ሐምሌ 7 ፣ 2013

የድሬዳዋ የሌሊት ሾፌሮች ትላንት እና ዛሬ

City: Dire Dawaመልካም አስተዳደርየአኗኗር ዘይቤአካባቢ

ከቀን ይልቅ በምሽት በምትደምቀው ድሬዳዋ ከተማ ሰዎችን ከቦታ ቦታ የሚያመላልሱት ተሽከርካሪዎች የሌሊት እና ቀን ምድብ ተሰጥቷቸው አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ሽፍት ያወጣላቸው የከተማው መስተዳድርም ወንጀልን ለመከላከል እንደሆነ አሳውቋል።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬዳዋ የሌሊት ሾፌሮች ትላንት እና ዛሬ

ድሬዳዋ ከቀን ይልቅ በምሽት ትደምቃለች፡፡ የቀኑን ኃይለኛ ጸሐይ ተሸሽገው የሚያሳልፉት ነዋሪቿ የጀንበርን ማዘቅዘቅ ተከትለው ጎዳናዎቿን ይሞላሉ፡፡ ድሬዳዋ ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በተለየ ብዛት ያላቸው ሰዎች ከምሽት እስከ ሌሊት እንደልብ የሚንቀሳቀሱባት ከተማ ናት፡፡ ይህንን የምሽት የበዛ የሰዎች እንቅስቃሴ የታዘበው የከተማው መስተዳድርም ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ሽፍት አውጥቷል፡፡ በከተማዋ በስፋት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ባለ ሦስት እግር ተሽርካሪዎች (ባጃጆች) የቀን እና የምሽት በሚል ፈረቃ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ሰንብተዋል።

ሰዎችን ከቦታ ቦታ የሚያመላልሱት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች የሌሊት እና የቀን ምድብ ተሰጥቷቸው አንዱ በአንደኛው ፈረቃ ገብተው እንዳይሰሩ የተደረገው ወንጀልን ለመከላከል እንደሆነ መስተዳድሩ ሕጉን ባጸደቀበት ጊዜ አሳውቋል፡፡ አዲስ ዘይቤ ተዘዋውራ ያነጋገረቻቸው የሌሊት ፈረቃ አገልግሎት ሰጪዎችም ሃሳቡን ይጋራሉ።፡፡

አዲስ ዘይቤ ያገኘችው መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁን ሰዓት የሌሊት ሽፍት የሚሰሩ 257 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በሌሊቱ እንቅስቃሴ ማጓጓዝ የሚችሉት የተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡

ወጣት በረከት ተፈራ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሰማራ ወጣት ሲሆን በሌሊት ፈረቃ መስራት ከጀመረ ሦስት ዓመት ማስቆጠሩን ይናገራል፡፡ በሦስት ዓመታት ቆይታው ብዙ ዓይነት ሰዎችን ከአንዱ ወደ ሌላ ቦታ አመላልሷል፡፡ የመውለጃ ጊዜያቸው የደረሰ ነፍሰ-ጡሮች፣ ህመምተኞች፣ ከቤተሰብ የተጣሉ፣ የሚዝናኑ፣ ወንጀለኞች፣ የሰከሩ፣… ብዙ ዓይነት ሰዎች እንዳጋጠሙት ይናገራል፡፡ ከአራት ወራት በፊት ከመደፈር ያስጣላትን ሴት ሁኔታ ከማይረሳቸው ገጠመኞቹ ውስጥ መድቧቸዋል፡፡

“ወጣቷ ቆንጆ የምትባት ዐይነት ናት፡፡ እድሜዋ በ20ዎቹ መጨረሻ ይገመታል፡፡ በምሽት የወጣችው ለመዝናናት ነበር፡፡ እንዴት እንደሆነ ባላወኩት መንገድ ኤም.ኤ ሆቴል አካባቢ የሆኑ ወጣቶች ለመድፈር ሲሞክሩ ተመለከትኩ፡፡ ወንዶቹ ሦስት ናቸው፡፡ በፍጥነት ፖሊስ ጠርቼ አስያዝኳቸው፡፡ አሁን እስር ላይ ይገኛሉ፡፡”

