የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ከአበባ እርሻዎች የሚለቀቁ ቆሻሻዎች ይዘታቸውን መቆጣጠርና መገደብ የሚያስችል ‘የኢትዮጵያ የተክል ምርት ዘርፍ ቆሻሻ አወጋገድ ልክ’ የተሰኘ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ አስገዳጅ ረቂቅ ደረጃ ማዘጋጀቱን አዲስ ዘይቤ ሰምታለች።
የሚዘጋጀዉ ደረጃ በዋናነት ሁለት ግቦችን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን የመጀመሪያው በአካባቢና በሌሎች የእርሻ ዘርፎች ጤናማነት ላይ የሚኖረውን ሚና ማረጋገጥ ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ የአበባ ምርቶቹ ሂደታቸው ጤናማ መሆኑን ማመሳከሪያ በማቅረብ፤ አሁን ባለው የአበባ ወጪ ንግድ ላይ እሴትን በመጨመር ተደራሽነቱን እና ተፈላጊነቱን አሳድጎ ሀገራዊ ፋይዳውን ማጉላት መሆኑን የኢንስቲትዩቱ የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ገልጸዋል።
‘የኢትዮጵያ የተክል ምርት ዘርፍ ቆሻሻ አወጋገድ ልክ’ ስርዓት ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ በአበባ እርሻ ምርት የተሰማሩ ማህበራት፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትና ሌሎችም አካላት እየተሳተፉበት ነው ተብሏል።
ስርዓቱ በረቂቅ ደረጃ ዝግጅቶች በመጠናቀቃቸው ለህዝብ ምልከታ ክፍት የተደረገ ሲሆን ከህዝቡ የሚገኙ ግብዓቶች የሰነድ ማሻሻያና ችግሮችን ቀድሞ የመለየት እድል የሚሰጡ በመሆናቸው አስተያየቶች ይታከሉበታል ተብሏል። ከእዚህ በተጨማሪ “የተቋማት በአዲስ መዋቀር የተወሰነ ጫና ሊፈጥር ስለሚችል በብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ቀርቦ ለማጸደቅ ጊዜ ሊወስድ ይችላል” ያሉት ዳይሬክተሩ ሰነዱ እስከሚጸድቅ ድረስ ግን በዘርፉ ላይ ለሙከራ እየተተገበረ ይቆያል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአደገኛ ቆሻሻዎች አወጋገድ በሀገሪቱ ከሚታዩ ችግሮች መካከል ዋነኛው ሆኖ መገኘቱን ተከትሎ የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1090/2010ን አውጃለች። ይሁን እንጂ ክፍተቶቹ አሁንም እየቀጠሉ መሆናቸው አሳሳቢነቱን ከፍ ያደርገዋል። በኢትዮጵያ በካይ እና ጎጂ ቆሻሻዎችን በስፋት ከሚያሰወግዱ ዘርፎች አንዱ የአበባ እርሻ ነው። በኢትዮጵያ ከ120 የሚበልጡ የአበባ እርሻዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ በአበባ እርሻም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቶች ለመዘርጋት የሚያስችሉ ብሔራዊ ልኬት/ ስታንዳርድ አልነበራትም።
የአበባ እርሻ ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያደርገው ዋነኛው ምክንያት በዘርፉ ጥቅም ላይ የሚውሉ የማዳበሪያ ዓይነቶች ለአበባ እርሻ ብቻ ታሳቢ ተደርገው የሚዘጋጁ መሆናቸው ነው ያሉት ሀላፊዉ ማዳበሪያዎቹ ከአፈር ጋር ሲቀላቀሉ በአፈር ሀብት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት አካባቢያዊ ስነ-ምህዳርን ከመጉዳት ባለፈ በስፍራው ላይ ሌሎች ሰብሎችን ማምረት እስከማይቻልበት ደረጃ ድረስ እክል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ በኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የማዳበሪያዎቹ የአሲድ ይዘት ከፍተኛ በመሆኑ በዙሪያው የሚገኙ የሰብል እርሻዎች ላይ ጫና የመፍጠር እድል መኖሩ ነው።
“የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እነዚህን ተግዳሮቶች ታሳቢ በማድረግ በአበባ እርሻዎች ላይ ወጥ የሆነ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትና ልኬት ለመፍጠር ነው እየሰራ የሚገኘው።” ሲሉ አቶ ይልማ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እንደሀገር በከፍተኛ ደረጃ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው እና ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ወሳኝ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ዉጤቶች አንዱ የአበባ እርሻ በመሆኑ በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው መስፈርት ሀገራዊ ጥቅሙን ሳይጎዳ ውጤቱን ለማሳደግ በጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።
የሚዘጋጀው መስፈርትም ቢሆን የአበባ ምርትን የሚገዙ ሀገራት ምርቶችን ከሚያወዳድሩባቸው መስፈርቶች ዋነኛው ጤናማ የምርት ሂደትን መከተላቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ይልማ መንግስቱ ይህም ለዘርፉ ትኩረት እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው ብለዋል።
በቆሻሻ አወጋገድ ወጥ የሆነ ስርዓት አለመኖሩ ለአበባ እርሻ የተገዙ ማዳበሪያዎች ሲተርፉ ከሚመለክታቸው አካላት እውቅና ውጪ ለሌላ የሰብል እርሻዎች የሚውሉበት እና አንዳንዴም ለአርሶ አደሮች እስከማከፋፈል ድረስ ሊሄድ የሚችል በመሆኑ በግብርና ዘርፍ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በማገናዘብ የአበባ እርሻ ዘርፍ ለመነሻነት የተመረጠ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በምርት ሂደቶች ላይ የሚወገድ ቆሻሻ ይዘቱ እስካልታወቀ ድረስ በፍጹም መወገድ የለበትም የሚል ዓለም አቀፍ መርህ አለ።
የአበባ እርሻን ጨምሮ አምራች ዘርፎች ወደስራ ሲገቡ እንደሀገር ትኩረት የሚሰጠው ምርታማነት እና የገብያ ተደራሽነት በመሆናቸው ይህ ነው የሚባል የተደራጀ መረጃ ባለመኖሩ በስርዓት ዝግጅቱ ላይ የተወሰነ ጫና ፈጥሯል ያሉት ዳይሬክተሩ በሁሉም ዘርፎች ያለውን የቆሻሻ ክምችት፣ የጉዳት መጠን እና የአወጋገድ ስርዓት የመለየት ስራም እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት በተለይም የኢንዱስትሪ ቆሻሻ፣ የግብርና ቆሻሻና የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ ያለውን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ለማጠናከር እየሰራ ይገኛል።