ኅዳር 9 ፣ 2014

የታዳጊዎች ራስን የማጥፋት ድግግሞሽ በአዳማ

City: Adamaጤናማህበራዊ ጉዳዮች

ራስን የማጥፋት መንስኤ መሆናቸው ከሚጠቀስ ገፊ ምክንያቶች መካከል ሱስ ግምባር ቀደሙ ነው።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የታዳጊዎች ራስን የማጥፋት ድግግሞሽ በአዳማ
Camera Icon

Photo: The Conversation

በአንድ የማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ በጸሐፊነት የምታገለግለው የሃያ ዓመቷ ቤተልሔም ኃይሉ ጓደኛዋ በአይጥ መርዝ ራሷን ስለማጥፋቷ ትናገራለች። “ራሷን ያጠፋችው ምህረት እድሜዋ ከአስራ ስድስት አይበልጥም። ራሷን ለማጥፋት የገፋፋት ሰበብ ከቤተሰብ ጋር የተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን ሰምቻለሁ” ትላለች። በወቅቱ በጓደኛዋ ሞት ምክንያት ከገባችበት ድብርት በብዙዎች ርብርብ ስለመውጣቷም አጫውታናለች።

ከሦስት ሳምንታት በፊት በተመሳሳይ መልኩ ሕይወቷን ያጣችው ታዳጊ በጸሎት ካሳዬ ትባላለች። በምትማርበት ትምህርት ቤት እና በመኖርያ አካባቢዋ በትወና ችሎታዋ ትታወቃለች። የባማ ኢንተርቴይመንት ኃላፊ መምህር ግዛቸው ጌታቸው አጋጣሚው አስደንጋጭ እና አሳዛኝ እንደነበር ይናገራል።

በተለምዶ 15 ቀበሌ እየተባለ የሚጠራ አካባቢ ኗሪው ደመላሽ አመነሸዋ ባለትዳር እና የልጆች አባት ነው። "አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አምስት ታዳጊዎች እና አንድ የቤተሰብ ኃላፊ ራሳቸውን ሊያጠፉ ሞክረዋል። ከእነኚህ መሀከል አንዲት ታዳጊ እና አንዲት የልጅ እናት ማለፋቸውን ሰምቻለሁ። ከዚህ በፊት በብዙ ጊዜያት ልዩነት አልፎ አልፎ የሚደመጠው ራስን የማጥፋት ዜና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተደጋገመ ነው። በሳምንት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ራሳቸውን እንዳጠፉ ይሰማል። የሚበዙት ደግሞ ታዳጊዊች ናቸው” ብሎናል።

የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ዕንደሚያሳየው በዓለም ዙርያ በየ40 ሰከንዱ አንድ ሰው ራሱን ያጠፋል። ከ15 እስከ 20 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ወጣቶች ሕይወታቸውን ከሚያጡባቸው ሰበቦች ሁለተኛውን ትልቅ ቁጥር እንደሚይዝም ይገልጻል። "Prevalence of suicidal ideation, suicidal attempt and completed suicide in Ethiopia: a systematic review and meta-analysis protocol" በሚል ርዕስ በአራት ኢትዮጵያዊያን በተሰራ ጥናት ደግሞ ራስን ስለማጥፋት ማውጠንጠን፣ ማቀድ፣ መሞከር እና መፈጸምን በተለያዩ ደረጃዎች ከፋፍሎ ይመለከታቸዋል። እንደ ጥናቱ ግኝት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ 100 ሺህ ሰዎች መካከል በዓመት 13.9 በመቶ ያህሉ ራሳቸውን ያጠፋሉ።

የኮሌጅ ሰፈር ነዋሪ የሆነው ፍራኦል መንግሥቱ 21 ዓመቱ ነው። ባሳለፍነው ወር ብቻ ራሳቸውን ስላጠፉ ሦስት ሰዎች መስማቱን ነግሮናል። ራሷን ስላጠፋችው ስለአብሮ አደጉ ሌሊሴ ሲናገር “የካምፖስ ተማሪ ነበረች። ከነርሰሪ እስከ 12ኛ አብረን ተምረናል ። ራሷን የገደለችው በገመድ ነው። ሌሎች ሁለት ወንዶችም እዚሁ ሰፈር ውስጥ በመርዝ ራሳቸውን ገድለል። ምን እየሆነ እንዳለ ግራ ያጋባል” ሲል ለአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ተናግሯል።  

የ‘ዴይ ስታር’ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የሆነችው መምህርት ትንግርት “በትምህርት ቤታችን እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም። በምኖርበት ‘ገንደ ሀራ’ ግን በቅርቡ አጋጥሞኛል” ትላለች። “ራሷን በገመድ ያጠፋችው ታዳጊ 16 ዓመቷ ነው። ቁምሳጥን ውስጥ ተንጠልጥላ ነው የተገኘችው። ሳር ተራ አካባቢም እንዲሁ አንዲት ታዳጊ እና ኮሌጅ አካባቢ ሌላ ታዳጊ መሞቱን ሰምቻለሁ” የምትለው መምህርቷ የነገሩን መደጋገም በመታዘብ ተማሪዎቿን ለመምከር እንደተሰናዳች አጫውታናለች።

በሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ውስጥ እንደልብ በሚገኙት የተባይ ማጥፊያ እና የአይጥ መግደያ መርዞች ራሳቸውን የሚያጠፉ ወጣቶች ቁጥር በየጊዜው ስለማሻቀቡ የሆስፒታሎች መረጃ ያመለክታል። የጉዳዩ ተደጋጋሚነት፣ የሟቾቹ እድሜ የአስራዎቹ አጋማሽ ላይ መሆን፣ ራሳቸው ላይ ጉዳት ሚያደርሱባቸው ገዳይ መርዞች በቀላሉ መገኘት፣ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል።

