ሐምሌ 5 ፣ 2013

የድሬዳዋ ልዩ መታወቂያ የሆኑት የመንገድ ላይ ምግቦች

City: Dire Dawaአካባቢማህበራዊ ጉዳዮች

ትኩስ የመንገድ ላይ ፈጣን ምግቦች ድሬዳዋ ከተማን ልዩ ከሚያደርጓት ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን ለድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎችም የተለመደ የአኗኗር ዘዬ ነው።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬዳዋ ልዩ መታወቂያ የሆኑት የመንገድ ላይ ምግቦች

ድሬዳዋ ከተማን ለመጀመርያ ጊዜ የረገጡ ሰዎች ከሚገረሙባቸው የአኗኗር ዘዬዎች መካከል የመንገድ ላይ ፈጣን ምግቦች ይገኙበታል፡፡ መደበኛ ባልሆነው የንግድ እንቅስቀሴ ውስጥ በመደበኛነት የሚሸጠው የበሰለ ምግብ የድሬዳዋን ሰው “ጣጣ የለውም” ካስባሉ ሁነቶች ውስጥ የሚመድቡትም አልጠፉም፡፡ እንደ የድንች ጥብስ (ቺብስ) በተለይ በጋራ መኖርያ ቤቶች አካባቢ እና የጀበና ቡና ያሉትን ካልሆነ በቀር አዲስ አበባን በመሰሉ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች እምብዛም የማይዘወተረው ፈጣን የመንገድ ላይ ምግብ በድሬዳዋ ብዙም የማይገርም የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስኳር ድንችና ድንች (በቅቅል)፣ በቆሎ (በጥብስ እና በቅቅል) የክረምቱን መግባት ተከትለው ለገበያ የሚቀርቡ ትኩስ የመንገድ ላይ የበሰሉ ምግቦች ቢሆኑም የድሬዳዋን ያህል ከዓመት እስከ ዓመት የሚዘወተሩ አይደሉም፡፡ 

‘ረሀ’ ነው የሚባልለት የድሬ ሰው ግን ትልቅ፣ ትንሽ፣ ሴት፣ ወንድ ሳይል የመንገድ ዳር የበሰሉ ምግቦችን ይመገባል፡፡ በተለይ ከቁርስ እና ከምሳ እንዲሁም ከእራት እና ከምሳ መካከል ላይ ባሉት ሰዓታት ሰዎች ሰብሰብ ብለው ለመጫወት፣ ከወዳጅ ጓደኛ ጋር ለመናፈስ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ደንበኞቻቸውን በቤታቸው ውስጥ ማስተናገድ የሚችሉት ቤቶችም የደንበኞቻቸው ምርጫ ውጭ ሆኖ መስተናገድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

ቆየት ላለ ጊዜ በተደጋጋሚ የሚተገበረው የነዋሪዎቿ ልማድ ድርጊቱን የከተማዋ ባህል ሆኖ እንዲቆጠር አስገድዷል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም የመኖርያ ሰፈሮች ማለት በሚቻል ሁኔታ ፈጣን የመንገድ ላይ ምግቦችን ይሸጣሉ፡፡

ከምሳ በስተቀር በቁርስና መክሰስ ወይም በከተማዋ ልጆች አጠራር “ካትረን” ሰዓት ጀምሮ በእራት ሰዓት ከሚቀርቡ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ፉል፣ ድንች፣ ፍርፍር፣ መለዋ፣ ባላንቺ (ፉል በድንች)፣ ሙዝ በኩርኩባ (ጥቅል ጎመን)፣ ፈጢራ፣ ፍርፍር በድንች፣ ድንች በሰላጣ፣ ሽሞ (ቦሎቄ) በድንች፣ አቦካዶ፣ ቱና ይገኙበታል፡፡ ሚጥሚጣና ቃሪያ ለማጣፈጫም ለማባያም ሲያገለግሉ ሻይ ቡናን ጨምሮ ውሃና ለስላሳ መጠጦችም ይቀርባሉ፡፡

አነስተኛ ሸራ ለብሰው በእንጨት ወይም በሸምበቆ ወይም በቀርከሃ የሚወጠሩት የምግብ ማብሰያዎቹ በእግረኛ መተላለፊያ ጎዳናዎች ወይም ወደ መንደሮች በሚያስገቡ ተገንጣይ መንገዶች አቅራቢያ ይገኛሉ፡፡ አንዱ ከአንዱ ብዙም ሳይርቅ በውሱን ኪሎሜትሮች ርቀት አለፍ አለፍ ብለው ደንበኞቻውን ሲያስተናግዱ ተመጋቢን የሚያስቀምጡበት ወንበር እንጂ ደንበኛን ከጸሐይ እና ንፋስ የሚያስጥሉበት ከለላ አይኖራቸውም፡፡ በባዶ የቀለም ቆርቆሮ፣ በዱቄት ወተት ቆርቆሮ፣ በኩርሲ፣ በፕላስቲክ ወንበር፣ በድንጋይ እና ብሎኬቶች ላይ ተቀምጦ የቁርስ እና የእራት ማዳረሻን እንዲሁም ቁርስ እና እራትን ከወዳጅ ጎረቤት ጋር መቋደስ ይዘወተራል፡፡

ፋብሪካዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የቀላል እና ፈጣን ምግብ አቅራቢዎቹ ቁጥር ይጨምራል፡፡ ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ በውስጣቸው በርካታ ቢሮዎች የሚገኙባቸው እንደ “ፋይናንስ” ወይም “ክንቲባ ሕንጻ” ዐይነት ስፍራዎች የመንገድ ላይ ትኩስ ቁርስ አቅራቢዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ወደ ቢሮዎቹ ጉዳይ ሊያስፈጽሙ የሚያመሩትን ሰዎች እና የተቋሙን ሠራተኞች ታሳቢ አድርገው የሚከፈቱት የዚህ አካባቢ ምግብ ቤቶች ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ የተጠቃሚውን መብዛት ያስተዋሉ ታዛቢዎች በከተማዋ ሆቴል ከመክፈት መሰል አነስተኛ የምግብ ማቅረቢያዎችን መክፈት አዋጭነት አለው እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ለእዚህ እንደማሳያ የሚያነሱት “እቴኑ”ን ነው፡፡ የ“እቴኑ”ን ትኩስ የመንገድ ላይ ምግብ መሸጫ የሚጎራበት አንድ ሆቴል አለ፡፡ በባህላዊ ወንበሮች ያኔጠው፣ በሜኑው ላይ ምርጥ የሚባሉ ምግቦችን ያካተተው ቤት ሰው ሳይኖርበት የእቴኑ ወንበር እስኪለቀቅ ቆም ብለው የሚጠባበቁ ወይም በቁማቸው ያዘዙትን ምግብ የሚመገቡ ሰዎችን መመልከት የዚያ አካባቢ ሰዎች እለታዊ አጋጣሚ ነው፡፡ 

በቀላል ነገሮች አዘውታሪነታቸው የሚታወቁት የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይ የቁርስ ሰዓታት ምግባቸውን በተዘጋጀላቸው ወንበር ላይ ተቀምጠው ከመመገብ ይልቅ ፈንጠር ፈንጠር ብለው በመቆም በቡድን እና በተናጠል፣ በእጃቸው እና በማንኪያ፣ በሚጥሚጣና በቃሪያ ሲመገቡ ይስተዋላል፡፡ የቁርሱ ሰዓት ሁሉም ወደ ጉዳዩ ለመሮጥ የሚጣደፍበት በመሆኑ ችኮላ የሚበዛው ሲሆን የምሽቱ ግን ተመግቦ ከመለያየት በዘለለ በሳቅ ጨዋታ ይታጀባል፡፡ የቁርስ ሰዓት ከማለዳው 12፡30 አካባቢ የሚጀምር ሲሆን የምሽቱ ከ“ካትረን” (መክሰስ) እስከ እራት ማለትም ከሥራ መውጫ 11፡00 እስከ ምሽት 4፡00 ይቆያል፡፡

 በድሬዳዋ ጎዳናዎች በእግረ መንገዳችን እንደልብ የምናገኛቸው ትኩስ ምግቦች ዋጋቸው ተመጣጣኝ ስለመሆኑ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ፡፡ መኖርያዋ “ነምበር ዋን” አካባቢ የሆነ አስተያየት ሰጪአችን ወ/ት መአዛ ንጉሤ ትባላለች፡፡ የምትሰራው የወንዶች የውበት ሳሎን ውስጥ ነው፡፡ ቁርሷን አብስላ ለመብላት ጊዜ በሚያጥራት ወቅት በአንዱ የሰፈሯ ጥግ ወይም በስራ ቦታዋ አካባቢ ከሚገኝ ቁርስ ቤት ጎራ ትላለች፡፡ እሷ እና ባልደረቦቿ የስራ ጥድፊያው ጋብ ሲልላቸው አቅራቢያቸው ወደሚገኘው የ“እመቤት” ቁርስ ቤት ጎራ በማለት ትኩስ ቁርሳቸውን ይመገባሉ፡፡ መአዛ “ቀለል ባለ ዋጋ እንዲህ ዓይነት ምግብ ማግኘት ጥሩ ነው፡፡ ምግቡ ጣፋጭ ነው፡፡ ትኩስና ጤነኛ ነው” የሚል ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሚያውቋቸው አገልግሎት ሰጪዎች ውስጥ “አክስቴ” አንዷ ነች፡፡ መገኛዋ ካራማራ አካባቢ ነው፡፡ ኬር ስኩዌር በኩል ወደ ቀኝ ሲታጠፉ የምትገኘው የትኩስ ምግብ አቅራቢ በ“ድንች በሰላጣ” ታዋቂ ነች፡፡

የጾም እና የፍስክ  አማራጮች የሚሰናዳው ድንች በሰላጣ በብዙ ዐይነት መንገድ ይዘጋጃል፡፡ የፍስኩ እንደተጠቃሚው ፍላጎት እንቁላል፣ ቱና ይጨመርበታል፡፡ የጾሙ ደግሞ አቦካዶ፣ ኩርኩባና (ጥቅል ጎመን)፣ ሙዝ ይጨመሩበታል፡፡

ከ“አክስቴ” ደንበኞች መካከል አንዷ የሆነችው ልእልት መኮንን የአምበሳ ባንክ ሠራተኛ መሆኗን ነግራናለች፡፡ “ከሥራ መልስ በአብዛኛው ‘አክስቴ’ ቤት እመጣለሁ፡፡ መንገድ ላይ መሆኑ ረብሾኝ አያውቅም፤ እንደውም አየር እየተቀበልኩ ስመገብ ደስ ይለኛል” ብላናለች፡፡

ሳቢያን ሰፈር ልዩ ስሙ መስቀለኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ቤትም ሌላው ስመጥር ቤት ነው፡፡ የቤቱ ባለቤት ወ/ሮ እቴኑ ቤት ውስጥ እና ከቤት ውጭ በተደረደሩ ወንበሮች አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆንም አብዛኛው ተመጋቢ ቤት ውስጥ ከመሆን ይልቅ ከቤት ውጭ ሆኖ መመገብን እንደሚመርጥ አስተውለናል፡፡ ለሜሳ ያደታ እና ትእግስት የተባሉት ጓደኛሞች ከቤት ውጭ መንገድ ላይ ከተደረደሩት መቀመጫዎች በአንዱ ተቀምጠው እየተመገቡ አገኘናቸው፡፡ ቤቱ ውስጥ መቀመጫ እያለ አስፋልት ዳር መሆንን ለምን እንደመረጡ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ውስጥ ሙቀት አለ፡፡ ውጭ አየሩ ደስ ይላል፡፡ ወጭ ወራጁን ዕያዩ መመገብም ለየት ያለ ነገር ነው” ብለዋል፡፡  

በመክሰስ ሰዓት ከተለመዱ የድሬዳዋ ምግቦች ውስጥ አንዱ የሆነውን “ፈጢራ” በልዩ ሁኔታ በማዘጋጀት ታዋቂ የሆነው ሰባተኛ አካባቢ የሚገኘው የኢብሮ ፈጢራ ቤት ነው፡፡ እንደ ድንች በሰላጣ ሁሉ ፈጢራም የጾም እና የፍስክ አለው፡፡ ተጠቃሚው ሲያዝ እንቁላል፣ ድንች፣ ሙዝ እንደየፍላጎቱ እንዲቀላቀሉለት ማድረግ ይችላል፡፡

በፈጢራ ቤቱ ሲመገቡ ያገኘናቸው ግሩም እና ኢዮኤል ሆዳቸውን ያዝ የሚያደርግ ምግብ ሲያሰኛቸው ይህንን ቤት እንደሚመርጡ እና ቤቱ ሞቅ ሞቅ የሚለው ከምሽት 12 እስከ 4 ሰዓት መሆኑን ነግረውናል፡፡

ለገሀሬ አካባቢ የሚገኙትን “ይመኙ” ድሬዳዋ የኖረ ሁሉ በ“ካትረን” ሰዓት ያስታውሳቸዋል፡፡ የይመኙ ቤት ሽሞ (ቦሎቄ) በድንች መገኛ ነው፡፡ የተቀቀለ ቦለቄ እና ድንች ከቱና፣ ከእንቁላል፣ ከአቦካዶ፣ ከሙዝ ጋር እንደየፍላጎታችን ተቀላቅሎ ይቀርብበታል፡፡ ለገሀሬ ተወልዶ ያደገው ናሆም “ይህች ቤት ለእኛ ለለገሀሬ ልጆች ባለውለታችን ነች” ሲል አሞካሽቷታል፡፡

እያንዳንዱ በድሬዳዋ የሚገኝ አካባቢ የራሱ የሆነ የአመጋገብ፣ የአነጋገርና የአለባበስ ባህል ቢኖረውም ሁሉንም ነዋሪ ከሚያመሳስሉ ጉዳዮች ውስጥ የአመጋገብ ስርአቱ አንዱ ምናልባትም ዋነኛው ይመስለኛል፡፡ ይህ ሐሳብ የበርካቶች መሆኑን በከተማዋ ተዘዋውረን ካነጋገርናቸው ሰዎች ለመረዳት ችለናል፡፡ “የድሬዳዋ የመንገድ ላይ ጣፋጭ ምግቦች የድሬዳዋ ድምቀት ናቸው” የሚል እምነት ያላቸውም በርካቶች ናቸው፡፡ ከተማዋን ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጠ ወዳጅ ዘመዳቸውን ለጉብኝት ይዘው የሚወጡ ነዋሪቿ በኩራት ሊያስጎበኙት ከሚወዱት የአኗኗር ዘያቸው ውስጥ ይመድቡታል፡፡

 

አስተያየት