በጎንደር ከተማ እና በዙርያዋ ከሚገኙ ጥንታዊያን ቅርሶች መካከል “እጨጌ” የሚል መጠሪያ ያላቸው ቤቶች ይጠቀሳሉ። በአብዛኛዎቹ ክብ ቅርጽ ቢኖራቸውም፤ ግማሽ ክብና አራት መአዘን ቅርጽ ያላቸውም ይገኛሉ። በከተማዋ የሚገኘው የቤቶቹ ቁጥር ከ300 በላይ እንደነበር ከጎንደር ከተማ ቅርስና ቱሪዝም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በአሁን ሰዓት ከቀድሞ መጠኑ ቀንሶ ወደ 74 ቢወርድም በቂ እንክብካቤ እና ጥበቃ እየተደረገለት ባለመሆኑ ከዚህም ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ታዛቢዎች ይገምታሉ። ከመካለላቸው 53 የሚሆኑት እጨጌ ቤቶች በግለሰብ፣ 21 ያህሉ ደግሞ በመንግሥት እና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
ከጎንደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ዕንደሚያሳየው የ“እጨጌ” ቤቶች የተገነቡት በዘመነ መሳፍንት ከ1769 – 1855 ዓ.ም. ድረስ ነው። የመጨረሻው የጎንደር ንጉሥ አጼ ዩዓስ አርፎ፣ ስሑል ሚካኤል ከትግራይ ወጥቶ፣ አጼ ቴዎድሮስ እስከሚነግሥ ድረስ በነበረው የሥልጣን ሽኩቻ ወቅት እንደተገነቡ ያስረዳል።
ቤቶቹ ከጭቃ፣ ከድንጋይ፣ ከጨፈቃ፣ ከጽድ፣ ከዋንዛ፣ ከወይራ እንጨቶች እና ከሌሎችም በአካባቢው የሚገኙ ቁሳቁሶች ተገንብተዋል። ጣርያቸው የሳር ክዳን ነው። የእሳት መቃጠልን እና የጦር መሳሪያ ጥቃትን እንዲቋቋሙ ታስቦ እንደተገነቡም ይነገርላቸዋል። ቃጠሎ ቢነሳ ከሳር ክዳኑ በስተቀር ሌሎች የቤቱን ክፍሎች እንዳያቃጥል ታስቦ ስለመገንባቱም ተነግሯል።
የእጨጌ ቤቶች የጎንደርን ባህል፣ ወግ፣ አኗኗር፣ ዘይቤ፣ ባህላዊ ስርአት ክንዋኔዎች፣ ትውፊቶች በሙሉ የሚተላለፉባቸው ናቸው። የጎንደር ከተማ ካሏት ጥንታውያን ቅርሶች መካከል የቀድሞውን ዘመን የታላላቅ ሰዎች የቤት አሠራር ጥበብ ያሳያሉ። በ1950ዎቹ አካባቢ አብዛኛዎቹ እጨጌ ቤቶች ከሳር ክዳን ወደ ቆርቆሮ በወራሾቹ አማካኝነት መቀየራቸውንም ሰምተናል።
በተለይ በግለሰብ ይዞታ ስር የሚገኙት ቤቶች ታሪካዊነታቸውን እንደጠበቁ ለትውልድ ሊሻገሩ የሚያስችል ይዞታ ስር እንደማይገኙ ታዛቢዎች ይናገራሉ። በአሁን ሰዓት ቤቶቹ ጠጅ ቤት፣ መኖሪያ ቤት፣ መስጊድ፣ ጠላ ቤት ሆነዋል። ወቅታዊ ይዞታቸው ጥንታዊነታቸውን የማይመጥን አገልግሎት ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ የፈረሱ፣ ፈርሰው ቆሻሻ መጣያና መጸዳጃ ቤት የሆኑ እንደሚገኙበት የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ታዝቧል።
አቶ ዑስማን ሃሰን ቀበሌ 12 አካባቢ በሚገኝ “እጨጌ” ቤት ይኖር እንደነበር ይናገራል። ክቡ እጨጌ ቤት ውስጥ ለ61 ዓመታት አካባቢ ከኖረ በኋላ ከ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከእድሜ ብዛት ምክንያት ቤቱ እንደፈረሰባቸው ይናገራል። “ታሪካዊው ቤት ተጠብቆ መኖር እንጂ መፍረስ አልነበረበትም” የሚለው የአቶ ሃሰን በምትክ ቤት ይሰጠኝ ክርክር ከሦስት ዓመታት በላይ ቢፈጅም ጉዳዩ አሁንም እንዳልተጠናቀቀ ነግሮናል። ቀበሌ 05 የሚገኘው የአቶ አይረሴ ብሩ ቤትም ከፈረሱት ታሪካዊ የእጨጌ ቤቶች መካከል አንዱ ነው።
