“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እየተባለ ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማ አልፎ የብርሃን ወጋገን የሚታይበት፤ ሰማይ ከጭጋግ ወደ ብሩህ እይታ የሚሸጋገርበት ወቅት እንደሆነና ከቡሄ በዓል በኋላ ጠንከር ያለ ክረምት እንደማይኖር ይበሰራል።
አብዛኛውን ጊዜ ከ 18 ዓመት እድሜ በታች የሆኑ ወንድ ልጆች ከቡሄ በዓል ቀደም ብለው ለጅራፍ የሚሆናቸውን ቁሳቁስ እያዘጋጁ ይጠብቃሉ። ቡሄ ሊደርስ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ በየኮረብታውና በየተራራው እየወጡ ጅራፍ ማጮህ ይጀምራሉ። በዚህ የጅራፍ ድምጽ የቡሄ በዓል መድረሱን ይጠቁማሉ።
የቡሄ (የደብረታቦር) በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ አንዱ ነው። በዓሉ በየዓመቱ ነሃሴ 12 ምሽት ላይ አባቶች በየቤታችው ደጅ ላይ ችቦ በማብራት፣ ወንዶች ልጆች “ሆያ ሆዬ” እያሉ በየቤቱ እየዞሩ በመጨፈር፣ እናቶች ለበዓሉ ያዘጋጁትን ሙልሙል ዳቦ ለልጆች በመስጠት ይጀመራል።
ቡሄ ወይም የደብረ ታቦር በዓል የሚከበረው እየሱስ ክርስቶስ ሶስት ደቀ መዝሙርቱን ይዞ ወደ ተራራ በወጣበት ጊዜ ፊቱ እንደፀሃይ በርቶ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆኖ፣ ከደመና የመጣ ነጎድጓዳ ድምጽ “የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እሱን ስሙት” በማለት የክርስቶስን መለኮትነት የገለጠበትን የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ለመዘከር እንደሆነ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ያታመናል።
በዚህ መሰረት በበዓሉ ዋዜማ የሚለኮሰው ችቦ በተራራው የታየውን ብርሃን ሲያመለክት፤ ልጆች ከከፍታ ቦታ ላይ የሚያጮሁት የጅራፍ ድምጽ ደግሞ ከደመናው የመጣውን(የተሰማውን) ድምጽ እንደሚያመለክት የኃይማኖት አባቶች ያስተምራሉ። ታሪኩ የተፈጸመበትን የታቦር ተራራን ምሳሌ በማድረግ በዓሉ “የደብረ ታቦር በዓል” እየተባለ በቤተ ክርስትያን ሲጠራ፤ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ “የቡሄ በዓል” ይባላል። 'ቡሄ' ማለት የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ገላጣ (ገለጠ) ማለት ነው።
በማግስቱ ሐምሌ 13 ቀን የቡሄ በዓል በጠዋት መከበር ይጀምራል። ከክረምቱ መብረቅ ድምፅ ባልተናነሰ በተከታታይ የሚሰማው የጅራፍ ጩኸት በዓሉን ለማያውቅ ሰው ልብ ያሸብራል፤ ያስደነግጣልም።
ልጆች ጅራፋቸውን እያስጮሁ ይቆዩና የቁርስ ሰዓት ሲደርስ በየቤታቸው የተዘጋጀላቸውን ዳቦ እየገመጡ፤ በቡድን በመሆን “ሆያ ሆዬ” እያሉ ሙልሙል ዳቦ ከጎረቤት መሰብሰብ ይጀምራሉ።
ድምፅህን ሰማና፣
በብሩህ ደመና።
የቡሄው ብርሃን ለኛ በራልን፣
ቡሄ በሉ ሆ
ቡሄ በሉ ሆ ~ ልጆች ሁሉ ሆ፣
የኛማ ጌታ ሆ ~ የአለም ፈጣሪ ሆ፣
የሰላም አምላክ ሆ ~ ትሁት መሀሪ ሆ፣
በደብረታቦር ሆ ~ የተገለፀው ሆ፣
ፊቱ እንደፀሀይ ሆ ~ በርቶ የታየው ሆ፣
ልብሱ እንደ ብርሃን ሆ ~ ያንፀባረቀው ሆ፣...እያሉ የበዓሉን ትርጉም በዜማ ያስረዳሉ።
ፎቶ፡ከማህበራዊ ሚድያ (ቡሄ ሲመጣ ወንድ ልጆች በየሰፈሩ እየዞሩ ሆያ ሆዬ ሲጨፍሩ እና እናቶች ለዚሁ በዓል የሚያዘጋጁት ሙልሙል ዳቦ ይታወሳል)
