በአለም ላይ የበይነ መረብ መምጣትን ተከተሎ የተለያዩ የመገናኛ አማራጮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ መጥተዋል፣ ይህም የመረጃ ስርጭትንና የጋዜጠኝነት ስራን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። በሂደቱም የዜና ተጠቃሚዎች መረጃ ለማግኘት አዳዲስ መንገዶችን እያገኙ ሳለ የህትመት ሚዲያው ግን አዳዲስ ፈተናዎች ገጥመውት ሲንገዳገድ ይታያል።
አሁን አሁን ዲጂታል ሚዲያ ዋነኛ የዜናና የመረጃ ምንጭ እየሆነ ሲመጣ በአንጻሩ የህትመት ሚዲያው ከተደራሽነትና ከገቢ አንጻር እየተፈተነ በመምጣቱ አንዳንዶች የተለመደ መንገዳቸውን በመቀየር ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ሚዲያው ሲዞሩ ተስተውሏል።
በሀገራችን ዲጂታል ሚዲያዎች በፍጥነት እያደጉ መሄዳቸው የሚስተዋል ሲሆን፣ የህትመት ሚዲያው የዲጂታሉን ለመፎካከር የሚያስችለውን አቅም ማጎልበት ካልቻለ ልዩነቱ እየሰፋ ሊሄድ ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ከተለያዩ ባለሙያዎች ይደመጣሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ "በዲጂታሉ ዘመን የህትመት ሚዲያዎቻችን እንዴት እየሆኑ ነው?" ስትል አዲስ ዘይቤ ጠይቃለች።
አቶ አማረ አረጋዊ በኢትዮጵያ ፕሬስ መድረክ ውስጥ ረዥም ጊዜ ከቆዩ ጋዜጦች ውሰጥ አንዱ የሆነው የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ ናቸው። የዲጂታል ሚዲያው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣት የህትመት ሚዲያዎችን ማዳከሙ አያጠያይቅም ይላሉ። ይህም የሆነው የህትመት መገናኛዎቹ የዲጂታል ሚዲያውን በሚፈለገው መልኩ አየተጠቀሙበት ባለመሆናቸው እንደሆነ ያነሳሉ።
“ይሁን እንጂ የህትመት ሚዲያ ዘርፎች እየተዳከሙም ሆነ እየወደቁ ያሉት በዲጂታል ወይም በማኅበራዊ ሚዲያው ጫና ብቻ አይደለም። ይህ አንዱ ምክንያት ይሁን እንጂ ብቸኛው እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል” በማለት በዋነኝነት መረጃ ከማቀበል አንጻር የህትመት ሚዲያው በዲጂታል ሚዲያው ለመዋጡ ዋነኛ ምክንያት የይዘት አቀራረብ ሳቢነት እንደሆነ ያስረዳሉ። በመሆኑም “በይዘት በኩል አብዛኛው ዲጂታል ሚዲያ ከህትመቱ ይልቅ ሳቢ ሆኖ መቅረቡ የሚታወቅ ሲሆን ደካማ አቀራረብ ይዞ የመጣ ማንኛውም ሚዲያ ከተፎካካሪዎቹ እኩል ለመራመድ እንዳይችል ይሆናል” ሲሉም ያክላሉ።
“በሌላ በኩል የኛ ሀገር የህትመት ሚዲያ መዳከም ከሌሎች እኩያ ከሚባሉ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር እጅግ የባሰ ነው፣ ለምሳሌ ከኛ በኢንተርኔት አቅርቦትም ሆነ በቴክኖሎጂ የላቀችው ኬንያን ብንመለከት አሁንም ድረስ የጋዜጣ አንባቢዎቿ ቁጥር የወረደ ሚባል አይነት አይደለም። ስለዚህ ከቴክኖሎጂው መስፋፋት ጎን ለጎን የህትመት ሚዲያው ቀድሞም የተዳከመ መሆኑ ሰውን ወደ በይነ-መረብ ሚዲያዎች እንዲያጋድል አስገድዶታል ብዬ አስባለው" የሚሉት አማረ ለነዚህ የህትመት ሚዲያዎች መዳከም ደግሞ መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳነትም ተጠያቂ ነው እላለሁ። መንግስት ሚዲያዎችን ባላንስድ የሆነ መረጃ ማቅረብ ያለባቸው ተቋማት እንደሆኑ ማመን ይገባዋል፣ ለየት ያለ ሃሳብ ይዞ በመጣ ቁጥር በተቃራኒ አቅጣጫ እንደቆሙ አድርጎ ማየቱ ልክ እንደ ህትመቱ ዲጂታሉንም ማዳከሙ አይቀርም ይላሉ።
“የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንደሚያሳየው እንደ አዲስ ነገር፣ ኢትኦጵ፣ ፋክት እና የመሳሰሉት እመርታ ማሳየት ችለው የነበሩት ጋዜጦች እና መጽሄቶች በመንግስት ጫና ስራ እንዳቆሙ ይታወሳል፣ ከነዚህ ጋዜጦች አዘጋጆች መካከል አንዳንዶቹ በአሁን ሰዓት የበይነ መረቡን በመጠቀም አድማጭ ተመልካቾቻቸው ጋር እየደረሱ እንደሆነም ይታወቃል። ይሁን እንጂ የመንግስት ለውጥ ሚዲያው ውስጥም በደንብ ሊገባ ይገባል፣ ያ ሲሆን ህትመቱንም መመለስ ይቻላል ዲጂታሉንም ማጠናከር ይቻላል” ብለዋል።
በተመሳሳይ ዓለም ላይ ባለው የመገናኛ ዘዴዎች ተለዋዋጭነት ሳቢያ የመገናኛ ብዙሃንና የማሰራጫ ዘዴዎቻችውን ጊዜው ወደሚጠይቀው አሰራር እየቀያየሩ መሄድ መቀጠሉ አያጠያይቅም የሚሉት ደግሞ የአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆኑት አቶ ሳምሶን ብርሃኔ ናቸው።
“ለረዥም ጊዜ የኅትመት ሚዲያ ሠፊውን የመረጃ አቅራቢነት ቦታውን ይዞ የቆየ ቢሆንም፣ ከኅትመት ወደ ሬዲዮ ከዛም ወደ ቴሊቪዥን አሁን ላይ ደግሞ የኢንተርኔት አግልግሎት መስፋፋትን ተከትሎ የዲጂታል ሚዲያ ዘመን ላይ ደርሰናል” በማለት ይገልጻሉ። አክለውም የዲጂታል ሚዲያ ደግሞ እንደ ሬዲዮ መደመጥ፣ እንደ ቴሌቪዥን መታየት እና እንደ ጋዜጣ መነበብ የሚችሉ ፕሮግራሞችን በአንድ ላይ ይዞ መምጣቱ ለማኅበረሰቡ ትልቅ እድል ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ፎርቹን ጋዜጣ በየሳምንቱ ከሚወጣው ጋዜጣ በተጨማሪ ዌብ ሳይትን ጨምሮ የተለያዩ የማሀበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ተደራሽ ያደረጋል። በመሆኑም ከዚህ ጋር በተያያዘ “ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬዱ አንደኛው በአንደኛው ላይ ጫና እንዲያሳድር አያደርግም ወይ?” ስትል አዲስ ዘይቤ ላነሳችላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “በትክክል ማስኬድ ከተቻለ እንደውም አንዱ ለአንዱ አጋዥ ነው ምክንያቱም የህትመት ሚዲያው አንዴ ከወጣ በኋላ ስህተት ለማረም ቀላል አይሆንም በተቃራኒው ዲጂታሉ ደግሞ እንደፈለጉ የማረም እድልን ይሰጣል፣ ይሁንና ህትመቱን ታሳቢ በማድረግ የሚሰራው ጥንቃቄ ለዲጂታሉም አትራፊ ይሆናል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንሳይት ዋና አዘጋጅ በበኩላቸው “መረጃን በፍጥነት ተደራሽ ከመሆን አንጻር ዲጂታል ሚዲያው ተመራጭ እየሆነ መገኘቱ መጀመርያ ማንኛውም ግለሰብ መረጃ አለኝ ብሎ በሚያስበው ጉዳይ ላይ እንዳሻው ማጋራት በሚችልበት ማህበራዊ ሚዲያ በኩል የመምጣቱ ምክንያት ይመስለኛል” ይላሉ።
እንደ አዘጋጁ ገለፃ ዲጂታል ሚዲያው በማህበራዊ ሚዲያዎች በኩል መምጣቱ የኤዲቶሪያል አመራሩ ከህትመት ሚዲያ በተሻለ ለፈጣን መረጃ መገኛ ሁነኛ አማራጭ አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪም የአንባቢውን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉና የሰውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን ለማቅረብ ከአንባቢው ጋር አስተያየት መቀባበል የሚቻልበት መንገድ ቀላል በመሆኑ ታርጌት አንባቢዎችን ወይም ተመልካቾችን በማግኘት ተደራሽ የሆኑ መረጃዎችን ለማቅረብ አመቺ ነው።
አብዛኞቹ ሚዲያዎች ለትርፍ የተቋቋሙ ከመሆናቸው አኳያ ከሁለቱ የሚዲያ ዘርፎች በአንጻራዊነት የቱ ይሻላል? አንደኛው በአንደኛው ገበያ ላይ የሚያሳድረው ጫናስ ምን ይመስላል? ስንል ለሪፖርተር ጋዜጣ ሽያጭ እና ግብይት ክፍል ሃላፊ ጥያቄ አቀረብን “በሁለቱም በኩል ያለው ልፋት እኩል ነው፣ ለምሳሌ አንድን አምድ ለንባብ ለማብቃት በግርድፉ እንመልከተው ከተባለ መረጃ ማሰባሰብ፣ መረጃን ማጠናቀር፣ የአርትኦት ስራን ማከናወን ወዘተ ከሂደቶቹ የሚጠቀሱ ተመሳሳይ ስራዎች ሆነው ሳለ የገበያ ሁኔታቸው ግን እንደየባህሪያቸው ይለያያል” የሚሉት ሃላፊው ሪፖርተር ለምሳሌ የህትመት ብቻ ስራዎችን ሲያቀርብ ይከተል የነበረውን መንገድ ወደ ዲጂታሉ ሲገባ ለመጠቀም ቢሞክር ለገበያው አስቸጋሪ ይሆን እንደነበር በመግለፅ በየፊናው የተለያየ መንገድ መጠቀሙ አትራፊ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።