በአዳማ ከተማ በበጎ አድራጎት ስራዎች የምትታወቀው ቆንጂት ሁሴን ከቤተሰብ ጋር የሚፈጠር አለመግባባት፣ በትምህርት ዝቅተኛ ውጤት ማምጣት፣ ሱስ፣ የፍቅር ግንኙነት መፋረስ ተደጋግመው የሚጠቀሱ ወጣቶች ራሳቸውን የሚያጠፉባቸው ሰበቦች መሆናቸውን ነግራናለች። ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የ5 ታዳጊዎችን ሞት መስማቷን ትናገራለች።

በአዳማ የተለያዩ ሆስፒታሎች ያገለገሉት የስነ-ልቡና እና የአዕምሮ ጤና ባለሙያው ዳዊት ሙሉጌታ “95 በመቶ የሚሆነው ራስን የማጥፋት መንስኤ የአዕምሮ ጤና ችግር ነው። 80 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ‘ሜጀር ዲፕረሲቭ ዲስኦርደር’ ነው” ይላሉ። ማንኛውም ሰው ራስን ስለማጥፋት ካወራበት ቅጽበት ጀምሮ ህክምናው እንደሚያስፈልገውም ይናገራሉ። የሱስ ተጋላጭነት እና ብቸኝነትም ችግሩን ከሚያባብሱት መካከል ናቸው።

“‘ሜጀር ዲፕረሲቭ ዲስኦርደር’ ያለበት ሰው በፍጥነት ተስፋ የመቁረጥ፣ የመኖር ፍላጎትን የማጣት ስሜቶች ይፈራረቁበታል። ሁኔታው በአፋጣኝ እልባት ካላገኘ አደጋው የከፋ ይሆናል፤ ስለዚህ የአዕምሮ ጤና ባለሞያ ጋር ቀርቦ ህክምና ማግኘት አለበት” እንደ ዶ/ር ዳዊት ሙሉጌታ ገለጻ ራስን ስለማጥፋት ማሰብ ወይም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮችን ማውራት እንደ በሽታ ምልክት የሚታይ ነው። ሊታከም እና ሊድንም የሚችል ነው።

“ከወንዶች በላቀ ቁጥር ሴቶች ራስን የማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ። የመትረፍ እድላቸውም ከፍተኛ ነው። የሚሞክሩት ወንዶች ቁጥር ቢያንስም የመትረፍ እድላቸው ግን አናሳ ነው” ብለዋል። በተጨማሪም የወጣቶች የባህርይ ለውጥ ከጉርምስና ጋር መያያዙ አደጋው እንዳይቀንስ ስለማድረጉ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነግረውናል።   

“ራስን ለማጥፋት መሞከር ወይም ማሰብ የበሽታ ምልክት ነው። ሞካሪው ግለሰብ ለመጋፈጥ የፈራው የህይወት አጋጣሚ ወይም የተወሳሰበበት የህይወት ክፍል ይኖራል። ያም ካልሆነ ነገ ላይ የሚያየው ተስፋ ጨልሞበታል ማለት ነው። ምክንያቱ እንደየሰዉ ቢለያይም ነገሩ የበሽታ ምልክት መሆኑ ግን አያጠያቅም” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በጉዳዩ ላይ የተሰራ ጥናት የለም” የሚሉት የአዳማ ከተማ የጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ ሲስተር ሰሚራ መሀመድ “ከመስከረም 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ራስን በማጥፋት 12 ሞት ተዝግቧል። ቁጥሩ ግን ከዚህም ሊበዛ ይችላል” ብለዋል።  

ራስን የማጥፋት መንስኤ መሆናቸው ከሚጠቀስ ገፊ ምክንያቶች መካከል ሱስ ግምባር ቀደሙ ነው። በየዓመቱ 2% ወጣቶች ለሱስ አስያዥ ነገሮች ተጋላጭ የሚሆኑባት አዳማ ይህንን ችግር ለመቀነስ እየተወሰደ ያለ እርምጃ ስለመኖሩ የጠየቅናቸው የአዳማ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊዋ ሲስተር ሰሚራ በቀላሉ የሚገኙትን የአይጥ እና የሌሎች ተባዮች ማጥፊያ መርዞች ሽያጭ ላይ የቢሯቸው ቁጥጥር እጅግ አናሳ መሆኑን ጠቅሰው የቁጥጥር አሰራር ቢዘረጋ ጥቂት ሰዎችን መታደግ ይቻል እንደነበር ነግረውናል። ጤና ጽ/ቤቱ የቁጥጥር ሥልጣን የሌለው መሆኑ የአሰራሩ ክፍተት መሆኑንም አንስተዋል።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ኃላፊ ኢንስፔክተር እቴነሽ በበኩላቸው “ወንጀል ነክ የሆኑ ጉዳዮች ካልሆኑ ወደኛ የመምጣት እድሉ ጠባብ ነው። በቅርብ ጊዜ በገመድ ህይወቱን ያጣ ታዳጊ ድርጊቱ በሌላ ሰው እንደተፈጸመበት በመጠርጠሩ ምርመራ ላይ ቢቆይም በራሱ ሲጫወት እንደሞተ በመረጋገጡ ጉዳዩ ተዘግቷል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታዳጊዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ የሚለው መረጃ ግን የተጋነነ ይመስለኛል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 536 መርዛማ እና አደገኛ የሆኑ ነገሮችን አለአግባብ ማቅረብ እንደሚያስቀጣ ደንግጓል። መርዛማ ቁሶቹን የሰራ፣ የሰጠ እና የሸጠ ከ3 እስከ 7 ዓመት እስር እና እስከ 100 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ አስቀምጧል።

አስተያየት