ሐምሌ 2 ፣ 2013

ከመዲናዋ ፕላን ጋር ያልተጣጣሙት ግንባታዎች

City: Addis Ababaአካባቢ

በከተማ መሃል ከሚገነቡ ትላልቅ የመኖሪያ ሕንፃዎች አንስቶ እስከ አዳዲስ የቢሮና የንግድ ሕንጻዎች ማደግ እና በመንግሥት የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መስፋፋት፣ በከተማዋ ላይ ለሚታየው ፈጣን የግንባታ መስፋፋት ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ከመዲናዋ ፕላን ጋር  ያልተጣጣሙት ግንባታዎች

በከተማ መሃል ከሚገነቡ ትላልቅ የመኖሪያ ሕንፃዎች አንስቶ እስከ አዳዲስ የቢሮና የንግድ ሕንጻዎች ማደግ እና በመንግሥት የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መስፋፋት፣ በከተማዋ ላይ ለሚታየው ፈጣን የግንባታ መስፋፋት ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ 

በመዲናዋ የሚታዩት ግንባታዎችም የከተማ ፕላን መስፈርትን አሟልቶ ከመሰራት ይልቅ የሕንፃ ቁጥር ለማብዛት እና ገበያ ለማግኘት በይድረስ ይድረስ ተሰርተው ለአገልግሎት የሚውሉት ቁጥራቸው እየጨመረ እንደሚገኝ ብዙዎች የሚስማሙበት ሃሳብ ነው። በዚህም ምክንያት ሕንፃዎች ረጅም ዕድሜን ሳያስቆጥሩ ወይበውና እርጅና ተጭኗቸው ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለይም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች ነገን ከማሰብ ይልቅ ዛሬን አሰቀድመው፤ ለከተማ ውበት ከማላበስ ውበትን የሚያጎድፉ ሁነው ይታያሉ፡፡ የጥራታቸው ጉዳይ አጠያያቂ ከመሆኑ ባለፈ ለነዋሪው ማህበረሰብ ምቾትን የሚነሱም ናቸው፡፡

የከተማ ፕላንና ግንባታ ሆድና ጀርባ ሆነው መሬት ላይ የመዋላቸው ጉዳይን በተመለከተ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ሲናገሩ “የአንድ ከተማ ፕላን የሚሰራው አራት ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ሲሆን የህዝብ ደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶችን ማዕከል ማድረግ፣ ዕድገቱን መምራት ማስቻል እና ለከተማው የሚሰጠው ውበት ላይ ትኩረት ማድረግ ናቸው። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን በተለያየ ጊዜ ለመቅረጽ ቢሞከርም አሁንም መመዘኛዎቹን ማሟላት አልቻለም።” ይላሉ፡፡

“ከከተማችን ህንፃዎች መካከል መመዘኛውን የሚያሟሉት ጥቂቶቹ ናቸው። ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋና ዋናዎቹ የመሬት ጥበትና የሕዝብ ብዛት ናቸው።” የሚሉት ዳይሬክተሩ “በኛ በኩል እነዚህን ቁልፍ ችግሮች ለመቅረፍ ብዙ የመፍትሔ አማራጮችን ይዘን እየተንቀሳቀስን ነው። በዚህም ማንኛውም ግንባታ በሚከናወንበት ጊዜ የከተማዋን ውበት ታሳቢ በማድረግና የሕዝብ መጨናነቅን በሚቀንስ መልኩ እንዲተገበር ይፈለጋል።” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።

“አዲስ አበባ ባለባት የሕዝብ ብዛትና የመሬት ጥበት ምክንያት ፕሮ-አክቲቭ ወይም በአማርኛው አጠራር አማታሪ የሚባለውን ፕላን መተግበር ተስኗት ይታያል። አሁን ያለው የከተማ ፕላን ችግሮች ከተፈጠሩና ከተባባሱ በኋላ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረግ እንቅስቃሴ የሩጫ ዓይነት ነው የሚሆነው። እንዲህ ዓይነቱ የከተማ ፕላን ደግሞ ሪ-አክቲቭ ፕላን ይባላል።” የሚሉት ደግሞ የኮንስትራክሽን/ግንባታ አማካሪ የሆኑት አቶ መሳይ ደጉአለም ናቸው፡፡ 

