የካቲት 13 ፣ 2015

ለግማሽ ምዕተ ዓመት በጣና ሀይቅ ላይ የነገሰችው “የጣናነሽ”

City: Bahir Darየአኗኗር ዘይቤ

የጣናነሽ በ1957 ዓ.ም በጀርመን ሀገር እንደተሰራችና በ1960 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ሀገር ወስጥ እንደገባች ይነገራል

Avatar: Abinet Bihonegn
አብነት ቢሆነኝ

አብነት ቢሆነኝ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ምሩቅ ሲሆን። ዜና እና የተለያዩ ዘገባዎች የመፃፍ ልምድ አለው። አሁን በአዲስ ዘይቤ የባህር ዳር ሪፖርተር ነው

ለግማሽ ምዕተ ዓመት በጣና ሀይቅ ላይ የነገሰችው “የጣናነሽ”
Camera Icon

ፎቶ፡ አብነት ቢሆነኝ

ከጣና ሀይቅ ዳርቻ በሰሜን-ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኝ ደልጊ ተብላ በምትጠራ ከተማ በሆቴል ስራ የምትተዳደረው ወ/ሮ አትጠገብ ለሆቴሏ የሚያስፈልጋትን አብዛኛውን ግብዓት ከባህርዳር ከተማ እንደምሸምት ትናገራለች። 

ከባህርዳር ደልጊ በመኪና ለመሄድ እንደልብ መኪና ከአለመኖሩ በተጨማሪ መንገዱ ምቹ አይደለም ትላለች። በመሆኑም ወደ ባህርዳር  ዕቃ ለመግዛት ስትመጣ ለዓመታት የጣናነሽን ምርጫዋ አድርጋታለች።

“ለዓመታት በየጣናነሽ ተመላልሻለሁ። ማዕበል ቢነሳም የጣናነሽ ግዙፍ በመሆኗ እንደሌሎች ጀልባዎች ምቾት አትነሳም" ትላለች ወ/ሮ አትጠገብ።

ዘጌ ከተማ በንግድ ስራ የሚተዳደረው አትንኩት በላይ በበኩሉ፣ ብዙ ጊዜ በየጣናነሽ እንደሚጠቀም ተናግሮ “ስራ በበዛበት ወቅት መሄድ ባልችል እንኳ ከባህር ዳር እቃ ተገዝቶ በየጣናነሽ ተጭኖ ይላክልኛል" ይላል።

ሌሎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ በጣና ሀይቅ ደሴቶች የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ ባህርዳር ለመሄድ የየጣናነሽ ደንበኛ ናቸው።

ሀምሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በጣና ሀይቅ ያገለገለችው የጣናነሽ ዕድሜዋን እና አበርክቶዋን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀይቁ ዙሪያ የሚገኙ ማህበረሰቦች "የጣና-አድባር" ይሏታል።

የጣናነሽ በትልቁ የጣና ሀይቅ ላለፉት 45 ዓመታት ተመላልሳበታለች። በሃይቁ ላይ ለበርካታ ዓመታት ከባህር ዳር ተነስታ ደቅ፣ ቁንዝላ፣ ደልጊ፣ በርበራ ፣ዘጌ እና ጎርጎራ ወደሚባሉ መዳረሻዎች መንገደኞችን አጓጉዛለች።

የጣናነሽ በጉዞዋ በጣና ሀይቅ የሚገኙ ሰባት ወደቦችን ታዳርሳለች። ዘወትር መነሻዋን ከባህርዳር ወደብ በለሊት አድርጋ ወደ  ዘጌ ታቀናለች። በታሪካዊቷ ዘጌ ከተማ ስትደርስ መንገደኛ እና የጫነችውን ዕቃ ታራግፋለች። ጉዞዋን ቀጥላ መዳረሻዋን ወደ ደቅ-ደሴት ታደርጋለች በደቅ ደሴት ለራሷም ለመንገደኞቿም መጠነኛ እረፍት ትሰጣለች። የጣናነሽ መንገዷን ቀጥላ ምሽት ላይ አዳሯን ቁንዝላ ላይ ታደርጋለች። ደግም በንጋት ከቁንዝላ ተነስታ ሁለት መዳረሻዎችን ካለፈች በኋላ በመጨረሻ ከበርበራ ወደብ ተነስታ ወደ ቤቷ ውቢቱ ባህርዳር ትመለሳለች። 

የጣናነሽ ረጅሙ የጉዞ መዳረሻዋ በበርበሬ ምርት የሚታወቀው ደልጌ ሲሆን እዚያ ለመድረስ ግማሽ-ቀን ይፈጅባታል። ደልጌ ስደርስም ረጅም መልህቋን ትጥላለች።

