በአማራ ክልል ከዚህ ቀደም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስር በዳሪክቶሬት ደረጃ በሥራ ላይ የነበረው ቢሮ አሁን “የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዳይ በባለሥልጣን” በሚል ስያሜ በባለሥልጣን ደረጃ ተቋቁሟል። የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ራሱን በባለስልጣን ደረጃ ማዋቀሩ የዘርፉን ችግርች የመቆጣጠር እና የመስፈፀም ስልጣን ሰጥቶታል። ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 280/2014 መሰረት ራሱን ችሎ በባለሥልጣን ደረጃ መቋቋሙ በሐገር አቀፍ ደረጃ ብቸኛ ያደርገዋል። አዲሱ ተቋም በክልሉ ከአሰሪና ሰራተኛ ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የሕግ ማቀፎችን መሰረት አድርጎ የራሱ የሆነ ተግባር እና ኃላፊነት ተደንግጎለት በአዲስ አደረጃት ሥራውን ጀምሯል። ቢሮው በያዝነው ዓመት አጋማሽ ከነበረበት ዳራክቶሬት ደረጃ በባለስልጣን ማደግ የተቋጣጣሪነት ሚና ስለሚኖረው የዘርፉን ችግሮች በመቅረፍ ረገድ ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል ተብሎለታል።
የባለሥልጣኑ ተወካይ ኃላፊ አቶ አጥናፉ በላይ “በክልሉ ለግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ እራሱን የቻለ ዘርፉን የሚመራ ተቋም ተመስርቷል” ብለዋል። አቶ አጥናፉ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ “በክልሉ በሚገኙ የግል ተቋማት፣ የመንግሥት ድርጅቶች፣ የልማት ድርጅቶች፣ የሕብረት ሥራ ማኅበራት ሰላማዊ የስራ ግንኙነት ወይም ምቹ የስራ ሁኔታ ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ ነው”
አሰሪዎችና ሰራተኞች ማኅበራት የማቋቋም መብና ነጻነታቸውን እንዲጠቀሙ ማገዝ ከተግባራቱ መካከል አንዱ የሆነው ተቋሙ “በግል ተቋማት ተቀጥረው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሰራተኞች የሕብረት ድርድሮች እንዲያካሂዱ፣ መብቶችና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ሊያግዝ በሚችል መልኩ ተቋሙ እንደ አዲስ ተደራጅቷል ብለዋል ኃላፊው።
በአማራ ክልል የግሉ ዘርፍ ተቀጣሪ ሰራተኞች በአብዛኛው በኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በእርሻና ኢንቨስትመንት እና በሜጋ ፕሮጀክቶች ተሰማርተው እንደሚገኙ ከክልሉ የስራና ክህሎት ቢሮ መረጃ ያመለክታል። በተጨማሪም የሰራተኞችን መብት ለማስከበር የተቋቋሙ ከ350 በላይ ማኅበራት ይገኛሉ።
በክልሉ በአሠሪና ሠራተኞች መካከል ዘወትር የሥራ ክርክር ከሚያስነሱ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ከጥቅማ-ጥቅም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መሆናቸውን ያነሱት አቶ አጥናፉ የአዲሱ ተቋም በቀዳሚነት ይፈታቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኝበት አንስተዋል። በባለሥልጣን ደረጃ የተቋቋመው አዲሱ ተቋም የማኅበራዊ ምክክር ስርአትና ሌሎች አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም የተቀላጠፈ እልባት እንዲያገኙ ማስቻል ከተቋሙ ተግባራት መካከል ይገኛሉ።
በተጨማሪም አቶ አጥናፉ “የስራ ሁኔታን፣ የሙያ ደህንነትን፣ ጤንነትንና የዘርፉን ሕግ የማስከበና የማስፈፀም ሥርዓት ለመዘርጋት ራሱን የቻለ አካል ማቋቋም ችግሮችን ለመቅረፍ ጅማሮ ነው። ባለስልጣኑ በአዲስ መልክ መደራጀቱ የመንግስት፣ የአሰሪ እና የሰራተኞች ግንኙነት ያጠናክራል። በተጨማሪ ያሉ ችግሮችን በቅርበት በመስራት ለመፍታት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሰራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰመኮ) ባህርዳር ቅርንጫፍ ኃላፊ በግሉ ዘርፍ በክልሉ የሚስተዋሉ ችግርችን በተመለከተ ሲናገሩ “በሕብርት ስምምነት ድርድር ማድረግ በአሰሪው በኩል ፍቃድ ማጣት፣ የወሊድ ፈቃድ መከልከል፣ ለሴቶች እና ወንዶች ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ አለመፈጸም፣ የስራ ስንብት ክፍያ መከልከል፣ አላግባብ የስራ ውል ማቆረጥ፣ ደሞዝ በወቅቱ አለመክፈል፣ የስራ ልምድ እና ሌሎች ማስረጃዎች አለመስጠት፣ የስራ ላይ ለሚፈጠር አዳጋ ኢንሹራንስ አለመኖር፣ የካሳ ክፍያ ችግር እና የመሳሰሉት አሁንም የሚስተዋሉ የዘርፉ ችግሮች ናቸው” ብለዋል።
አቶ መኮንንት ታከለ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ባለስልጣን እንደ አዲስ መቋቋም የዘርፉን ችግሮች ይፈታል የሚል ተስፋ ጥለውበታል። “የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዳይ ብቻ የሚመለከተው ራሱን የቻለ ተቋማዊ አደረጃጀት ያለው የመንግስት ተቆጣጣሪ ተቋም መኖሩ መልካም አጋጣሚ ነው” የሚሉት አቶ መኳንንት ምክንያታቸውን ሲያብራሩ የግሉን ዘርፍ መነቃቃት ተከትሎ የተቀጣሪ የሰው ኃይል ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በእድገቱ ልክ ሊያገለግል የሚችል ተቋም በማስፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ተቋሙ ከሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር እያለ ኢሰማኮ ከማኅበራዊ ዘርፉ ጋር የሚሰራቸው ስራዎች ወደ ሌላ ተቋም በመሄዳቸው እንደ ኮንፌዴሬሽኑ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል ይላሉ።
አቶ ሱለይማን ኢብራሂም የአማራ ክልል አሰሪዎች ፌድሬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ናቸው። “ባለስልጣን መስሪያቤቱ ራሱን ችሎ መደራጀቱ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል” ይላሉ። የግሉ ዘርፍ ሰራተኞች የያዘ በመሆኑ በሰራተኞች እና አሰሪዎች እንዲሁም በመንግስት መካከል ለሚኖረው ግንኙነት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ያምናሉ። በተመሳሳይ እንደ አሰሪዎች ፌድሬሽን ተቋሙ እራሱን ችሎ እንዲደራጅ ጥያቄ ሲቀርብ እንደነበር አቶ ሱለይማን አስታውሰዋል።
በክልሉ መንግስት ራሱን በባለስልጣን ደረጃ አደራጅቷል። የአሰሪ ማኅበራት ስብስብ ደግሞ እራሳቸውን በፌድሬሽን አደራጅተዋል። የሰራተኞች ማህበራት ስብስብ በኮንፌድሬሽን ተደራጅተዋል። የዘርፉ ሦስት ተዋናዮች ራሳቸውን በዚህ መልኩ ማደራጀታቸው የዘርፉን ችግሮች እንደሚፈታ በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበታል።