ሰኔ 2 ፣ 2013

ለ12 ዓመታት የተጓተተው የመንገድ ግንባታና የነዋሪዎቹ ሮሮ

City: Jigjigaትንታኔዜናዎች

የመጓተቱ ምክንያት የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡

Avatar: Addis Zeybe
አዲስ ዘይቤ

የኢትዮጵያን አስደናቂ የከተማ ባህል፣ ታሪክ፣ ወቅታዊ ዜና እና ሌሎችንም ያግኙ።

ለ12 ዓመታት የተጓተተው የመንገድ ግንባታና የነዋሪዎቹ ሮሮ

በሶማሊ ክልል ሊበን ዞን፣ ፍልቱ-ዶሎ መንገድ የመሰረት ድንጋዩ ተጥሎ የግንባታ ሂደቱ ከተጀመረ 12 ዓመታት አልፈዋል፡፡ የመንገድ ሥራ ግንባታው በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት እየተገነቡ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የመጓተቱ ምክንያት የመንገድ ግንባታውን ለማከናወን ኮንትራት በወሰደው ተቋም እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ስለመሆኑ ለአዲስ ዘይቤ መረጃውን የሰጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል፡፡ 

18 ኪ.ሜ. የሚሸፍነው የገጠር መንገድ ፕሮጀክቱ የተጀመረው በ2001 ዓ.ም. ሲሆን በሊበን ዞን የሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎች ለማገናኘት ያለመ ነበር፡፡

የአዲስ ዘይቤ ጅግጅጋ ዘጋቢ ከነዋሪዎቹ መረዳት እንደቻለው የግንባታው ለ14 ዓመታት መጓተት የዞኑን ነዋሪዎች ለእንግልት ዳርጓል፡፡ የፍልቱ ከተማ ነዋሪው አቶ ናስር አብዱላሂ መንገዱ በፍጥነት ባለመጠናቀቁ ከተማረሩ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ “መንገዱ ባለመጠናቀቁ ለሕገ-ወጥ አሽከርካሪዎች ዳርጎናል” የሚሉት አቶ ናስር “በአንድ ሞተር እስከ አምስት ሰዎች በመጫን እየዘረፉን ይገኛሉ አንድ የጭነት (አይሱዙ) መኪና ከ60 በላይ፣ 12 ሰው የሚጭን ሚኒባስ ደግሞ እስከ 25 ተሳፋሪዎችን ጠቅጥቀው እየጫኑ መጫወቻ አድርገውናል፡፡ ሕጻናትና ነብሰ ጡርሴቶች ታርጋ በሌላቸው በሕገ-ወጥ ሞተሮች ይገጫሉ፡፡ መፍትሔ የሚሰጥ አንድም አካል የለንም” ሲል ቅሬታቸውን አጋርተውናል። 

የፍልቱ ከተማ 01 ቀበሌ ወረዳ ነዋሪው አቶ አብዲራህማን አብዱላሂ የአቶ ናስርን ሃሳብ ይጋራል “ተጓዥ መንገደኞች አማራጭ ስለሌላቸው ለመንገደኞች ያልተፈቀዱ የጭነት ተሽርካሪዎችን፣ ሞተር ሳይክል እና የግለሰብ ተሽከርካሪዎችን በአማራጭ መጓጓዣነት እየተጠቀሙ ነው፡፡ ይህ ሁለት ጉዳት አለው፡፡ የመጀመርያው ከፍ ላለ ወጪ መዳረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው አደጋ ነው፡፡ መንግሥት መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል›› ይላል።

“በሶማሊ ክልል በጀት ይሰራል የተባለው መንገድ በጣም እያሰቃየን ነው፡፡ አይሱዙ በ30 ብር፣ አንድ ሞተር እስከ 5 ሰዎች በመጫን ከአንድ ሰው እስከ 50 ብር ያስክፍላሉ” ሲል ሐሳቡን ያጋራን አቶ ኤሊያስ መሀመድ የተባለ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ነው፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ዝቅተኛ የሥራ አፈፃፀም ማሳየቱን የዞኑ ኮንትራክተር አስተዳደር ቡድን ኃላፊ፣ አብደላ ዩሱፍ ለአዲስ ዘይቤ ገልጿል፡፡ ኃላፊው ከነዋሪዎች የተነሳው ቅሬታ ትክክለኛና ተገቢ ነው ካሉ በኋላ፤  “በፍልቱ ዞን ስር የሚገኙ ወረዳዎች የሚያገናኝ ይህ መንገድ በመንገዶች ባለሥልጣን እና በመንገዱ ተቋራጭ መሐከል በተፈጠረ አለመግባባት ሕጋዊ ርክክብ ስላልተደረገ ኮንትራቱ እንዲቆም ተደርጓል፡፡” ብለውናል፡፡ በተጨማሪም ባለሥልጣኑ የዛሬ 11 ዓመት በ2012 ዓ.ም. ከሊበን ዞን ጋር በመነጋገር በዞኑ የጥገና ዘርፍ አማካኝነት ቀሪውን የመንገድ ሥራ እንዲያጠናቅቅ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡ በአሰራር ስርዓቱ መሰረት ሕጋዊ ርክክብ ሳይፈጸም ጥገና ማድረግ እንደማይቻል ቢታወቅም መንገዱ እስካሁን ሁለት ጊዜ ጥገና እንደተደረገለትም አቶ አብደላ አስታውሰዋል፡፡