የጣናነሽ በ1957 ዓ.ም በጀርመን ሀገር እንደተሰራችና በ1960 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ሀገር ወስጥ እንደገባች ይነገራል። ከ1960 ዓ.ም  ጀምሮ ለ10 ዓመታት ያህል መኖሪያዋ እና እንቅስቃሴዋ አርባ-ምንጭ ከተማ እንደነበር ታሪኳ ይገልጻል። 

በወቅቱ ግዙፍ የሆነችውን የጣናነሽ አርባ ምንጭ ያለው የውሃ መጠን ማንቀሳቀስ ባለመቻሉ ከጣና  ሀይቅ አንዲት አነስተኛ ተመሳሳይ ስያሜ ያላት የጣናነሽ  የምትባል  ጀልባ ወደ አርባ ምንጭ ተልካ በምትኩ የጣናነሽ ከሰባት ተቆራርጣ ወደ ጣና ሀይቅ መጣች። 

በ1970 ዓ.ም ከሰባት ተቆራርጣ የመጣችው የጣናነሽ በጣና ሀይቅ ጎርጎራ ወደብ በነበረው ትልቅ “ወርክሾፕ” ተገጣጥማ አገልግሎት መስጠት ጀመረች።

የጣናነሽ በጣና ሀይቅ ላይ በሰጠችው አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት የውጭ ሀገር ካፒቴኖች እንደነበሯት ይወሳል። በሂደት ኢትዮጵያውያን ካፒቴኖች ስራውን ተረክበው መስራት ጀምረዋል። የጣናነሽ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ካፒቴን አቶ ስራው አስፋው ይባላሉ።

ካፒቴን ስጦታው አላምረው አሁን ላይ የጣናነሽ ዘዋሪ ሲሆኑ አምስተኛው ካፒቴን እንደሆኑ አጫውተውናል። ካፒቴን ስጦታው ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ከየጣናነሽ ጋር የነበሩ ሲሆን ለ15 ዓመታት ደግሞ ዋና ካፒቴን በመሆን አገልግለዋል።

እንደ ካፒቴን ስጦታው ገለፃ የጣናነሽ አራት መቶ ሰው እና ስምንት መቶ ኩንታል የመጫን አቅም ያላት ሲሆን ዕቃ ሳትጭን እስከ አንድ ሺህ ሰው የመጫን አቅም አላት።

በጣና ሀይቅ አስጎብኚ እና የትንሽ ሞተር ጀልባ ካፒቴን የሆነው ታዲዎስ ታደሰ እንደሚናገረው በጣና ሀይቅ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሩም የየጣናነሽ የዕድሜ ባለፀግነትና ግዝፈት በርካታ ጎብኚዎችን ስለ ጀልባዋ የማወቅ ፍላጎት እንዲያሳድርባቸው አድርጓል ይላል። ይህ በመሆኑም የጣናነሽ በአብዛኛው መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት የምትሰጥ ብትሆንም ጎብኚዎች በየጣናነሽ የመጓዝ ፍላጎታቸውን ሲያንፀባርቁ ይታያሉ።

የጣናነሽ  ሀምሳ ዓመት በተጠጋው አገልግሎቷ የከፋ አደጋ አስተናግዳ አታውቅም። ለዚህም የጀልባዋ ክብደት በምክንያትነት ይጠቀሳል። እንደ ካፒቴን ስጦታው ማብራሪያ የጣናነሽ  አንድ መቶ ቶን (ወደ 90,718.5 ኪ.ግ) የምትመዝን ስትሆን ይህም ጣና ኃይቅ ላይ ሊነሳ የሚችል ማዕበል በቀላሉ አያንቀሳቅሳትም።

የጣናነሽ በአያሌ አመታት አገልግሎቷ እምብዛም የከፋ አደጋ ባታውቅም፣ በ1994 እና 1995 ዓ.ም የጣና ሀይቅ የውኃ መጠን በከፍተኛ መጠን ቀንሶ በነበረበት ወቅት የሞተር ተርባይኗ በተደጋጋሚ አደጋ ደርሶበት እንደነበርና በብዙ ወጪ ጥገና እንደተደረገለት ካፒቴን ስጦታው ያስታውሳሉ።  

በቅርብ ዓመታት በጣና ሀይቅ በስፋት በተከሰተው እንቦጭ ምክንያት የጣናነሽን እንደ ልብ እንዳትንቀሳቀስ እክል መፍጠሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ቢሆንም አሁን ላይ ግን እንቦጭ የጣናነሽ ስጋት አለመሆኑን ካፒቴኑ ያረጋግጣሉ። 