አያይዘውም “የህትመት ስራዎች ለገበያ የሚቀርቡባቸው አስር እና ሀያ ብሮች የወረቀቱን ወጪ ያህል መመለሳቸውንም እንጃ እንጂ አትራፊ አይደሉም ስለዚህ ትርፍ የሚገኘው በማስታወቂያ ይሆናል ማለት ነው፣ ያ ደግሞ የሚገኘው የህትመት ጋዜጣዎቹንም ሆነ የዲጂታል ሚዲያዎቹን የሚፈልገው ታርጌት ኦዲየንስ የቱ እንደሆነ የመለየት ስራ በመስራት ለነሱ የሚሆን ምርት የሚያቀርቡ የንግድ አካላትን ለማስታወቂያ አነጋግሮ ደንበኛ መሆን አዋጪ ነው” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት መኩርያ መካሻ “አሁን ላይ እንኳን ሳምንታዊ ህትመቶችን ይቅርና ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ ላይ ዕለታዊ የዜና ሰዓት ጠብቄ የምከታተልበት ምንም ምክንያት የለኝም” ይላሉ “በዲጂታል ሚዲያ መረጃዎችን በፍጥነት ማግኘት እየቻልኩ፣ ለምን ቀናትን ወይም ሰዓታትን መጠበቅ ያስፈልገኛል?” ሲሉም ጥያቄ ያነሳሉ።
መኩርያ የዲጂታል ሚዲያውን ጥንካሬ ሲያነሱ ጉድለቱንም ይጠቅሳሉ። “ከተአማኒነት አንጻር በዲጂታል ሚዲያው ላይ ሠፊ ችግር ያለ ቢሆንም፣ ከተለያየ ምንጮች እያመሳከሩ ትክክለኛነቱን ለማጣራትም በዛው ልክ ቀላል ነው” ይላሉ። አያይዘውም መረጃን በፍጥነት የዲጂታል ሚዲያው የአብዛኛውን ሰው ትኩረት ለመሳብ ያስቻለው አሁን ላይ በብዛት የመረጃ ጥያቄ ያለባቸውን ወጣት የሚባሉትን የእድሜ ክልል መያዝ በመቻላቸው ነው” ይላሉ።
አብዛኛው የዲጂታል ሚዲያው ተጠቃሚ ወጣቱ ትውልድ ከመሆኑ አንጻር መረጃን በፍጥነት ካንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ለመዘወር ቀላል እንዳደረገው እንደሚታመን በማንሳትም ህትመት ላይ ብቻ የሚሰሩ ሚዲያዎች አሁን ያለው ትውልድ ባብዛኛው በስፋት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ ጥራት ያለው መረጃ ለመስጠት የሚያስችለውን ዲጂታል ሚዲያ በመቀላቀል በብዛት፣ በጥራት እና በፍጥነት መወዳደር እንዲችሉ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ።
በሌላ በኩል አጀንዳ ከመፍጠር አንጻር ግን በዲጂታሉም በህትመቱም በኩል ጥንካሬም ድክመትም አለ በማለት ሙያዊ ሐሳባቸውን ያነሳሉ። በዚህ ረገድ ሁለቱም ዘርፎች የራሳቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ አንዱ ከሌላኛው የተሻለ ሀሳብ ይዞ ይቀርባል ብሎ ለመደምደም ግን እንደሚቸገሩ ይናገራሉ። በዲጂታል ሚዲያው በኩል የሚስተዋለውን የመረጃ ተዓማኒነት ከማጥራት አንጻር ትልቅ ክፍተት ይታይባቸዋል በማለት የመረጃ አጣሪዎች ማነስ ለዚህ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ። ይሁንና የዲጂታሉ ሊበልጥ ቢችል እንጂ በህትመት የሚዲያ ተቋማትም ላይ የሚታይ ጉዳይ መሆኑ ሁለቱም የሚጋሩት ክፍተት እንደሆነም ጨምረው ያነሳሉ። “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማጣራትና ለሕብረተሰቡ ለማሳወቅ የተወሰኑ ግለሰቦች እና ተቋማት ብቅ ብቅ እያሉ መሆኑ ቢበረታታም በነሱ ጥረት ብቻ የሚሣካ ጉዳይ ባለመሆኑ ሁሉም የዘርፉ አካላት ጉዳዩን በትኩረት ሊያዩት ይገባል” ሲሉ የህትመት ሚዲያዎች በዲጂታል ሚዲያው የተጋረጠባቸውን የመረጃ ፍሰት ችግርና የሕልወና ስጋት ለመፍታት ያላቸውን ዓቅም አሟጠው መጠቀም ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።