ባለሙያው አሁን ላይ በአዲስ አበባ በግንባታዎች ጥራት ማነስ ሳቢያ የሚስተዋለውን የከተማዋን የውበት ችግር ለመፍታት የመሬት አጠቃቀም አማራጮችን ያቀርባሉ፡፡ ከመሬት ስር ውስጥ ለውስጥ፣ ገጸ መሬት ላይ ያለ  እና  ከመሬት በላይ አየር ላይ ያለን ቦታ መጠቀም ናቸው። የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው እየበዛ ይሄዳል በማለት የወደፊቱን ታሳቢ አድርጎ መስራት እና ቀድሞ ማልማት እንደሚያስፈልግ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

የኮንስትራክሽን አማካሪው “ሌላኛው አማራጭ ተቀናጅቶ የሚሰራ ወይም ኢንተግሬትድ ወይም የተቀናጀ  ተብሎ የሚጠራው ፕላን ሲሆን ይህም ከተቀናጀ ፕላን ጎን ለጎን ሁሉንም እኩል ለማስተናገድ ሰፊ ዕድል ይሰጣል።” በማለት አብራርተው እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች የከተሞቻቸውን ፕላንና ፅዳት ያስጠበቁት እንዲህ ዓይነቶቹን ውጤታማ የከተማ ልማት ስትራቴጂዎች በመተግበር መሆኑን ያስረዳሉ። 

ከውበት ጋር ያልተቆራኘው የቤቶች ግንባታ

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መስከረም ዘውዴ በበኩላቸው “አነዚህ ሪል ስቴቶች በብዛት ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የአዲስ አበባን ውበት ታሳቢ ያላደረጉ  ናቸው ሲሉ ይተቻሉ። ነገር ግን  እየተሰራ የሚገኘው ችግሮችን የመቅረፊያ መፍትሄ ከሌሎች እህት ከተሞች ጋር እርስ በእርስ በመመካከርና በመቀናጀት ስለሚሰራ ከአዲስ አበባም አልፎ በመላው ኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ ማሳየት ይችላል።” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

“ከከተማ ውበት አኳያ መንግስት የሚሰራቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውጤታማ ናቸው ማለት ይቻላል ወይ?” ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄም “በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት ኮንዶሚኒየም ቤቶች በኩል የሚታዩ ጥቂት የውበት ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አይካድም፤ ይህ የመጣው ደግሞ በዋናነት ከአረጁና ለመኖሪያ ምቹ ካልሆኑ አካባቢዎች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ከዚህ ቀደም ከተማዋ የልማት ዕቅድን መሰረት በማድረግ ወይም በማስተር ፕላን ላይ የተመሰረተ ልማት ማድረግ ላይ ድክመት ስለነበረባት ነው፡፡ ይህም ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መምጣቱ በአዳዲሶች ግንባታዎች እየታየ ነው።” ሲሉ መልሰዋል።

“በአዲስ አበባ የመጨረሻው የዲዛይን ለውጥ የተደረገው በዚህ በቤቶች ልማት ፕሮጀክት ቢሮ ነው፡፡ ይህን ሥራ የማደራጀት ሂደት ደግሞ በከተማ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ቅርንጫፎች በኩል ይሰራል፡፡ ከዚህ አኳያ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ቢሮ በተመረጡት የቤቶች ልማት አካባቢዎች ለሚሰሩ ህንጻዎች ዲዛይን እንዲቀርብ ውድድር አውጥቶ የውድድሩ አሸናፊዎች ዲዛይኑን እንዲሰሩ ይደረግና የተመረጡት ዲዛይኖች የግል አማካሪዎችና የመንግሥት አርክቴክቶች ላሉበት የገምጋሚ ቡድን ቀርቦ ማስተካከያ ተደርጎበት እንዲሰራ ይደረጋል” በማለት አብራርተዋል።

ሃላፊዋ “በጥራት እና በውበት መካከል ያለው ልዩነት ግን ግልጽ ሊሆን ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል። “የመኖርያ ቤቶቹ የግንባታ ጥራትም በፊትም አሁንም በየሳይቶች በመገኘት ፍተሻ በሚያደርጉ አማካሪዎች ተረጋግጦ ነው ሚሰራው” ብለዋል።

