ኅዳር 28 ፣ 2014

“በሌ ሀዋሳ” ትኩረት የተነፈገው ሰው ሰራሽ ሐይቅ

City: Hawassaቱሪዝም

ሰው ሰራሽ ሀይቁ በራሳቸው የተፈጠሩ ሁለት ደሴቶች አሉት።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

“በሌ ሀዋሳ” ትኩረት የተነፈገው ሰው ሰራሽ ሐይቅ

በሌ ሐዋሳ ስያሜዋውን ያገኘችው 1957 ዓ.ም. እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ከወላይታ ዞን የክንዶ ኮይሻ ወረዳ  ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ደጅአዝማች ገ/ወልድ ስያሜውን የሰጧት በተፈጥሮ የታደለች መሆኗን ተመልክተው ነው። በወላይታ ዞን በግቤ (ኦሞ) ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ተከትሎ የተፈጠረው በሌ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከወላይታ ዞን በምዕራብ በኩል 45 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል። በሀይቁ ዙርያ ከሚገኙ ተራራማ ሥፍራዎች በሚመነጨው ውሃ አማካኝነት በሰው ሰራሽ ሀይቁ የሚጠራቀመው የውሃ መጠን እንደወቅቱ ቢለያይም ከፍታው እስከ 500 ሜትር የሚደርስ ጥልቀት አለው።

ሀይቁ ከኦሞ ወንዝ የሚገቡ የአሳ ዝርያዎችንም ይዟል። ዓይነታቸው በጥናት ያልተረጋገጠውን በቁጥር የበዙ የአሳ ዝርያዎች ጨምሮ አዞ፣ ጉማሬ፣ አእዋፋት የሀይቁ እና የዳርቻው ተፈጥሯዊ ድምቀቶች ናቸው።

ሰው ሰራሽ ሀይቁ በራሳቸው የተፈጠሩ ሁለት ደሴቶች አሉት። ደሴቶቹ በክረምት ወቅት በውሃ የሚዋጡ ሲሆን በበጋ ወራት እስከ 890 ሜትር ከውሃ ሽፋን ውጭ ይሆናሉ።   

ግቤ እና ኦሞ ወንዞች ዋነኛ ገባሮቹ የሆኑለት በሌ ሐዋሳ ዌቢ፣ ዴንጫያ፣ ጎጅብ፣ ሙኒ፣ ኡስሮ እና ሌሎቹ ደግሞ ትንንሽ ገባሮች ስለ መሆናቸው በኦሞ ወንዝ ዙርያ የተጻፉ ጥናታዊ ጽሑፎች ያስረዳሉ። አራት ዓመታት ያስቆጠረው በሌ ሐዋሳ ሀይቅ በቱሪዝም እና በአሳ ሀብት ልማት ዙርያ መስጠት የሚገባውን ግልጋሎት እንዳልሰጠ ብዙዎች ይስማማሉ።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶችን ቀልብ ሊስብ የሚችለው አካባቢ ትኩረት እንደተነፈገው ማሳያ ከሚሆኑ ሰበቦች መካከል በኅብረተሰቡ ዘንድ በሰፊው አለመታወቁ መሆኑን የሚያስቀምጡ በርካቶች ናቸው። ለአዲስ ዘይቤ ሐሳባቸውን ያጋሩ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ስለ ሰው ሰራሽ ሐይቁ ሰምተው እንደማያውቁ ታዝቧል። የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጭምር በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ አሳሳቢነቱን ያጎላዋል።

“ሀይቁ እና የሀይቁ ዙርያ አካባቢ የሰዎችን ቀልብ ይስባል” የሚለው አቶ በረከት ዓለማየሁ በፌደራልም ሆነ በክልል መንግሥታት ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ ተረስቷል ብሎ እንደሚያምን ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

“የሀይቁ ተገቢውን እውቅና አለማግኘት የሁሉም ማኅበረሰብ ጥያቄ ነው” የሚሉት የወላይታ ዞን የክንዶ ኮይሻ ወረዳ  የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፕላኑ ሙልነህ ናቸው። “ከተመሰረተ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው ሀይቁ እስካሁን እውቅና አልተሰጠውም። በመዋቅር ደረጃ እየተሰራበት ቢሆንም ተግባራዊ አለመደረጉ የጎብኚዎችን ቁጥር ቀንሶታል” ብለዋል። በስፍራው ጎብኚዎች ጊዜ የሚያሳልፉበት ማረፊያ አለመኖር፣ የሰው ኃይል እጥረት እና መሰል ሁኔታዎች ደግሞ በተግዳሮትነት ከቀረቡ ምክንያቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ወጣት አያልቅበት ማርቆስ ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በሌ ሐዋሳ ሀይቅን በየሳምንቱ እንደሚጎበኝ ይናገራል። “በሌ ሀዋሳ ደስ የሚል ነፋሻማ አየር ስላለው የመዝናኛ ምርጫዬ ነው። ከተፈጥሯዊ አቀማመጡ ውጭ የጎብኚን ምቾት የሚጠብቁ መስተንግዶዎች ቢኖሩት ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆን ነበር” የሚለው ማርቆስ “ሕዝብ እንዲያውቀው ፕሮሞሽን መሰራት አለበት። እኔ ያወቅኩት በአጋጣሚ ነው። ሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ይህንን የመሰለ ቦታ እንዳለ እንዲያውቁ ማስታወቂያዎች መሰራት አለባቸው” የሚል ሐሳቡን ሰጥቶናል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች በቅርበት ባለመኖራቸው ሊዝናኑ ወደ አካባቢው ከመጡ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች መካከል የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን አዲስ ዘይቤ ከአካባቢው ሰዎች ሰምታለች። የሕይወት አድን ሰራተኞችን ጨምሮ በአካባቢው ውሎ ለማደር የሚሆኑ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ የምግብ እና መጠጥ መስተንግዶ እና ሌሎችም ጎብኚዎችን ለማቆየት የሚረዱ ሥራዎች መከናወን እንደሚገባ ያነጋገርናቸው ጎብኚዎች እና ነዋሪዎች ሐሳብ ነው።

የወላይታ ዞን የክንዶ ኮይሻ ወረዳ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አበበች ስራቾ "በበሌ ሐዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ያለውን እምቅ የሰው ኃይል መጠቀም ቢቻል በቱሪዝሙ ላይ ያሉትን ክፍተቶች በማየት በተፈለገው ልክ ለጎብኚዎች ክፍት ማድረግ ይቻላል። ሌላው በሀይቁ ዙሪያ ማስታወቂያ ባለመሰራቱ ምክንያት በስፋት እንዳይታወቅ ቢሆንም ይህን ለመቅረፍ ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።

“በአዲሱ መዋቅር ምክንያት የወረዳው ኢንቨስትመንት ቢሮ ወደ ዞን ሄዷል። ከዚሁ ጋር የተያያዘ በተለይ ለወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የሆቴሎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች የሚገነቡ ባለሐብቶችን መሳብ ያስፈልጋል። የአሳ ምርቱም የግል ባለሐብቶችን እንደሚስብ መሰራት አለበት” ያሉን የወረዳው ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፕላኑ ናቸው።

የክንዶ ኮይሻ ወረዳ በግብርና ቢሮ ውስጥ የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ነጁ በበኩላቸው በሰው ሰራሽ ሀይቁ ዙሪያ ሊሰሩ ስለታቀዱ ነገሮች ነግረውናል። "ከሀዋሳ ሀይቅ ከአስር ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩቶች በማምጣት ሰባት ዓይነት ዝርያዎች በሌ ሀዋሳ ውስጥ እንዲኖሩ ሆናል። ከዚያ በተጨማሪ በተፈለገው ልክ የዓሳ ምርት ማቅረብ ቢቻል ለሀይቁ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል" ብለዋል። አቶ ነጁ አክለውም በሀይቁ ልማት ኢንቨስተሮችን መሳብ ትልቁ የቤት ስራ መሆኑን አንስተዋል።

አስተያየት