ሐምሌ 6 ፣ 2014

ከትግል ፍሬ እስከ ፋሲል ከነማ

City: Gonderባህል የአኗኗር ዘይቤስፖርት

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የ2013 ዓ.ም የዋንጫ አሸናፊ የነበረው ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ የግማሽ ምዕተ አመት ጉዞ

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከትግል ፍሬ እስከ ፋሲል ከነማ
Camera Icon

Credit: Fasil Kenema FC

በኢትዮጵያ በርካታ ትውልድ ሊዘክራቸውና ሊማርባቸው የሚገቡ አስደናቂ የአመሰራረት ሂደት ያላቸው የስፖርት ቡድኖች ይገኛሉ ። በቀደመው ጊዜ የነበሩ እንደ የክቡር ዘበኛው ምድር ጦር የወለዳቸው መቻልና መኩሪያ ፣ ዳኘው ፣ የፖሊስ ሰራዊትን የሚወክሉ ኦሜድላ ፣ የድሬዎቹ ባቡርና ጥጥ ፣ ቴሌ፣ አየር ሃይልን የሚወክለው ንብ እና ቀይባህር ተጠቃሽ ናቸው ። ከዚያ በኋላ የመጡት ደግሞ የከተማ ነዋሪዎች ማህበራት (ከነማ) ክለቦች ሲሆኑ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ዝናን በማትረፍ ደጋፊዎችን እያበዛ የመጣው ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን ተጠቃሽ ነው ። 

በ1938 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሻምፒዮና መጀመሩን ተከትሎ እግር ኳስ በመላው ሃገሪቱ መስፋፋትና መወደድ ሲጀምር ስፖርቱ በታሪካዊው ፋሲል ግቢ የተነሳ የአፍሪካ ካሜሎት በመባል በምትታወቀው ጎንደር ከተማ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ተቀባይነት ሊያገኝ ቻለ። በተለይ 1950ዎቹ በከተማዋና በአጎራባች አውራጃዎች የተለያዩ ቡድኖች ማቆጥቆጥ የጀመሩት ወቅት ነበር። ያ ጊዜ ዞብል ፣ ዋሊያ ፣ አፍሪካ ፣ አውራ ጎዳና እንዲሁም ነጋዴ የሚባሉ ቡድኖች በተለያዩ የግልና የመንግስት ተቋማት ተመስርተው ውድድራቸውን ያካሂዱ የነበረበት ወቅት ነበር።

እነዚህ ቡድኖች የሚያደርጉትን ግጥሚያ ይመለከቱ የነበሩ በጎንደር ከተማ በተለምዶ ቸቸላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ተማሪዎች የሚወክላቸውን ቡድን ለማቋቋም በማህበር በመደራጀት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ የማህበሩ አባላት ተማሪዎች እንደመሆናቸው ለቡድኑ ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችና ገንዘብ ማግኘት ትልቅ ፈተና ሆኖባቸው ነበር። 

ተጫዋቾቹ እና የማህበሩ አባላት በተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ግለሰቦች ቤት እየዞሩ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመሩ። በተሰበሰበውም ትንሽ ገንዘብ ለቡድኑ የሚያስፈልጉ የመጫወቻ ጫማዎች ፣ ማሊያዎች ፣ኳሶችንና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመግዛት የፋሲል ቡድን በ1960 ዓ.ም ተመሰረተ። 

የፋሲል ቡድን ሲቋቋም 13 አባላት ነበሩት። የመጀመሪያ ስያሜው ፋሲል ቢሆንም ለቡድኑ ስም እንዲሆኑ ሌሎች በርካታ አማራጮች ቀርበው እንደነበር በተለያዩ ጊዜ የታተሙ የፋሲል ከነማ መጽሄቶች ይገልጻሉ። አጼ ቴዎድሮስ የተወለዱበት ቋራ ፣ የነገሱበት ደረስጌ ማሪያም ፣ የሞቱበት መቅደላ ፣ የኢትዮጵያዊያን የስዕልና የህንጻ ጥበብ የተንጸባረቁበት የደብረብርሃን ስላሴ ፣ በሃገራችን ትልቁ ተራራ የሆነው ራስ ደጀን ፣ ቁስቋምና ጉና ተራራ ለቡድኑ ስያሜ እንዲሆኑ የቀረቡ አማራጮች ነበሩ። 

