መስከረም 8 ፣ 2014

80 ዓመት ያለፋቸው የድሬደዋ ሲኒማ ቤቶች

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮችኪነ-ጥበብ

በድሬዳዋ ከተማ የመጀመርያዎቹ ሲኒማ ቤቶች ሥራ የጀመሩት በ1930ዎቹ አካባቢ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በጊዜው አጀብ የተባለላቸው ሲኒማ ማሳያ ቤቶች የተገነቡት በተመሳሳይ ወቅት ነው። በወቅቱ ድሬደዋ ከተማ...

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

80 ዓመት ያለፋቸው የድሬደዋ ሲኒማ ቤቶች

በድሬዳዋ ከተማ የመጀመርያዎቹ ሲኒማ ቤቶች ሥራ የጀመሩት በ1930ዎቹ አካባቢ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በጊዜው አጀብ የተባለላቸው ሲኒማ ማሳያ ቤቶች የተገነቡት በተመሳሳይ ወቅት ነው። በወቅቱ ድሬደዋ ከተማ ከነበራት ስምና ዘመናዊነት ጋር የውጪም ይሁን የሀገር ውስጥ ነዋሪዎቿ የመዝናኛ አማራጭ እንዲያገኙ የማስቻል አላማ እንደነበራቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሲኒማ ቤቶቹ “ሲኒማ ኢንፓየር” እና “ሲኒማ ማጂስቲክ” የሚል ስያሜ አላቸው። የመጀመሪያ ብቻ ሳይሆኑ ብቸኛም እንደሆኑ ዘልቀዋል።

ሲኒማ ኢንፓየር በፊታውራሪ ተስፋዬ ቀጀላ የተነባ ነው። (ፊታውራሪ ተስፋዬ የጣልያን ወረራን የመከቱ አርበኛ ናቸው) ፊታውራሪ ከመኖርያ ቤታቸው አጠገብ ያስገነቡት ይህ ሲኒማ ማሳያ በ4 መአዘን ቅርፅ ክፍት ሆኖ የተሰራ ነው። የፊልም ማሳያው ስክሪን በግንብ የተሰራ ሲሆን 6 ሜትር ቁመትና 13 ሜትር ርዝመት አለው። የዋናው በር መግቢያ ባለ 2 ተካፋች የእንጨት በር ሲሆን የውጭው ከፍርግርግ ብረት የተሰራ ነው። ከተመልካች በስተኋላ በኩል 5 ክፍሎች ያሉት ባለ1ፎቅ ህንፃ ይገኛል። ከፎቁ ላይ የክቡር ትሪቡን ቦታዎች በግራና በቀኝ ይገኛሉ። በአሁን አጠራሩ “ቪአይፒ” ተብሎ በሚታወቀው ሰገነት ላይ ሆኖ ለመታደም ከመደበኛው ከፍ ያለ ሂሳብ መክፈል ከጥንት ጀምሮ ይጠየቅ ነበር። 

የሲኒማ ኢንፓየር 486 መቀመጫዎች ሲኖሩት፤ በክፍት ቦታዎች ላይ ወንበሮች በመጨመር ከ750 በላይ ሰዎች የመያዝ አቅም አለው። ማጀስቲክ ሲኒማ ደግሞ 383 ሰዎችን ያስተናግዳል።

ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር በነበረችባቸው ዓመታት ሲኒማ ኢንፓየርን ጣሊያኖች ብቻ ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ የተለያዩ የመዝናኛ ፊልሞችና የተለያዩ የፕሮፖጋንዳ ፕሮግራሞች ይተላለፉበት እንደነበር ይነገራል።

ሌላኛው ድሬደዋ ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊው ሲኒማ ቤት “ሲኒማ ማጂስቲክ” ሲሆን በ1930ዎቹ አካባቢ በከተማዋ ይኖሩ በነበሩ ግሪካዊያን እንደተገነባ የታሪክ መዛግብት ያብራራሉ። ግሪኮች በወቅቱ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እና የግሪኮችን ትምህርት ቤትም ገንብተዋል። እነዚህ ሲኒማ ቤቶች በ1965 ዓ.ም. የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተቀረፁ ድምፅ አልባ ፊልሞች አና የተለያዩ ብሄረሰቦች ሙዚቃ እና ጭፈራዎችን ያሳዩ ነበር። የኢሳዎች፣ የአፋሮች፣ የሀረሪዎች፣ አርጎባ እና የመሳሰሉትን የጭፈራ ዓይነቶች የፊልም ዕይታው አካል ነበሩ።

በ1970ዎቹ ገናና የነበረው “ማዘር ኢንዲያ” የተሰኘ የሕንድ ፊልም በሲኒማ ቤቱ ለዕይታ ከበቁ ገናና ዓለም አቀፍ ፊልሞች ውስጥ ይመደባል። ፊልሙን 1 ብር ከፍለው እንደተመለከቱ የሚናገሩት የእድሜ ባለጸጋ የ80 ዓመት አዛውንት ናቸው። ወ/ሮ ዓለምነሽ ጉርሙ ይባላሉ። አዛውንቷ በዓሁን ሰዓት በህይወት ከሌለው ባለቤታቸው ጋር ሆነው ሲኒማ ይመለከቱ እንደነበር ያስታውሳሉ።