በቤተክርስትያን ከሚካሄደው መንፈሳዊ ዝማሬ በተጨማሪ በአብዛኛው ጊዜ የሚደመጠው “ሆያ ሆዬ” የሚሉት የልጆች የቡሄ ጨዋታ ግጥሙ እንደቦታውና እንደዘመኑ ቢለያይም፤ የመግቢያና የመሰናበቻ ግጥሞቹ ተመሳሳይ ናቸው።
“መጥተናል በዓመቱ ኧረ እንደምን ሰነበቱ፣
ክፈት በለው በሩን የአባብዬን/የእማምዬን”... በማለት ወላጆች በር እንዲከፍቱላቸው ካደረጉ በኋላ ፊት ለፊታቸው በመቆም ሁሉም ልጆች በአንድ ላይ “ሆ” እያሉ በያዙት ዱላ መሬት እየደበደቡ የሆያ ሆዬ ጨዋታቸውን ያሰማሉ። በዜማቸው መሃል ዳቦ ወይም ገንዘብ እንዲሰጣቸው ቤቱን አባወራና እማወራ በግጥም ያሞካሻሉ፣ ያወድሳሉ።
“እዚያ ማዶ አንድ ጀበና እዚህ ማዶ አንድ ጀበና፣
የኔማ ጋሼ የኢትዮጵያ ጀግና።
እዚህ ማዶ አንድ ጎጆ እዚያ ማዶ አንድ ጎጆ፣
የኔማ እመቤት የኢትዮጵያ ቆንጆ”...እያሉ ያዜማሉ። እንዲህ እያወደሱ ከቆዩ በኋላ ብዙ መቆየታቸውን ለመግለጽ
እና ዳቦ እንዲሰጣቸው ሲያመለክቱ ደግሞ፥
“የኔማ እምዬ የማር ጥንቅሽ፣
ዝናቡ መጣ ወዴት ልሽሽ፣
አብዬ ጋሼ የኔ ጠንበለል፣
ዝናቡ መጣ ወዴት ልጠለል።
በል ስጠኝና ልሂድልህ፣
እንዳሮጌ ጅብ አልጩህብህ።
ኧረ በቃ በቃ ጉሮሯችን ነቃ”.... ካሉ በኋላ ከቤቱ አባወራ ወይም ከቤቱ እማወራ የሚሰጣቸውን ሙልሙል ዳቦ ወይም ገንዘብ ይቀበላሉ።
በመጨረሻም
“አውዳመት ዓመት ድገምና ዓመት፣
የአባብዬን/የእማምዬን ቤት ወርቅ ይፍሰስበት።”
“የወፍ ደግ የወፍ ደግ፣
የወለዱት ይደግ” ...በማለት በልጅ አንደበታቸው መርቀው ይሰናበታሉ።
የቡሄ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች መካከል የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ዋነኛው ነው። በተለይም በአማራ ክልል በጎንደር አካባቢ በስፋት ይከበራል። በዚሁ አካባቢ ልጆች በየሰፈሩ እየዞሩ ሙልሙል ዳቦ ከተቀበሉ በኋላ አንድ የሚጠብቁት ከሩቅ ወይም ከቅርብ የሚመጣ ሌላ ዳቦ አለ። እሱም ከክርስትና አባታቸው ወይም ከክርስትና እናታቸው የሚሰጣቸው የቡሄ ዳቦ ነው።
ፎቶ፡ አቶ ሄኖክ (ከደብረ ታቦር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ) በቡሄ በዓል ለልጆች የሚሰጠው ዳቦ እንዲህ ባለ መልኩ ይጋገራል።
ልጆች የሰበሰቡትን ሙልሙል ዳቦ ይዘው በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ከፍታ ቦታ ወይንም ተራራ ላይ ወጥተው ጅራፋቸውን እያስጮሁ ይቆያሉ። ሲደክማቸም ቁጭ በማለት ዳቧቸውን እየበሉ “የኔ ዳቦ ይጣፍጣል፤ ያንተ አይጣፍጥም” እየተባባሉ ይጨዋወታሉ። ሆዳቸው ሲሞላ ጅራፍ ማስጮሃቸውን ይቀጥላሉ። ልጆች ዳቦ በልተው ሲጠግቡ እና ጅራፍ ማስጮህ ሲደክማቸው ባዘጋጁት ጅራፍ በቡድን በመከፋፈል መገራረፍ ይጀምራሉ።
ታዲያ በግርፊያ መካከል ጸብ የሚባል ነገር የለም። ቡድን በመመስረት በጅራፋቸው መገራረፍ ሲጀምሩ ህግ እና ደንብን ማክበር እንዳለባቸው ይነጋገራሉ። ከህጋቸው መካከል ጅራፉ አይን ላይ ካረፈ አይን ሊያጠፋ ስለሚችል ከአንገት በላይ መጋረፍ ፈጽሞ የተከለከለ መሆኑን ቃል ይገባባሉ።
መገራረፉ የሚፈቀደው ከአንገት በታች ሲሆን በብዛት ወደ እግራቸው በኩል ይገራረፋሉ። እግራቸውን ሲገረፉ እንዳያማቸው መከላከያ የሚሆን ልብስ ወይም የበግ ቆዳ(ለምድ) ያለዚያ ዱላ ነገር ይጠቀማሉ። የመገራረፍ ጨዋታውን ያሸነፈ በተሸናፊዎቹ በኩል ዳቦ ይቀበላል ወይም አሸናፊው ቡድን ከተሸናፊው ዳቦ ይወስዳል።
