ታህሣሥ 1 ፣ 2014

ዝዋይ ሐይቅ አደጋ ላይ ነው

City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮች

ማራኪ ገጽታ ያለው ሐሮ ደምበል በአሁኑ ሰዓት አደጋ ላይ ነው።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ዝዋይ ሐይቅ አደጋ ላይ ነው

የባቱ ሐሮ ደምበል (የዝዋይ ሐይቅ) በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ ሐይቆች መካከል ይመደባል። አነስተኛ የጨው መጠን በውስጡ ቢኖርም ለመጠጥም ሆነ ለመስኖ ተስማሚ ስለመሆኑ ይነገርለታል። ሐይቁ ብርቅዬ በሆኑ አእዋፋቱ፣ በልዩ ልዩ የአሳ ዝርያዎቹ እንዲሁም በጉማሬ መገኛነቱ ይታወቃል። ታሪካዊ የኦርቶዶክስ ሐይማኖት ገዳማት የሚገኙባቸው 5 ደሴቶች (ገሊላ፣ ደብረ ሲና፣ ቱሉ ጉዶ፤ ጠዴቻ እና ፉንዱሮ) መገኛም ነው። ከደሴቶቹ በአንዱ በ11ኛው ክፍለ ዘመን በዘመነ ዮዲት ታቦተ-ጽዮንን በመደበቅ ከጥፋት እንደታደገ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ። ወደ 2 ሚሊየን የሚጠጉ በሐይቁ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችና ወደ 1.9 ሚሊየን የሚጠጉ እንስሳት ህወታቸው በሐይቁ እና በተፋሰሱ ላይ የተመሠረተ እንደሆነም ከባቱ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ማራኪ ገጽታ ያለው ሐሮ ደምበል በአሁኑ ሰዓት አደጋ ላይ ነው። በቅርብ ጊዜያት ይፋ የሆኑ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ36 ሄክተር በላይ የሚሆነው የሐይቁ ክፍል በእምቦጭ አረም ተወሯል። ፍጥነት ያለው የአረሙ መስፋፋት በአቅራቢያው በሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሊገታ የማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በ160 ኪ.ሜ. ከአዳማ ደግሞ 115 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘው ሐዋሳ ሐይቅ 434 ኪ.ሜ.2 ስፋት እና 137 ኪ.ሜ. ርዝመት አለው። የሐይቁ ከፍታ ከውሃ ጠለል በለይ ከ1600ሜ. – 1700ሜ. ነው። የሐይቁ አማካይ ጥልቀት 2.5ሜ. ሲሆን ከፍተኛ ጥልቀት ደግሞ 9ሜ. መሆኑን ስለ ሐይቁ የተፃፉ መዛግብት ያስረዳሉ።

ወጣት ሆለታ ደቤሳ ዓሳ አስጋሪ ነው። በሥራው ከአስር ዓመት በላይ እንደቆየ ነግሮናል “ሌሊት 11:00 ከቤቴ በመውጣት መረቤን በሀይቁ ላይ እጥላለሁ። ከዚህ በፊት ከመቶ እስከ መቶ ሃምሳ ዓሳዎችን ይዤ እመለስ ነበር። አሁን ግን በሐይቁ ላይ ያለው የእንቦጭ አረም እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ስጋትም ጭምር ሆኖብናል። በአረሙ ምክንያት መረቡን የምጥልበት ቦታ አጥተናል። መንጠቆ በመጠቀም ከሃያ አምስት እስከ ሃምሳ ዓሳ እይዛለሁ፤ ነገር ግን በጣም አድካሚና ረዥም ሰዓት የሚወስድ ሥራ ነው”

ለሐይቁ ዋና መጋቢ የሆኑ ሁለት ወንዞች አሉ። እነርሱም መቂ እና ቀታር ናቸው። የመቂ ወንዝ በሰሜን አቅጣጫ፣ ቀታር ደግሞ በሰሜናዊ ምሥራቅ በኩል ወደ ሐይቁ ይቀላቀላሉ። በሌላ በኩል፣ ከዝዋይ ሐይቅ በመነሳት፣ ከሐይቁ ደቡባዊ ምዕራብ ጫፍ ዘልቆ፣ ለ48 ኪ.ሜ. (30 ማይል) በመጓዝ ወደ አቢያታ ሐይቅ የሚፈሰው የቡልቡላ ወንዝ ይገኛል። ሐይቁ በ3 የምስሥራቅ ሸዋ ዞን ወረዳዎች የተከበበ ሲሆን እነኚህ ወረዳዎችም ከሐይቁ በስተምዕራብ በኩል የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ፣ ከሐይቁ በስተደቡብ ተነስቶ እስከ ሐይቁ በስተሰሜን ድረስ የዝዋይ ዱግዳ ወረዳ እና ከሐይቁ በስተሰሜን ምዕራብ በኩል የዱግዳ ቦራ ወረዳ ናቸው።

ወጣት አያልቅበት እና ዘመድኩን በጋራ ሆነው ዓሳ በማስገር ይተዳደራሉ። ወጣቶቹ ሐይቁ እንዲህ በእንቦጭ አረም ከመመታቱ በፊት ለስራችን ምቹ እና የዕለት ጉርሻችንን ከማግኘትም በላይ ቤተሰባችንን አስተዳድረንበታል” ብለዋል፤ አክለውም "በማኅበር ተደራጅተን አምስት ሆነን ነበር የዓሳ ማስገሩን ስራ የምንሰራው አሁን ግማሹ የሐይቁ ክፍል በእንቦጭ አረም ስለተመታ ሁለት ሆነን ለመስራት ተገደናል" ይላሉ። የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በማስጎብኘት ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችም የዓሳ አስጋሪዎችን ስጋት ይጋራሉ።

የፌደራል አከባቢ ጥበቃ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሚንስተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር የእንቦጭ አረሙን ከሀይቁ ላይ ለማስወገድ ያለመ ንቅናቄ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን መምከራቸው ተሰምቷል።

በአከባቢው ላይ የሚገኙ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በአቅራቢያው ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚወጡ ፍሳሾች ለሐይቁ መቆሸሽ መክንያት ከመሆኑም ባሻገር ለእንቦጭ አረም መነሻ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይገምታሉ።

የባቱ ከተማ የአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ አበበ በየነ ሐይቁ ላይ በየጊዜው የእንቦጭ አረሙ እየተስፋፋ ይገኛል።አሁን ላይ በተጠናው ጥናት መሰረት 36 ሄክተር የሚያህለው በእንቦጭ አረም ተወሯል። ይህ ማለት ደግሞ ሐይቁ መጎዳቱን እና ትኩረት እንደሚያስፈልገው የሚያመላክት እንደሆነ አንስተዋል" ኃላፊው አክለውም "እንደ አከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ማኅበረሰቡን በማስተባበር ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

አስተያየት