ታህሣሥ 5 ፣ 2014

አዳማ እና ሐውልቶቿ

City: Adamaባህል ቱሪዝም

የአንድ መቶ ዓመት እድሜ ባለጸጋዋ አዳማም በግለሰቦች እና በመንግሥት የተገነቡ ሐውልቶች ይገኙባታል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

 አዳማ እና ሐውልቶቿ

ሐውልቶች ሰዎች በጽሑፍ መግባባት ካልጀመሩበት ዘመን አንስቶ ግልጋሎት ላይ መዋላቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። በየዘመኑ የሚገነቡት ሀውልቶች የወቅቱን ነዋሪዎች አስተሳሰብ፣ የኪነ-ሕንጻ ደረጃውን እና ታሪክን ይዘክራሉ። የትላንት ትዝታን የዛሬ ቴክኖሎጂን እና የነገ መታሰቢያን በአንድ አጣምረው የያዙ ስለመኖራቸው ባለሙያዎች ያብራራሉ። የአንድ መቶ ዓመት እድሜ ባለጸጋዋ አዳማም በግለሰቦች እና በመንግሥት የተገነቡ ሐውልቶች ይገኙባታል። በከተማዋ አደባባዮች እና በመዝናኛ ሥፍራዎች የሚገኙት ሐውልቶች ከተሰሩበት ጥሬ እቃ፣ ከታሪካዊ እና ተገቢነታቸው፣ ከትርጓሜአቸው፣ የኪነ-ሕንጻን ሕግ በሚያሟላ መልኩ ስለመገንባታቸው በማንሳት ብዙ የሚባልላቸው ናቸው። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሐውልቶቹን መገኛ ስፍራዎች ማስተዋወቅ ላይ ነው።


                                                        የሰማዕታት ኃውልት

በመደበኛ መጠሪያው “የኦሮሞ ሰማዕታት ኃውልት” የሚል ነው። ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ መግቢያ ላይ ከገልማ አባ-ገዳ መሰብሰቢያ አዳራሽ አጠገብ ይገኛል። ከፍ ባለ ኮረብታማ ስፍራ ላይ ግዙፍ ሆኖ የተገነባውና የከተማዋ ምልክት ለመሆን የበቃው ኃውልት በሥፍራው የቆመው በ1995 ዓ.ም. ነው። የኃውልቱ ሙሉ ወጪ የተሸፈነው በኦህዴድ አባላት መዋጮ ነበር። የአዳማ ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ በዳሳ ፉራ "በአሁን ወቅት ይህ የኦሮሞ ሰማዕታት ኃውልት “አዳማ ስምጥ-ሸለቆ እንቁ” ከሚለው መሪ-ቃል ጋር የአዳማ ከተማ ምልክት ሆኖ እንዲያገለግል በኦሮሚያ ከተማ ልማት ቢሮ ጸድቋል” ብለዋል። 

የዳሌ አጥንት ቅርጽ ያለው ኃውልቱ የኦሮሞ ህዝብ ለነጻነቱ ያደረገውን ጽኑ ትግል እንዲሁም የጀግኖቹን ከባድ መስዋዕትነት ለማስታወስ የቆመው ኃውልት መሰብሰቢያ አዳራሽን ጨምሮ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውል መናፈሻ ይገኝበታል።

                                                                              አባ-ገዳ 

ኃውልቱን ከቀረጸው ዘውዱ ቢረዳ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ስለአዳማ የኃውልት ግንባታ እና ስለአባ-ገዳ ኃውልት አሰራር አጫውቶናል።

ቀራጺ ዘውዱ ቢረዳ "በከተማዋ የኃውልት ጥበብ ያለው እድገት እጅግ ዝቅተኛ ነው። ሰዎች ኃውልትን ከሌሎች የቅርጻ ቅርጽ እና ጌጣጌጦች ለይቶ ያለመረዳት ችግር ለእድገቱ መቀርፈፍ ትልቁ ምክንያት ነው" ሲል ይናገራል።

