ታህሣሥ 27 ፣ 2013

ባዕድን ከምግብ -  መፍትሄ ያጣው የወንጀል ድርጊት

City: Jimmaንግድ

“ባዕድ ነገሮች ከዕለት ምግባችን ጋር ተደባልቀው እየተሸጡ ነው” የሚል ዜናን መስማት አሁን ላይ ለጆሮዋችን አዲስ እየሆነ አይደለም።

Avatar: Workineh Diribsa
Workineh Diribsa

I am Workineh, lecturer and researcher at Jimma University; journalist/correspondent for Addis Zeybe media.

ባዕድን ከምግብ -  መፍትሄ ያጣው የወንጀል ድርጊት

 “ባዕድ ነገሮች ከዕለት ምግባችን ጋር ተደባልቀው እየተሸጡ ነው” የሚል ዜናን መስማት አሁን ላይ ለጆሮዋችን አዲስ እየሆነ አይደለም። በየቀበሌው እና በየከተማው በርበሬን ከቀይ አፈር፣ እንጀራን ከጀሶ እና ከሰጋቱራ ጋር ደባልቀው የሚሸጡ ግለሰቦችን ማደንም የፖሊስ የዘወትር ተግባር ሆኗል።

ለዚህም ደግሞ ታህሳስ 25፣2013 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክ/ከተማ ከወልደ አማኑኤል ዱባለ አደባባይ አለፍ ብሎ  ሙሉ ግቢ ተከራይተው ይህን ህገወጥ ተግባር ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙት ግለሰቦች አንድ ማሳያ ናቸው፡፡

የከተማው ፖሊስ ጉዳዩ በህግ አግባብ በጥልቀት እስኪጣራ ድረስ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ቢቆጠብም ግለሰቦቹ እንጀራን ከባዕድ ነገር ጋር ደባልቀው ለገበያ ሲያቀርቡ እንደነበር ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

በተመሳሳይም ሰሞኑን የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በደቡብ ክልል ከፋ ዞን ዋቻ ከተማ ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ሊሸጥ የነበረ 93ኩንታል ቅቤ በቁጥጥር ስር መዋሉን አዲስ ዘይቤ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡ ቅቤው ወደ ጅማና አዲስ አበባ ከተሞች ለመውሰድ ታስቦ የነበረ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ በቃሉ አረጋ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል፡፡

ባሁኑ ግዜም 11 የቅቤና ማር ናሙናዎች ተወስዶ ምርመራ ላይ ሲሆኑ በቁጥጥር የዋሉ ግለሰቦችም መጣራት እየተደረገባቸው መሆኑን ዳይሬክተሩ አክሏል፡፡

ይሁን እንጂ በየጊዜው ከባዕድ ነገር ጋር የተደባለቁት ምግቦች ላይ እንጂ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀሙት ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ የሚያርም እንዳልሆን ዳይሬክተሩ ይናገራል።

“የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ምርቶቹ ላይ እንጂ ወንጀለኞቹ ላይ እርምጃ መውሰድ አይችልም። ያለው ህግም በዘርፉ የሚታዩ ህገወጥ ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ለመቆጣጣር የሚያስችል አይደለም።” ይላል በቃሉ

ለአብነትም በ2012 ዓ.ም የአዲስ ዓመት በዓል ላይ የተፈጠረውን አስታውሷል፡፡ ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀለ 200ኩንታል የሚገመት ቅቤ ከነወንጀለኞቹ በጅማ ከተማ በቁጥጥር ስር ውለው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በወንጀሉ የተሳተፉ ሰዎችን ተከታትሎ ተገቢውን የህግ ቅጣት ባለመቀጣታቸው ቦታቸውን ቀይረው ስራቸውን ሰልመቀጠላቸው መስማቱን በቃሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

 

ከዚህም ባለፈ ድርጊቱን ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ የሚያዙት ሰዎች እንኳን ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ማስረጃዎች በአግባቡ ስለማይቀርቡ እና ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ስለማይጠየቅ የሚወሰነው ወሳኔም አሰተማሪ አይደለም ብሏል።

“ለማሳያነትም ምግቡ ስንት ሰዎችን አሳምሟል? ስንት ሰዎችን ገሏል? የሚሉ ጥያቄዎች በፍርድቤት ይጠየቃሉ፡፡ ሆኖም በተፈጥሮው ባዕድ የሆኑ ነገሮች በምግብ ላይ ሲጨመሩ ወዲያውኑ ተበልቶ የሚያሳምሙ ወይም የሚገሉ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ወንጀለኞቹን ለመያዝ ያለው ክፍተት እንዳለ ሆኖ ወንጀሉን ሲሰሩ እጅ ከፍንጅ ከተያዙ በኋላ እንኳን ተገቢና አስተማሪ የሆና ቅጣት አይጣልባቸውም፡፡” በማለት ቅሬታውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

ይህም ሆኖ ባለስልጣኑ በአቅሙ አሰፈላጊውን ሁሉ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ለአዲስ ዘይቤ የገለፀው በቃሉ የበዓል ወቅት ሲሆን ደግሞ ሸማቾች ስለሚበዙ የባለስልጣኑ ሰራተኞች ሸማች በመምሰል ወደ ገበያ በመሄድ መረጃ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡

 ይህን ዘገባ ከጅማ እና ከሀዋሳ ያጠናቀሩት የአዲስ ዘይቤ ጋዜጠኞች ወርቅንህ ድሪብሳ እና ሙሉነህ ካሳ ናቸው፡፡

 

አስተያየት