ሐምሌ 2 ፣ 2013

የኮማሪው “አራዳ”

City: Addis Ababaንግድ

ሁለት ጓደኛሞች ተቀምጠው ሲጨዋወቱ እንደድንገት የመጣ ሃሳብ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አድጎ ኮማሪ መጠጦች የተሰኘ ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር ተቋቋመ። የሁለቱ ጓደኛሞች እቅድ ከመቶ በላይ ሰራተኞች ለተግባራዊነቱ የሚተጉለት ተቋም ሆነ፡፡

Avatar: Ruth Taye
ሩት ታዬ

Ruth is a digital curator and reporter at Addis Zeybe.

የኮማሪው “አራዳ”

ሁለት ጓደኛሞች ከአዲስ አበባ የመዝናኛ ስፍራዎች በአንዱ ተቀምጠው ሲጨዋወቱ ለጊዜ ማሳለፊያ፣ ለሐሳብ መለዋወጫ፣ ለመዝናኛ እና ለአዕምሮ ማፍታቻ ሐሳቦች እየተነሱ ሲጣሉ እንደዋዛ አንድ ሐሳብ ተሰነዘረ፡፡ ይኸውም እነዚህ ጓደኞች ያነሱት ሃሳብ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ አድጎ አዲስ ጣዕም ይዞ ገበያውን የመቀላቀል ዓላማውን እውን ሊያደርግ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ሥራ ጀመረ፡፡ ኮማሪ መጠጦች ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር ተቋቋመ፡፡ የሁለቱ ጓደኛሞች እቅድ ከመቶ በላይ ሰራተኞች ለተግባራዊነቱ የሚተጉለት ተቋም ሆነ፡፡ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም. ላይ ‘አራዳ’ ሲል የሰየመውን አዲስ የታሸገ መጠጥ ለተጠቃሚዎች አስተዋወቀ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ አዲስ ጣዕም ያላቸው የ’አራዳ’ አልኮል መጠጦችን የግብይት ሰንጠረዡ ውስጥ ማስገባት ቻለ፡፡ የኮማሪ መጠጦች ድርጅት በደብረ-ብርሃን ከተማ ዳርቻዎች የፋብሪካውን ግንባታ ማጠናቀቁን በጥር 2013 ዓ.ም ይፋ ሲያደርግ በሰዓት 27,000 ጠርሙስ መጠጦችን የማቀነባበር፣ የማሸግ እና የማምረት አቅም አለኝ ብሏል፡፡

አራዳ የአልኮል መጠኑ 5 በመቶ የሆነ፣ ከስኳር ነጻ መጠጥ ነው፡፡ ለተጠቃሚዎች በአናናስ፣ በአፕል እና በሎሚ የጣዕም አማራጮች ቀርቧል፡፡ አሁን ገበያ ላይ የሚገኙትን የአራዳ ጣዕሞች ለመቀመም እና ለመወሰን እንዲሁም ሦስቱ አማራጮች እንዲመረቱ ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎች መካሄዳቸውንየመረጣ ሂደቶች መታለፋቸውን የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊው አቶ አንተነህ ተስፋዬ ለአዲስ ዘይቤ ይናገራሉ፡፡ በሙከራ ጥናቱ ወቅት የጣዕም አማራጮች የቀረቡላቸው ሰዎች የወደዷቸው ጣዕሞች ተመዝግበው በበርካታ ሰዎች ተወዳጅነትን ያገኙት ሦስቱ ተመርጠው ወደ ምርት ሂደቱ ተገብቷል፡፡ የመጠጥ አምራቹ ተቋም ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሳወቀው ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ለሙከራ የተዘጋጁ 12 ዓይነት ቃና ያላቸው መጠጦች ቀምሰው ደረጃ ሰጥተዋል፡፡ ከሁን የቀረቡት ሦስት ዓይነት ቃና (Flavor) ያላቸው መጠጦች የተመረጡት ይህንን መሰል የግምገማ ደረጃዎችን ካለፉ በኋላ ነው፡፡

የሐሳቡ ጠንሳሽና ፈጣሪ አቶ አንተነህ ተስፋዬ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት 132 ሰራተኞችን ቀጥሮ ወደ ሥራ የገባው ኮማሪ የመጠጥ አምራች ድርጅት በምርት ሂደቱ ላይ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ መሳሪያዎችን የሚገጥሙ ባለሙያዎች ከቻይና የማስመጣት ሂደቱ መዘግየት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎች ቢራዎችን ማስተዋወቅ መከልከሉ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ “ይሁን እንጂ” ይላሉ ኃላፊው፡፡ “ይሁን እንጂ ጠንካራ የሆነ እና በደንብ የታሰበበት የማስታወቅያ እና ምርት የማስተዋወቅ ስራ በመስራታችን ተግዳሮቶቹን አልፈን ውጤታማ መሆን ችለናል።" ብለዋል።

በሌላ በኩል ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኦጁና መኮንን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተቋማችን በወጣት ሠራተኞች የተሞላ ነው ብለዋል፡፡ “ኮማሪ ከአብዛኛው ኩባንያዎች የሚለይ ከሆነ ልዩነቱ የመነጨው በሴት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሚመራው የአስተዳደር ቡድን በወጣት እና ትኩስ ኃይሎች በመሞላቱ ነው፡፡ የትንሹ ሠራተኛችን እድሜ 27 ዓመት ሲሆን ትልቁ 40 ነው፡፡ የኩባንያው አመራር ቡድን ከዓለም ሐገራት ዜጎች የተውጣጡ አባላት አሉት፡፡ ተመሳሳይ ሕልም ያገናኛቸው ኢትዮጵያዊ፣ አሜሪካዊ፣ እንግሊዛዊ፣ እና የደች ዜግነት ያላቸው አሳቢዎች የመሰረቱት ነው፡፡" ብለዋል።

የራሱን ቀለም ይዞ በልዩነት ገበያውን የተቀላቀለው ‘አራዳ’ ከአጠማመቁ እስከ አስተሻሸጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግበታል፡፡ አራዳ የምርቱ ደንበኞች እንደሚሆኑ የሚጠበቀው ከፍተኛ ተጠቃሚዎች (Target Audience) ብሎ ያስቀመጠው ዕድሜአቸው ከ21 እስከ 45 ዓመት የሚገመት ወጣቶችን ነው፡፡ አስተሻሸጉ፣ ቀለሙ፣ የጠርሙሱ ቅርጽ፣ ጣዕሙ እና መአዛው ይህንን ተጠባቂ ደንበኛ ለመማረክ እንዲችል ያለመ ነው፡፡

 የአልኮል መጠጦችን ገበያ፣ የቅርብ ጊዜ እድገቶች እና በመደበኛ ኢንዱስትሪ ስኬት ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ የሚመረምረው የኢትዮጵያ የመጠጥ ኢንዱስትሪ ሪፖርት እንደሚያሳየው ሪፖርቱ ካካተታቸው 16 የመጠጥ ኩባንያዎች መካከል የአልኮል መጠጥ 52% የሚሆነውን የገበያ ድርሻ ይይዛል። በተጨማሪም ኢንዱስትሪውን በመምራት ላይ ከሚገኙት ውስጥ በቢራ ጠመቃ 3 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር ዓመታዊ የማምረት አቅም ያለው ቢጂአይ እና በአገሪቱ ትልቁ የወይን አምራች የሆነው አዋሽ የወይን ማምረቻ ድርጅት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

አስተያየት