ነሐሴ 27 ፣ 2013

አሳሳቢው የትምህርት ቤቶች ዋጋ ጭማሪ ጉዳይ በአዳማ

City: Adamaኢኮኖሚማህበራዊ ጉዳዮች

ሰሞኑን የዜና ዘገባ ርዕሰ-ጉዳይ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ የግል ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ አንዱ ነው፡፡ ጉዳዩ የብዙኃንን በር አንኳኩቷል። አሳሳቢነቱና አነጋጋሪነቱም ቀጥሏል። የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በአዳማ ያለውን ሁኔታ ዘግቧል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አሳሳቢው የትምህርት ቤቶች ዋጋ ጭማሪ ጉዳይ በአዳማ
Camera Icon

Photo: Adama Sister Cities International

ሰሞኑን የዜና ዘገባ ርዕሰ-ጉዳይ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ የግል ትምህርት ቤቶች የዋጋ ጭማሪ አንዱ ነው፡፡ ጉዳዩ የብዙኃንን በር አንኳኩቷል። አሳሳቢነቱና አነጋጋሪነቱም ቀጥሏል፡፡ ማንኛውም የትምህርት ተቋም የተማሪዎቹን  የወርሃዊ ክፍያ ዋጋ ለመጨመር ሲያቅድ ከሦስት ወራት አስቀድሞ ለወላጆች ማሳውቅ እንዳለበትከዓመት በፊት በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡ መመሪያው በግልጽ እንዳስቀመጠው ጭማሪው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ክፍያ ጋር ሲነጻጸር ከ25 በመቶ መብለጥ የለበትም።

አዲሱ የ2014 የትምህርት ዘመን ሊጀመር ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ በቀረው በዚህ ወቅት የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በአዳማ ከተማ ተዘዋውሮ የዋጋ ጭማሪው ከ2013 የትምህርት ዘመን ጋር ያለውን ልዩነት ተመልክቷል፡፡ የግል ት/ቤቶቹ የመመዝገቢያ ክፍያውን ሳይጨምር ከዓምናው ክፍያ ላይ ከ11 እስከ 50% የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የትምህርት ተቋማት የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያውን ሕጉን ተከትለው እንዳከናወኑ ይናገራሉ፡፡ ተቋማቱ “በቀጣይ ዓመት የሚኖረው የዋጋ ጭማሪ ምን ያህል እንደሆነ ለእያንዳንዱ ወላጅ በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡ ከወላጅ ኮሚቴ ጋርም በጉዳዩ ላይ መክረናል” ይበሉ እንጂ በወላጆች ከፍተኛ ቅሬታ በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡

በሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ንግድ ስራ ለላይ የተሰማራችው ወ/ሮ አዜብ ኃይሌ ሁለት ልጆቿን በግል ትምህርት ቤት ታስተምራለች፡፡ የልጆቿ ወርሃዊ የትምህርት ቤት ክፍያ የትራንስፖርት ወጪአቸውን ጨምሮ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር “እስከ 1,000 ብር ልዩነት አለው” ትላለች፡፡ “በጣም አሳሳቢ ነው” የምትለው ወ/ሮ አዜብ ትምህርት ቤቱ በስብሰባ ወቅት ስለ ዋጋ ጭማሪ ቢያነሳም የወላጆች ምላሽ “ጭማሪው የበዛና ወቅታዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ነው” የሚል እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ሌላዋን ወላጅ ያገኘናቸው ልጃቸው በገጠመው አደጋ ምክንያት ያመለጡትን ፈተናዎች የማሟያ ፈተና (Make-up Exam) ሲያስፈትኑ ነው፡፡ ያነሳነውን ርዕሰ ጉዳይ አስመልተን ሐሳባቸውን ስንጠይቅ ስሜን ደብቁልኝ ብለውናል፡፡ “ባለፈው ዓመት በወር የምንከፍለው 630 ብር ነበር፡፡ አሁን ወደ 930 ከፍ ብሏል፡፡ የክፍያ ጭማሪን አስመልክቶ በተጠራው ስብሰባ ተሰብሳቢው ወላጅ ጭማሪው ላይ ባይስማማም ት/ቤቱ ግን በአንድ ጊዜ 300 ብር ጨምሯል” ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በአዳማ ከተማ ከሚገኙ የግል ት/ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው ሆሊ ኤንጅልስ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑትን መምህር ኤርሚያስ ወ/ጊዮርጊስ የቤት ኪራይ ጭማሪ፣ የትምህርት መሳሪያ ዋጋ ጭማሪ እና የመምህራን እና አስተዳደር ሰራተኞች ክፍያ ማነስ ለወርሃዊ ክፍያ ጭማሪው ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በትምህርት ዘመኑ ስለሚኖረው ጭማሪ ለተማሪ ወላጆች በደብዳቤ እና በወላጆች ቀን ዝግጅት ላይ ማሳወቃቸውንና ወላጅም በሐሳቡ መስማማቱን ይገላጻሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ ከ50 እስከ 200 ብር ለመጨመር ጥያቄ አቅርቦ በወላጆች በተወሰነው መሰረት በሁሉም የክፍል እርከኖች ላይ በፊት ከነበረው የ100 ብር ጭማሪ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ቁጥራቸው ውስን የሆኑ ወላጆች በዋጋ ጭማሪው ባለመስማማት ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤቱ እንዳስወጡ እንዲሁ ነግረውናል፡፡

