ከክልሉ አልፎ የምስራቅ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የንግድና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንባት ደማቋ የጅግጅጋ ከተማ ምንም እንኳን የክልሉ ርእሰ መዲና ብትሆንም እንደሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የተጠናከረ የመብራት ተጠቃሚ ለመሆን እንዳልቻለች ነዋሪዎቿ ይናገራሉ።
የመብራት መቆራረጥ፣ የመብራት አገልግሎት ከተቋረጠ ለበርካታ ቀናት ሳይጠገን መቆየትና አብዛኛው የኤሌክትሪክ ፖሎች የበሰበሱና ያረጁ በመሆናቸው ዝናብ በዘነበ ቁጥር የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በከተማው ህዝብ ዘንድ የተለመዱ ችግሮች ናቸው።
በጅግጅጋ ከተማ በተደጋጋሚ ጊዜ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሚቋረጥባቸው አከባቢዎች መካከል በ05 ቀበሌ ከካራማራ ሆስፒታል ጀርባ የሚገኘው ሰፈር ተጠቃሽ ነው። በዚህ አከባቢ የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በንግድና በሌሎች አነስተኛ ስራዎች ህይወታቸውን የሚመሩ ሲሆን በተደጋጋሚ የሚከሰተው የመብራት አገልግሎት መቋረጥ በስራና ኑሯቸው ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል።
በአከባቢው መለስተኛ የንግድ ሥራ በመስራት ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው አቶ አብዲ ሱሌይማን የመብራት ችግር በአከባቢው በየእለቱ የተለመደ ችግር መሆኑን ይገልፃሉ።
በአከባቢው በተለይም በዝናብና ንፋስ ወቅት በተደጋጋሚ ጊዜ መብራት እንደሚጠፋ የሚገልፁት አቶ አብዲ መብራት በሚጠፋበት ጊዜ ለሚመለከተው አካል ብናሳውቅ ሳይሰራ እስከ አምስት ቀናት ድረስ እንደሚቆይ በምሬት ይናገራሉ።
በተደጋጋሚ የመብራት መጥፋት ችግር በአከባቢው ያለው ያረጀ የኃይል ተሸካሚ ትራንስፎርመርና የበሰበሱ ፖሎች በአግባቡ ያልተዘረጉ የኤሌክትሪክ ሽቦዎች እንደሆኑ ጠቁመው የኤሌክትሪክ ሰራተኞች ጥገና ለጊዜያዊ ችግር መፍቻ እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዳላመጣ አስረድተዋል።
‹‹መብራት ለሰው ልጅ መሠረታዊ ነገር ነው›› የሚለው አቶ አብዲ የአካባቢው ነዋሪ ይህ መሰረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶለት እንደማያውቅ ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ አብዲ ገለጻ በእንጨትና በብረታ ብረት ስራ የሚተዳሩ ግለሰቦች በመብራት መቆራረጡ ምክንያት ምርቶችን በጊዜው ማድረስ ባለመቻላቸው ከደንበኞች ጋር ግጭት ውስጥ ስለመግባታው ያስረዳሉ።
ኤሌክትሪክ በተቋረጠ ቁጥር ከሚሰሩት ስራ ጋር በተያያዘ ጀነሬተር የሚጠቀሙ በመሆኑ አለአግባብ ለነዳጅና ሌሎች ወጪዎችን ለማውጣት እንደሚገደዱ የሚገልፁት ግለሰቡ ችግሩ ባለመፈታቱ ስራቸውን ለመስራት አለመቻላቸውን በተስፋ መቁረጥ ይናገራሉ።
በአከባቢው ቺብስና ሳንቡሳ በመጥበስ ስራ ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ እመቤት በነበሩ ምንም እንኳን ስራቸውን የሚሰሩበት ማሽን ቢገዙም በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ሥራቸውን በከሰልና በእንጨት እየተጨናበሱ ለመስራት እንደሚገደዱ ተናግረዋል።
በዚሁ አከባቢ የሚገኙ ሌሎች በተለያዩ የስራ መስክ ህይወታቸውን የሚመሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችም እስካሁን መፍትሄ ያልተገኘለት የአከባቢው የመብራት ችግር የእለት ተእለት አንገብጋቢ ችግራቸው በመሆኑ ለዚህ ዘላቂ መፍትሄ ይፈልጋሉ።
በአሁኑ ጊዜ በሁለተናዊ መስኮች ፈጣን እንቅስቃሴ ላይ በምትገኘው የጅግጅጋ ከተማ በየአከባቢው የሚታየው የመብራት መቆራረጥ በህዝቡና በሚካሄዱ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዘ የጅግጅጋ ዲስትሪክት የዲስትሪቢዩሽንና ኦፕሬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ቴድሮስን ያነጋገርናቸው ሲሆን በአካባቢው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር እንደነበረ አንስተው ከሳምንት በፊት አዲስ የመስመር ማሻሻያ ዝርጋታ በማካሄድ ችግሩን ለመፍታት መቻሉን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የቀሩ ስራዎችን በአስቸኳይ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ስራውን በሚያከናውኑበት ወቅ የኃይል መቋረጥ ሊገጥም ስለሚችል ለዘላቂ መፍትሄ ሲባል ማኅበረሰቡ እንዲታገሳቸውም ጠይቀዋል።