ሐምሌ 17 ፣ 2013

የክረምቱ ዝናብና የጎርፍ አደጋ ስጋት

City: Addis Ababaየከተማ ልማትአካባቢማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

የክረምት መምጣትን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተለያዩ አከባቢዎች የጎርፍ አደጋ ስጋቶች መጠኑ ይለያይ እንጂ በ4ቱም አቅጣጫዎች ይስተዋላሉ። ይህም የጎርፍ አደጋን ሊያስከትል የሚችል ሲሆን፤ የተቀመጡት መፍትሄዎችስ?

Avatar: Haymanot Girmay
Haymanot Girmay

የክረምቱ ዝናብና የጎርፍ አደጋ ስጋት

የክረምት መምጣትን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተለያዩ አከባቢዎች የጎርፍ አደጋ ስጋቶች መጠኑ ይለያይ እንጂ በ4ቱም አቅጣጫዎች ይስተዋላሉ። በዘንድሮ አመት 2013ዓ.ም እስከ ሀምሌ 24 የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ተብለው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜትሮሎጂ የተጠቀሱ ቦታዎችን እና በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተቀመጠውን የመፍትሄ አቅጣጫ በዚህ ፅሁፍ ለመዳሰስ እንሞክራለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ የአየር ሁኔታ እና ትንበያ ባለሙያ ታምሩ ከበደ “ዝናብ እየከበደ ስለሆነ ከፍተኛ ዝናብ፣ ነጎድጓድ አዘል ዝናብ እና ጎርፍ ሊከሰት ይችላል” ሲሉ በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ ቦታዎችን ይጠቅሳሉ።

በምዕራብ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ምዕራብ አጋማሽ፣ ምስራቅ ሸዋ እና ሰሜን ሸዋ እንደ ምሳሌ የሚያስቀምጡት ባለሙያው ቦታዎችን በመነጣጠል ያብራራሉ።

በኦሮሚያ ክልል ከሆለታ፣ ጊንጪ፣ ሰበታ፣ ቱሉ ቦሎ እና እስከ አፋር፣ ስልጤ፣ ሀድያ፣ ከንባታ፣ጉራጌ፣ ምራብ እና ምስራቅ ጎጃም እና ባህር ዳር በወንዝ ሙላት ለጎርፍ ተጋላጭ ናቸው።  ምዕራብ ኦሮሚያ ጅማ አከባቢ፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ለከባድ ዝናብ እንዲሁም ምስራቅ ሸዋ እና ሰሜን ሸዋ በመካከለኛው ተጋላጭ ናቸው። 

ሀላፊው እንደሚሉት ነጕድጓድ አዘል ዝናብም ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን አዲስ አበባ ላይ ብዙም የሚያሰጋ ነገር የለም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሜቲዎሮሎጂ  ኤጀንሲ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በየ10 ቀን ካስፈለገም በየቀኑ ጥቆማ እንደሚሰጥ ባለሙያው ገልፀዋል።

በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው ከብሄራዊ ሜትሮሎጂ የሚደርሳቸውን መረጃ መሰረት በማድረግ ምን እንደሚመጣ አስቀድሞ ለማወቅ እና ዝግጅት ለማድረግ እንደሚጠቀሙበት ይናገራሉ። 

"አደጋ ከመድረሱ በፊት አደጋን የመቀነስ ስራ መስራት " የተቋሙ ተግባር መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ከሜትሮሎጂ ጥቆማውን ካገኙ በኃላ ለሚመለከታቸው የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ከግንቦት ወር ጀምሮ 3 ጊዜ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ያስታውሳሉ።

በክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑት 10 ክልል እና 2 ከተማ መስተዳድር ሲሆኑ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ እና ትግራይ ክልል የመሬት መንሸራተት ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ። ለዚህም በክረምት ወቅት ለሚገጥም ችግር ለመጠባበቂያ የሚሆን ከ3 ቢሊዮን በላይ ብር መመደቡን አክለዋል።

"በሀገራችን ብዙ ጊዜ የምናውቃቸው አደጋዎች ያጠቁናል" የሚሉት ዳይሬክተሩ ይህን ጉዳይ አስቀድሞ ለመከላከል በአንድ መስሪያ ቤት ብቻ እንደማይቻል በማብራራት ነው። ለምሳሌ በአዲስ አበባ ለሚፈጠር የውሀ መሙላት የመንገዶች ባለስልጣን፣ ጤና ቢሮ፣ ውሀ ፍሳሽ እና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይመለከተዋል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ጎርፍ በሚከሰትባቸው ቦታዎች ላይ ነዋሪዎች ከአከባቢው እንዲነሱ በማድረግ እና የጎርፍ መከላከያ ግድብ በመስራት ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚቻል የሚጠቁሙት ሀላፊው በድሬዳዋ የሚሰራውን የጎርፍ መከላከያ ግድብ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ነው። ይህም በመንግስት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን በማስተባበር የሚሰራ ስራ መሆኑንም ጭምር ገልፀዋል። 

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ እና የተፋሰስ ልማት ስራዎች የጎርፍን እንቅስቃሴ በመገደብ ደረጃ ብዙ ጉዳቶችን መቀነሳቸውን የሚገልፁት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ይላሉ። ተቋማቸው ብሄራዊ የአደጋ ስጋት እና አመራር ኮሚሽን መረጃ በመስጠት እና ከሚመለከታቸው ጋር አብሮ በመቀናጀት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

አስተያየት