ነሐሴ 28 ፣ 2013

ኢትዮጵያና ፓራሊምፒክስ

City: Addis Ababaስፖርት

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክስ ጨዋታዎች መሳተፍ የጀመረችዉ እ.ኤ.አ በ1968 በእስራኤል ቴላቪቭ በተካሄደው ውድድር ላይ ሲሆን ሁለት አትሌቶች በአትሌቲክስ እና በጠረጴዛ ቴኒስ የውድድር ዘርፍ ኢትዮጵያን ወክለዉ ተሳትፈዋል።

Avatar: Kirubel Tesfaye
ኪሩቤል ተስፋዬ

Kirubel works as a fact-checker at Addis Zeybe for HaqCheck. He is interested in learning and expanding his writing and journalistic skills.

ኢትዮጵያና ፓራሊምፒክስ

ኦሎምፒክ መላውን የአለም አቀፍ ማህበረሰብ በአንድ ላይ የሚያገናኝና በርካታ የስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱበት መድረክ ከመሆኑም ባለፈ እያንዳንዱ ሃገር ያለውን ባህል እና ትዉፊት ለሌሎች የማስተዋወቂያ መድረክ ተደርጎም ይወሰዳል።

እ.ኤ.አ በ1960 በጣልያን ሮም በተዘጋጀው ውድድር ላይ የስቶክ ማንደቪል ጨዋታዎች ወደ ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ስያሜያቸው ተቀየረ። በጊዜውም ከተለያዩ 23 ሃገራት የተውጣጡ 400 አትሌቶች ተሳትፈዋል።

ፓራሊምፒክስ ጨዋታ በየአራት አመት ልዩነት ከኦሎምፒክ ጨዋታዎች ጎን ለጎን የሚካሄድ ውድድር ሲሆን ውድድሩ ለአካል ጉዳተኛ አትሌቶች የሚዘጋጅ የውድድር አይነት ነው።

ዘንድሮም የቶኪዮ ኦሎምፒክን መጠናቀቅ ተከትሎ በቶኪዮ 2020 የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ከነሀሴ 18፣ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በጃፓን ቶኪዮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ስፖርት እንደሌሎች የአትሌቲክስ ዘርፎች በደንብ የተሰራበት አይመስልም። በመደበኛዉ የኦሎምፒክ ዉድድሮች ላይ በመካከለኛና በረዥም ርቀትና በማራቶን ሩጫ ዉድድሮች የተለያዩ አኩሪ ድሎችን ያስመዘገበችዉ ኢትዮጲያ በፓራሊምፒክስ ጨዋታዎች ግን በተሳትፎም ሆነ  በዉጤት እዚህ ግባ የሚባል ታሪክ የላትም፡፡

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክስ ጨዋታዎች መሳተፍ የጀመረችዉ እ.ኤ.አ በ1968 በእስራኤል ቴላቪቭ በተካሄደው ውድድር ላይ ሲሆን ሁለት አትሌቶች በአትሌቲክስ እና በጠረጴዛ ቴኒስ የውድድር ዘርፍ ኢትዮጵያን ወክለዉ ተሳትፈዋል።

የአበበ ቢቂላ የፓራሊምፒክስ ተሳትፎ

ታዋቂው የኢትዮጵያ የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያ ባለቤት እና በጣልያን ሮም በተዘጋጀው ውድድር ላይ በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት የሆነው ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ እ.ኤ.አ መጋቢት 22፣ 1969 ባጋጠመው የመኪና አደጋ ምክኒያት ውድድር ለማቆም ተገደደ፡፡

ይህን ተከትሎም አበበ ለጊዜዉ ትኩረቱን ወደ ፓራሊምፒክስ በማዞር በዉድድሩ መሳተፍ የሚያስችለዉን ልምምድ ማድረግ ጀመረ፡፡

አበበ ቢቂላ በለንደን ከተማ ልምምድ ሲያረግ

እ.ኤ.አ ሐምሌ 20፣ 1970 ለ19ኛው የስቶክ ማንደቪል ውድድሮች በእንግሊዟ ከተማ በኪንግሃምሼር በተንቀሳቃሽ ዊልቼሩ ላይ በመሆን የቀስት ልምምድን አድርጎ ነበር።

