ታህሣሥ 26 ፣ 2013

ድንች በዳጣ፤ የመንገድ ዳር ምግብ ስራ ፈጣሪዋ | ልኬ -የታታሪነት ዉሃ ልክ

City: Hawassaየአኗኗር ዘይቤ

በከተማዋ የመንገድ ዳር መዳረሻዎች ላይ ድንች በዳጣ አለ የሚሉ ፅሁፎች፤ ከተማዋ ለእንግዶቿ አንደምትቸረው ፍቅር ናኝተዋል።

ድንች በዳጣ፤ የመንገድ ዳር ምግብ ስራ ፈጣሪዋ | ልኬ -የታታሪነት ዉሃ ልክ

በምስራቅ የምትወጣው ፀሀይ ብርሀኗን አላብሳ በመጥለቂያዋ ሰአት ለሀዋሳ ሀይቅ የውበት ነፀብራቋን እንደምትቸረው፤ ህዝቦቿም ዘወትር አመሻሹ ላይ ቸር ማውጊያ፣ አምሮት መወጫ፤ የመክሰስ ማዕድ መቋደሻ ያሉትን የመንገድ ዳር ምግቦችን ሲያላምጡ ማየት የተለመደ ነው። አሁን አሁን ደግሞ በከተማዋ የመንገድ ዳር መዳረሻዎች ላይ ድንች በዳጣ አለ የሚሉ ፅሁፎች፤ ከተማዋ ለእንግዶቿ አንደምትቸረው ፍቅር ናኝተዋል። 

ልኬ እሸቱ ትባላለች፤ ይህ ስም ለአብዛኛው የከተማዋ ነዋሪዎች አዲስ አይደለም፤ ውልደቷም እድገቷም ሀዋሳ ነው። ድንችን በዳጣ እያጣቀሱና እያዋዙ መመገብ ያስለመደች ስራ ፈጣሪ ሴት ናት። ለስምንት አመታት በመታተር፤ ተምሳሌት የሆነችው ልኬ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና የሁለት ልጆች እናት ከመሆኗም በላይ ለተጨማሪ ሁለት ሰው የስራ እድልን ፈጥራለች። "አላማዬ ሀሳቤን ማሳካት እና ትልቅ ቦታ መድረስ ነው፤ እንደምደርስም እርግጠኛ ነኝ" ትላለች ስራ ፈጣሪዋ። "ለመኖርያ በተከራየሁበት ቤት፤ ከግቢው በራፍ ላይ ከስምንት አመታት በፊት አከራዮቼን አስፈቅጄ ትንሽዬ የጀበና ቡና ጀመርኩ፤ ብዙም አልቆየሁም ድንች ቀቅዬ ቡና ለሚጠቀሙ ደምበኞቼ አቀረብኩ፤ የነሱም ፍላጎት መጨመር እና ሞራል ሰጪነት ነው እዚህ ያደረሰኝ" ስትል ደምበኞቿን በማመስገን ትጀምራለች፤"ስራውን ስጀምር አብዛኞቹ ደምበኞቼ በትምህርት ተቋማት ላይ የሚሰሩ እና የትምህርት ቤት ጓደኞቼ እንዲሁም የቢሮ ሰራተኞች ከስራ ሲወጡ ጎራ የሚሉ ናቸው" ስትል አዲስ ዘይቤን አጫውታታለች።

ደምበኞቿ የሆኑ መምህራን በተማሪዎቻቸው ፊት እና የስልጠና ቦታዎች ላይ የሷን የስራ ጥረት ስሟን ጠቅሰው እንደማስተማርያ ግብአትነት ይጠቀሙበታል። ከዚህ ቀደም በስራ ፈጣሪነት (entrepreneurship)  የመመረቂያ ፅሁፍ ለሚሰሩ ሁለት ተማሪዎች የስራ ጥረት ተሞክሮዋን እንዳካፈለቻቸው ታስታውሳለች። "ዳጣ አልገዛም እራሴ ነኝ እቤት ውስጥ የማዘጋጀው፤ ደምበኞቼም የምሰራውን ስራ ሁሉ ፊትለፊት አዘገጃጀቱን እያዩት ስለሚታደሙ መርጠውኛል" ትላለች። 