ስለአባ-ገዳ ኃውልት እንዳጫወተን በወቅቱ የነበረው የከተማዋ አስተዳደር ከፍተኛ የሆነ ቱሪስት መስህብ ቦታዎችን የመስራት ፍላጎት ነበረው። በዚህ መነሻነት ነበር የቀድሞ ስራዎቼን ተመልክተው ስራውን የሰራሁት። ከዚያ በኋላ ብዙ ስራዎች ይኖራሉ ብዬ ተስፋ ሰንቄ ነበር ነገር ግን ነገሮች በተቃራኒው አመሩ። ብዙ ቦታ አረንጓዴ ቦታዎች ቢኖሩም ምንም የሃውልት መሰል የጥበብ ስራ አልተሰራባቸውም።

ከስምንት ዓመታት በፊት ኃውልቱ ከሲሚንቶ እና ፌሮ እንደተሰራ የሚናገረው ዘውዱ ቢረዳ “ባለሙያው የበለጠ ውበት ያላቸው ስራዎችን መስራት ቢችልም በሕብረተሰቡ፣ እና በመንግሥት ዘንድም የተሰጠው አጠቃላይ ትኩረት ደካማ መሆኑ ያለንን አቅም አውጥተን እንዳናሳይ ሳንካ ሆኗል” ይላል።

"እንደ ከተማ በየእለቱ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ያሉት መዳረሻ ነው። በመሃል ከተማ መገኘቱ ለዚህ ከፍተኛ  አስተዋጽኦ እንዲኖረው አድርጓል። ከዚህም ትሩፉቱም በሁለት ፈረቃ ተደራጅተው በፎቶ ማንሳት ስራ ላይ የተሰማሩ 50 ወጣቶች ይገኛሉ"  የሚሉት የአዳማ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ባለሙያዋ ወ/ሮ መስታወት ሸዋዬ ናቸው። በተጨማሪ በጽዳት፣ በጫማ ጽዳት እንዲሁም በተለያዩ ቁሳቁሶች ሽያጭ እስከ 70 ለሚደርሱ ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል ፈጥሯል።

                                                               ቶርበን ኦቦ

ቶርበን ኦቦ ሥላሴ ጤና ጣቢያ አካባቢ የሚገኝ ሐውልት ነው። በ2007 ዓ.ም. በአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሲአርጂ ከተባለ ዓለምአቀፍ ድርጅት በተገኘ 1.8 ሚሊየን ብር ተገንብቶ በከተማ አስተዳደሩ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት የሚተዳደር መናፈሻ ነው። በ6 ሔክታር ላይ ያረፈው ፖርኩ በውስጡ መናፈሻ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ ቤተ-መጸሕፍት፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና የካፍቴሪያ አገልግሎት የሚሰጥ ፖርክ ነው። በፖርኩ መሐከል በኦሮሞ ማሕበረሰብ ሴቶች ለወተት ማለቢያነት እና ለመያዣነት በሚያገለግል "ቡቹማ" አምሳያ የተሰራ ኃውልት ይገኛል።

ስለኃውልቱ አሰራር ያነጋገርናቸው የአዳማ ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ባለሞያዋ ወ/ሮ መስታወት ሸዋዬ "ይህ ኃውልት በተለይም ስያሜው ከቱለማ ኦሮሞ ቶርበን ኦቦ ጎሳ ጋር የተገናኘ ቢሆንም አዳማ የሁሉም ማዕከል እንደመሆኗ "ቡችማ" ደግሞ  የአርሲ እና ባሌ አካባቢ ሴቶችን ባህል ያሳያል" ብላናለች።

                                                               ንስሯ

 ከዓመታት በፊት በውስጡ የተለያዩ አነስተኛ ቅርጻ-ቅርጾችን እንደማስጌጫ ይጠቀም የነበረው ኤግል ሬስቶራንት ፈርሶ እንደ አዲስ ኤግል ሆቴል ሆኖ ስራውን ሲቀጥል ኃውልት አቁሟል። 

 ይህንን ኃውልት የቀረጸው ዘውዱ ቢረዳ ኃውልቱ ዋና ዓላማው ከሆቴሉ ስያሜ ጋር የተገናኘ እንደሆነና በባለቤቶቹ ሀሳብ አመንጪነት እንደተሰራ ነግሮናል። ኃውልቱን ለመገንባት ሲሚንቶ እና ፌሮ ጥቅም ላይ ማዋሉን ነግሮናል። 

