ዲጂታል ገንዘብ ተጨባጭ ያልሆነ የመገበያያ ዓይነት ነው። የተለመደውን የወረቀት እና የሳንቲም ገንዘብ ለመተካት እየተንደረደረ ያለ ይመስላል። ከመደበኛው ገንዘብ ጋር ተመሳሳይ ባህርይ ቢኖረውም ፈጣን እና ድንበር የለሽ ዝውውሩ ከነባሩ ገንዘብ ይለየዋል። ምናባዊ ገንዘቦች (virtual currencies) እና ክሪፕቶከረንሲዎች የዲጂታል ገንዘብ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው። እንደ አካላዊ ገንዘቦች ሁሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን ለመሸመት ጥቅም ላይ ይውላሉ። ለተወሰኑ አገልግሎቶች ማለትም ለኢንተርኔት ጨዋታዎች (online game) ወይም ማኅበራዊ አውታረ መረብ (social network) ብቻ እንዲያገለግሉ የተገደቡ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚም ሰፊ ነው።
ዲጂታል ገንዘቦች የተማከሉ እና ያልተማከሉ በሚል በሁለት ይከፈላሉ። የተማከተሉት በሀገራት ማዕከላዊ (ብሔራዊ) ባንኮች በኩል ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። በሞባይል ባንኪንግ፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ፣ በኤቲኤም ማሽኖች የሚንቀሳቀሱ ገንዘቦች የተማከለ ዲጂታል ገንዘብ ምሳሌዎች ናቸው። በተቃራኒው የገንዘብ አቅርቦቱ ቁጥጥር እና መገኛ ከተለያዩ ምንጮች ከሆነ ደግሞ ያልተማከለ ዲጂታል ገንዘብ ወይም ክሪፕቶከረንሲ ይባላሉ። ምናባዊ ገንዘቦች (Virtual currency) እና ክሪፕቶከረንሲ የዚህ ምሳሌዎች ናቸው።
ክሪፕቶከረንሲ ምንድን ነው?
ክሪፕቶከረንሲ ማለት የክሪፕቶግራፊ ዕውቀትን ተመርኩዞ የሚሰራ የዲጂታል ገንዘብ ነው። ክሪፕቶግራፊ በዲጂታል መልዕክት መላላክያ ዘዴ ውስጥ መረጃዎች ከሚመለከተው አካል ውጪ ለሦስተኛ ወገን እንዳይመዘበር የሚከላከል አሰራር ነው። ሌላው (Double Spending) የተባለውን አሰራር በማስተካከል ማንኛውንም በዲጂታል ዋጋ ያለው ነገር ቅጂ ሳያስቀሩ መላክ የሚቻልበትን መንገድም አስተዋውቋል።
ክሪፕቶከረንሲ የዲጂታል ገንዘብ ዓይነት ሆኖ የእያንዳንዱ የገንዘብ ዝውውር ምዝገባ እና ማረጋገጫ በተለያዩ አካላት በክሪፕቶግራፊ አማካኝነት የሚሰጥበት የገንዘብ ዓይነት ነው። በዓለም ዙሪያ ቢትኮይን፣ ኢተረም፣ ላይትኮይን፣ ካርዳኖ በጣም ታዋቂ ናቸው። ክሪፕቶከረንሲ ገንዘብ ከአንድ ዲጂታል ዋሌት (አካውንት) ወደ ሌላ ለመላክ እጅግ ቀላል መሆኑና በማንኛውም ስማርት የሞባይል ቀፎ አልያም ኮምፒወተር መገልገል መቻሉ ተመራጭ ያደርገዋል።
በእነኚህ ያልተማከሉ ገንዘቦች ዝውውር በሙሉ ብሎክቼይን በተባሉ ለማንኛውም ሰው ክፍት በሆነ መዝገብ ላይ መመዝገባቸው ያልተገባ የሆነ የገንዘብ አጠቃቀም እንዳይኖር ለማድረግ መርዳቱ የገንዘቦቹ አንድ ተመራጭ ጎን ነው።
ብሎክቼይን መረጃዎች እንዳይጠፉ እንዳይሰረቁ እና እንዳይቀየሩ የሚያደርግ የተበታተነ ዳታቤዝ የሚጠቀም የመረጃ መመዝገቢያ ስርዓት ነው።
