መስከረም 8 ፣ 2014

የ2013 ዓ.ም. ዐበይት ክስተቶች

City: Bahir Darፖለቲካማህበራዊ ጉዳዮች

ከዓለም አቀፍ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ እስከ ሐገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ከዋጋ ግሽበት እስከ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የሱዳን ወረራ፣ መፈናቀሎች፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በርካታ ክስተቶች አልፈዋል።

Avatar: Ayele Addis
አየለ አዲስ

Ayele Addis is an award winner Journalist, Journalism, Trainer, Researcher, and Media & Communication Development Consultancy for Thomson Reuters' Foundation, Africa News Channel, Amhara Media, and Journalists Association. Ethiopian Mass Media Action (EMMA News), ARMA Media Production.Woldia University and Bahir Dar University and founder of Journal of Ethiopian Media and Communications.

የ2013 ዓ.ም. ዐበይት ክስተቶች
Camera Icon

Photo: africaglobalvillage.com , bethany.org , ethiopoint.com , wvi.org , for-africa.com

ያሳለፍነው 2013 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ አስቸጋሪ የሚባል ዓመት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። 2014 ዓ.ም. በርካታ ያልተወራረዱ ሂሳቦችን ከቀደመው ዓመት ተረክቧል። ከዓለም አቀፍ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ እስከ ሐገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ከዋጋ ግሽበት እስከ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የሱዳን ወረራ፣ በርካታ የሐገር ውስጥ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በርካታ ክስተቶች በፍጥነትም በብዛትም አልፈዋል። አብዛኛዎቹ እልባት ሳያገኙ የምንገኝበትን ዓመት ተቀላቅለዋል።

ከአሁን ጀምረን አሮጌ በምንለው 2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ሰፊ ደም መፋሰስ፣ አለመረጋጋት እና የቀውስ ዜናዎች በብዛት የተደመጡበት ሆኖ አልፏል። በዚህ ጽሑፍ በዓመት ውስጥ የነበሩ ዋና ዋና ክስተቶችን በወፍ በረር እንመለከታለን።

የፖለቲካ ወጥረት

2014 ዓ.ም. ከተሻገሩ ውድመት ያስከተሉ ክስተቶች ውስጥ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል የተካሄደው አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ነው። የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽሟል በሚል በህወሓት ኃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ጦርነት ተካሂዷል። የፌደራሉ መንግሥት ‹‹ሕግ ማስከበር›› ሲል የጠራው የሦስት ሳምንታት ወታደራዊ ዘመቻ ሲጠናቀቅ ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. የክልሉን ዋና ከተማ መቐለን መቆጣጠሩን ይፋ አድርጓል።

በ2013 በመጀመሪያ ወራት የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ህወሃት እና በፌደራል መንግስቱ መሀከል በተፈጠረ የፖለቲካ ውጥረት የጀመረው ዓመት፤ ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ የበርካቶችን ህይወት የተቀጠፈበት፣ ንብረት የወደመበትና በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁበት ዓመት ሆኖ ተጠናቋል። በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ የሚያገረሹ ግጭቶች፣ ዓለምን የሚያምሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና በየጊዜው እያሻቀበ የሚሄደው የዋጋ ግሽበት ግለሰቦችን፣ ተቋማትንና ሀገርን እየፈተኑ ይገኛሉ።

በታህሳስ 2013 ዓ.ም. በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ የተከሰተው ግጭት የሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የአርሶ አደሩን ንብረት የዘረፉበት እና ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ወረራ የፈጸሙበት ነው።  

ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳንን ከመሰሉ ጎረቤቶቿ ጋር የገጠመችው ውዝግብ የናረበት፣ አወዛጋቢ የድንበር አካባቢ ግዛቶቿ በውጪ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉበት፣ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት የሻከረበትም ዓመት ነበር።

የቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግድቡን የተመለከተ የሰጡት አወዛጋቢ አስተያየትም የተደመጠውም ባሳለፍነው 2013 ዓ.ም. ነበር።

ባሳለፍነው ዓመት ከጥር እስከ መጋቢት በነበሩት ሦስት ወራት አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ የሚያስፈልገዉ ኢትዮጵያዊ ቁጥር 23.5 ሚሊዮን ነበር። 

የተፈጥሮ አደጋ

በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው የአምበጣ መንጋና የጎርፍ አደጋም እንዲሁ በእርሻ ምርቶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ምስራቅ ኢትዮጵያ ከመስከረም እስከ ሕዳር ወር ድረስ ወትሮ ከሚያገኙት መደበኛው የዝናብ መጠን ከፍ ያለ በመሆኑ ለከፍተኛ የአንበጣ ስጋት ተዳርገዋል።

