ አደር አትንኩት አውለው ቅሬታ አለው። “ለውሃ መሳቢያ ማሽን ቤንዚን አጥቼ በጥቁር ገበያ እየገዛሁ ያመረትኩትን ስንዴ በፈለኩት ዋጋ ለፈለኩት አካል መሸጥ እፈልጋለሁ” የሚለው አርሶ አደሩ ቢምረው፣ በተሻለ ዋጋ መሸጥ እየቻለ ለህብረት ስራ ማህበራት በዝቅተኛ ዋጋ የሚሽጥበት ምክንያት እንደማይወጥለት በግርምት ያስረዳል።

በሌላ በኩል በባህር ዳር ከተማ የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት የሆኑት አቶ አለህኝ አስረስ ከበጋ መስኖ ስንዴ ግብይት ጋር በተያያዘ የመንግስትን ውሳኔ አጥብቀው ይተቻሉ። “በነፃ ገበያ የምትመራ ሀገር እንደመሆኗ መንግስት ጣልቃ ሊገባ አይገባም” የሚሉት የዱቄት ፋብሪካ ባለቤቱ “ስንዴ መግዛት ካልቻልን የፋብሪካችን ህልውና አደጋ ውስጥ ይገባል” ይላሉ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ የዱቄት ፋብሪካ ባለቤትም ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት መንግስት የዱቄት ፋብሪካ ባለቤቶች እና ነጋዴዎች ስንዴ እንዳይገዙ መከልከሉ እህሉ በኮንትሮባንድ እንዲሸጥ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ህብረተሰቡ በፈለገው መጠንና ጊዜ ዳቦ እና የዳቦ ዱቄት ማግኘት ያልቻለበት ሁኔታ በመኖሩ ስንዴ በብዛት ቢመረትም መንግስት ወደ ውጭ የመላክ ፍላጎቱን እንደገና ሊያጤነው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የዱቄት ፋብሪካ ባለቤቱ እንደሚያስረዱት “የዱቄት ፋብሪካ ባለቤቶች ስንዴ ከውጭ የማምጣት አቅም የሌላቸው ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ቢያስገቡ እንኳን ስንዴ ከውጭ አስመጥቶ የህብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ ዋጋ ለመሸጥ ይቸገራሉ”። 

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ እና የምጣኔ ሐብት መምህርና ተመራማሪ ይስማው አየልኝ (ዶ/ር) "የዓለም ከፍተኛ ስንዴ አምራች የሆኑ ሀገራት የቅድሚያ ትኩረታቸው የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ሳይሆን የሀገር ውስጥ የምግብ እና የኢንዱስትሪዎቻቸውን ፍጆታ ማረጋገጥ ነው" ይላሉ።

ይስማው (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ትልቁ ግብ እና አጀንዳ ሊሆን የሚገባው የሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታን ማረጋገጥ እንዲሁም የፋብሪካዎችን የጥሬ ግብዓት አቅርቦት ጥያቄ በሚፈታ መንገድ ተደራሽ ማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ። 

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የዱቄት ፋብሪካ ማኅበራት እና ባለቤቶች ገና ከጅምሩ ስንዴ በኮትሮባንድ ገበያ ላይ መውደቁ ለፋብሪካዎቻቸው ስጋት መሆኑን ጠቁመው፣ አብዛኛዎቹ “ፋብሪካዎች ከተዘጉ ለምንድን ነው ወደ ውጭ መላክ ያስፈለገው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ለምርት እጥረትም ሆነ ለዋጋ ግሽበት መፈጠር የመንግስት በግብይት ሥርዓት ውስጥ እጁን ማስገባት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ እምነት አላቸው። 

የምጣኔ ሀብት ተመራማሪና መምህሩ ይስማው አየልኝ (ዶ/ር) በዚህ ይስማሙና ሃሳቡን ሲያጠናክሩት “የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በምርት ሂደት ላይ የረዘመ እጅ ሲኖረው ብቻ ነው” ይላሉ። 

የኢትዮጵያ መንግስት ስንዴ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን ይፋ ሲያደርግ የሀገሪቱን ሕዝብ የስንዴ ፍጆታ በማይጎዳ መንገድ ግመታዊ ጥናት ሰርቻለሁ ማለቱ ይታወሳል። በግምታዊ የፍጆታ ጥናቱ መሰረት 32 ሚሊዮን ኩንታል የሀገሪቱ ዓመታዊ ፍጆታ መሆኑ ተገልፆ ነበር።

ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ከ2.9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ለዓለም አቀፍ ገበያ መሸጥ የሚያስችል ውል ለመፈራረም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር በቅርቡ አስታውቋል። ሱዳን እና ኬንያን ጨምሮ ስድስት ሀገራት ከኢትዮጵያ ስንዴ ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ወደ ሀገሪቱ የሚገባዉን የስንዴ መጠን በሂደት በመቀነስ ለግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለሌላ ልማት ለማዋል በመኸር ወቅት ከሚመረተዉ ስንዴ በተጨማሪ፣ የመስኖ ውኃን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ስንዴ እየተመረተ ይገኛል። በዚህ ሂደትም በአራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ ጥገኝነት ነፃ ሆና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ትሆናለች ተብሎ ትንበያው ተቀምጧል። 

ዘንድሮ በአማራ ክልል ብቻ ከ213 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ የተሸፈነ ሲሆን በድምሩ ከ720 ሺህ በላይ ሰዎች በምርት ሂደቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከ440 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ፣ 298 ሺህ 151 ኩንታል ምርጥ ዘር እንዲሁም ከ28 ሺህ 122 በላይ የውኃ መሳቢያ ማሽኖች በስራ ላይ ውለዋል።

አስተያየት