ሆኖም ግን በ1624 ዓ.ም ጎንደር ከተማን የቆረቆሯት የአጼ ፋሲለደስ ስምና በከተማዋ ያስገነቡት ቤተ መንግስትን መሰረት አድርገው በመስራቾቹ አብላጫውን ድጋፍ ሊያገኝ በመቻሉ የቡድኑ ስያሜ ፋሲል ሊሆን በቃ። 

ፋሲል በውድድሩ ጀማሪ እንደመሆኑና ልምድ በሌላቸው ተጫዋቾች እንደመዋቀሩ የመጀመሪያዎቹን አመታት ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን አልቻለም። በተጫወተባቸውም ሁለትና ሶስት አመታት ከተሳታፊነት የዘለለ ውጤት ሳያስመዘግብ ቀረ። ሆኖም ግን በጊዜ ሂደት ነባር ተጫዋቾች ልምድ እያገኙ፣ ከተለያዩ ቦታዎች ሌሎች ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችም ወደ ቡድኑ እየተቀላቀሉ ቡድኑ ራሱን አጎለበተ። 

በዚህም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ በመቅረብና በ1965 ዓ.ም በከተማዋ የተዘጋጀውን የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር በማሸነፍ በሃገር አቀፍ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚያደርገውን ውጤት ማስመዝገብ ቻለ። 

ከዚህ በኋላ ነበር ቡድኑ ጎንደርን በመወከል የሰሜንና የበጌምድር ቡድኖች ውድድር ላይ ተሳታፊ በመሆን ከየአውራጃው ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ስምንት ያህል ግጥሚያዎችን አድርጎ ስድስቱን በማሸነፍ እና ሁለቱን አቻ በመውጣት ያለምንም ሽንፈት ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለው። ይህ ውጤት በ1965 ዓ.ም. ፋሲል በወቅቱ የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት የተባለችውን ጎንደርን በመወከል አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው የኢትዮጵያ የጠቅላይ ግዛት አሸናፊዎች ውድድር ተሳታፊ ለመሆን አበቃው። 

በወቅቱ ከገንዘብ አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ውድድሩን ለማካሄድ ተስኖት የነበረው ፋሲል ከነማ ከጎንደር ማዘጋጃ ቤት በተገኘው 300 ብር እና ደጋፊዎች ባዋጡት 400 ብር በድምሩ በ700 ብር በጀት ውድድሩን እንዲሳተፍ ተደረገ። 

ፋሲል በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ አስተናገደች። ወቅቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝባዊ አብዮት ተብሎ የሚታወቀው ምዕራፍ የጀመረበት ነበር። የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት የሃገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ መዋቅሩንም ቀየረው። የለውጡ አንድ አካል የነበረችው ጎንደር ከተማም በስር ነቀል ሂደቱ ውስጥ ስታልፍና ወጣቶቿም ወደፖለቲካው ሲሳቡ በከተማዋ የሚገኙ ስፖርቶች መቀዛቀዝ ጀመሩ። 

በወቅቱ ውድድር ለማድረግ አስቸጋሪ ስለነበር በርካታ ቡድኖች መፍረስ እጣ ፈንታቸው ሆኖ ከስመዋል። አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ በነበሩት ጥቂት አመታት በየቡድኑ የነበሩ ተጫዋቾች የተወሰኑት በፖለቲካው መስመር ሲሰለፉ፣ በርካቶች ደግሞ በወቅቱ “ቀይ ሽብር” ተብሎ ይታወቅ የነበረውን የደቦ ፍጅት ሸሽተው ሃገር ለቅቀው ተሰደዱ። 

ለፋሲል ቡድን ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት ባለሃብቶችና ስፖርት ወዳጆችም በሞት ፣ በስደትና በተለያዩ ምክንያቶች ስለተበተኑ ለቡድኑ የሚደረገው ድጋፍ እየተመናመነ መጣ። በዚህ ምክንያት የፋሲል ቡድን ያጋጠመውን የመፍረስ አደጋ መቋቋም ተስኖት ቡድኑ ከተመሰረተ ከስምንት አመታት በኋላ በ1968 ዓ.ም ፈረሰ።

