ሐምሌ 7 ፣ 2013

በቆሎ እሸት - ክረምትና የአዲስ አበባ ጎዳናዎች

City: Addis Ababaገበያየአኗኗር ዘይቤንግድ

በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ በተለይም የክረምትን መግባት ተከትሎ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በቆሎ ሻጮችን እና ተገበያዮችን መመልከት የተለመደ ነው። በበቆሎ ገበያው ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩ ግን ይሄን ኡደት ያስተጓጎለው ይመስላል።

Avatar: Haymanot Girmay
Haymanot Girmay

በቆሎ እሸት - ክረምትና የአዲስ አበባ ጎዳናዎች
Camera Icon

A woman sells corn at a Addis Ababa market. Anadolu Agency / Contributor / Getty Images

በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ በተለይም የክረምትን መግባት ተከትሎ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በቆሎ ሻጮችን መመልከት የተለመደ ነው። በምሽት ጎዳና ላይ ወደ ማደሪያው ለመሄድ የሚርመሰመሰው ሰው ለአምሮት ይሁን ለእራት መዳረሻ ከእጁ ላይ የተጠበሰ እና የተቀቀለ አሊያም ከቤተሰቦቹ ጋር አብሮ ለመቋደስ ጥሬ የበቆሎ እሸት ሸክፎ ሲጓዝ ይስተዋላል።

በዘንድሮ የክረምት ወቅትም የእሸት በቆሎ ንግድ የቀጠለ ቢሆንም የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ በበቆሎ  ግብይቱ ላይ የገበያ መቀዛቀዝ መከሰቱን አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ሰዎች ይናገራሉ። 

''በፊት በፊት መንገዱ በሙሉ በሚጠበስ እና በሚቀቀል በቆሎ ሽታ ስለሚታወድ ሳልገዛ ማለፍ አልችልም ነበር'' የሚለው ገዛኸኝ በአንድአምላክ የታክሲ ሹፌር ሲሆን በተለይ በክረምት ወራት ከበቆሎ እሸት ጋር የነበረውን ቁርኝት ያስረዳል። 

ገዛኸኝ ለ1 የተጠበሰ በቆሎ  15 ብር የሚከፍለው ካለው በቆሎ የመብላት ፍላጎት አንፃር እንጂ ዋጋው በተለይም አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላለው ሰው የማይቻል እንደሆነ ያስረዳል። አንድ በቅርበት የሚያውቀውን ሰው ታሪክ በማንሳት ጉዳዩን የሚያብራራው ገዛኅኝ 1 በቆሎ ምሳ ወይም እራት በልቶ ኑሮውን የሚገፋ ሰው እንደነበር በማስታወስ ነው። "አሁን ያለው የኑሮ ውድነት በልቶ ለማደር እራሱ ከባድ ሆኗል" ይላል ገዛኸኝ።

በተለይ ከዚህ ቀደም በአንፃራዊ ዋጋው ይቀንሳል እና በሁሉም ቦታ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው በቆሎ  እንዲህ ለሻጮችም ሆነ ገዢዎች የምርት ማነስ እና መወደድ ጥያቄ እንደሆነበት ገዛኸኝ ገልጿል።

ከ1 አመት በፊት በቆሎ እሸት ይሸጥበት ከነበረው የገንዘብ መጠን በእጥፍ መጨመሩን የምትናገረው አየርጤና አከባቢ አውራጎዳና ላይ በቆሎ እየጠበሰች በመሸጥ የምትተዳደር አንዲት እንስት ናት። አምና 3 በቆሎ 15 ብር ማለትም 1 በቆሎ በ5 ብር ዋጋ ይሽጥ እንደነበር በማስታወስ ዘንድሮ 3 በቆሎ በ30 አንዱ ደግሞ በ10 ብር እየተሸጠ መሆኑን ትናገራለች።

''እኛ የምናተርፈው ከ3 በቆሎ 4 ብር ብቻ ነው ነገር ግን ዋጋ ሲጨምር ሻጭ የተለየ ትርፍ እንደሚያገኝ ገዢው ያስባል” በማለት የደንበኞቿን ቅሬታ ትገልጻለች። የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ብዙ ሰው ለመግዛት ፍቃደኛ ስለማይሆን የሻጮች ቁጥር መመናመኑን የምትናገረው በቆሎ ሻጭ ''ምንም እንኳን የኑሮ ውድነት በሁሉም የምግብ አይነቶች ላይ ቢሆንም ሸማቹ በቆሎ እሸት አንደወትሮዉ የመግዛት ፍላጎት አንያሳየ አይደለም፣ ሰዎች መግዛት የቀነሱ ይመስላል'' በማለት ለሽያጭ ምታቀርበውን የበቆሎ ቁጥር ለመቀነስ መገደዷን ትገልጻለች። 

በቆሎ በኢትዮጵያ በፍተኛ መጠን በመመረት ከጤፍ 40 በመቶ ከማሽላ 56 በመቶ እና 75 በመቶ ስንዴ ላይ ብልጫ እንዳለው እ.ኤ.አ በ2008 በአለም አቅፍ የምግብ መመሪያ የጥናት ማእከል የተጠናው ጥናት ያሳያል።  

በበቆሎ ምርት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካን በመከተል 3ኛ ደረጃን የምትይዝ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ200 ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የበቆሎ  ምርት ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች። ነገር ግን ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ይልቅ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ምርት እጅጉን የጎላ ነው። 

በአምራች ገበሬው እና በተጠቃሚውም ዘንድ ከሌላው የጥራጥሬ ዘር በበለጠ በቆሎ በኢትዮጵያ አብዛኛው ክፍል ግልጋሎት ላይ እንደሚውል ይነገራል። ለምግብ ፍጆታ ከሚውልባቸው የአሰራር መንገዶች ውስጥ አንዱ ገና እሸት እንዳለ አብስሎ የመጠቀም የአበላል ዘዴ መሆኑ በብዙሃን ኢትዮጵያውያን ዘንድ አዲስ ጉዳይ አይሆንም። 

በግብርና ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ለአዲስ ዘይቤ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አጭር ምላሽ "በቆሎ እንደሌሎቹ ሰብል ለምሳሌ እንደ ስንዴ ገበያ ላይ ገብቶ ተፈጭቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል እንጂ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የበቆሎ እሸት ገበያ ላይ እንዲውል ፍላጎት የለውም" በማለት የበቆሎ እሸት ግብይት የሚፈፀመው በገበሬው እና በተጠቃሚው ፍላጎት እንጂ በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ይሁንታ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በቆሎ በእሸትነቱ ለገበያ አንዲቀርብ አንደማያበረታታ የሚናገረዉ ግብርና ሚኒስቴር በገበያዉ ላይ የቦቆሎ እሸት ቢቀንስ ወይም ቢጨምር መስሪያ ቤቱ መረጃ አንደሌለዉ አስታዉቋል፡፡

አስተያየት