ማስታወቂያ

ለ“ሄፕታይተስ” ባህላዊ ሕክምና አማራጭ እየሆነ ይሆን?

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀኅዳር 17 ፣ 2014
City: Gonderጤናማህበራዊ ጉዳዮች
ለ“ሄፕታይተስ” ባህላዊ ሕክምና አማራጭ እየሆነ ይሆን?

በሳይንሳዊ መጠርያው “Hepatitis A” በመባል የሚታወቀው የጉበት በሽታ “የወፍ በሽታ” የሚል ባህላዊ መጠርያ አለው። ህመሙ በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ለበርካቶች ሞት ምክንያት ነው። በገጠራማው የጎንደር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ዘንድ የችግሩ መዳኛ ባሕላዊው ሕክምና ነው የሚል እምነት በስፋት እንደሚስተዋል ባለሙያዎች ይናገራሉ። የህመሙ ተጠቂዎች ብዛት ከከተማ ነዋሪዎች ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ እንደሆነ ቁጥራዊ መረጃዎች ያሳያሉ። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከአንድ ቤተሰብ በትንሹ ሁለት ሰዎች በበሽታው የመጠቃት እድል አላቸው። “በጾታ ረገድ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በበለጠ የሚጠቁ ይመስለኛል” የምትለው ብዙነሽ ኪዳን በሕመሙ ተይዛ ስለማገገሟ ነግራናለች። “በአካባቢዬ የሚገኝ የመንግሥት የጤና ተቋም እንዲሁም የግል ክሊኒክ ሂጄ ተመርምሬአለሁ። መድኃኒት ቢታዘዝልኝም አላሻለኝም። መፍትሄ ሳጣ ወደ ገጠራማው ክፍል ረዥም መንገድ በእግሬ ተጉዤ የባህል መድኃኒት አዋቂዎችን አገኘሁ። በእድሜ የገፉት ባህላዊ መድኃኒት አዋቂም ከሕመሙ ስቃይ ገላገሉኝ” ስትል ለአዲስ ዘይቤ አብራርታለች።

የባህል መድኃኒት አዋቂው የታማሚውን ዐይን አተኩረው ከተመለከቱ በኋላ በስለት የታችኛውን የምላስ ክፍል በመቅደድ አነስተኛ ደም እንዲፈስ ያደርጋሉ። ድርጊታቸው የህመም ስሜቱን ያቀለዋል ሲሉ ታማሚዎች ለአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ተናግረዋል። በባህላዊ መድኃኒት አዋቂው የሚሰጣቸው የተቀመመ መድኃኒትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሕመማቸው እንደፈወሳቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ወ/ት ሜሮን ተስፋዬ በበኩሏ ከጥቂት ወራት በፊት በህመሙ ተይዛ እንደነበር እና በተመሳሳይ መንገድ ፈውስ ማግኘቷን ትናገራለች። በፍጥነት እንድታገግም ያስቻሏትን መድኃኒት አዋቂዎች ያገኘችው ከዚህ በፊት ከተመሳሳይ በሽታ በዳኑ ሰዎች ጥቆማ ነው። ለአገልግሎቱ 120 ብር የሚያስከፍለው ባህላዊ ሐኪሙ የ“ወፍ በሽታ” ምልክት ካልታየው ለሌላ ቀን ቀጠሮ በመስጠት ታካሚዎችን የሚያሰናብት ሲሆን ለምርመራ ምንም ዐይነት ክፍያ እንደማያስከፍል ሰምተናል።  

የህክምና ባለሙያው ዶ/ር ዓባይነው ተሾመ በጎንደር ጤና አጠባበቅ ጣቢያ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። በተለምዶ “የወፍ በሽታ” ስለሚባለው የጉበት ሕመም ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥቶናል።  

““Hepatitis A” በዓይን የሚታዩ እና የማይታዩ ምልክቶች አሉት። በዓይን ከሚታዩት ለውጦች መካከል የቆዳ፣ የሽንት እና የዓይን ቀለም ለውጥ ዋነኛው ነው። ምልክቱ ጉበት ትክክለኛ ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ያሳያል። የቀለም ለውጡ ጉበት መርዛማ ንጥረ ነገር (ቶክሲን) እየለቀቀ መሆኑን ስለሚያሳይ የህክምና ድጋፍ ያሻዋል። የሽንት ቀለምም ጠቆር ያለ ቢጫ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ መሆኑ የኩላሊት ጤና መታወኩን ያሳያል። ታማሚው በተጨማሪም ማቅለሽለሽ እና የድካም ስሜት ያጋጥመዋል”   