ወታደራዊው የደርግ ስርዓት የነበሩበትን ተግዳሮቶች በማስወገድ ሃገሪቱን ሙሉ ለሙሉ ሲቆጣጠርና ሲጠናከር በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ተቀዛቅዞ የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴ በመጠኑ መነቃቃትን ማሳየት ጀመረ። ከተወሰኑ አመታት በፊት የፈረሰው የፋሲል ቡድን አባላት የነበሩ ጥቂት ተጫዋቾችና የፋሲል ቡድን መሪ በመሆን ያገለገሉት አቶ ስዩም ደምሌ ቡድኑን መልሶ ለማቋቋም እና ፋሲልን ለመመለስ እንቅስቃሴ ለመጀመር በወቅቱ ለነበረው የከተማዋ አስተዳደር የማስጀመሪያ ፍቃድ ጥያቄ  አቀረቡ። 

ማዘጋጃ ቤቱም ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በከተማዋ ከፍተኛ የቀበሌ ውድድሮች ላይ ልቀው የተገኙ ወጣቶችን በመሰብሰብ ወቅቱ የትግል ነበርና የቡድኑን ስም “ትግል ፍሬ” በማለት ፋሲል በ1971 በድጋሚ ተቋቋመ። የትግል ፍሬ እግር ኳስ ቡድን በየአመቱ በሚደረጉ ውድድሮች ከመካፈል የዘለለ አመርቂ የሚባል ውጤት ሳያስመዘግብ ቆይቶ በ1973 ዓ.ም የስም ለውጥ በማድረግ “አጠቃላይ ከነማ” ተባለ።

የአጠቃላይ ከነማ ቡድንም እንደቀድሞ ከስም ለውጥ በስተቀር ተፎካካሪ ያልነበር ሲሆን የከተማ አስተዳደሩም አልፎ አልፎ ለቡድኑ ምግብ ከማቅረብና የላብ መተኪያ ጥቂት ብር ከመስጠት ውጭ ድጋፍ አያደርግም ነበር። ይሁን እንጂ ተጫዋቾች ለቡድናቸው ሲሰጡት የነበረው አገልግሎት አስገራሚ እንደነበር በዚያን ጊዜ ለአጠቃላይ ከነማ ይጫወቱ የነበሩት አቶ ቢተው ያሉትን ከጎንደር ከተማ ፅ/ቤት መረጃዎች አግኝተናል። 

“በእኛ ጊዜ እና ከእኛ በኋላ ለነበሩ የፋሲል ተጫዋቾች ቋሚ ክፍያ ተብሎ የሚሰጥ ገንዘብ አልነበረም። በጫዋታና ልምምድ ወቅት የላብ መተኪያ ተብሎ ለምግብና ለገላ መታጠቢያ ብቻ ይሰጠን ነበር። የተጫዋቾቹ ክፍያቸው የህዝቡ እርካታ እና ደስታ ነበር” በማለት ተናግረዋል አቶ ቢተው። 

በወቅቱ የደርግ ስርዓት በህብረተሰቡ ላይ በሚያደርሳቸው ተፅዕኖዎች ምክንያት ውድድሮች ተጀምረው ሳይጨረሱ የሚቀሩበት ጊዜያት በርካታ ነበሩ። በተለይም በስርዓቱ የመጨረሻ አመታት አካባቢ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ውድድሮች ቆመው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይገልጻሉ። ይህን ከመሰለ ቆይታ በኋላ ደርግ ተሸንፎ ኢህአዴግ ስልጣኑን ሲረከብ ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ተሸጋገረ። 

የተካሄደውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በ1983 እና 84 ዓ.ም. ውድድሮች ሙሉ ለሙሉ ቆመው የነበሩ ሲሆን ከፋሲል በስተቀር ሁሉም በድርጅቶችና በተለያዩ የግል ተቋማት ተይዘው የነበሩ ቡድኖች ፈርሰው ሌሎች ቡድኖች ተመሰረቱ። ከሽግግር መንግስት በኋላ በተፈጠረው የከተሞች አደረጃጀት የአጠቃላይ ከነማ ቡድኖች ሲመሰረቱ ቀድሞ የያዘውንና አሁን ድረስ የዘለቀውን “ፋሲል ከተማ ነዋሪዎች ማህበር” የሚለውን ስም በ1985 ዓ.ም ያዘ።

ወቅቱ የከተማዋ ማህበረሰቦች የተለያዩ ስፖርቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ጊዜ በመሆኑ የከተማዋ አስተዳደር የላብ መተኪያ ብሎ ከሚሰጠው ትንሽ ገንዘብ በተጨማሪ ለቡድኑ የሚሆን አመታዊ በጀት ይዞ መንቀሳቀስ ጀመረ። የከተማዋ አስተዳደር በ1987 ዓ.ም 7 ሺህ ፣ በ1988 ዓ.ም 9 ሺህ እንዲሁም በ1990 ዓ.ም 14 ሺህ ብር ለቡድኑ ይዞ ነበር። 

በክለቦች ሻምፒዮና ከየክልሉ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የሚወጡ ቡድኖች በብሄራዊ ሊግ (ሶስተኛ ዲቪዚዮን) ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን ፋሲል ከነማ ከተፎካካሪነት ጀምሮ በተከታታይ አመታት የምድብ መሪ በመሆን ቢያጠናቅቅም በአመቱ መጨረሻ በሚዘጋጁ የማጠቃለያ ውድድሮች ላይ ማሸነፍ ባለመቻሉ ወደ ብሄራዊ ሊጉ ማደግ ተስኖት በነበረበት እንዲቆይ ተገዷል።  

ብሄራዊ ሊግ ከፕሪሚየር ሊግ እና ከፍተኛ (ሱፐር) ሊግ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሊግ ነው። ወደዚህ ሊግ የሚገቡት ከክልል ዲቪዥኖች ተወዳድረው አሸናፊ የሆኑ ቡድኖች ናቸው።  

በ1993 ዓ.ም ደብረብርሃን ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የክለቦች ሻምፒዮና ማጠቃለያ ጎንደርን በመወከል ተሳታፊ የነበሩት አዘዞ ድማዛ እና ፋሲል ከነማ ነበሩ። በውድድሩ ፋሲል ከነማ አስደናቂ የሚባል ጉዞን አድርጎ እስከ ፍጻሜ መዝለቅ በመቻሉ በ1994 ዓ.ም ለሚደረገው የብሄራዊ ሊጉ ውድድር የሚያሳትፈውን ውድድር የሚያሳትፈውን ውጤት አስመዘገበ።

ፋሲል ከነማ በብሄራዊ ሊጉ ተሳታፊ ከሆነበት 1994 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ውድድር በመሳተፍ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለማደግ ለበርካታ አመታት ጥረት አድርጓል። ቡድኑ ከተፎካካሪነት ጀምሮ በተከታታይ አመታት የምድብ መሪ በመሆን ቢያጠናቅቅም በአመቱ መጨረሻ በሚዘጋጁ የማጠቃለያ ውድድሮች ላይ ሳይሳካለት  ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደግ ተስኖት በነበረበት ቆይቷል። 

አፄዎቹ የሚል የኩራት መገለጫ ቅፅል ስም በደጋፊዎች የተቸረው ፋሲል ከነማ በብሄራዊ ሊግ የ14 አመታት ቆይታው እንደ ትልቅ ስኬት ሊጠቀስለት የሚችለው በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ተሳታፊ የነበረበት የ2000 ሚድሮክ ሚሊኒየም ዋንጫ ነው። በ1999 ዓ.ም የፕሪምየር ሊግ ቡድኖች ከአወዳዳሪው አካል (ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን) ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ምክንያት ሊጉ ለሁለት ተከፈለ። በዚህም ምክንያት በ2000 ዓ.ም የውድድር ዘመን እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የመሳሰሉት ዝነኛ ቡድኖች ከውድድሩ ራሳቸውን ሲያገሉ አፄዎቹ በፕሪሚየር ሊግ ለመካፈል በቁ። ራሳቸውን ከፕሪሚየር ሊጉ ባገለሉት ቡድኖች ተተክተው ከገቡት ቡድኖች ውስጥ ፋሲል ከነማ አንዱ ሊሆን የቻለው ከብሄራዊ ሊጉ ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ ነበር። የ2000 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ የሚድሮክ ሚሊኒየም ዋንጫ ተብሎ የተካሄደ ነበር። 

ነገር ግን አጼዎቹ በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ መቆየት የቻሉት የ2000 ዓ.ም የውድድር ዘመንን ብቻ ነበር። ተፎካካሪ ሆነው መዝለቅ ባለመቻላቸው በ2001 ዓ.ም ከፕሪሚየር ሊጉ ወረዱ።  

በ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በፕሪምየር ሊጉ የሚሳተፉ ቡድኖች ቁጥር ከ14 ወደ 16 ከፍ እንዲሉ በወሰነው መሰረት ረዘም ላሉ አመታት በየዞኑ ተከፋፍለው ሲደረጉ የነበሩ የብሄራዊ ሊግ ውድድሮች በሁለት ምድቦች በተከፈሉ 32 ቡድኖች በከፍተኛ ሊግ እንዲወዳደሩ ማድረግ ተጀመረ። 

በ2008 ዓ.ም በሁለተኛ ዙር ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ሽንፈትን አስተናግዶ ባስመዘገባቸው ተደጋጋሚ ድሎች ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በማስፋት ውድድሩ አራት ጨዋታዎች እንደቀሩት በ26ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ መድህንን 1 ለ 0 በማሸነፍ ፋሲል ከነማ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሚያደርገውን ውጤት ማስመዝገብ ቻለ። 

አቶ አብዮት ብርሃኑ የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ ናቸው። እንደ እሳቸው ገለጻ ፋሲል ፕሪምየር ሊጉን እንዲቀላቀል የደጋፊዎች ማህበር አባላትና ደጋፊዎች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ። በክለቡ ስም የንግድ ትርዒት (ባዛር) በማዘጋጀትና ገቢ በማሰባሰብ እንዲሁም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ድጋፍና በከተማው ወጣቶችና አጋር የስፖርቱ ቤተሰቦች ጥረት ቡድኑ ከነበረበት የገንዘብ ችግር አገግሞ አመቱን በስኬት እንዲያጠናቅቅ ትልቁን እገዛ አድርገዋል ብለውናል። 

ክለቡ ዘመናዊ አደረጃጀትን የተላበሰ ነው የሚሉት ስራ አስኪያጁ ብቁ የሆነ የወጌሻ አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ እንዳላቸው አክለዋል። ፋሲል ከነማ “እንባና ሳቅን በዘመናት አፈራርቆ ያለፈ ህዝቡን በልዩ ሁኔታ የሚያስተሳስር የአንድነት ገመድ ሆኖ እያገለገለ ያለ ክለብ ነው” ሲሉ ገልጸውልናል። 

የክለቡ ደጋፊዎች ፋሲል ከነማ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው በሃገራችን የክለቦች ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን የ75 ሚሊዮን ብር የአምስት አመት ስፖንሰር ከዳሽን ቢራ ለክለባቸው በማስገኘት የአንበሳውን ድርሻ መወጣታቸውን የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማህበር አባላት ይገልጻሉ። ስራ አስኪያጁ አቶ አብዮትም ለደጋፊዎቹ ሚና እውቅና በመስጠት ከማሊያ ስፖንሰሩ በተጨማሪ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች የተለያዩ ተቋማት ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥረው ክለቡ ተሽከርካሪዎችን ፣ የተጫዋች ማደሪያዎችና ተጫዋቾቹ ሲጎዱ የነጻ ህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን እድል የማመቻቸት ስራ ሰርተዋል ብለውናል።

በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፒሪሚየር ሊግን ከፌድሬሽኑ ተረክቦ በበላይነት እያስተዳደረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ውድድሩን በቀጥታ ለማስተላለፍ ከDSTV ጋር ውል ወሰደ።  በስምምነታቸውም ቤትኪንግ የተሰኘው ካምፓኒ በአይነቱና በይዘቱ ከፍ ያለ ዋንጫ ለአሸናፊው ቡድን ለማቅረብ ተስማምቶ በአመቱ መጨረሻ ላይ እንግሊዝ ሃገር በሚገኝ ግዙፍ ካምፓኒ ተሰርቶ ሃገር ውስጥ ገባ።

በ2012 ዓ.ም አለማቀፍ ክስተት የነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ተጽዕኖ ምክንያት ያጡትን የሊግ ክብር ለማሳካት 2013ን የጀመሩት በከፍተኛ መነሳሳት ነበር ። ስያሜውን ወደ ቤትኪንግ በቀየረውና በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ ዲኤስቲቪ (Dstv) አማካኝነት የቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን ባገኘው የ 2013 ዓ.ም የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በተመረጡ የሃገሪቱ ከተሞች ብቻ ተወስኖ ውድድሩ እንዲካሄድ ተደረገ። 

ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያውን የሊጉን ስድስት ጨዋታ እንድታደርግ የተመረጠችው የሃገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ስትሆን አፄዎቹ ለዋንጫ ቅድመ ግምት ያገኘውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ድል በማድረግ ውድድራቸውን በድል ጀመሩ። ፋሲል በአዲስ አበባ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፎ በአንዱ አቻ ወጥቶ በአንዱ ደግሞ ሽንፈትን አስተናግዶ በቀጣዩ በጅማና ባህርዳር ከተሞች በተደረጉ የሊግ ጨዋታዎች አስደናቂ ግስጋሴን በማድረግ የሊጉን የመጀመሪያ ዙር በመሪዎች ቁንጮ በመቀመጥ አጠናቀቀ። 

አጼዎቹ የአራተኛው ዙር አስተናጋጅ በሆነችው የምስራቋ ድሬዳዋ ከተማ ከመጀመሪያው ዙር ይበልጥ ጠንክረው በመቅረብ የዋንጫ ጉዟቸው የገፉ ሲሆን የሊጉ መዝጊያ መርሃግብር በተካሄደበት ሃዋሳ ከተማ አራት ጨዋታዎች እንደቀሯቸው የ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆናቸውን አረጋገጡ። አጼዎቹ ባደረጉት 24 የሊግ ጨዋታዎች አስራ ስድስቱን አሸንፈው በስድስቱ አቻ ወጥተውና ሁለቱን ተሸንፈው 46 ጎሎችን ተጋጣሚ መረብ ላይ በማሳረፍ 10 ጎሎችን ደግሞ ተቆጥረውባቸው በ54 ነጥብ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ቻሉ። 

ከአጼዎቹ የድል ማግስት አስተያየታቸውን የሰጡትና የጎንደርን ክለብ ለአመታት የናፈቀውን የሊግ ዋንጫ ያሳካውን ቡድን በአሰልጣኝነት የመሩት ዋና አሰልጣኙ ስዩም ከበደ ስለ ድሉ ሲናገሩ "ለረጅም ጊዜ ይህንን ክብር በጉጉት ሲጠብቅ ለነበረው የጎንደር ኳስ አፍቃሪና ስፖርት ወዳድ እንኳን ደስ አላችሁ፣ ይሄ ደጋፊ ከዚህም በላይ ይገባዋል" ብለው ነበር።  

ቡድኑን በአንበልነት እየመራ ዋንጫውን የተረከበው ተከላካዩ ያሬድ ባየህ በበኩሉ "ይህ ውጤት የበርካታ አመታት ልፋት እና የብዙ ጥረቶች ውጤት ነው። ከጎናችን ያልተለዩ ደጋፊዎች ነውና ያሉን ይህ ለነሱ የሰጠነው ትንሹ ድል ነው፣ በቀጣይ አመታትም ከዚህ የበለጠ ጠንክረን በመስራት ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ መድረክ ደምቀን ለመታየት እንሞክራለን"  ሲል ሃሳቡን መሰንዘሩን በፋሲል ከነማ መጽሄት ላይ አቶ ተመስገን ተዋቸው አስቀምጦታል።