ከጣናነሽ ጋር በተያያዘ በሰው ህይወት ላይ አደጋ አጋጥሞ ባያውቅም በአንድ ወቅት የአእምሮ-ህመምተኛ መሆኑ ያልታወቀ አንድ መንገደኛ ድንገት ሳይታሰብ ወደ ሃይቁ ራሱን ከወረወረ በኋላ የነብስ-አድን ጥረት ቢደረግም ሳይገኝ ቀርቶ ከሰባት ቀን በኋላ አስክሬኑ በፍለጋ መገኘቱን የጀልባዋ ሰራተኞች ይናገራሉ። 

የጣናነሽ ወደ ታላቁ የጣና ሀይቅ ከመጣች አርባ አምስት ዓመታትን አሳልፋለች። በጣና ሀይቅ ላይ ዳህላክ፣ ፋሲለደስ፣ ንጋት፣ አንድነት እና ሌሎች ጀልባዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ሆኖም የጣናነሽ በጣና ሀይቅ ከሚገኙ ጀልባዎች በዕድሜ እና በመጠን ትልቋና አንጋፋዋ ናት።

በሀይቁ ካሉ ጀልባዎች ግዙፏ የጣናነሽ 27 ሜትር ስፋት እና 8 ሜትር ቁመት አላት። የጣናነሽ ባለሁለት ፎቅ ቁመና ሲኖራት፣ በሁለተኛው ፎቅ እየተዝናና መሄድ የፈለገ መንገደኛ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ መጓጓዝ የሚችልበት ክፍል አላት። በውስጧም ሁለት መፀዳጃ-ቤቶች እና የሠራተኞች ማደሪያ መኝታ ክፍሎች ይዛለች።

የጣናነሽ የምድር ቤቷ ውስጥ በርካታ ዕቃ ይጫንባታል፤ በተጨማሪም ውኃ ሰርጎ እንዳይገባ የሚቆጣጠር Air Bag ወይም የአየር-ቦርሳ አላት። ጀልባዋ ሁለት ሞተሮች ያላት ሲሆን በአንደኛው ሞተሯ ብቻ በሰአት 11 ኪሎ-ሜትር ትጓዛላች።

ወደ ጀልባዋ መሾፈሪያ ክፍል ስንዘልቅ ሁለት መሪ ያላት ሲሆን፤ ሦስት ሰዎችን አደላድላ የምታስቀምጥበት ቦታን ይዛለች። ታሪካዊቷ ጀልባ ገመድ አልባ ስልክ እና የጂፒኤስ መሳሪያም ተገጥሞላታል። በተጨማሪም ለመንገደኞች የሻይ ቡና መስተንግዶ የምትሰጥበት ካፌም አላት።

የጣናነሽ ውሃ ሲጎድል ውኃው ስለመጉደሉ መረጃ የሚሰጥ (Depth Indicator) የተባለው የውሃ ጥልቀት መለኪያ መሳሪያ የላትም። በዚህም ምክንያት ውኃ በሚጎድል ጊዜ አደጋ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት የጉዞ ፕሮግራሟ በተደጋጋሚ የተሰረዘበት አጋጣሚ መኖሩን ካፒቴኑ ይናገራሉ።

የጣና ሀይቅ ውሃ ጨዋማ ባለመሆኑ የጀልባዋ የውስጠኛው ክፍል እስከ አሁን ቀለሙ አለመልቀቁን እንደ ምሳሌ በማንሳት የጣናነሽ በጥሩ ይዞታ ላይ እንደምትገኝ ካፒቴን ስጦታው በኩራት ይናገራሉ። አሁን ላይ የጣናነሽን ጨምሮ ሌሎች የሀይቁ ጀልባዎችን የፌዴራል ተቋም የተረከባቸው በመሆኑ የውሃ ጥልቀት መለኪያ መሳሪያን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ እቃዎች ተሟልቶላቸው አስፈላጊ ጥገና ያገኛሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሏል።

ለበርካታ ዓመታት በጣና ሀይቅ ያገለገለችውን የጣናነሽ ጨምሮ ሌሎች ጀልባዎች በመጀመሪያ "ውስኪ" የሚባል የጣሊያን ድርጅት ያስተዳድራቸው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።

“ነቪጋ ጣና” የተባለ የመጀመሪያው ሀገር በቀል ተቋም በጣና ሀይቅ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን እስከ እዚህ ዓመት መጀመሪያ ድረስ “ጣና ትራንስፖርት” የተባለ ድርጅት በሀይቁ ላይ የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል።

ከወራት በፊት የጣናነሽን ጨምሮ በጣና ሀይቅ ያለውን ሙሉ የትራንስፖርት አገልግሎት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ማስተዳደር ጀምሯል።

አስተያየት