በደብረታቦር ሪፈራል ሆስፒታል በማገልገል ላይ የሚገኘው ዶ/ር ምስጋነው ተዘራ በበኩሉ “Hepatitis A ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ሚያጠቃ ህመም ሲሆን ህጻናት ላይ በብዛት ይታያል። ዋነኛ መተላለፊያው በንክኪ ሲሆን፤ በበሽታው የተጠቃ ሰው በሚያስወግዳቸው የሰውነት ፈሳሾቹ ውስጥ ሁሉ ይገኛል። በበሽታው አማጭ ቫይረስ በተበከለ ውሃም ይከሰታል” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአካባቢው የባህል ህክምና አገልገሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው ወ/ሮ ዘውዳለም ድረስ የበሽታውን ምልክቶች በተመለከተ ተመሳሳይ ነገር ነግረውናል። የቀለም ለውጡና አካላዊ ሁኔታውን ተመልክተው የህመሙን ዓይነት ካረጋገጡ በኋላ መድኃኒቱን ወደ መስጠት እንደሚያመሩ ሰምተናል። ወ/ሮ ዘውዳለም የበሽታው አምጪ የሌሊት ወፍ ናት መፍትሔውም ወፏን ፈልጎ መመገብ ነው የሚለውን አይቀበሉትም። “ብዙዎች ወፏን ለማግኘት ይደክማሉ። በዚህ መኃል ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ ህይወታቸው ያልፋል” ይላሉ። መድኃኒቱ የሚቀመምባቸውን የቅጠል ዓይነቶች ለመናገር ፈጽሞ ፈቃደኛ ያልሆኑት ሀኪም ዘውድዓለም የምላስ ስር መብጣትን ጨምሮ በጠላ፣ በማር እና በኑግ የሚሰጥ መድኃኒት እንደ ታካሚዎቻቸው ፍላጎት እንደሚሰጡ ነግረውናል።  

የበሽታውን መዛመት ለመቆጣጠር ንጽህናን መጠበቅ ዋነኛው መከላከያ ስለመሆኑ የሚናገሩት የህክምና ባለሙያዎቹ ከHepatitis A ለማገገም ከሁለት ሳምንት እስከ ሦስት ወራት ሊወስድ እንደሚችል በጥናት አስደግፈው አብራርተዋል። “ህመሙ ከተከሰተ በኋላ የፕሮቲን ይዘት ያላቸውን የምግብ ዓይነቶች ከመመገብ መቆጠብ የጉበትን ሥራ ስለሚቀንስ ቶሎ ለማገገም ይረዳል” የሚሉት ዶ/ር ምስጋናዬ ጣፋጭ ምግቦችን ግን መመገብ ይመከራል ብለዋል።

በህመሙ የተያዙ ሰዎች በዘመናዊው ህክምና ያላገኙትን ፈጣን ፈውስ በባህላዊ መንገድ እያገኙ ስለመሆኑ መናገራቸውን በማንሳት የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ያቀረበላቸውን ጥያቄ ዶ/ር ምስጋናዬ ሲመልሱ “ህጻናትን በወቅቱ ማስከተብ፣ ንጽህናን መጠበቅ ዋነኛ መከላከያዎቹ ናቸው። የባህላዊውን ህክምና ፈውስ ለመናገር ግን ሰፋ ያለ ጥናት ይጠይቃል። ሰዎቹ በርግጥ ድነዋል? ራሱ ትቷቸው ነው ወይስ ህክምናው ረድቷቸው? አብዛኛዎቹ ከዘመናዊው ህክምና በኋላ ስለሚሄዱ የትኛው መድኃኒት ፈወሳቸው? እነዚህ ሁሉ ጥናት እና እርግጠኝነት የሚጠይቁ ናቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

Author: undefined undefined
ጦማሪጌታሁን አስናቀ

Getahun is Addis Zeybe's correspondent in Gondar.