ከብዙ ትግስትና ጥበቃ፣ ከረጅም ውጣ ውረድ በኋላ የተገኘውን ድል የአጼዎቹ ደጋፊዎች በአዲስአበባ ፣ በባህርዳር ፣ በጎንደርና ደብረታቦር ከተሞች በድምቀት አከበሩት። በተለይም የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች የድል ዋንጫቸውን ይዘው ወደ መናገሻ ከተማቸው ጎንደር ሲገቡ የተደረገላቸው አቀባበል ደማቅ ነበር። 

2013 ዓ.ም ከኮሮና ቫይረስ በተጨማሪ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ፋሲል ከነማን ጨምሮ ድፍን ኢትዮጵያን የፈተነ አመት ነበር። የፋሲል ከነማ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆን ይህን አስጨናቂ ስሜት ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በጎንደር የኳስ ደጋፊዎች ዘንድ አደብዝዞት ነበር።  

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊነቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ቅድመ ውድድር ቢያደርግም ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።  

በኢትዮጵያ ቤቲኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የ2013 ዓ.ም የውድድር ዘመን የዋንጫ አሸናፊ የሆነው ፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ሜዳ ውስጥ ካሳየው ውጤታማ አጨዋወት ጀርባ የክለቡ አስተዳደርና አመራሮች ጠንካራ ስራ እንደሚገኝ በእግር ኳስ ውስጥ ያሉ ሙያተኞች ይናገራሉ ።

ክለቡን ከመንግስት ጥገኝነትና ድጎማ ጨርሶ በማላቀቅ የራሱ የሆነ የማሰልጠኛ አካዳሚ እንዲኖረው እና በህዝቡ ድጋፍ እንዲተዳደርና እንዲጠነክር ማድረግ የቦርዱ ቀጣይ ስራዎች አንዱ አካል ነው ይላሉ የክለቡ ስራ አስካሄጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ። በአሁኑ ወቅትም በስሩ ከ15 እስከ 23 አመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ተተኪዎችን በየደረጃው የሚያበቃበትን ፕሮጀክት ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። ባለፉት አመታት ክለቡ ሻምፒዮን እንዲሆን ዋና ትኩረት አድርገው በመስራታቸው ሌሎች ቦታዎች ላይ መጠነኛ ክፍተቶች እንደተስተዋሉ ገልጸው የታዳጊዎች ልማት ላይ መቀዛቀዞች እንዳሉና እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ  እየሰሩ መሆናቸውንም ነግረውናል ።

የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ በጎንደር ከተማ ከንቲባ የበላይ ጠባቂነት በስፖርት ፅ/ቤት ይመራል ። ስፖርት ፅ/ቤቱ ከተለያዩ የጎንደር ዞኖችና ወረዳዎች የተዋቀሩና በሁለት አመት አንዴ ጠቅላላ ጉባኤ የሚያደርግ ሲሆን የጎንደርን ክፍለ ሃገር የሚወክሉ ሁሉም ወረዳዎች በጠቅላላ ጉባኤው ይወከላሉ። ክለቡ ተጠሪነቱ ለጠቅላላው ጉባኤው የሆነ የከተማው ባለሃብቶች፣ የደጋፊዎች ማህበርና አጋር አካላት ያሉበት የቦርድ አባላት በመዋቅሩ ውስጥ አካትቶ ይዟል። ፋሲል ከነማ በዚህ ስዓት 4719 የተመዘገቡ ደጋፊዎች አሉት።

ፋሲል ከነማ በያዝነው 2014 አመት የውድድር ዘመንም ከዝነኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ጋር በአንድ ነጥብ ብልጫ ብቻ እስከመጨረሻው የውድድር እለት ድረስ የዘለቀ ሲሆን ሰኔ 24 ቀን ባህር ዳር ላይ በተመሳሳይ ሰዓት በተለያየ ሜዳ ተጫውተው ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊ ሊሆን ችሏል። 

ከ19 መቶዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ማሳረፍ የቻለው ፋሲል ከነማ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግንባር ቀደም የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድኖች አንዱ በመሆን ጉዞውን ቀጥሏል። 

አስተያየት