የዋጋ ጭማሪ ያደረግነው ከአራት ዓመት በኋላ ነው የሚሉት የናፍያድ ት/ቤትች አስተዳደር አቶ ደጀኔ ደለለኝ ናቸው። ከ300 በላይ ነፃ የትምህርት እድል የተሰጣቸው ተማሪዎች እንዳሉና ት/ቤቱ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚሳተፍ ይናገራሉ። የዋጋ ጭማሪው ከሰራተኛ ደሞዝ፣ ከጽሕፈት መሳሪያ ዋጋ መናር ጋር የተገናኝ አንድምታ እንዳለውም ለሪፖርተራችን አብራርተዋል፡፡ የሰራተኞች ደሞዝ ማተካከያም የተማሪዎች ምዝገባ ተጠናቆ ስራ ሲጀመር ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ሌላው በቦሌ ክፍለ ከተማ ገንደ-ሀራ የሚገኘውና ከአስር ዓመት በፊት በ30 አባላት ተመስርቶ ስራ ላይ የሚገኘው አብዲ ቦሩ ት/ቤት ለመጪው የ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አለማድረጉን የት/ቤቱ ስራ አስከያጅ አቶ አድማሱ ደበላ ይናገራሉ፡፡ በወቅታዊ የሰላም፣ የኮቪድ እና የዋጋ ንረትን ሁነቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በትምህርት ቤቱ ቦርድ ውሳኔ መሰረት በሁሉም የክፍል ደረጃዎች ከጀማሪ እስከ ሁለተኛ ደረጃ እነዲሁም በአዲሶቹ የመሰናድኦ ክፍሎች ላይ በ2013 ዓ.ም. ከተሰራበት ክፍያ ምንም ዓይነት የወርሃዊም ሆነ የመመዝገቢያ ክፍያ ዋጋ ጭማሪ አለመደረጉን ይናገራሉ፡፡

ከመምህራን እና አስተዳደር ሰራተኞች ደሞዝ አንጸር በሚያዝያ ወር ከ18 እስከ 30 በመቶ ጭማሪ መደረጉን የሚናገሩት የአብዲ ቦሩ ርዕሰ መምህር መሐመድ አህመድ በመጪው የትምህርት ዘመን ከቀድሞ የበለጠ ቁጥር ያለው ተማሪ የሚመዘገብ ከሆነ የተሻለ አዲስ ተማሪ ብዛት የሚኖር ከሆነ ለሰራተኞች ደሞዝ ለመጨመር ከመምህራን ጋር  መነጋገራቸውን፤ ወላጆችም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

በዘገባው ላይ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አንድ የግል ትምህርት ቤት መምህርት እንደተናገረችው ከሆነ ጥቂት የማይባሉ ወላጆች በክፍያ ጭማሪው ምክንያት ወደ ሌሎች የግል እና የመንግስት ትምህርት ቤቶች ያስገቡ ወላጆች እንዳሉ ትናገራለች። ሌሎች ወላጆች የጊዜውን የዋጋ ንረት በመመልከት እንደተከናወነ እንደሚረዱ ትናገራለች። ከመምህራን ደሞዝ ጋር በተገናኘ ከመጪው መስከረም ወር በኋላ የደሞዝ ጭማሪ እንደሚኖራቸውና ይህም የሚሆነው በሚመዘገቡ ተማሪዎቸ ልክ እንደሆነም ትናገራለች፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት 14/12/2013 ዓ.ም. በአዳማ ትምህርት ቢሮ ለግል የትምህርት ዘርፍ ባለቤቶች፣ አመራሮች እና የጉድኝት ማዕከል ተቆጣጣሪዎች በተደረገ የስብሰባ ጥሪ የተገኙት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ የትምህርት ቤቶች የክፍያ ዋጋ  ከወቅታዊ የሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ ጋር ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ እንዲሆንና የትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

አስተያየት