ነሐሴ 12 ፣ 2014

የቡሄ በዓል በድሬዳዋ

City: Dire Dawaባህል ማህበራዊ ጉዳዮችከተማ

የአሁኖቹ ልጆች በጣም ህፃናት ከመሆናቸው የተነሳ ግጥሙን በደንብ አይችሉም። ሁለት መስመር ይሉና ቶሎ ብለው ስለ ብር ያዜማሉ።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የቡሄ በዓል በድሬዳዋ
Camera Icon

ፎቶ፡ ከማህበራዊ ድረገጽ (በቡሄ በዓል የሚለኮሰው ችቦ በታቦር ተራራ ለታየው ብርሀን ምሳሌ ይነገራል)

አቶ አማኑኤል የልጅነት የቡሄ ትዝታውን ሲያስታውስ፤ እሱና ጓደኞቹ ቆርኪ በመቀጥቀጥ በክብ ሽቦ ላይ በመሰካት “ከሽ ከሽ” የሚል ድምፅ የሚያውጣ ለሆያ ሆዬ ጨዋታ ማድመቂያ የሚሆን ነገር ሰርተው፣ ዱላ ይዘው በየቤቱ በመዞር “ሆያ ሆዬ” ሲሉ ያመሻሉ። በመጨረሻ ላይ የሰበሰቡትን ብር ተከፋፍለው ይለያያሉ እንደነበር ይናገራል። 

በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሆህተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን የስብከተ ወንጌል ሀላፊ መምህር የማነህ ብርሀን ጥላሁን “ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሀነ መለኮቱን በደብረ ታቦር ተራራ የገለጠበት በዓል ነው። ደብረ ታቦር የቤተ ክርስትያን ምሳሌ ነው። ቤተ ክርስትያንም በዓሉን በደማቅ ስነስርዓት ታከብረዋለች” ብለዋል። 

በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢ እንደሚከበረው የቡሄ በዓል በጅራፍ ድምፅ ባይደምቅም፤ በዓሉ በድሬዳዋ ከተማም በልጆች የሆያ ሆዬ ጨዋታ ታጅቦ ሲከበር ቆይቷል። የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎችን በማናገር ያለውን የቡሄ ድባብ እንዲህ አጠናቅራለች። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተውኀዶ ቤተ ክርስትያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት መካከል አንዱ የደብረ ታቦር በዓል ነው። ደብረ ታቦር በግዕዝ የታቦር ተራራ ማለት ነው። የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው። የደብረ ታቦር በዓል በአብዛኛው ህዝብ ዝንድ የቡሄ በዓል እየተባለ ይጠራል። 

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን አስተምሮ ቡሄ ማለት በገዕዝ “ገላጣ” ወይም “የተገለጠ” ማለት እንደሆን ይነገራል። ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብርሀን የታየበት፣ ድምፀ መለኮት የተሰማበት ስለሆነ፤ የሚለኮሰው ችቦ በተራራው የታየውን ብርሀን ያመለክታል። ይህ በዓል በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 17÷1-8 ያለውን ታሪክ መሰረት በማድረግ እንደሚከበር የኃይማኖቱ መምህራል ያስረዳሉ።

እንደ መምህር የማነህ ብርሀን ገለፃ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋሪያት መካከል ያዕቆብን ዮሃንስን እና ጴጥሮስን መርጦ ወደታቦር ተራራ ይዟቸው ወጣ። ፊቱም በብርሃን ተሞላ። ከእርሱ ጋርም ሙሴ እና ኤልያስ ታዩ። ጴጥሮስም 'ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው። ሶስት ዳስ እንስራ አንዱን ላንተ አንዱን ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ' አለ። ወድያውም ድምፅ ከደመናው መጥቶ 'በርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እርሱን ስሙት' ብሎ ተናገረ። በዚህም ድምፅ ተደናግጠው ሀዋርያት በፊታቸው ተደፉ” ሲሉ የደብረ ታቦር በዓል ሀይማኖታዊ መሰረት አብራርተዋል።

በድሬዳዋ የቡሄ በዓል በሁለት ዓይነት መልክ ሲከበር ይስተዋላል። ትንንሽ ወንድ ልጆች ዱላ ይዘው “ሆያ ሆዬ” እያሉ በየቤቱ እየዞሩ ሲጨፍሩ፤ በሌላ በኩል የቤተ ክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት ዘማሪያን ወጣቶች በሚያገለግሉበት ቤተ ክርስትያን ዙሪያ ወደ አሉ ምዕመናን ቤት በመሄድ ይዘምራሉ።  

በዋዜማው እና ቀደም ባሉት ቀናት ምሽት ላይ ወንድ ልጆች በቡድን በቡድን በመሆን በየቤቱ እየዞሩ “ሆያ ሆዬ” እያሉ ይጨፍራሉ።እንዲህ በማለት፣

መጣና ባመቱ ኧረ እንድምን ሰነበቱ(2×)

ሆያ ሆዬ ሆ ሆያ ሆዬ ሆ፣

እዝያ ማዶ ሆ ጭስ ይጨሳል፤

አጋፋሪ ሆ ይደግሳል።

ቡሄ በሉ ሆ ልጆች ሁሉ፣ 

ቡሄ መጣ ሆ ያ መላጣ፣ 

ቅቤ ቀቡት ሆ ጸጉር ያውጣ።

ሰንበት ትምህርት ቤት ዘማሪያን ወጣቶች በበኩላቸው በበዓሉ ዕለቱ ነሃሴ 13 ጥዋት ላይ ከቤተ ክርስትያን በመጀምር የበዓሉን መንፈሳዊ ዝማሬ ለምዕመናን ያቀርባሉ። እንዲህ እያሉ፣

ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና (2×)

