ሐምሌ 26 ፣ 2014

የምግብ ዘይት ጉዳይ በጎንደር

City: Gonderየአኗኗር ዘይቤንግድ

የቅባት እህሎችን በስፋት የሚያመርተው የጎንደርና የአካባቢው ህዝብ የምግብ ዘይትን ለማግኘት እየተቸገረ ይገኛል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የምግብ ዘይት ጉዳይ በጎንደር
Camera Icon

ፎቶ፡ በጌታሁን አስናቀ (ከአዲስ ዘይቤ)

“ቡና የለም እንጂ ቡናማ ቢኖር፣ አይ አገር አይ አገር አይ አገር ጎንደር” እያሉ አዝማሪዎች የሚዘፍኑላት ጎንደር፤ አምርታ የምታቀርበው ቡና ባይኖራትም ተፈጥሮ የሰሊጥ ምርትን አብዝታ ሰጥታለች። የሰሊጥ ምርት በብዛት ከሚመረትባቸው እና ለውጭ ገበያ በመላክ ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ቦታዎች መካከል ጎንደርና አካባቢው አንዱ ነው። በተጨማሪም ኑግ እና መሰል የቅባት እህሎችም ይመረትበታል። ሰሊጥ በዋነኝነት የምግብ ዘይትን ለማምረት የሚውል የቅባት እህል ነው። 

ታድያ ይህን የቅባት እህል በስፋት የሚያመርተው የጎንደርና የአካባቢው ህዝብ የምግብ ዘይትን ለማግኘት እየተቸገረ ይገኛል። በጎንደር ከተማ ውስጥ የአካባቢውን ምርት በመጠቀም የምግብ ዘይትን ለማምረት በአርሶ አደር ማህበራት አማካኝነት የተቋቋሙ ፋብሪካዎች ቢኖሩም የገበያውን የምርት ፍላጎት ለማሟላት አልቻሉም። አንዳንዶቹም ዘይት የማምረት ስራቸውን ሊያቆሙ እየተንደረደሩ ነው።  

ጎንደር ከተማ ውስጥ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት የሚስተዳደሩ 299 የሚሆኑ ፋብሪካዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ጥቂት የምግብ ዘይት አምራች ፋብሪካዎች ይገኛሉ። ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዬን ዘይት ፋብሪካ ከነዚህ አንዱ ነው። በውስጡ 149 መስራች ማህበራትና 139,000 የሚደርሱ አባል አርሶ አደሮችን አቅፎ የያዘ የዘይት ፋብሪካ ነው። 

ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዬን ዘይት በማምረት አቅርቦቱን ያሻሽላል በተለይ የዋጋ ንረትን ለመከላከል ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ፋብሪካው በ 70 ሚሊዮን ብር በጀት ተገንብቶ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ስራ ገብቷል። ለተከታታይ ስድስት ወራቶች በቀን 10ሺ ሊትር ዘይት እያመረተ እንደነበር ይሁንና አሁን ላይ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንዳልሆነ የፀሐይ ዩኒዬን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ይሁኔ ዳኛው ተናግረዋል። 

    ፎቶ፡ በጌታሁን አስናቀ (ከአዲስ ዘይቤ) 

አቶ ይሁኔ ዳኛው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዬን ፋብሪካው የምግብ ዘይት ከማምረት በተጨማሪ በውስጡ ጥራቱን የሚፈትሽ የማጣሪያ ላቦራቶሪ፣ በቀን 40 ኩንታል የሚያመርት የእንስሳት መኖ ማምረቻ ማሽን፣ የፕላስቲክ መፍጫ እና የማሸግ ስራዎችን ይሰራ እንደነበርም ገልጸዋል።  ፋብሪካው በውስጡ 91 ቋሚ እና 6 ኮንትራት በድምሩ 97 ሰራተኞች እንዳሉትም አስረድተዋል።

ፋብሪካው ለምን በሙሉ አቅሙ ማምረት አልቻለም ? ተብሎ ከአዲስ ዘይቤ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ይሁኔ ሲመልሱ “አሁን ላይ ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉ ስራዎች ማከናውን አልቻልንም። ዩኒዬኑ የፋይናንስ ችግር እንዲሁም 87 ሚሊዬን ብር እዳ፣ የካፒታል እጥረት እና የጥሬ እቃ ችግር በመኖሩ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ ዋና ምክንያቶች ሁነዋል” ብለዋል።

አቶ አለበል (ስሙ የተቀየረ) የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው። የፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዬን በዓመት ከ70,000 ኩንታል በላይ የቅባት ምርቶችን በግብዓትነት ይጠቀም እንደነበር ተናግረው። “ገበሬው የሚያመርተውን ምርት ከእጅ ወደ አፍ ከሚያደርገው ኑሮ ሊያላቅቀው የሚችለው ዘመናዊ ፋብሪካዎች ማቋቋም ሲቻል ነው። አርሶ አደሩ ምርቱን አምርቶ በበዝባዢ ነጋዴዎች እንዳይበሉ ያመረቱትን ምርት አምጥተው ሽጠው ዘይታቸውን ይዘው ይሄዱ ነበር። አሁን ላይ የዘይት ዋጋ ሰማይ በነካበት ጊዜ ፋብሪካው ምንም አይነት አገልግሎት እየሰጠ አይደለም” ይላሉ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ግርማይ ልጅዓለም በበኩላቸው “አሁን ፋብሪካው በፋይናንስ ችግር ምክንያት በሙሉ አቅሙ እየሰራ አይደለም። በንግድ ባንክ እና አባይ ባንክ እዳ ተይዟል። አንዳንድ ማሽነሪዎች ከጥቅም ውጭ ሁነዋል። እነዚህን ችግሮች መፍታት ስላልቻለ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዳይገባ አድርጎታል” ብለዋል።

ፀሐይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዬን ዘይት ፋብሪካ ሲያመርት የነበረውን ዘይት ያካክሳሉ ተብለው የታሰቡ፤ በጎንደር እና አካባቢው ያሉ ግብዓቶችን ተጠቅመው የኑሮ ውድነትን በተለይ የዘይት ዋጋ ንረትን ችግር ይፈታሉ ተብለው የታቀዱ ፋብሪካዎች አሉ። “በሶስት አመት ውስጥ ተጠናቀው ስራ የሚጀምሩ 16 የዘይት ፋብሪካዎች በሂደት ላይ ናቸው” የሚሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ልማት ቡድን መሪ አቶ ፋሲል ዘውዱ ናቸው።

እንደ አቶ ፋሲል ገለጻ ከሆነ ወደ ዘይት ምርት ለመግባት ግንባታ ያጠናቀቁ 7፣ በግንባታ ላይ ያሉ 5፣ ካርታ ወስደው ቅድመ ዝግጅት ላይ ያሉ 4 የዘይት ፋብሪካዎች እንዳሉ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል።

ጎንደርና አካባቢው ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ከሰሊጥ፣ ከኑግና ከጥጥ ምርት ጋር በተያያዘ በርካታ የተፈጥሮ ኃብት ያለው አካባቢ ነው። ከዚህም አኳያ በከተማዋ እነዚህ ፕሮጀክቶች ይበልጥ በውጤታማነት እንዲተገበሩ እየጣሩ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨትስመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ግርማይ ልጅዓለም አስረድተዋል።

አስተያየት