የሪል ስቴት ግንባታዎች

በሪል ስቴቶች በኩል የሚገነቡ ቤቶች ከጥራትና ዉበት አንፃር እንዴት ይታያሉ ስንል ላነሳነው ጥያቄ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህንፃ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ጥበቡ አሰፋ የሚከተለውን ሙያዊ ምላሽ ሰጥተዋል፣ “የሪል ስቴቶች ፕላን የህዝብን ደህንነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎቶቹን ማዕከል አድርጎ መሰራት አለበት ከመባሉ አንፃር አዲስ አበባ የተዋጣላት ናት ማለት አይቻልም። አሁን ላይ ከከተማዋ ውበት አኳያ ተጨንቀው በመስራት ላይ ያሉ አንዳንድ ሪል ስቴቶች ቢኖሩም በብዙዎቹ የተዳከመ ግንባታ አንፃር አዲስ አበባ በሪል ስቴቶች በኩል ውበቷ ተጠብቆላታል ለማለት አያስደፍርም። ሕዝቡ በከተማ ውስጥ ሞልቶ ተትረፍርፎ እየፈሰሰ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በከተማዋ ውበት፣ የንግድ፣ የጽዳት አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች አሉ። የነዚህ ሪልስቴቶች ፕላን ለነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ አይደለም። ምክንያቱም አዲስ አበባ ላይ ያለው ሁኔታ ሲታይ ጥቅም ላይ እየዋለ ካለው ቦታ አብዛኛው በፕላኗ መሰረት የተደለደለ አይደለም።” ሲሉ አብራርተዋል።

‹‹አሁንም መከላከልና መፍታት የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ›› ሲሉም ያለመርፈዱን ምክር ደጋግመው ይገልፃሉ። እንደ ሙያዊ ምክራቸው ለከተማዋ ውበት የሚያግዙን ዘመናዊ የግንባታ መንገድን መከተል እንደሆነ ያሳውቃሉ። 

“ግንባታዎቻችንን የከተማዋን ውበት እና የነዋሪውን ጤንነት ታሳቢ እንዲያድርጉ እንፈልጋለን፡፡”  የሚለው ደግሞ የጃምቦ ሪል እስቴት ግብይት እና ሽያጭ ክፍል ሀላፊ የሆኑት አቶ መርሻዬ ሀይሉ ናቸው።  “ከተማዎች የፊት ለፊት እንቅስቃሴያቸው ሞቅ ደመቅ ያለና ቀልብ ሳቢ መሆን እንዳለበት ስለምናምን በከተማ ፕላን ዕቅድ መሰረት ለንግድ ግንባር ቦታዎች ላይ ስንገነባ ለተለያዩ ቢሮዎች እና ለመኖሪያ የሚሆኑ ህንፃዎችን ደግሞ ገባ አርጎ በመገንባት የመጀመርያውን ደረጃ እናልፋለን። ከዛ በተጨማሪ መስታወቶቹ ለአይን ማይጎዱ እና የግንባታው መሰረት እና የህንጻው ዲዛይን ውበቱ አስተማማኝ እንዲሆን ማድረግ አንዱ ስራችን ነው።” ሲሉም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አዲስ ዘይቤ ከከተማ ውበት አኳያ የሪል ስቴታችሁ አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው ብላ የጠየቀቻቸው የኖህ ሪል ስቴት የኮንስትራክሽን አስተዳደር ምክትል ሃላፊ አቶ ህላዌ ሰውነት ሲመልሱ “አሁን ባለንበት ሁኔታ ከፍተኛ የቦታ ጥበትና የሕዝብ ብዛት ጎልቶ በሚስተዋልበት አዲስ አበባ የሪል ስቴቶች የውበት ችግር የመጣው በከተማዋ ፕላን ችግር ምክንያት እንጂ ከግንባታ ሙያተኛው ብቃት ማነስ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። በከተማዋ ውስጥ የቦታ ጥበት ብቻ ሳይሆን ብክነትም እንዳለ ግልፅ ነው።” ይላሉ

እንደሃላፊው ገለፃ የቦታ ጥበትን ከሕዝብ ብዛት እና ውበት ጋር ለማስታረቅ ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ። በአጠቃላይ አዲስ አበባ ከኮንስትራክሽን ሙያ አንፃር ሲያስተዋውሏት ከከተማ ፕላን ጋር አብሮ የማይሄድና የማጣጣም ግንባታዎች፣ መንገዶች፣ መንገድ መካች ልሙጥ ግድግዳዎች ለነዋሪዎቿ መስጠት የሚገባቸውን ጥቅም አለመስጠት፣ የትላልቅ መሥሪያ ቤትና ህንፃ አጥሮች የማህበረሰቡን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍላጎትና የከተማዋን ዘላቂ ዕድገት ታሳቢ አድርገው አለመታነፅን እንደችግር ይጠቀሳሉ።

አስተያየት