ወቅታዊው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየጎዳቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ህክምና ይገኝበታል። ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከአስተኛ የህክምና ግብአቶች ጀምሮ አብዛኛዎቹ የህክምና መሳሪያዎችና መድኃኒቶች ሐገር ውስጥ አለመመረታቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዘርፉን ክፉኛ እንዲጎዳው ምክንያት ሆኗል። እንደ አብዛኛዎቹ የህክምና ቁሳቁሶች ሁሉ ለኩላሊት እጥበት ‘ዲያሊሲስ’ የሚውሉ ግብአቶች በውጭ ምንዛሪ ሐገር ውስጥ የሚገቡ ናቸው።
የ4መቶ 48 ሺህ ሰዎች የሚኖሩባት አዳማ ከተማ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት የግል ጤና ተቋማት ይገኙባታል። በከተማዋ የሚገኘው ትልቁ የመንግስት የጤና ተቋም የአዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የስድስት ሚሊዮን ዜጎች የሪፈራል ማዕከል ቢሆንም የኩላሊት እጥበት አገልግሎት መስጠት አልጀመረም።
አዳማ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ጥገና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ያሬድ ኃ/ማርያም በሆስፒታሉ በወር ከ12 እስከ 15 ሰዎች ከኩላሊት ጋር በተገናኘ የቀዶ ህክምና እንደሚካሄድ ነግረውናል። ይህ ቁጥር በተመላላሽ እና በድንገተኛ የሚመጡ ታካሚዎችን እንደማያጠቃልል ገልጸው። በሆስፒታሉ እስከአሁን የዲያሊስስ አገልግሎት አለመጀመሩንም ነግረውናል።
የዲያሊሲስ አገልግሎት ከሚሰጡ የግል ሆስፒታሎች አንዱ አዳማ ጀነራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ነው። የሆስፒታሉ ሜትረን ሜሮን እሸቱ ሆስፒታሉ ስራ ከጀመረበት 2004 ዓ.ም. ጀምሮ የዲያሌሲስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ ትናገራለች። "በአሁን ወቅት 24 ቋሚ ታካሚዎች አሉ። ከእነኚህ ውስጥ 4 ታካሚዎች በሆስፒታሉ እርዳታ በነጻ የሚታከሙ ናቸው” ብላለች።
የህክምና ቁሳቁሶች ዋጋ በኩል ጭማሪ ማሳየቱን ሜሮን ትናገራለች። “ከ3 ወራት በፊት በ9መቶ ብር ይገዙ የነበሩ ግብዓቶች አሁን እስከ 1ሺህ 2መቶ ብር ደርሰዋል" ትላለች። የዋጋ ጭማሪው ታካሚዎች የሚጠቀሟቸው መድኃኒቶችም ላይ እንደሆነ ትናገራለች።
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ከማል ከቢርም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የህክምና ግብዓቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ስለማምጣቱ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል "በአሁን ወቅት ለአንድ ዙር ዲያሊሲስ የግብዓቶች ዋጋ 1 ሺህ 8መቶ ብር በላይ ሆኗል" ይላሉ። በ4 ማሽኖች የሚሰራው ተቋሙ ለአንድ ጊዜ የዲያሊስስ አልግሎት ክፍያ 2ሺህ 2መቶ 50 ብር ያስከፍላል።
በሙሴ ጠቅላላ ሆስፒታል በአጠቃላይ በአሁን ወቅት 21 ቋሚ የዲያሊስስ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች አሉት። የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ዳግም ተቋሙ ከሦስት ወራት በፊት የዲያሊስስ ህክምናን መስጠት መጀመሩን ይናገራሉ። ሆስፒታሉ የዲያሊስስ አገልግሎትን ያለ ትርፍ የወጣበትን ዋጋ ብቻ እንዲመልስ በማድረግ ለመስጠት ቢያስብም በገበያ ላይ ያለው ህክምናውን ለመስጠት የሚውሉ ሪኤጀንቶች ዋጋ መጨመር ውጥናቸው ያሰቡትን ያክል ግብ እንዳይመታ ማድረጉን ነግረውናል።
"አገልግሎቱ የተጀመረው ከሦስት ወራት በፊት ቢሆንም በዚህ ጊዜ ውስጥ የሪኤጀንቶች ዋጋ 25 በመቶ ጭማሪ ዓሳይቷል" የሚሉት ዶ/ር ዳግም አሰፋ ህክምናው ህይወትን የማሰንበት ትግል ነውና ከመንግስትም ትኩረት ያሻዋል” ይላሉ። ከሦስት ወራት በፊት ለአንድ ጊዜ የዲያሊሰስ ስራ የሚሆን ሪኤጀንት እስከ 1ሺህ 4መቶ ብር ድረስ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶ/ር ዳግም አሁን ግን 4መቶ ብር ያህል መጨመሩን ይናገራሉ “ዋጋው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ አገልግሎቱን መስጠት እና የዜጎችን ህይወት መታደግ አይቻልም” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
የዲያሊስስ ህክምና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፋውንዴሽን ለማቋቋምና በሆስፒታሉ በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ነግረውናል። "የዲያሊስስ ህክምና ቀላል ግን ውድ ዋጋ ያለው ነው” የሚሉት ዶ/ር ዳግም ህክምናው በመንግስት ሊደገፍና በጤና ኢንሹራንስ ሊጠቃለል እንደሚገባ መክረዋል።