ሰኔ 7 ፣ 2014

በጋሞ ዞን ስለሚገኘዉ "የደም ምንጭ" ምን ያህል ያዉቃሉ?

City: Hawassaቱሪዝም

በማዜ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሚያልፉ ወንዞች ጋር የሚቀላቀለው "የደም ምንጭ" መዳረሻዉ በጋሞ እና በጎፋ መሐከል የሚገኘዉ ኦሞ ወንዝ ነው።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በጋሞ ዞን ስለሚገኘዉ "የደም ምንጭ" ምን ያህል ያዉቃሉ?
Camera Icon

ፎቶ: የጋሞ ጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ

“የደም ምንጭ” በመባል የሚጠራው ውሃ በደቡብ ክልል ጋሞ  ዞን ቁጫ አልፋ ወረዳ ጫባ ሶንባ ቀበሌ ይገኛል። ውሃው ከመሠረቱ ሲፈልቅ ደም ስለሚመስል የአካባቢው ሰዎች ቦታውን "የደም ምንጭ" ብለው ሰይመውታል፡፡ በአካባቢው ማህበረሰብ ቋንቋ በሆነው ጋሞኛ  "ሱታ ፑልቶ" ይባላል።  

ደም በተፈጥሮ ሕይወት ካላቸው እንዲሁም ከቦታ ወደ ቦታ ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት ጋር ብቻ የሚዛመድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በጋሞ ዞን ቁጫ ወረዳ የሚገኘዉ ምንጭ “ደም” ሕይወት ከሌላቸው አለቶች ሥር እንደ ውሃ ሲፈልቅ አሳይቶናል። 

የአካባቢዉ ማህበረሰቦች ለ "ደም ምንጭ" አክብሮት አላቸው። ማንኛውም ግለሰብ በፈለገዉ ልክ ለእርሻና ለእንስሳት እርባታ የሚጠቀመዉ ሳይሆን ብዙ ትውልዶች ሲፈራረቁ ሳይነጥፍ የኖረ የተፈጥሮ ስሪት በመሆኑ ክብር ይሰጠዋል ። 

አለቶችን እየታከከ የሚወርደዉ እና በመጠኑም ቢሆን ሞቃታማ ሆኖ አነስተኛ ኩሬ የሚፈጥረው "የደም ምንጭ" ከኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ 468 ኪ.ሜ. ይርቃል። የአካባቢው መሰረተ ልማት እድገት ዝቅተኛ በመሆኑ ምንጩ አጠገብ ለመድረስ ቢያንስ 24 ኪ.ሜ. ርቀት በእግር አልያም በሞተር ሳይክል መጓዝ ግድ ይላል።  

የጋሞ ጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የሆቴሎች እና ቱሪዝም አገልገሎቶች የብቃት ማረጋገጥ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አስማማው ደረሰ እንደሚናገሩት ውሃው የአካባቢውን ማህበረሰቦች ከተለያዩ የዉስጥ እና የዉጪ በሽታዎች ስለሚፈዉሳቸዉ በእንክብካቤ ይዘዉት ይገኛል። ከዘመናዊ ህክምናው ባልተናነሳ ተፈጥሯዊ ወደሆነዉ “ፈዋሽ” ውሃ ይመጣሉ።

የቡድን መሪው እንዳሉት በምንጩ ዙሪያ የሚኖሩት የማህበረሰብ ክፍሎች  የ"ደም ምንጭ"ን ንፁህ በመሆኑ በመጠጣት እንዲሁም የበሽታ ስሜት ያለበት የሰውነታቸው አካል ላይ በመቀባት እንደሚጠቀሙት ገልጸውልናል ። ይህን ሲያደርጉም ከኩላሊት፣ ከጨጓራ፣ ከልብ ህመም፣ ከቆዳ በሽታ ፣ ከጉልበት መሸማቀቅ እንዲሁም ከሌሎች የተለያዩ በሽታዎች እንደሚፈወሱ ያምናሉ ። 

የጋሞ ዞን በተፈጥሯዊ መስህቦቹ የሚታወቅ ሲሆን ለአብነትም ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ እና በመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ ዉስጥ የሚገኘዉ ወደ 220 የሚጠጋ ኪ.ሜ. ስፋት ያለዉ የማዜ ብሔራዊ ፓርክ ተጠቃሽ ናቸዉ ።

በማዜ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከሚያልፉ ወንዞች ጋር የሚቀላቀለው "የደም ምንጭ" መዳረሻዉ በጋሞ እና በጎፋ መሐከል የሚገኘዉ ኦሞ ወንዝ እንደሆነ ከጋሞ ጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘዉ መረጃ ያሳያል ። 

ከሌሎች የምንጭ አይነቶች በተለየ በምን ምክንያት ከለሩ ሊቀየር እንደቻለ የጠየቅናቸው አቶ አስማማው በዚህ ምንጭ ላይ ጥናት እንዳልተሰራ እና ሁለት መላ ምቶች ግን እንዳሉ ነግረውናል። 

የአካባቢው መሬት ቀይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዉሃዉ ከአለት ስር በሚፈልቅበት ጊዜ የአፈሩን መልክ ይዞ ሊወጣ ይችላል የሚለዉ አንደኛው መላ ምት ነው። በውሃው ላይ የሚገኘው ቀይ አልጌ (ክሎሮፊል) የተባለው ህዋሳት ለውሃው ቀለም የተለየ መሆን አስተዋጽኦ እንዳደረገም ይገመታል።  

ከአለት ስር የሚፈልቀዉ እና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው “የደም ምንጭ” በአጎራባች ዞኖችም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ታዋቂነት የለውም። ውሃውን ለማስተዋወቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች ፣ በመፅሔቶች እና በበራሪ ወረቀቶች ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ እና ነገር ግን  በቂ እንዳልሆነ አቶ አስማማዉ ደረሰ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል ። 

“በዞኑ የተፈጥሮ መስህቦች በሚገኙባቸው ስፍራዎች የሚስተዋለዉ የመሰረተ ልማት ችግር አካባቢውን ማስተዋወቅ እንዳንችል አግዶናል” የሚሉት ኃላፊዉ ለሚመለከታቸዉ አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች አቅረበው ምላሻቸዉን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በጋሞ ዞን የሚገኘዉ የተፈጥሮ ሀብት ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቷም የቱሪዝም ዘርፍ ቀላል የማይባል ድርሻ እንዳለው ተናግረዉ "በተፈጥሮ አጠባበቅ ላይ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ የሚሰሩ የመንግስት አካላት ፣ ግለሰቦች እንዲሁም ድርጅቶች ለዚህ ውሃ ትኩረት ቢሰጡት መልካም ነው" ብለዋል። 

አስተያየት