ሌላው የሌሊት ሰራተኛ ተካልኝ ከበደ (ቤንች) “የሌሊት ሽፍት አገልግሎት ሰጪ መሆኔ ጠቅሞኛል” ይላል፡፡ በአብዛኛው የሚሰራበት መንገድ ከአሸዋ ሳቢያን ያለውን እንደሆነ ነግሮኛል፡፡

“በሌሊት ፈረቃ ለአጫጭር መንገዶች ከፍ ያለ ገንዘብ እንጠይቃለን፡፡ ያንን ብር በቀን ቢሆን አናገኘውም፡፡ የቀኑ ጸሐይ እንደልብ አያሰራም፡፡ ለእኔም ለባጃጄም አይመቸንም፡፡ ቀን ቀን ብቻ ብሰራባት ባጃጄም እድሜ አይኖራትም፤ በዚያ ላይ የመንገዱ መጨናነቅ እና የትራፊክ መብራቶች ያሰለቹኝ ነበር፡፡ ስለዚህ ቀን ተኝቼ ማታ ለስራ እወጣለሁ፡፡ አየሩም ገቢውም ጥሩ ነው፡፡ ሌሊት ተኝቼ ቀን አለመነሳቴ አይቆጨኝም” ሲል ሐሳቡን አጋርቶናል። 

የሌሊት ሹፌሮቹ የሚጭኑበት ስፍራ መጥተው ከሚያገኟቸው አልፎ ሂያጅ ተጠቃሚዎች በተጨማሪ “በስልክ የሚጠሩን ቋሚ ደንበኞች አሉን” ይላሉ፡፡ ከደንበኞቻቸው መካከል የጫት ነጋዴዎች፣ የምግብ ቤት ባለቤቶች፣ ባለሱቆችና፣ የሚዝናኑ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ ጅቡቲን ጨምሮ ከተለያዩ የድሬዳዋ አጎራባች ከተሞች ወደ ድሬዳዋ የሚገቡ ወይም ከድሬዳዋ የሚወጡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን፣ የታሸጉ ምግቦችን ያጓጉዛሉ፡፡ ፈቃድ ያላቸው የምሽት አጓጓዦች በመሆናቸው በደንበኞቻቸው ዘንድ አመኔታን አትርፈዋል፡፡ አቶ ተካልኝ ከበደ ስለገቢው ሲናገር “ሌሊት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ለታማኝነታችንም ደንበኞቻችን አሪፍ ብር ይከፍሉናል” ብሏል፡፡  

“በቀደመው ጊዜ የሌሊት እና የቀን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ባለመለየታቸው፤ መንገድ ትራንስፖርትም እነማን የት ቦታ እንደሚንቀሳቀሱ የሚያውቅበት አሰራር ባለመኖሩ፤ ብዙዎች ለዝርፊያ እና ማጭበርበር ተዳርገዋል፡፡ ሴቶች ለመደፈር አደጋ ተጋልጠው ነበር” የሚለው ዳግም እንደገው አሁን ላይ ወንጀሉ ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል ባይባልም በከፍተኛ መጠን ስለመቀነሱ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

እንደ አቶ ተካልኝ ገለጻ የሌሊት አገልግሎት ሰጪዎቹ ሥራቸውን የሚጀምሩት ምሽት 12 ሰዓት ነው፡፡ የሌሊት አገልግሎት ስለመስጠታቸው ፈርመው ወደ ሥራቸው ይሰማራሉ፡፡ ማለዳ ላይ ሌሊቱን የገጠማቸውን ለፖሊስ እና ለትራፊክ ፖሊስ አሳውቀው የዕለቱን ተግባራቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ ወደቤታቸው ይበታተናሉ፡፡ አሰራሩ ግልጽና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተመቸ ነው ሲል ያስረዳል።

ሹፌሮቹ በተጨማሪ በሥራ ገበታቸው ላይ እያሉ ችግሮች ሲገጥሟቸው ለፀጥታ አካላት በስልክ ያሳውቃሉ፡፡ “መረጃውን በስልክ የተቀበለው ፖሊስ አፋጣኝ መፍትሔ ይፈልጋል” ያሉን ሲሆን፤ የተሽከርካሪዎቹ መለያ የሆነውን የታርጋ ቁጥር ቀለም በመመልከት ብቻ ተገልጋዮች ፈረቃውን ማወቅ የሚያስችላቸው አሰራር መዘርጋቱም ሌላው በጥሩ ጎን የተነሳው ጉዳይ ነው፡፡

በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሐገሪቱ ክፍሎች ባለ ሁለት እግር ሞተርን፣ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ)ን፣ መኪናን በመጠቀም የሚካሄዱ የማጭበርበር እና የስርቆት ወንጀሎች በርክተዋል፡፡ ይህንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ የወንጀል እንቅስቃሴ ለመግታት የድሬዳዋ ከተማን ዐይነት የቁጥጥር ስርአት መዘርጋቱ ጠቀሜታ እንዳለው ያነጋገርናቸው የምሽት ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች አሳስበዋል፡፡

የልብ ሕመም ያለባት ወ/ት ሳምራዊት መካሻ ከአንድ ዓመት በፊት ያጋጠማትን እንዲህ አስታውሳናለች፡፡ “አንድ ቀን በመንገድ ላይ እየተጓዝኩ በትከሻዬ ያንጠለጠልኩትን ቦርሳ ነጠቁኝ፡፡ ሌቦቹ ባጃጁ ውስጥ የተሳፈሩት ሁለት ሆነው ነው፡፡ አንደኛው ቦርሳዬን ሲነጥቅ አንደኛው ባጃጇን በጣም በፍጥነት ያሽከረክር ነበር፡፡ በድንገት ውልብ ሲል የገጨኝ መስሎኝ ነበር፡፡ በሁኔታው በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ታመምኩ፡፡ በዚያ ምክንያት ለበርካታ ቀናት ሆስፒታል ተኝቻለሁ” ስትል ትውስታዋን ለአዲስ ዘይቤ አጋርታለች።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ከእንቅልፍ ተነስተው ምግብ (ቁርሳቸውን) በመብላት ሥራቸውን የሚጀምሩት ሾፌሮቹ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ምሳቸውን ይበላሉ፡፡ ከአነስተኛ የትኩስ ምግብ አቅራቢዎች ጀምሮ መካከለኛ እና ትልልቅ ሆቴሎችም የሌሊት አገልግሎት አላቸው፡፡ ተጠቃሚው እንደ አቅሙ እና እንደፍላጎቱ ምግብ የሚያገኝባቸው አማራጮች አሉለት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ “ሼል” በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

“ሼል” በመባል የሚታወቀው የከተማዋ መንደር ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ንጋት የሚሰሩ አነስተኛ ምግብ አቅራቢዎች መገኛ ነው፡፡ ካራማራ፣ ፖሊስ መሬት፣ አሸዋ፣ ምድር ባቡር፣ ድልጮራ ሆስፒታል አካባቢ በየትኛውም የሌሊት ክፍል ምግብ የማይታጣባቸው ሰፈሮች ናቸው፡፡ ዋጋቸው ግን በቀን የሚሸጡበትን እጥፍ ይሆናል፡፡

በድሬደዋ የሚገኙ የሌሊት ሹፌሮች ከስራቸው ጎን ለጎን የተለያዩ በጎ አድራጎት ተግባራት ላይም ይሰማራሉ፡፡ የሚያስተባብሯቸው ሰባት አባላት ያለው ኮሚቴ መርጠው የደከሙትን ለመደገፍ ይጥራሉ፡፡ አቶ ወንድማገኝ ተሬሳ ከኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ትላንትን እና ዛሬን አነጻጽሮ ተከታዩን ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡ “የድሬዳዋ የባጃጅ አሽከርካዎች ስም ጥሩ አልነበረም፡፡ አሁን ግን እየተስተካከለ መጥቷል፡፡ በማኅበራችን አማካኝነት ማኅበረሰባችንን የሚጠቅሙ ሥራዎን እየሰራን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ስማችንን እያደስን ነው፡፡ በበጎ አድራጎት በኩል አቅም ለሌላቸው የትምህርት መሳሪያዎች ድጋፍ፣ የደም ልገሳ አከናውነናል፡፡ በቀጣይም የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴዎች ላይ በሰፊው ለመሳተፍ እቅድ አለን፡፡”

አስተያየት