በመጨረሻም ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው ዳቧቸውን እየገመጡ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ። በዚህ ዓይነት የሰበሰቡት ሙልሙል ዳቦ እስኪያልቅ ድረስ ጅራፋቸውን እያጮሁ እስከ ሳምንት ይቆያሉ።
ፎቶ፡ ከአርትስ ቲቪ የተወሰደ (በጅራፍ መገራረፉ የሚፈቀደው ከአንገት በታች ሲሆን በብዛት ወደ እግራቸው በኩል ይገራረፋሉ)
የቤተክርስቲያን አገልጋይ የአብነት ተማሪዎች በበኩላቸው በየመንደሩ እየዞሩ “ስለ እመብርሃን” በማለት ለዳቦ የሚሆን ዱቄት፣ ለጠላ የሚሆን ድፍድፍ እና የተለያዩ የእህል አዝዕርት ከነዋሪዎች በመሰብሰብ በሚኖሩበት ቤተክርስቲያን ጠላ ጠምቀው፣ ሙልሙል ዳቦ ጋግረው ድግስ ያዘጋጃሉ። በቡሄ እለት ወደ ቤተ ክርስትያን ለሚመጡ ምዕመናን “ስለ ቡሄ” እያሉ ያዘጋጁትን ድግስ ያቀርባሉ።
ድምፅህን ሰማና፣
በብሩህ ደመና።
የቡሄው ብርሃን ለኛ በራልን...እያሉ በዝማሬም በዓሉን ያከብራሉ።
የቡሄ በዓል “የደብረ ታቦር በዓል” ከሚለው ስያሜ ጋር በተያያዘ በደቡብ ጎንደር ዞን በደብረ ታቦር ከተማ እና አካባቢው በድምቀት ይከበራል። “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል መጠሪያ በፌስቲቫል መልክ ላለፉት ጥቂት አመታት ሲከበር ቆይቷል። ይህም የአካባቢው አንዱ የቱሪዝም መስኅብ ሆኖ የቆየ ሲሆን በ 2013 ዓ.ም በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ሳይከበር ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ከቱሪስቶች ይገኝ የነበረው ገቢ መቋረጡን የደብረታቦር ከተማ ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አዳነ ደምሴ ያስረዳሉ።
ፎቶ፡ አቶ ሄኖክ (ከደብረታቦር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ) በቡሄ በዓል ለደብረታቦር ከተማ ተጨማሪ የቱሪዝም መስኅብ እየሆን መጥቷል።
አቶ አዳነ ደምሴ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረጉት ቆይታ አምና በዓሉ ባለመከበሩ ከ600 ሺህ ብር በላይ ማጣታቸውን ተናግረው፤ ዘንድሮው በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ነግረውናል። “በዓሉ ላይ ከ10 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች እንደሚገኙ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል። ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት፤ እንዲሁም በዕለቱ ከአንድ የቴሌቪዥኝ ጣቢያ ጋር በቀጥታ የሚዲያ ሽፋን ለማስተላለፍ መዘጋጀታቸውንም ነግረውናል።
የቡሄ በአል በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች በደምቀት መከበሩ የቀጠለ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በከተሞች በዓሉ ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ በራቀ መልኩ የጨዋታዎቹ ግጥምና ዜማ የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥና ትውፊት እየለቀቀ እንደሆነ ብዙዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።