ጥቅምት 30 ፣ 2014

በቅርሶቿ የማታጌጥ ከተማ

City: Dire Dawaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮችቱሪዝም

ድሬዳዋ ከተማ የሐገር ውስጡንም ሆነ የውጭውን ጎብኚ የሚስቡ ቅርሶች ብትይዝም ለቱረዝም ተመራጭ ከሆኑት ተርታ ስትቀመጥ እምብዛም አይስተዋልም።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

በቅርሶቿ የማታጌጥ ከተማ

የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ዓይነተ ብዙ ክፍልፋይ አላቸው። ከተለመዱት የሐይማኖት፣ የመዝናኛ፣ የስፖርት፣ የህክምና፣ የትምህርት የቱሪዝም ዓይነቶች ጀምሮ እስካልተለመዱትና ውሱን ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚሳተፉባቸው የጀብድ፣ የአቶሚክ፣ የጨለማ፣ የጦርነት፣ የሻርክ እስከሚባሉት ድረስ ቁጥራቸው የበዛ ነው። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከተለመዱት የሐገር ውስጥ ቱሪዝም ምክንያቶች ውስጥ የሐይማኖት እና የመዝናኛ ቱሪዝም ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝ ጥናቶች ያሳያሉ። እንደ ጎንደር፣ አክሱም፣ ላሊበላ ያሉ ከተሞች ለሐይማኖታዊ ቱሪዝም ተጠቃሽ ምሳሌዎች ሲሆኑ ሐዋሳ፣ ናዝሬት፣ ዝዋይን የመሰሉት ከተሞች ደግሞ መዝናናትን ጉዳዬ ያሉ የሐገር ውስጥ ተጓዦች ከሚያዘወትሯቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

ድሬዳዋ ከተማ የሐገር ውስጡንም ሆነ የውጭውን ጎብኚ የሚስቡ ቅርሶች ብትይዝም ለቱረዝም ተመራጭ ከሆኑት ተርታ ስትቀመጥ እምብዛም አይስተዋልም። በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ በረራዎችን በማስተናገድ ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ያላት፣ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነችው፣ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያገናኝ የመንገድ አውታር ያላት፣ የባቡር ትራንስፖርት የሚገኝባት ከተማ የሚጠበቀውን ያህል የጎብኚ ቁጥር ያልኖራት ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ይዘን ባለድርሻዎችን አነጋግረናል።

በድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ የማርኬቲንግ ማስተርስ ተማሪ የሆነችው ትንሳኤ ካሳሁን የከተማዋ ቅርሶች በበቂ መጠን ተደራሽ ላለመሆናቸው ምክንያት ናቸው ያለቻቸውን ጉዳዮች ዘርዝራለች።

“ደረጃውን የጠበቀ የፕሮሞሽን ስራ አለመሰራቱ፣ የቅርሶች እና መስህቦች ልማት ዝቅተኛ መሆን፣ በአብዛኛው የተመዘገቡ ቅርሶች በግለሰብ እጅ ያሉ መሆናቸው፣ ቅንጅታዊ አሰራር አለመጠናከር፣ የአደረጃጀት፣ የክህሎትና የበጀት እጥረት፣ የአመለካከት እና የትኩረት ማነስ፣ በመስህብ ስፍራዎች የመሰረተ ልማት አለመስፋፋት፣ የግል ሴክተሩ ተሳትፎ ውስን መሆን ለድሬደዋ ቱሪዝም በዚህ ደረጃ መውረድ ምክንያት ናቸው”

ድሬዳዋ ተወልዶ እንዳደገ የሚናገረው ኢዮኤል በባለሙያዋ ሐሳብ ይስማማል። “ድሬዳዋ ውስጥ ስላሉት ቅርሶች ምንም የማውቀው ነገር የለም። እኔ እዚህ ሆኜ ሳላውቀው ሌላ ሰው እንዴት ሊያየው ይችላል?” 

አቶ ጉያ መሀመድ የድሬደዋ ኮኔል ሰፈር ነዋሪ ነው። በልጅነቱ ያሳደጉት አያቱ ስለድሬደዋ ቅርሶች በስፋት ይነግሩት እንደነበር ያስታውሳል። “ይሁን እንጂ ቅርሶቹ በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዳልዋም” ይላል።

ትንሳኤ በበኩሏ “ዋነኛው ማነቆ በድሬደዋ የሚገኙትን ቅርሶች ማስተዋወቅ ላይ ጠንካራ ስራ አለመሰራቱ ነው” ትላለች። የቱሪስት ፍሰቱ በጨመረ ቁጥር የአንድ ሀገር እድገት በዛው ልክ እንደሚጨምርም ትገልፃለች። “በተለይ አሁን ሀገራችን የምትገኝበት ሁኔታ ቱሪስትን ከሚያሸሹት ነገሮች ዋነኛው ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ ሰላም ከታጣ እና የእርስ በእርስ ግጭቶች ካሉ የቱሪዝም ዘርፉ ክፉኛ ይጎዳል” ስትል ገልፃለች።

ቅርሶችን በወፍ በረር

ቅዱስ አልአዛር ማተሚያ ቤት

በ1908 እ.ኤ.አ የተቋቋመው አልአዛር ማተሚያ ቤት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ማተሚያ ቤት እንደሆነ የድሬዳዋ ባህል እና ቱሪዝም መረጃ ያመላክታል። ታሪካዊዎቹ የመጀመርያው የአማርኛ ልብ ወለድ ጦቢያ እና አዕምሮ ጋዜጣ የታተሙት በዚሁ ማተሚያ ቤት እንደሆነም መረጃው ያሳያል።