“በወቅቱ እኔና ባለቤቴ ፍቅር የጀመርንበት ወቅት ነበር እና እዛ እየወሰደ ፊልም ያሳየኝ ነበር እና ሲኒማ ኢንፓየር በተለይ የገባን ጊዜ ደስታውን አልችለውም አሁንም በዛ በኩል ሳልፍ ባለቤቴን ያስታውሰኛል” ብለውናል።

የድሬዳዋና አካባቢዋን ነዋሪዎች ሲያገለግሉ ከ80 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ሲኒማ ቤቶች አሁን የሚገኙበት ሁኔታ አሳዛኝ የሚባል ነው። ሲኒማ ቤት ያልነበራቸው ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች አዳዲስ ሲኒማ ቤቶችን እየገነቡ በሚገኙበት በዚህ ዘመን ቀደምት የሲኒማ ታሪክ ያላት ድሬዳዋ የሚታይ እንቅስቃሴ ስትከውን አይስተዋልም። አልፎ አልፎ ከሚመደረኩት የቲያትር ሥራዎች በቀር ሲኒማ ቤቱ ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት እንዲሰጥ የማስቻል የጎላ ተግባር አልተከወነም። የአዲስ ዘይቤ ድሬዳዋ ሪፖርተር የሚመለከታቸውን አካላትና ነዋሪዎችን “ለምን?” ስትል ጠይቃለች።

የአቢሲንያ የቲያትር ቡድን ዋና ሰብሳቢ ወጣት ፍቅሩ ሽፈራው የቲያትር ቡድኑን ሥራዎች ለህዝብ ለማድረስ “ማጅስቲክ” ሲኒማ ቤትን እንደሚጠቀሙ ይናገራል። እንደ ፍቅሩ ገለጻ ሲኒማ ቤቶቹ ቲያትር ለማሳየት ምቹ ባይሆኑም “ከምንም ይሻላል” በሚል እየተገለገሉባቸው ነው። ለቲያትሩ ድባብ በመፍጠርና ስሜት በመስጠት የሚያግዙት እንደ የድምጽ ግብአቶች፣ የብርሃን፣ የመድረክ ገጽ ያሉት አልተሟሉለትም። ፍቅሩ ማብራሪያውን ሲቀጥል “በእነዚህ ሁሉ ውስጥ አልፈን ልናሳይ ብንሞክር እንኳን አዳራሹ ምቾት ያንሰዋል። ተመልካች ዘና ብሎ ትርኢቱን እንዲታደም አያደርግም። የሙቀት መቆጣጠሪያ ባለመኖሩ ከፍተኛ ሙቀት አለ” ሲል ያጋጠመውን አጫውቶናል። በመጨረሻም “በሱሰኛነት የሚታማው የድሬዳዋ ወጣት ጊዜውን ጥሩ ቦታ የሚያሳልፍበት አማራጭ ማግኘት እንዲችል የሚመለከተው አካል ቢያስብበት ጥሩ ነው። መስተዳድሩ ትኩረት ይስጠው” የሚል ምክሩን ለግሷል።

የሦልስ የቲያትር ቡድን አባል የሆነው ማቲዮስ ሁንዴሳም የፍቅሩን ሐሳብ ይጋራል። የእነማቲዎስ ቡድን ለልምምድም ሆነ ለትርኢት ማሳያ የሚጠቀሙበት “ኢምፓየር ሲኒማ” ለቲያትር ምቹ ባለመሆኑ ሥራዎቻቸውን ሆቴሎች ውስጥ ለማሳየት መገደዳቸውን ይናገራል።

“በ2010 ዓ.ም. ሁለቱንም ሲኒማ ቤቶች ወደ 1 ሚልዮን ብር በሚገመት ወጪ ቢታደሱም፤ ከቀለም ቅብ ውጪ መሰረታዊ የሚባል ማስተካከያ አልተደረገላቸውም” ከሚል ትዝብቱ በኋላ፤ አዲስ አበባ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ፊልም ሰሪዎች አዳዲስ ፊልሞቻቸውን እያስመጡ የማሳየት ፍላጎት ቢኖራቸውም የአዳራሾቹ ምቹ አለመሆን እንቅፋት ስለመሆኑ ነግሮናል።

በድሬደዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ባለሞያ አቶ ደረጀ ታደሰ አሁን ሲኒማ ቤቶቹ የሚገኙበትን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት ምላሽ “ሲኒማ ቤቶቹ ተረስተዋል” የሚለውን አባባል እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።

“ሁለቱም ሲኒማ ቤቶች አገልግሎት ላይ ናቸው። የኳስ ትዕይንቶች፣ የውጪ ሐገር ፊልሞች፣ የሀገር ውስጥ ፊልሞችና ቲያትሮች ሲያሳዩ ቆይተዋል። የሰርግ፣ የምርቃት፣ የስብሰባ እና ሌሎች ማኅበራዊ፣ ሕዝባዊ፣ ፖለቲካዊ ዝግጅቶችን አስተናግደዋል። በአሁን ሰዓት ነገሮች የቀዘቀዙ የመሰሉት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ነው።” 

እንደ አቶ ደረጀ ገለፃ የቀን እና የምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ የሚጠበቀው ሲኒማ ቤቶቹ የጀነሬተር፣ የድምጽ ሲስተም እና ሌሎች ግብአቶች እንዲሟሉላቸው እቅድ ተይዟል። ከኢትዮጵያዊ ባህል ጋር የማይቃረኑ የተለያየ ‘ዣነር’ ያላቸው ፊልሞችን ለማሳየትም ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው።