ሚያዝያ 14 ፣ 2011

የአምስት ቀናት ጉብኝት አስመራ

ጉዞምጣኔ ሀብት

ትንሽ ቆየት ብሎ ለአምስት ቀናት ጉብኝት አስመራ ሄጄ ነበር፡፡ አስመራ በበጎ መልኩ ብዙ ሊባልላት ይችላል፡፡ እኔ ላጋራችሁ የወደድኩት ግን ኢኮኖሚያዊ…

የአምስት ቀናት ጉብኝት አስመራ

ትንሽ ቆየት ብሎ ለአምስት ቀናት ጉብኝት አስመራ ሄጄ ነበር፡፡ አስመራ በበጎ መልኩ ብዙ ሊባልላት ይችላል፡፡ እኔ ላጋራችሁ የወደድኩት ግን ኢኮኖሚያዊ ትዝብቴን ነው፡፡ አብረን እንጓዝ …

ምነው ሱቆች ባዶ ሆኑ?

በአስመራ ጉዳናዎች ስዘዋወር ከገረሙኝ ነገሮች አንዱ የሱቆቹ “ግማሽ ባዶ” መሆን ነው፡፡ የሱቆቹ መደርደሪያ መራቆት “ምነው የግብር ትመና ወቅት ደርሶባቸው ይሆን?” ብዬ ራሴን እንድጠይቅ አርጎኛል፡፡ ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ በግብር ትመና ወቅት ሱቆች ሸቀጦቻቸውን እንደሚያሸሹት አስመራም እንደዚያ ከሆነ ብዬ፡፡ ግን አይደለም፤... ከቅርብ አመታት ወዲህ የአስመራ ሱቆች ሁሌም እንዲህ ናቸው፤ ግማሽ ባዶ፡፡ የሱቆቹ መደርደሪያ ባዶ መሆን ብቻ ሳይሆን ገበያተኛም ብዙ አይታይም፡፡ ብዙ ሱቆች ውስጥ ሻጩ ብቻ ነው የሚታየው ……. ምናልባት የሚያዋራው ጎረቤት ወይም ጓደኛ ሊኖር ይችላል፡፡ ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እና የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለገበያው መቀዛቀዝ ዋነኛው ምክንያቶች እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡት ነጥቦች ለገበያው መቀዛቀዝ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ሀ) በኤርትራ የመንግስት ሠራተኛ አማካይ ደሞዝ 2,000 ናቅፋ አካባቢ ቢሆን ነው፡፡ (ሁነኛ ከሚባል ሰው ጠይቄ እንደተረዳሁት)፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ መንግስት ጥቂት ሠው ነው የሚቀጥረው (ወታደርን ሳይጨምር)፡፡ ከመንግስት ውጪ የስራ እድል ሊፈጥር የሚችል የግል ዘርፍ ደግሞ የለም፡፡ በጥቅሉ ሥራ የለም፤ ያለውም ቢሆን ደሞዙ ትንሽ ነው፡፡

ለ) ኤርትራ ውስጥ አንድ ሠው በወር ከ5,000 ናቅፋ በላይ ከባንክ ማውጣት አይችልም፡፡ ገንዘብ ቢኖረውም ማውጣት አይችልም፡፡ አንድ ቤተሰብ እንደ ሠርግ ላሉ ማህበራዊ ድግሶች ከ5,000 ናቅፋ በላይ ማውጣት ቢፈልግ ከመንግስት ልዩ ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡

ሐ) መንግስት እንደ ስኳር፣ ዳቦ፣ የዳቦ ዱቄት የመሳሰሉትን መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች በቀበሌ በኩል ያከፋፍላል፡፡ (እዚህ ላይ ኤርትራ በአመዛኙ ከደርግ ሶሻሊስታዊ ኢትዮጵያ ጋር፤ በከፊል ደግሞ ከአሁኗ ኢትዮጵያ ጋር ትመሳሰላለች፡፡)

መ) በሃገሪቷ ያለው ዝቅተኛ የማምረት አቅም እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ከውጭ ምርቶችን ማስገባት አለመቻል አቅርቦቱን ገድቦታል፡፡