የ 32 ዓመቷ ልኬ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ያላት ሲሆን እናትነት በስራው ላይ ብዙም ተፅዕኖ እንዳልፈጠረባት እና ባለቤቷም የስራውን ባህሪ ስለሚረዳት እንደሚያግዛት ትናገራለች። አዲስ ዘይቤ ስለምትጠቀመው የድንች አይነት ልኬን ጠይቃት ነበር  "ኡደኖ የሚባለውን የድንች ዝርያ ነው የምጠቀመው፤ ውድ  ነው፤ ሌሎች እንደእኔ ያሉ ነጋዴዎች ስለማያዋጣቸው አይደፍሩትም” ትላለች።

“በቀን ከአንድ እስከ ሁለት ድስት እቀቅላለሁ፤ እንደደምበኞቼ ብዛት ነው የማዘጋጀው፤ ሌሎች ድንቹን ልጠውት ነው የሚቀቅሉት፤ እኔ ጣዕሙን እንዳያጣ ከተቀቀለ በሁዋላ ነው በትኩስነቱ ተልጦ ሁለት ሦስት ቦታ በመፈረካከስ ከተከታይ ዳጣ ጋር ለእንግዶቼ የማቀርበው። ይህም አዘገጃጀቱ የደምበኞችን ቀልብ ሳቢ አድርጎታል” ትላለች።

“ስራውን ስጀምር በትንሽ የሸራ ዳስ ውስጥ ብቻዬን ያለ አጋዥ ነበር የምሰራው፤ ከመጀመርያው የኑሮ ደረጃም ተሻሽያለሁ፤ የስራ ቦታዬንም፤ የሸራ ዳሱን ሰፋ አድርጌ ለሁለት ሰዎች የስራ ዕድልን ፈጥርያለሁ፤ ቤተሰብ አስተዳድራለሁ” ስትል አዲስ ዘይቤን አጫውታታለች። 

ልኬ ለወደፊት ብዙ ነገር ታስባለች “ስራውን ማስፋት እና በትልቅ ምርት ደረጃ ብራንድ (brand) የማድረግ እቅዱ አለኝ፤ ይህም ሊሳካ የሚችለው የመስሪያ ቦታ እጦቴ ተቀርፎ ምቹ ቦታ ሲመቻችልኝ እና የመንግስትን ድጋፍ ሳገኝ ነው”  ስትል ለአዲስ ዘይቤ ተናግራለች። 

ርብቃ ደመቀ፤ ልኬ ጋር የስራ ዕድል ካገኙት መካከል አንዷ ናት "ሁለት አመት ሆኖኛል ከእሷ ጋር ስሰራ፤ እሷ እንደ አሰሪ አይደለችም ትለያለች፤ ታች ወርዳ ነው ከእኛ ጋር የምትሰራው" ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። 

እዛው ድንች በዳጣ እያዋዛ ሲመገብ ያገኘነው አቶ ሀብታሙ ተፈራ "የልኬ ምግብ አዘገጃጀቱ እና ንፅህናው ስለሚስበኝ አዘውትሬ እጠቀማለሁ፤ ከአራት አመታት በላይ ነው በደምበኝነት የማውቃት” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። አቶ ቢኒያም ታደሰ በበኩሉ "የልኬን የስራ ጥረት ተማሪ እያለሁ ጀምሮ አውቀዋለሁ ታታሪ ናት፤ የስራ ዘርፉ ቢስፋፋ እና በስራ ዕድል ፈጠራው ዘርፍ ለሚሰለጥኑ አንደመንደርደሪያ ሀሳብ ቢቀርብ እና ተሞክሮዋንም እንድታካፍል ቢጋብዟት፤ እንዲሁም በሚመለከተው አካል ድጋፍ ቢደረግላት ከዚህም በላይ እንደምታሳየን እርግጠኛ ነኝ" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

አስተያየት