                                                                ዓለም እና የፈረሶቹ

በቀድሞ ግሎሪ መናፈሻ የአሁኑ ኦሮሞ አርት ኢንስትዩት ውስጥ ይገኛል። ኃውልቱ የሉል እና ዙሪያውን ያሉ ስምንት ፈረሶችን የያዘ የውሃ ፏፏቴ ነው።

የኃውልቱን በጋራ ከነደፉት መሀከል አንዱ እና የቀረጸው ደጀኔ አይፎክሩ "ኃውልቱ ላይ የዓለምን ካርታ የያዙት አምስት እጆች አምስቱን ኦዳዎች የሚያሳዩ ሲሆኑ ስምንቱ ፈረሶች ደግሞ በየአስምንት ዓመት የሚቀያየረውን የገዳ ስርዓትን እርከኖች ያሳያል" ይላል። በስራው ላይ የኤሌክትሪክ ዝርገታ ባለሙያዎች፣ የቧንቧ ሰራተኞች እና ሌሎችም በቅንጅት መሳተፋቸውን ይናገራሉ።

                                                                "የባይተዋሩ" ኃውልት

መብራት ኃይል አብዲ ጉዲና ሕንጻ (በተለምዶ ጨለማ ፎቅ) ላይ ስራው ያልተጠናቀቀ ኃውልት ይገኛል። ይህ ኃውልት ለብዙ ዓመታት ከሰዎች ዕይታ ተሰውሮ በመኖሩ ተረስቷል። የአዳማ ሪፖርተራችን ባደረገው ማጣራት ስለ ኃውልቱ ባለቤት እና አሰራር የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሯል።

አቶ ጀንበሩ ገብሬ በአካባቢው በልብስ ስፌት ስራ ተሰማርተው የሚገኙት አዛውንት ናቸው። "ይህ ሕንጻ ከዚህ ቀደም የአቶ ሰይድ አህመድ ነው። ኃውልቱም ለእርሱ አባት መታሰቢያ እንደተሰራ ሰምቻለው። ማነው የሰራው እንዲሁም ስለእድሜው ላነሳንላቸው ጥያቄ ብዙ እንደቆየ እንጂ በትክክል ጊዜውን እንደማያውቁ ነግረውናል።

ሌላኛው በዚህ ጉዳይ ላይ ያወራነው ሰዓሊ እና ቀራጺ ብሩክ ተሾመ እንደነገረን "በ90 ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው የተሰራው። ኃውልቱን የሰራው ፈለቀ አርምዴ የተባለ ከመጀመሪያዎቹ የአዳማ የአርት ምሩቃን መሀከል የነበረ ሰው ነው። የአራቱ ሀዋሪያትን ኃውልት ለመስራት ከቤ/ክ ጋር ተዋውሎ ቢጀምርም ሳይጨርስ ቀርቷል" ሲል ነግሮናል። ኃውልቱ አሁን ባለበት ቦታ ሊገኝ የቻለው ቀራጺው የሕንጻው ባለቤት ወዳጅ በመሆኑና እዛው ሕንጻ ላይ ይሰራ ስለነበረ ነው ሲል አክሎ አጫውቶናል። በጉዳዩ ላይ አቶ ሰይድ አህመድን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደገነው ጥረት አልተሳካም።

                                                   ወደፊትስ ምን ታቅዷል?

የቱሪዝም ባለሞያዋ መስታወት ሸዋዬ ለወደፊት በከተማዋ ስያሜ ከተሰጣቸው አደባባዮች እንደ ጀነራል ታደሰ ብሩ፣ አርቲስት አሊ ቢራ፣ ሻለቃ ዋሚ ቢራቱ ያሉ አደባባዮች ኃውልቶች እንደሚቆምላቸው ነግረውናል። ኃውልቶቹ በአባ-ገዳ ኃውልት አሰራር መሰረት የአረንጓዴ ቦታ እና መናፈሻ እንደሚኖራቸው ነግረውናል።

አስተያየት