የአውራ ጎዳናዎቹ ጭር ማለት

ከአስመራ እስከ ምፅዋ 110 ኪ.ሜ በመኪና ስጓዝ በተቃራኒው አቅጣጫ ሲመላለሱ ያየኋቸው መኪናዎች ብዛት 30 አይሞላም፡፡ ከዚያ ውስጥ 10 የሚሆኑት በቅርቡ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈቱን ተከትሎ ከኢትዮጵያ የሄዱ መኪናዎች ናቸው፡፡ ከዋና ከተማዋ ወደ ሁለተኛ ከተማ (ያውም የወደብ ከተማ) የሚወስደው መንገድ እንዲህ ጭር ማለት አገሪቷ ምን ያህል እንቅስቃሴ አልባ እንደሆነች ያሳያል፡፡ በ110 ካ.ሜ ርቀት 30 መኪና ማየት ማለት በእያንዳንዱ መኪና መካከል 3.7 ኪ.ሜ ርቀት ይኖራል ማለት ነው፡፡ አንባቢ ይህንን የትራፊክ ፍሰት ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ከሚወስደው መንገድ ካለው እንቅስቃሴ ጋር እንዲያነፃፅር ጋብዣለሁ፡፡

የመከልከል አባዜ

የኤርትራ ኢኮኖሚ መዝገበ ቃል ውስጥ “የለም” እና “አይቻልም” የሚሉት ቃላቶች በደማቁ ተፅፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ቢሆን “የለም” እና “አይቻልም” ይበዛዋል … ኤርትራ ግን በዚህ ረገድ ታስከነዳናለች፡፡ ኤርትራ ውስጥ የሚታይ የግል ሃብት የለም፤ “ነብስ ያለው” ሱፐር ማርኬት የለም፤ ብዙ የግል ህንፃ የለም፤ የስልክ ኢንተርኔት ‘Data Service’ የለም፤ የግል ባንክ የለም፤ ATM የለም … የለም … የለም … የለም፡፡

በአይቻልም በኩል ደግሞ በወር ከ5,000 ናቅፋ በላይ ማውጣት አይቻልም፤ አዲስ ቤት መገንባት አይቻልም፤ መኪና ማስመጣት አይቻልም፤ ት/ቤት መውደቅ አይቻልም …አይቻልም ... አይቻልም…አይቻልም፡፡ በነገሬ ላይ በኤርትራ 11ኛ ክፍል ተማሪዎች ሁሉ ለሁለት አመት ትምህርት ወደ ካምፕ ይገባሉ፡፡ 12ኛ ክፍል ያለፉት ዩኒቨርስቲ/ኮሌጅ ሲገቡ የወደቁት ደግሞ ሳዋ ይገባሉ፡፡ የሚያልፈው ተማሪ በጣም ጥቂት ነው፡፡ እናም ሳዋ መግባት ያልፈለጉ ተማሪዎች 11ኛ ክፍል እንዳይደርሱ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ መውደቅ/መድገም አበዙ፡፡ እናም ሻቢያ ነቄ አለች፤ ህግ አወጣች …“ከንግዲህ ወዲያ ክፍል መድገም ወይም መውደቅ አልቻልም” የሚል፡፡ ዜሮ ከመቶ ያመጣ ተማሪም ቢሆን እንዲወቅድ አይፈቀድለትም፡፡

ሌላኛው በጣም የገረመኝ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ አንድ ሠው ከአንድ መጠጥ ቤት ከሁለት ቢራ በላይ ማዘዝ አይችልም የሚለውን መስማቴ ነው፡፡ ይህ ገደብ በአሁኑ ወቅት የለም፤ እኔም አላየሁም፡፡ ከአመት በፊት ግን ይህ ገደብ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው 4 ቢራ መጠጣት ቢፈልግ ሁለቱን አንድ መጠጥ ቤት ይጨልጥና ቀሪውን ሁለት ቢራ ለመጠጣት ጎረቤት ያለው መጠጥ ቤት እንዲገባ ይገደዳል፡፡ ቢራ የመግዛት ገደብ የተቀመጠው የዜጎችን ደህንነትና ጤንነት ለመጠበቅ ቢሆን ኖሮ “እሰየው!” ያስብል ነበር … ግን አይደለም፡፡ ገደብ ያስፈለገው የቢራ እጥረት ስለነበረ ነው፡፡ በነገሬ ላይ ላይ ኤርትራ ውስጥ አንድ የቢራ አይነት (አስመራ ቢራ) ብቻ የሚመረት ሲሆን እሱም በጥሬ እቃ እጥረት እና ሌሎች ምክንያቶች በተደጋጋሚ የምርት መስተጓጎል ያጋጥም እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡

ገቢ በማንኪያ፤ ወጪ ባካፋ

አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ከውጭ በ Remittance መልክ የሚላከውን ገንዘብ ካልቆጠርን በቀር የኤርትራ ነዋሪዎች ገቢ በጣም ትንሽ ነው አማካይ ደሞዝ ከ2000 ናቅፋ አይበልጥም … እሱም ስራው ሲገኝ ነው፡፡ ከዚህ ትንሽ ደሞዝ እንዲሁም አነስተኛ የንግድ ገቢ አንፃር ወጪዎች ደግሞ ትልቅ ናቸው፡፡

ሁለት ሊትር የታሸገ ውሃ 25 ናቅፋ፤ ቢራ 20 ናቅፋ፤ ቤንዚን በሊትር 30 ናቅፋ፤ የአንድ ፀዳ ያለ ምግብ ቤት አማካይ የአንድ ምግብ ዋጋ 200 ናቅፋ …፡፡ ይህ ወጪ ከገቢያቸው ጋር ሲነፃፀር በጣም ዉድ የሚባል ነው፡፡ አንድ የመንግስት ሠራተኛ በየቀኑ ሦስት የታሸገ ባለሁለት ሊትር ውሃ ልግዛ ቢል ደሞዙ አይበቃውም፤ አንድ አማካይ ደሞዝተኛ 5 ቀን ምሳና ራቱን ሆቴል ቢበላ ምንም ቀሪ ብር አይተርፈውም፤ አንድ አማካይ ደሞዝተኛ መኪና ቢኖረው እንኳ የወር ጠቅላላ ደሞዙ ከ66 ሊትር ነዳጅ በላይ አይገዛም፤ አንድ ደሞዝተኛ 10 ሺ ናቅፋ የሚያወጣ ሶፋ ልግዛ ቢል ሳይበላ ሳይጠጣ 5 ወር ማተራቀም አለበት፡፡

ማስተባበያ፡- ከላይ የተጠቀሱት ወጪዎች ባለፈው ነሐሴ/ መስከረም ላይ የነበረ ነው፡፡ በቅርቡ የምግብ እና ሌሎች ሸቀጦች ዋጋ መቀነሳቸው እየሰማሁ ነው፡፡

የሁለት ደካማ ኢኮኖሚዎች ወግ

ኢትዮጵያ በማያጠያይቅ ሁኔታ ደካማ ኢኮኖሚ ያላት ሃገር ብትሆንም ከኤርትራ ለሚመጣ ሠው ግን “ዱባይ” ልትመስል ትችላለች፡፡ አዲስ አበቤ የዱባይ ሠማይ ጠቀስ ፎቆችን እና ግዙፍ ግብይትን አይቶ ሊገረም እንደሚችለው ሁሉ ኤርትራውያንም በአዲስ አበባ ፎቆች እና የገበያ ግዝፈት ሊደነቁ እንደሚችሉ እገምታለሁ፡፡ በቅርቡ የወጣው ዘ-ኢኮኖሚስት መፅሔት ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከገረማቸው ነገር ዋነኛው ረጃጅም የግል ህንፃዎች እና ATM  ማየታቸውን እንደሆነ ፅፏል፡፡ ምስኪን … በአንድ ወቅት ስልጡን ይባል የነበረው ኤርትራዊ አሁን የግል ሕንፃ እና ATM ሲያይ የሚደነቅ “ሠገጤ” ሆኗል፡፡

ጓደኛዬ እንዳጫወተኝ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ አንድ ኤርትራዊ ውቅሮ አካባቢ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ቀርፆ አስመራ ላሉ ጓደኞቹ ሲያሳይ፣ ኤርትራ ያሉት ጓደኞቹ ባለማመን ስሜት እንዳዩት ነግሮኛል፡፡ ኤርትራውያን የተደመሙት እንደ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አዋሳ ባሉት ከተሞች አይደለም፤ “በትንሿ” ውቅሮ እንጂ፡፡ አዲስ አበበን እርሷት … ለአስመራ “አስማት” ናት፡፡ይህ ኤርትራ እንዴት ባለችበት እንደቆመች ወይም ቁልቁል እንደወረደች ማሳያ ነው፡፡

ሁለት ደካማ ኢኮኖሚዎችን ማነፃፀር ብዙም ትርጉም ላይሰጥ ይችላል፡፡ ግን አነፃፀር ከተባለ ከኢትዮጵያ አንፃር ኤርትራ እጅግ ትንሽ ኢኮኖሚ ናት፡፡ የ CIA Factbook እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ጠቅላላ የኢኮኖሚ መጠን (በ Nominal GDP ሲለካ) 80 ቢልየን ዶላር ሲሆን የኤርትራ GDP ደግሞ 6 ቢልየን ዶላር ነው፡፡ ይህም ማለት የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኦኮኖሚ የኤርትራን 13 እጥፍ ይሆናል፡፡ ንፅፅሩን እንለጥጠው፡፡

  • የኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ (Construction Sector) ብቻ ከኤርትራ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ይበልጣል፡፡ (የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው የግንባታው ዘርፍ አጠቃላይ ገቢ በ2009 ዓ.ም 287 ቢልየን ብር ነበር፡፡)
  • የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመታዊ ገቢ ብቻ የኤርትራን አጠቃላይ ኢኮኖሚ ከግማሽ በላይ ይሆናል፡፡ (የኢትዮጵያ አየር መንገድ አጠቃላይ ገቢ በ2010 ዓ.ም 89 ቢልየን ብር ደርሷል)
  • የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ሀብት (Asset) ከኤርትራ ጠቅላላ ኢኮኖሚ ከ3 እጥፍ በላይ ይሆናል፡፡ (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ሃብት በሰኔ 2010 ዓ.ም ብር 566 ቢልየን ደርሷል፡፡)

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሌላኛው ደካማ ኢኮኖሚ ጋር ሲነፃፀር የገዘፈ ቢመስልም ከጠንካራ ሃገራት ጋር ሲነፃፀር ግን እጅግ ደቂቃ ነው፡፡ ዎልማርት የተባለው ችርችሮ ካምፓኒ አመታዊ ገቢ ከኢትዮጵያ አመታዊ አጠቃላይ ምርት (GDP) ስድስት እጥፍ ይበልጣል፡፡

የኢትዮ-ኤርትራ ወዳጅነት ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች

የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈቱ ለኤርትራዉያን ብዙ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶችን አምጥቷል፡፡ እነዚህን ትሩትቶች ለመጥቀስ ያህል፡-

  1. ቀዳሚው የሠላም ትሩፋት፡- ኤርትራ በቅርቡ በተፈጠረው ሠላም በዋነኛነት የምታተርፈው ነገር ቢኖር ለመከላከያ ስታወጣ የነበረውን ወጪ እና የሰው ሀይል ወደ ልማት በማዞር የምታገኘው ጠቀሜታ ነው፡፡ የኤርትራ ኢኮኖሚ ችግር ዋነኛው መነሻ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚል የፖለቲካ አቅጣጫ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ Trading Economics የተባለ ድረገፅ የኤርትራ የመከላከያ ወጪ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚያዋ (GDP) ያለው ድርሻ እ.ኤ.አ በ1990 (በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት) ወደ 40 በመቶ ተጠግቶ እንደነበር እና ከዚያም ወዲያ ቢሆን የመከላከያ ወጪው ድርሻ ከጠቅላላ ኢኮኖሚው 20 በመቶ እንደሚበልጥ ያሳያል፡፡ይህ ትልቅ ድርሻ ያለው ወጪ ወደ ልማት ሲገባ ኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡
  2. የገበያ መረጋጋት፡- በአንድ ወቅት በአስመራ 11,000 ናቅፋ (ብር 19,800) ደርሶ የነበረው፤ ለብዙ ጊዜያት ደግሞ 4,500 ናቅፋ (8,100) ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ጤፍ በአሁኑ ወቅት ወደ 1,500 ናቅፋ ወይም 2,700 ብር ወርዷል፡፡ በቆይታዬ ከኢትዮጵያ የግንባታ እቃዎችን፤ እህል እና የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎች ጭነው አስመራ የገቡ የንግድ መኪኖችን አይቻለሁ፡፡ ይህም በአስመራ ገበያ አቅርቦትን በመጨመር የገበያውን ዋጋ ለማረጋጋት ያስችላል፡፡
  3. የኢኮኖሚው መንቀሳቀስ፡- የድንበሩ መከፈት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በየቀኑ ሁለት በረራዎችን ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመኪና ወደ ኤርትራ የሚገቡ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ምፅዋ ባረፍኩበት ሆቴል ውስጥ አብዛኛው ደንበኛ ከኢትዮጵያ የሄደ ነበር፡፡ ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ የኤርትራን የቱሪዝም ገቢ በመጠኑም ቢሆን ያሳድገዋል፡፡
  4. ትልቁ ተስፋ፡- አሁን በመጣው ሠላም ለኤርትራ ኢኮኖሚ ትልቅ ተስፋ የሚሆነው ኤርትራ ከወደቦቿ ልታገኝ የምትችለው ጥቅም እንዲሁም ይህን ተከትሎ ሊጠናከር ከሚችለው የንግድ ግንኙነት የምታገኘው ትርፍ ነው፡፡

አስተያየት