የፍልቱ ወረዳ መንገዶች ባለስልጣን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ኢደሪስ አህመድ በበኩላቸው የመንገድ ሥራውን መጓተት አስመልክቶ ከአዲስ ዘይቤ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ “እስከአሁን ሕጋዊ ርክክብ አልተደረገም፡፡ የትራንስፖርት ቢሮው ለመንገዱ ታሪፍ ለማውጣት ርክክብ የተደረገበትን ሰነድ ይፈልጋል፡፡ ታሪፉ ታውቆ፣ ተሽከርካሪዎች እንዲመደቡ ለማድረግ ያልተቻለው በርክክቡ መጓተት ምክንያት ነው” ብለዋል፡፡

በርካታ ተጓዦችን ለተጨማሪ ወጪ የዳረገውን፣ ጥቂት የማይባሉ ሕገ-ወጦች ያልተፈቀደ ተግባር እንዲፈጽሙ ያስቻለውን፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ለንብረት ብልሽት የዳረገውን ጉዳይ አስመልክቶ የጠየቅናቸው አቶ ሁሴን አብዲሰላም “ስለ መንገዱ ፕሮጀክት ታሪክ የማውቀው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ አቶ ሁኔን የሶማሊ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ጥገና ዳይሬክተር የፍልቱ ቅርንጫፍ ኃላፊ ናቸው፡፡

“ፕሮጀክቱ ለምንና እንዴት እንደተቋረጠ አላውቅም፡፡ የጥገና ሥራውን እንዲሠራ በ2012 ዓ.ም. ከሶማሊ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር ማሽነሪዎች አስገብተን ወደ ሥራው ገብተናል፡፡ አሁንም ጥገና እያካሄድን እንገኛለን” ሲሉ የራሳቸውን እና የሚመሪትን ቢሮ ሐሳብ አንጸባርቀዋል፡፡

የሲማሊ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊ፣ አቶ ባሽር ሻፍ በበኩላቸው የመንገዱ ቁጥጥር በሶማሊ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ክትትል በመሆኑ ስለ ፕሮጀክቱ ዝርዝር ሁኔታዎች የማወቅ እድል እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ለምንና እንዴት እንደተቋረጠ ኃላፊው “የማውቀው በሶማሌ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የተጻፈ ደብዳቤ ወደ መንገድ ጥገና ዘርፍ ፍልቱ ቅርንጫፍ መምጣቱን እና መንገዱ እየተጠገነ መሆኑን ብቻ ነው” ብለዋል፡፡

“አላውቅም”፣ “አውቃለሁ”፣ “ተቋርጧል”፣ “ጥገና ላይ ነው” የሚሉትን ተቃራኒ ምላሾች ይዘን የፍልቱ ወረዳ የህዝብ ንግኙነት ኃላፊ ዘንድ አምርተናል፡፡ ኃላፊው አቶ ሁሴን አሊ “12 ዓመታት በአግባቡ ሥራ ሳይጀምር የከረመው 18 ኪ.ሜ የሚሸፍን የጠጠር መንገድ ለሕገ-ወጥ አጓጓዦች ምቹ ሁሄታ ፈጥሯል፡፡ አጋጣሚውን ባለ ሦስት እግር እና ሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ያልተገባ ገንዘብ ለመሰብሰብ ተጠቅመውበታል፡፡ የወረዳው ህዝብ በድርጊቱ ቢማረር አይፈረድበትም፡፡ አሽከርካሪዎች ለመጫን፣ ተሽከርካሪዎች ለመሳፈር በሚያደርጉት ጥረት በሚፈጠር ግፊያ ጉዳቶች ይደርሳሉ፡፡ በመሆኑም የወረዳው ፖሊስ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ባደረገው ቁጥጥር በሕገ-ወጥ ሥራ ተሰማርተዋል የተባሉ 150 ሞተሮችና 50 ብስክሌቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ የተያዙት ሁሉም ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ እንደሌላቸውና ከፊሉ ደግሞ የጎረቤት ሐገር ኬንያ ታርጋ የለጠፉ ነበሩ፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራዎች እየተጣሩ ነው›› ብለዋል፡፡

ኃላፊው በተጨማሪም “ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የታሰበ ነገር ስለመኖሩ አዲስ ዘይቤ ላነሳችው ጥያቄ ከፍልቱ ዞን የመንገዶች ባለሥልጣን ጋር በመነጋገር በጊዜያዊነት 15 ሰው የሚጭን ሁለት የህዝብ ማመላለሻ ዶልፊን ተሽከርካሪዎች ተመድበዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንገዱ በፍጥነት መጠናቀቅ የሚችልበትን መንገድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር እንነጋገራለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በስተመጨረሻም አዲስ ዘይቤ የመንገዱ ፕሮጀክት ለምንና እንዴት እንደተጓተተ፣ ከኮንትራክተሩ ጋር ለምን ስምምነት እንዳቋረጠ፣ ምንም አይነት ህጋዊ ርክክብ ሳይደረግ እንዴት ወደ ጥገና እንደተገባና የማን ጥፋት እንደሆነ በዝርዝር ለማጣራት ወደ ሶማሊ ክልል መንግዶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የጥገና ዘርፍና የመንገድ ሀብት አስተዳደር ሥራስኪያጅ፣ አቶ ሮብሌ ቡኡል  እንዲሁም የመንገዱን አሰራርና ስራ ፕሮጅክትን ከመጀመሪያ አንስቶ ሲከታተል የነበረው ስሆን ኮንትራቱ ከእነሱ በጀት ስልጣን ላይ የነበረ ሰዎች እንደተዋዋሉ በመጥቀስ ከለዉጡ በሗላ ደግም እንደ አደረ ለማሰጀመር የተካሄደበት መንገድ እንዳለ በመጥቀስ በ2014 ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ እንገባለን ሲል ተናግሯል። ምን ሆነ?

አስተያየት