መጋቢት 17 ፣ 2013

ሥራ የበዛበት ቄራ እና ሥራ ፈቱ ቄራ (የሁለት ቄራዎች ወግ)

ዘገባከተማ

ድሬዳዋ ከተማ መሐል ያለና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረና ከከተማ ርቆ የሚገኝ በቅርብ ተመርቆ ሥራ ያልጀመረ የእርድ ማከናወኛ ማእከላት ይገኛሉ፡፡

ሥራ የበዛበት ቄራ እና ሥራ ፈቱ ቄራ  (የሁለት ቄራዎች ወግ)

ድሬዳዋ የሁለት ቄራዎች ባለቤት ናት፡፡ ከተማ መሐል ያለና ከከተማ ርቆ የሚገኝ፤ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረና በቅርብ ተመርቆ ሥራ ያልጀመረ፤ ነዋሪዎች የሚያማርሩበትና አገልግሎቱን የሚናፍቁት፤… የእርድ ማከናወኛ ማእከላት በድሬዳዋ ይገኛሉ፡፡ የተቃርኖውን ሰበብ ለማጣራት እና ስለ ሁኔታው ለመረዳት ቀበሌ 02 አምርቻለሁ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችን የጤና ባለሙያዎችን እና የሕግ ባለሙያዎችን ሐሳብም ጠይቄአለሁ፡፡ በንባብ ተከተሉኝ፡፡

የነዋሪዎቹ ምሬት


‹‹ሰዒዶ›› ተብሎ የሚጠራው ቀበሌ 02 የሚገኘው ሰፈር በመጥፎ ጠረኑ ተቀበለኝ፡፡ የድሬዳዋ ቄራ አገልግሎት ድርጅት በጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በግል መኖሪያዎች እና በቀበሌ ቤቶች፣ ፖሊስ ጣቢን ጨምሮ በልዩ ልዩ የንግድ ተቋማት ተከቦ አገልግሎቱን ቀጥሏል፡፡ ተፈላጊውን የክርስቲያን እና የሙስሉም እርድ እያከናወነ፣ የማይፈለገውን ጠረን ለከባቢ አየሩ እየበተነ ሥራውን እየሰራ ነው፡፡ ከአካባቢው በፍጥነት መራቅን በሚያስመኘው ሽታ መሀል እንዴት እየኖሩ እንደሆነ የጠየቅኳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መጥፎ ሽታው በሚያይልባቸው ሰዓታት ከሰፈራቸው ርቀው ሌሎች ቦታዎች ላይ ለማሳለፍ እስከመገደድ መድረሳቸውን ነግረውኛል፡፡


ወጣት ኔድዮን አበበ ‹‹ከቀኑ 6ሰዓት አካባቢ ሽታው በጣም ይጠነክራል፡፡ በዚያ ሰዓት ቤት አልገባም፡፡ በጣም ግዴታ ካልሆነብኝ ከሰፈሬ ርቄ ነው የማሳልፈው›› ይላል፡፡ ‹‹የሰባተኛ›› ሰፈር ነዋሪ የሆኑን ወ/ሮ እመቤት በላይም ከበሽታ ጋር እየታገሉ በመኖር ላይ የሚገኙት አማራጭ በማጣት እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ ለአፍንጫ የሚከብደው ጠረን ልጀጆቻቸውን ጨምሮ ራሳቸውንም ለህመም ዳርጓቸዋል፡፡ ‹‹ሽታው ሲጠነክር ጉሮሮን የሚከረክር ስሜት አለው፡፡ እዚህ ሰፈር ጉንፋን የሁሉም ሰው እና የሁልጊዜ በሽታ ነው፡፡ ራስ የማዞር ስሜት አለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምግብ መብላት ሁሉ ያቅተናል›› ሲሉ ምሬታቸውን አካፍለውኛል፡፡


በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው አቶ ሀምዲ ሽኩር ከቄራ የሚወጣው መጥፎ ጠረን በአክባቢው ለማለፍ እንኳን እንደሚያስቸግር አንስቷል፡፡ ‹‹የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል›› የሚለው አቶ ሀምዲ ቄራው ከከተማው በቅርብ ርቀት ወደተገነባው አዲሱ ቄራ ይሸጋገራል ብሎ ቢጠብቅም ‹‹እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉ አስገርሞኛል›› ይላል፡፡


ይህንን የመሰለ ዕለታዊ ችግር እየተጋፈጡ እንደሆነ የሚናገሩት የቀበሌ 02 ቄራ አካባቢ ነዋሪዎችን ወደ በላይ አካላት ሄዶ አቤቱታውን ያሰማ ሰው ይኖር እንደሆነ ጠየኳቸው፡፡ ‹‹በተናጠል የሄደ ካለ እንጂ ተደራጅተን አልጠየቅንም›› የሚለውን አስገራሚ ምላሽ ተቀብዬ ተባባሪዎቼን አመስግኜ ከመጥፎ ጠረኑ ለመራቅ እርምጃዬን አፈጠንኩ፡፡

 

የጤና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

 

ወ/ሮ ኤደን ግርማ ይባላሉ፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ቀበሌ 05 ጤና ጣቢያ በጤና መኮንንነት በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ መጥፎ ጠረን በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዲነግሩን ጠየቅኳቸው፡፡ መልሳቸውን የጀመሩት መጥፎ ጠረን እንዴት ጉዳት ያስከትላል የሚለውን ከማብራራት ነው፡፡

 

