በሲዳማ ባህል ደስታን፣ ሀዘንን፣ ማግኘትን፣ ማጣትን እና የመሳሰሉትን ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩ የጸጉር አሰራሮች አሉ። አሰራሮቹ እንደ ሴቷ እድሜ እና የጋብቻ ሁኔታ ይለያያሉ። አንዳንዶች ነገሩን ሲገልጹ “በሲዳማ ባህል የሴት ልጅ እድሜ እና የወንድ ልጅ ደሞዝ አይጠየቅም የሚለው የተለምዶ ተረት ተሰብሯል” ይላሉ። የዚህ አባባል ምክንያት የጸጉር አሰራሩ ልጅቷ በየትኛው እድሜ ላይ እንደምትገኝ ስለሚጠቁም ነው። የሲዳማ ሴት በጸጉር አሰራር ዘዬዋ ብቻ ማግባቷን፣ ባሏ እንደሞተባት፣ ለትዳር የደረሰች ወይም ማግባት የምትፈልግ መሆኗን፣ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ህጻን መሆኗን ማወቅ ይቻላል።
በሲዳማ ባህል ከአስራ አምስት በላይ የፀጉር አሰራር እንዳለ ይነገራል። የጸጉር አሰራር ዘዬዎቹ የራሳቸው የሆነ መጠሪያ እና ትርጉም እንዳላቸው የባህሉ አስተምህሮ ያስረዳል። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ስንመለከት “ጉደሮ”፣ “ፋጊኖ”፣ “ቦንኮዬ” በስፋት ከተለመዱት መካከል ይጠቀሳሉ።
“ጉደሮ” ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ የሲዳማ ሴቶች የሚሾረቡት የጸጉር አሰራር ነው። የተወሰነው የጸጉር ክፍል መላጣ፣ ሌላው ሹሩባ ይሆናል። በማጅራት በኩል ያለው የጸጉር ክፍል ደግሞ አጠር ብሎ ይለቀቃል። የማኅበረሰቡን የጸጉር አሰራር የተመለከተ ማንኛውም ሰው ልጅቷ ለአቅመ ሄዋን እንዳልደረሰችና ከ7 እስከ 12 የእድሜ ክልል ውስጥ እንደምትገኝ ማወቅ ይችላሉ።
የወለደች ሴት የምታጌጥበት የፀጉር አሰራር “ቦንኮዬ” የሚል ስያሜ አለው። በ“ቦንኮዬ” ያጌጠች ሴት ያገባች ሙሽራ እና የወለደች ብቻ ናት። አሰራሩም ክብ ነው ይህም እድሜዋም ከ 15 በላይ መሆኑን ያሳያል።
"ፋጊኖ" የመጀመሪያ ባሏ የሞተባት ሴት የምትሰራው ነው። አሰራሩ ደግሞ ልክ እንደሹርባ ወደታች ሶስት ትሰራዋላች ይህም በወፍራሙ ነዉ በዚህ ጊዜ ሀዘን ላይ መሆኗን በጸጉሯ ትገልጻለች።
ጎዳዮ
“ጎዳዮ” አንዲት ሴት ለጋብቻ ዝግጁ እንደሆነች ለመግለጽ የምትሾረበው የጸጉር አሰራር ነው። የጸጉር አሰራሩ ትርጓሜ ልጃገረዶች ለአቅመ ሄዋን ደርሻለሁ የሚሉበት ነው። ለጋብቻ ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳዩበት ነው። በፊተኛው የጭንቅላት ክፍል እንደ ቁንጮ ጉብ ያለ ፀጉር ይተዋል። ከመሃል አናት ጀምሮ ያለውን የጸጉር ክፍል ነጭ እና ቀይ ቀለም ያለው ክር እየተደባለቀበት ወደ ታች ይጎነጎናል።
ወ/ሮ ማርታ ታዲዮስ የሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው። "ጎዳዮ ከቀደምት ከእናቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላዊ የጸጉር አሰራራችን ነው። ጎዳዮን እንድትሰራ የሚፈቀድላት ያላገባች ልጃገረድ ሴት ብቻ ናት። ሴቷ በራሷ ፍላጎት ትሰራዋለች እንጂ የሚያስገድዳት ወይም የሚያዛት ሰው የለም። በአካልም በአእምሮም ለማግባት መድረሷን ለማኅበረሰቡ የምታሳይበት መግባቢያ ነው” ብለውናል።
ጎዳዮን የተሰራች ሴት የምትታይባቸውን ቦታዎች በተመለከተ የነገሩን ወ/ሮ አመለወርቅ ናቸው። በጎዳዮ ያጌጠችው ትዳር ፈላጊ ልጃገረድ ሰዎች በብዛት በተሰበሰቡባቸውን ቦታዎች ትገኛለች። ይህንን የምታደርገውም በጸጉሯ ማስተላለፍ የፈለገችውን ሐሳብ ለሌሎች ሰዎች ለማሳየት ነው። የገበያ ሥፍራዎች፣ ከቤት ውጭ የሚከበሩ የበዓላት ቦታዎች ከመገኛዎቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
ለማግባት የተዘጋጀችው ልጃገረድ “ጎዳዮ”ን ስትሰራ እናቷም ጸጉሯን “ብክቻ” (አፍሮ) ታደርገዋለች። የእናትየውን የጸጉር ሁኔታ የተመለከተ የሲዳማ ሰው የምትድራት ልጅ ያላት እናት መሆኗን ይገነዘባል።
“ጎዳዮ በሲዳማ ማኅበረሰብ ዘንድ ክብር ይሰጠዋል” ያሉት በሲዳማ ክልል ባህልና ቱሪዝም ስፖርት ቢሮ የባህል ታሪክ ቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሌዳሞ ናቸው። “የጸጉር አሰራሩ ከባህላዊ እሴቶቹ መካከል የሚመደቡ ናቸው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የጎዳዮን ይዘት እና ባህላዊ አስተምህሮ ያልጠበቁ አሰራሮች እየተመለከትን ነው። ይህም መስተካከል ይገባዋል። በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ እንደደረሰው ባህላዊ አካሄድ ሴቶች ማንነታቸውን በሚገልጽ መልኩ እየተሰሩ ባህሉን ጠብቀው ለትውልድ እንዲያሻግሩት ሁሉም ሰው ኃላፊነቱን ይወጣ” ብለዋል።