አቶ ዓይቸው አዲሱ የጎንደር ከተማ ቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ናቸው። የ“እጨጌ” ቤቶችን ለየት የሚያደርጋቸው ሰዎች ከባለሥልጣናት ጋር ሲጣሉ እና መጠጊያ ሲያጡ እንደ መደበቂያ ግልጋሎት ይሰጡ ስለነበር እንደነበር ነግረውናል “እጨጌ ጳጳስ ማለት ነው። የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመሬት ጉዳይ፣ ከመንግሥት ጋር በሚኖር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቤቶቹ አገልግሎት ሰጥተዋል። የ“ግዞት” ሥፍራም ሆነው አገልግለዋል” ብለዋል።
“እጨጌ ቤቶች በጎንደር እና አካባቢዋ ካሉ ቅርሶች ጋር ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በቅርስነት ተመዝግበዋል። ቅርሶች በግለሰብ ወይም በመንግስት ይዞታ ስር መሆናቸው ቅርስነታቸውን አያስቀረውም” የሚሉት አቶ ዓይቼው በአዋጅ 209/1992 ደንብ ቁጥር 39/2011 ላይ የእጨጌ ቤቶችን የተመለከተ የጎንደር ከተማ ክብቤቶች ማስፈጸሚያ አዋጅና ደንብ ወጥቷል። ሰነዱ ቅርሶቹ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣ እንዲጠበቁና፣ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላልፉ፣ ያለሙያተኛ ድጋፍና ፈቃድ እንዳይጠገኑ፣ በግለሰብ ይዞታ ስር ያሉት ሲሸጡና ሲለዋወጡ ቅርስ ጥበቃ አካል እንዲያያቸውና ሊያማክሩ እንደሚገባ፣ ከምንም በላይ ንክኪ እንዳይደረግ፣ እንዳይፈርሱ፣ እንዳይደረመሱ የሚሉ መርሆዎችን ያካተተ መሆኑንም አብራርተዋል።
እጨጌ ቤቶች ባህልና ቱሪዝም ተረክቧቸው በመንግሥት እንዲተዳደሩ የተወሰነ ቢሆንም ተግባራዊ እንዳልተረገ ገልጸዋል። ለጥገና የሚሆን በጀት እንዲያዝላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ተፈጻሚነት እንዳላገኘም አክለው ገልጸዋል። “በጀት በየዓመቱ ስንጠይቅ ሁለት ዓመት አልፏል። መንግሥት ቅርሶቹን ለመንከባከብና ለመጠገን የሚሆን በጀት አልመደበልንም። ቅርሱ ከእድሜ ብዛት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል። በእርግጥ እነኚህን የመንከባከብ ኃላፊነት የሁላችንም ቢሆንም። መንሥት ከፍ ያለውን ድርሻ መያዝ አለበት። ሕብረተሰቡም የአንድ ወገን ጠባቂ ሳይሆን የራሱን እንቅስቃሴ ቢያደርግ መልካም ነው” ብለዋል።
የጎንደር ከተማ የቤቶች ማስተላለፊያና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ልሳኑ ታምሬ “ቤቶቹ ቅርሶች በመሆናቸው እንደ ቅርስ መጠበቅ ይገባቸው ነበር” ብለዋል። ከከተማ ልማት እና ከማስተር ፕላን አንጻር ደግሞ ፈርሰው የልማት ሥራዎች ሊሰሩባቸው ይገባል የሚሉ መኖራቸውን አንስተው ጥያቄው አወዛጋቢ እየሆነ እንደሚገኝ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል። ይፍረሱ ወይስ ይጠገኑና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይካሄድባቸው የሚለው ጥያቄ ከሚገባው የመንግሥት አካል ጥርት ያለ ምላሽ ባያገኝም የእጨጌ ቤቶችን መረጃዎች አሰባስቦ የመሰነድ ሥራ በቢሯቸው አማካኝነት እንደተሰራና መረጃዎቹ በባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ተሰብስበው በጥናት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።