የነጋድራስ ሐሲብ የድሊቢ መኖሪያ ቤት

በድሬደዋ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ እድሜ ጠገብ የኪነ-ሕንፃ ቅርሶች መካከል የነጋድራስ ሐሲብ የድሊቢ መኖርያ ቤት አንዱ ነው። ሐሲቢ የድሊቢ የድሬደዋ ከተማ አስተዳዳሪና የሐረርጌ ነጋድራስ ሆነው በ1915 እ.ኤ.አ በልጅ ኢያሱ ተሹመው አገልግለዋል። ነጋድራስ ሐሲብ  በኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ ለፍተኛ ሥልጣን የተሾመ የመጀመርያው የውጭ ሀገር ዜጋ ናቸው። መኖርያ ቤታቸው የወቅቱን ገጽታ በሚያሳዩ ቅርሶች የተሞላ ነው።

የኢትዮ- ጅቡቲ ምድር ባቡር እና ሆስፒታል

የኢትዩ ጅቡቲ ምድር ባቡር ኩባንያ በ1903- 1908 ባሉት ዓመታት እንደተመሰረተ ይነገራል። በመሀል ከዚራ የሚገኝኘው ባቡር ጣቢያው የእንግዶች ማረፊያ ሆኖ አገልግሏል። በ1911 የተመሰረተው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ሆስፒታል ነው። ለድሬዳዋ የመጀመርያ የሆነው ሆስፒታሉ በምድር ባቡር ተቋቁሞ እስከ አሁን ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

እድሜ ጠገብ ዋሻዎች

ጥንታዊ የዋሻ ውስጥ ስዕሎች ከሚገኙባቸው እድሜ ጠገብ ዋሻዎች መካከል የለገኦዳ፣ ፓርክ ኤፒክ፣ የጎደ አጀዋ ዋሻዎች ተጠቃሽ ናቸው። በድሬደዋ አስተዳደር በገጠራማ አካባቢ የኖሩትን የማኅበረሰብ ክፍሎች የአኗኗር ዘይቤ የሚያሳዩ አሻራዎች ይገኙበታል። በዋሻዎቹ ውስጥ የሚገኙት ስእሎች ከ5-7ሺህ ዓመታት በፊት የተሳሉ ስለመሆናቸው የክልሉ ቱሪዝም መረጃዎች ያመላክታሉ።

አብያዚዝ መስጂድ

ከ500 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚገመተው አብያዚድ መስጂድ ከድሬዳዋ ነባር ቅርሶች መካከል ይመደባል። በአሁን ሰዓት በቦታቸው የሚገኘው ፍርስራሹ ብቻ ነው። በግምት 50 ሜትር ያህል ርዝማኔ ያለው የማዕዘን ድንጋይን ጨምሮ ሌሎች የመስጂዱ ቅሪተ አካል በሥፍራው ይገኛል። ጠንካራዎቹ የሐርላ ጎሳዎች እንደገነቡት የሚታመነው መስጊድ የወቅቱን የግንባታ ጥበብ የሚያሳይ የድሬዳዋ ከተማ ቅርስ ነው።

ማዘጋጃ ቤት (ካሳ ሊቶሪያ/ casa Littoria)

የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ድሬደዋን በተቆጣጠረበት ጊዜ በኢጣሊያኖች የተገነባ ነው። ለፋፊስት ፓርቲ ዋና መስሪያ ቤት ሆኖ አገልግሏል። የፋሺስቱ ድሬደዋን ለቆ ከወጣ በኋላ ሕንጻው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ሆኖ አገልግሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻ

ባለ አንድ ፎቁ የንግድ ባንክ ሕንጻ የተገነባው በ1930ዎቹ በጣሊያን ወረራ ወቅት ነው። በአሁን ሰዓት የፎቁ የታችኛው ክፍል (ምድር ቤት) ለባንክ አገልግሎት፣ የላይኛው ክፍል ለኃላፊዎች መኖርያ እያገለገለ ይገኛል።

እጅግም ከማይታወቁት በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ ቅርሶች መካከል የተወሰኑትን በወፍ በረር እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

በድሬደዋ አስተዳደር በ2002 ዓ.ም. የነበረው የቱሪስት ፍሰት 26ሺህ 109 መሆኑ ተጠቅሷል። በ2006 ዓ.ም. ደግሞ 78ሺህ 928 ሆኗል። አሃዙ ፍሰቱ እያደገ እንዳለ የሚያሳይ ቢሆንም መሆን ከሚገባው አንጻር በቂ እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። የከተማዋ ጎብኚዎች  

በድሬደዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ባለሞያ አቶ ደረጀ ታደሰ በቅርቡ ድሬደዋ የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ዘርፉ የሚመራበትን ፖሊሲ በመቅረፅ፣ ለሴክተሩ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ  የሚያበረክተውን ሀገር አቀፍ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በማቋቋም ወደስራ መግባቷን ገልጿል። “ለቅርስና መስህብ ልማት በቂ ትኩረት መስጠት፣ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩትን በማበረታታት፣ ደረጃውን የጠበቀ የፕሮሞሽንና የመልካም ገፅታ ግንባታ ስራዎች ማከናወን፣ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀምን ማሳደግና ማጎልበት ላይ እየሰራን እንገኛለን። ነገር ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም። እነዚህን ነገሮች አጠናክረን ለመቀጠል በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለን” ብሏል።

አስተያየት