‹‹መጥፎ ጠረንን የሚያስከትሉት ኬሚካሎች ናቸው፡፡ ኬሚካሎቹ ጤና ላይ ችግር ያስከትላሉ ለማለት የኬሚካሉ ዐይነት፣ አየር ላይ ያለው የክምችት መጠን፣ የግለሰቡ የተጋላጭነት መጠን፣ የቆይታ ጊዜው መታየት አለባቸው፡፡ መጥፎ ጠረን የጤና ችግር የሚያስከትል መሆኑ ቢታወቅም፤ ሁሉም ሰዎች እኩል ምላሽ (sensitivity) አይኖራቸውም፡፡ አንድ ኬሚካል በሁሉም ሰው ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖ ላያሳድር ይችላል››

 

‹‹እንደየሰዉ ቢለያይም መጥፎ ጠረን የሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች ምን ምን ናቸው?›› የሚለው ቀጣዩ ጥያቄዬ ነበር፡፡

 

‹‹መጥፎ ጠረንን የሚያስከትሉ ኬሚካሎች የዓይን፣ የመተንፈሻ አካላት (የአፍንጫ፣ የጉሮሮ ወይም የሳንባ /irritation) ጉዳት፣ የሳምባ ምች፣ ተስቦ፣ ኮሌራ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የአስም በሽታን ያባብሳል፡፡ የኬሚካል መጠኑ እየጠነከረ ከሄደ ደግሞ የማቃጠል ስሜት ይፈጥራል፡፡ ሳል እና የመተንፈስ ችግር፣ ራስምታት ወይም ማዞር፣ ማቅለሽለሽ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ እንደ ግለሰቡ የተጋላጭነት መጠንም መነጫነጭ፣ የድብርት እና ሌሎች የስነልቦና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል›› በማለት አብራርተውልኛል፡፡ እነዚህ ሊከተሉ የሚችሉ ሕመሞች ሽታውን ብቻ መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡ የቄራ አገልግሎት መስጫው በመኖርያ አቅራቢያ እንደመገኘቱ በአቧራ፣ በእግር እና በሌሎች ቆሻሻው ወደ መንደር የሚገባበት እድል ሰፊ ነው፡፡ የመጠጥ ውሃን እና የቧንቧ ውሃን፣ ሳይበስሉ ለምግብነት የሚቀርቡ ምግቦችን፣… የመበከል እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ይህንን ተያያዥ ጉዳይ እያሰብን ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ከዘረዘርን ጊዜ እና ወረቀት ስለማይበቃን እንተወው፡፡ የነገሩን አደገኛነት ግን ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

የሕግ ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

 

በጥብቅና ሥራ ላይ የተሰማሩት የሕግ ባለሙያው አቶ ኢዩኤል ታሪኩ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡ ‹‹ሕጉ በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም›› የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡

 

‹‹የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ አዋጅ (Environmental impact assessment proclamation) ላይ የትኛውም የልማት ንድፈ-ሀሳብ ሲዘጋጅ መከተል የሚገባውን ሂደት የሚያስቀምጥ ነው፡፡ የልማት እቅዱ አካባቢያዊ፣ ኦኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ ተጽእኖው መተንተን አለበት ይላል፡፡ በጥናት ተመስርቶ ተጽእኖዎቹን በመተንበይ፣ አስቀድሞ በማረም፣ በመገምገም እንዲጸድቅ የውሳኔ ሀሳብ መሰጠት እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ (Environmental pollution control proclamation) ደግሞ የፍጡራንን ደህንነት፣ የተፈጥሮን ስነ ውበት፣ መጠበቅና ማቆየት የሁሉም ተግባርና ኃላፊነት ነው ይላል፡፡ እነዚህን አዋጆችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ማስፈጸም የሚገባው አካል ምንም ዐይነት እርምጃ ሲወስድ በግሌ ዐላየሁም፡፡ ሕብረተሰቡም መብቱን ሲጠይቅ አላጋጠመኝም›› ብለውኛል፡፡

 

የአዲሱ ቄራ ጉዳይ

 

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት የተመረቀው አዲሱ ቄራ 127 ነጥብ 6 ሚልዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ከከተማዋ ወጣ ብሎ በቅርብ ርቀት በሦሰት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የግንባታውን ወጪ የሸፈኑት ULGDP/UIIDP እና የከተማ መስተዳድሩ ናቸው፡፡   ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እንደተገባ የተነገረለት፣ ከተመረቀ 5 ወራት ያለፈው አዲሱ ቄራ አገልግሎት መስጠት ያልጀመረው ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄዬን ይዤ የድሬዳዋ ቄራዎች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ጋር አመራሁ፡፡ አቶ ኢብራሂም፡- ‹‹አሁን እያገለገለ የሚገኘው ቄራ ሲገነባ ቦታው ከከተማ ውጭ ነው በሚል ሐሳብ ነበር፡፡ ከተማዋ እየሰፋች በመምጣቷ አሁን መሀል ሆኗል፡፡ በሰዎች መኖሪያ ተከቧል፡፡ አዲሱ ቄራ ግንባታው ቢጠናቀቅም መሟላት የሚገባቸውን ግብአቶች በሙሉ አላሟላም፡፡ ሥራ መጀመር ያልቻልነው አንዳንድ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

ለማንም ያልጠየቅኩትን ጥያቄ በውስጤ እያጉተመተምኩ ተመለስኩ፡፡ ‹‹ሥራ የማይጀምርበት ደረጃ ላይ ሆኖ ለምን ተመረቀ?›› 

አስተያየት