አስገራሚ ክስተተቶች

ዓመቱ ሠላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ በጥገኝነት የኖሩት ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታ ተደርጎላቸው በነፃ የተሰናበቱበት ነው። ይህ የአንድ ወጣት እድሜን ያክል በአንድ ቅጥር ግቢ ያሳለፉት እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ እና ሌፍተናንት ጄነራል አዲስ ተድላ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ላለፉት ሦሰት አስርት ዓመታት ቆይተዋል።

ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ አንድ ቀን ቀደም ብለው በጣሊያን ኤምባሲ ውስጥ ከተጠለሉት አራት የወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣንት አቶ ብርሃኑ ባይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ሌፍተናንት ጀነራል አዲስ ተድላ የሠራዊቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ነበሩ።

በዘመነ ኢህአዴግ የሞት ፍርደኞች የነበሩት ባለሥልጣናቱ ከተሸሸጉበት ኤምባሲ ሳይወጡ በሌለሉበት የተከናነቡት የሞት ፍርድ በርዕሰ ብሔሯ አማካኝነት ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮላቸዋል። ዐቃቤ ሕግም በተመሳሳይ የተላለፈባቸው የሞት ፍርድ ወደ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀነስ በይቅርታ እና ምህርት ቦርድ በኩል ለርዕሰ ብሔሯ ጥያቄ አቅርቦ ከ30 ዓመታት የቁም እስር በኃላ ወጥተዋል።

የዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለኢትዮጵያ ስጋታቸውን እየገለጡ፣ የ2013ቱ አለመረጋጋት፣ ጦርነት፣ ግጭት፣ የአንበጣና የኮሮና ወርሺኝ፣መፈናቀልና መባረር ሲታከልበት ከድሕነት ጠገግ በታች የሚኖረዉ ሕዝብ ወደ 40 ሚሊዮን ከፍ እንዳለ ወደ 2014 ተሸጋገረ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2012 ዓ.ም. በድሕነት ጠገግ እንደሚኖር የተገመተው ኢትዮጵያዊ 31 ሚሊዮን ነበር።

ምንደስታ አለ

በ2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን በብዙ ተግዳሮቶች መሃል የዓለም አቀፉን የኃያላን እና የጎረቤት ሀገራት ትንኮሳ ተቋቁማ የሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መከናወኑ አንዱ የሀገሪቱን ተስፋ ያመላከተ ነው።

ነፍጥ አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎች በ2013 ዓ.ም. ምርጫ በህዝብ ድምጽ ሥልጣን ለመያዝ መወዳደራቸው አንዱ ተስፋ ሰጪ ክስተት ነው። ኢትዮጵያ በጦርነት እና ስጋት ውስጥ ሆና ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና የተሻለ ፉክክር የታየበት አገራዊ ምርጫ አካሂዳለች።

ቁጥሮች

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለ2013 ዓ.ም. የመጨረሻው በሆነው ስብሰባ ለ2014 ዓ.ም. ያጸደቁት በጀት ካለፈው ዓመት ጋር ሲወዳደር በብር 18 በመቶ ቢጨምርም በዶላር ግን ቀንሷል።

የተሰናበተው 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት በብር 476 ቢሊዮን፤ በዶላር ደግሞ 13.7 ቢሊዮን ገደማ ነበር። የዘንድሮው በብር ወደ 561.7 ከፍ ቢልም በዶላር 12.9 ቢሊዮን ሆኗል::

የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ሪፖረት እንደሚያሳየው የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ1,000 ዶላር በላይ ሆኗል።

የኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን (GDP) ወደ 4.2 ትሪሊዮን ብር ወይም ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። 

የጠቅላይ ምኒስትሩ ሪፖረት በ2013 ዓ.ም. እንደሚያሳየው ከአንድ ትሪሊዮን በላይ ብር በባንክ ተዘዋወሯል፤ የባንኮቹ ጥሪት ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ ወደ 1.9 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።

ኢትዮጵያ በዓመቱ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ለውጭ ገበያ ካቀረበቻቸው ሸቀጦች አግኝታለች።

ከውጭ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የገባው መዋዕለ ንዋይ (በዓይነት እና በመጠን) በ20 በመቶ አድጎ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል።

አስተያየት