አበበ ቢቂላ በደረሰበት የመኪና አደጋ መራመድ ባይችልም ከወገብ በላይ ያለው ሰውነቱ መንቀሳቀስ ስለጀመረለት እ.ኤ.አ በ1970 በእንግሊዝ ለንደን በተዘጋጀው የስቶክ ማንደቪል ውድድሮች ላይ የቀስት ውርወራና የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል። አበበ በዉድድሮቹ ሜዳሊያ ማግኘት ባይችልም በዉድድሩ በመሳተፉ ብቻ በርካቶች ለስፖርቱ ያለዉን ፍቅር አድንቀዉለታል፡፡

አመርቂ ድል ያልተመዘገበባቸዉ ዉድድሮች

ኢትዮጵያ ከዚያ በኋላ ለአስርት አመታት በውድድሩ ላይ አልተሳተፈችም። እ.ኤ.አ በ1976 ኢትዮጵያ በአብርሃም ሃብቴ ስትወከል በአትሌቲክስ እና በቴኒስ ውድድር እንዲሁም በላውን ቦውሊንግ ውድድር ተሳትፏል።  

ከዚያ በኋላ በ2004 አንድ ሯጭ አትሌትን በውድድሩ ላይ እስክትልክ ደረስ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ከፓራሊምፒክ ውድድሮች ርቃ ቆየች።

ከአራት አመታት ቆይታ በኋላ በ2008 ኢትዮጵያ በሁለት አትሌቶች ተወክላ የነበር ቢሆንም በዚህም ጊዜ የተመዘገበዉ ዉጤት አመርቂ አልነበረም።

እ.ኤ.አ በ2012 በተዘጋጀው የፓራሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸዉና ዉጤት ካስመዘገበችባቸዉ ዉድድሮች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በዉድድሩ ኢትዮጵያ ወንድዬ ፍቅሬ በተባለ አትሌት አማካኝነት በወንዶች 1500 ሜትር ሩጫ የመጀመሪያውን የብር ሜዳልያ አግኝታለች።

በቀጣይ ከአራት አመታት በኋላ በብራዚል ሪዮ ከተማ በተዘጋጀው የፓራሊምፒክ ውድድር በመክፈቻ ዝግጀት ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለበ የገባው ታምሩ ደምሴ በ1500 ሜትር ለኢትዮጵያ በታሪክ ሁለተኛውን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።

ለኢትዮጵያ የመጀመርያዉ ወርቅ

በውድድሩም ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ በትዕግስት ገዛኸኝ አማካይነት አገኝታለች፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ትዕግስት፣ ቅዳሜ ነሐሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው በጭላንጭል የሚያዩ የ1500ሜ ሩጫ፣ የራሷን ምርጥ ሰዓት 4:23.24 በማስመዝገብ ነው ለፓራሊምፒክ አሸናፊነት የበቃችው፡፡ ትዕግስትን ተከትላ በ2ኛነት የገባችው አሜሪካዊቷ ሊዛ ኮሮሶ ስትሆን፣ ቱኒዝያዊቷ ሶማያ ቡሰይድ በ3ኛነት አጠናቃለች፡፡

ኢትዮጵያ አስረኛ ቀን ላይ በደረሰው 16ኛው የበጋ ፓራሊምፒክስ ጨዋታ የደረጃ ሰንጠረዥ በትዕግስት መንግስቱ ብቸኛ ወርቅ 56ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

በፓራሊምፒክ ውድድሩ ላይም ኢትዮጵያ ከረጀም አስርት አመታት በኋላ በፓራሊምፒክ ስፖርት ስትጠብቅ የነበረውንና የመጀመሪያዉን የወርቅ ሜዳሊያ በሴቶች 1500 ሜትር በትዕግስት ገዛኸኝ አማካኝነት አግኝታለች።