የቡሄው ብርሀን ለኛም በራልን (2×)

ያቆብ ይሃንስ ሆ እንዲሁም ጴጥሮስ ሆ፣ 

አምላክን አዩት ሆ ሙሴ ኤልያስ ሆ፣

አባትም አለ ሆ ልጄን ስሙት ሆ፣

ቃሌ ነውና ሆ የወለድኩት ሆ፣

መምህር የማነህ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ ህፃናትም ልክ ጴጥሮስ 'በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው' እንዳለው ስርዓቱንና ቱፊቱን ጠብቀው፤ ቃለ እግዚአብሔርን እየሰሙ መዝሙሩን እየዘመሩ በዓሉን በቤተ ክርስትያን ማክበር መልካም ነውና ትውልዱ ይህንን ቢከተል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እና ልብስ እንደ ፀሀይ ባበራ ጊዜ ከተራራው ስር የነበሩ እረኞች በብርሀኑ እየተገረሙና እየተደነቁ ብርሀኑን እያዩ ወደቤት ሳይሄዱ መሸባቸው። የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች በምሽት ችቦ ለኩሰው የሚበላ ዳቦ ይዘው ወደ ልጆቹ ሄዱ። ይህንንም በማሰብ የእምነቱ ተከታዮች ችቦ በመለኮስና ለልጆች ሙልሙል ዳቦ በማዘጋጀት ይሰጣሉ።

(በቡሄ በዓል እናቶች ለልጆች ሙልሙል ዳቦ በማዘጋጀት ይሰጣሉ)

ልጆች በየሰፈሩ የሚያጮሁት ጅራፍ ደግሞ በደመና ተገልጦ የተናገረው የድምፀ መለኮት ምሳሌ ነው። ጅራፍ ሲጮህ እንደሚያስደነግጥ ሁሉ ሐዋርያትም በድምፀ መለኮቱ መደንገጣቸውን እንደሚያመለክት የኃይማኖቱ መምህራል ያስረዳሉ። በገጠርም ሆነ በከተማ ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ሙልሙል ዳቦ ሲያዘጋጁ ይሰነብታሉ። 

ወደ ድሬዳዋ የቡሄ(የደብረ ታቦር) በዓል አከባበር ስንመለስ ቀደም ሲል በድሬዳዋ በቡሄ ሰሞን በቡድን ሆነው በየአካባቢዊ በብዛት ሆያ ሆዬ ሲጨፍሩ ይታዩ የነበሩት ህጻናት ዛሬ ላይ ቁጥራቸው መቀነሱን የታዘቡት ይናገራሉ። 

አቶ አማኑኤል ሶምሶን ተወልዶ ያደገው ድሬደዋ ሲሆን  የሆህተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ሰንበት ተማሪ ነው። አማኑኤል ልጅነቱን ሲያስታውስ በእነሱ ጊዜ ልጆች እስከ 15 ዓመታቸው ድረስ ሆያ ሆዬ ይጨፍሩ እንደነበር ይናገራል። “በአሁን ጊዜ የ13 እና 14 ዓመት ልጆች ለቡሄ ጭፈራ ያላቸው ፍላጎት የቀዘቀዘ ነው። ከዛ ይልቅ ስለፊልምና ዘፈን ይጨነቃሉ። ልጆቹ ባህላቸውንና ሀይማኖታቸውን እንዲያውቁ ወላጆች ማስተማር አለባቸው” ይላል።

ራሔል አደባ በድሬዳዋ ልዩ ስሙ ገልደቦዬ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪ ናት። እንደ ራሄል ገለፃ “ልጆች ቡሄ ሲደርስ ማንም ሳይነግራቸው ነው የሚዘጋጁት። ነገር ግን ድሮ ከነበረው ጋር አይነፃፀርም። ምክንያቱም የአሁኖቹ ልጆች በጣም ህፃናት ልጆች ናቸው ግጥሙን በደንብ አይሉም። ሁለት መስመር ይሉና ቶሎ ብለው ስለ ብር ያዜማሉ። ህጻናቱ ትኩረት የሚደርጉት ስለሚያገኙት ብር ላይ ነው” ስትል ተናግራለች።

አቶ አማኑኤል በሰንበት ት/ቤት ውስጥ ከበዓሉ ቀደም ብለው የመዝሙር ጥናት እንደሚጀምሩና ከቤ/ክ ውጪ እየዞሩ እንደሚዘምሩና ማህበረሰቡም የሰንበት ተማሪዎች ባህሉን ጠብቀው ስለሚዘምሩ በደስታ እንደሚቀበሏቸው ተናግሯል።

ወ/ሮ ሊባኖስ ዮሴፍ በበኩሏ “በአሁኑ ሰዓት ቱፊቱን የሚያስተላልፍ እየጠፋ ነው። ማህበረሰቡ ውስጥ በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዟል። በዓሉ በምን ምክንያት እንኳን እንደሚከበር አብዛኞቹ ህፃናት አያውቁትም። ችግሩ ያለው እኛ ወላጆች ጋር ነው” ብላለች። 

ወ/ሮ ሊባኖስ አሁን ላይ የሰፈር ልጆች የቡድን ስሜቱ እየጠፋ እንደሆነና በፊት ወደ አስር የሚጠጉ ህፃናት ተሰብስበው እንደሚጨፍሩ አስታውሳ “አሁን ግን ሶስት ሆነው ይመጣሉ። ምክንያታቸው ድሬዳዋ ላይ ብር መስጠት የተለመደ ስለሆነ ብዙ ከሆኑ ብሩን ሲካፈሉት ትንሽ ስለሚሆንባቸው ነው። ነገር ግን ልጆች ከብሩ ይልቅ ድባቡን ነበር የሚወዱት” ስትል ሀሳቧን ገልፃለች።

አስተያየት