ለሳይበር ውንብድና ተጋላጭነቱ፣ የምንዛሬ ዋጋው ፈጣን ተለዋዋጭነት፣ ሁነኛ ተቆጣጣሪ አካል አለመኖሩ የክሪፕቶከረንሲ ድክመቶች ናቸው።
ሳቶሺ ናካሞቶ እና ቢትኮይን
ቢትኮይን የመጀመሪያው ያልተማከለ ዲጂታል ገንዘብ ነው። ገንዘቡ በ2008 እ.ኤ.አ ከተዋወቀ በኋላ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል። የstatista.com መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም 6000 ያክል ያልተማከሉ ዲጂታል ገንዘቦች ይገኛሉ።
የመጀመሪያው ያልተማከለ ዲጂታል ገንዘብ ቢትኮይን ከተዋወቀ ወዲህ አሰራራቸው ከፈጠረው የደህንነት ስጋት በተጨማሪ ትክክለኛ ፈጣሪ እና ተቆጣጣሪው በውል አለመታወቁ መንግሥታትን፣ ድርጅቶችን እና ግለሰቦችን እንዳሰጋ ቀጥሏል። በቢትኮይን ፈጣሪነቱ ሲገለጥ የከረመው ሳቶሺ ናካሞቶ ማንነቱ በውል ሳይታወቅ እስከዛሬም እንቆቅልሹ አልተፈታም። በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች ሳቶሺ ናካሞቶ እንደሆኑ ቢናገሩም ግን በብዙዎች ዘንድ አመኔታን ሊያገኙ አልቻሉም።
ሰሞነኛው የፍርድ ቤት ጉዳይ
በ2015 ጊዝሞዶ የተሰኘ የሳይንስ ዌብሳይት በ2013 በቤቱ ህይወቱ አልፎ የተገኘውን የኮምፒወተር ፎረንሲክ ባለሞያ ዴቪድ ክሌማን በቢትኮይን ፈጠራ ሳይሳተፍ እንዳልቀረ ጥርጣሬውን ገልጿል። ዴቪድ ክሌማን የተለያዩ ወታደራዊ አገልግሎቶች ላይ የተሳተፈ፣ በኮምፒውተር ደህንነት ባለሞያ እንዲሁም የተለያዩ መጻሕፍት ደራሲ እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያሳያል።
የዴቪድ ክሌማን ወንድም እና ሕጋዊ ወራሽ በፌብሯሪ 2018 በፍሎሪዳ ፍርድ ቤት በክሬግ ራይት ላይ በጥቅም ይገባኛል እና አዕምሯዊ ንብረት መብት ክስ መስርቷል። የዴቪድ ክሌማን ቤተሰቦች ጠበቃ ከክሬግ ራይት ጋር ከ1 ሚልየን ቢትኮይን በላይ በጋራ ማበልጸጋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ በእጃቸው እንዳለ ቢናገሩም ነዋሪነቱ ለንደን የሆነው አውስትራሊያዊ ክሬግ ራይት ጠበቃ ደንበኛቸው ቢትኮይንን ብቻውን እንዳበለጸገው እና ለፍርድ ቤቱም ይህንን የሚያስረዳ ማስረጃ አለመቅረቡን ተናግረዋል።
እንደከሳሾቹ አባባል የአውራሻቸው ድርሻ 1 ሚልየን ቢትኮይን አልያም በአሁኑ ምንዛሬው ከ64 እስከ 70 ቢልየን ዶላር እንደሆነ ገልጸዋል። በብሎክቼይን አሰራር አንድ ሰው ሁለት ቁልፎች ይኖሩታል ፥ የግል ቁልፍ (Private key) እና የህዝብ ቁልፍ (Public Key)። የግል ቁልፍ ለማንም የማይሰጥ እና የባለቤቱ ማንነት የሚለይበት ቁልፍ ነው። በዚህ አሰራር መሠረት ብዙዎች ዘንድ የጉዳዩ እልባት ያለው በሳቶሺ ናካሞቶ ስም ያለው አካውንት የግል ቁልፍ (Private Key) የያዘ አካል ብቻ እንደሆነ ይስማማሉ።
ፕራይቬት ኪይ በክሪፕቶግራፊ ውስጥ ግለሰቦች የራሳቸውን አካውንት ለመገልገል የሚጠቀሙበት ውስብስብ የይለፍ ቃል ነው። እንግዲህ ይህንን ጥያቄ ለመፍታት መፍትሔው የሳቶሺ ናካሞቶን ፕራይቬት ኪይ የያዘው አካል ነው ትክክለኛ ባለመብት ሲሉ ይደመጣሉ።